አዲስ አበባ፦ ሀገሪቱ በቱሪዝም ዘርፍ ያለችበትን ደረጃ የሚያሳውቅ እና ከቱሪዝም ዘርፉ የሚገኘውን ገቢ የሚያሳይ የቱሪዝም ሳተላይት ሥርዓት ሊዘረጋ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ ዘርፉን ለማዘመን ከሃገር ውስጥና ከውጭ ሀገር ከመጡ ባሙያዎች ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።
በቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ፕሮሞሽን መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ይስፋልኝ ሀብቴ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ ሀገሪቱ በቱሪዝም ዘርፍ ያለችበትን ደረጃ የሚያሳውቅ እና ከቱሪዝም ዘርፉ የሚገኘውን ገቢ የሚያሳይ የቱሪዝም ሳተላይት ሥርዓት በቅርቡ ይዘረጋል። ይህንን ለማድረግም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው።
ሥርዓቱ በቱሪዝም የሚገኘውን ገቢ ከተለያዩ ተቋማትና ኤጀንሲዎች የተሰበሰበ የተስተካከለ መረጃ ያቀርባል ያሉት አቶ ይስፋልኝ፣ የሚዘረጋው የቱሪዝም ሳተላይት ሥርዓት ሀገሪቱ በቱሪዝም ከሌሎች ሃገራት አንጻር ያለችበትን ደረጃ የሚያሳውቅ ዘመናዊ ሥርዓት መሆኑን ጠቅሰዋል። ሥርዓቱን ተግባራዊ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ ከገቢዎች ሚኒስቴር፣ ከግሉ ዘርፍ እና ከሌሎች ተቋማት የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል።
በኬንያ የቱሪዝም ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዴቪድ ጊቶንጋ እንደተናገሩት፤ ለአፍሪካ ቱሪዝም ዋና ችግሩ የዘርፉን ትክክለኛ መረጃ ማመንጨት አለመቻሉ ነው። የባለድርሻ አካላት በጊዜ የአመራር ፈረቃ ላይ ተገቢውን መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውም በተመሳሳይ በዘርፉ ያለ ችግር መሆኑን ጠቁመዋል።
የቱሪዝም ሳተላይት ሥርዓቱ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍና ዘርፉ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላያ ያለውን ድርሻ በመለካት ለፖሊሲ ቀረጻ ትልቅ ግብዓት ይሆናል ያሉት ሥራ አስፈፃሚው፤ በዚህም ኬንያ የኢትዮጵያን ቱሪዝም ዘርፍ ለመደገፍ እና ያላትን ልምድ ለማካፈል ሁሌም ዝግጁ ናት ብለዋል።
ኬንያ ሥርዓቱን ከመተግበሯ በፊት ከዓለም አቀፍ ቱሪስቶች የምታገኘው ገቢ በቅጡ የማይታወቅ በመሆኑ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም የማታገኝ እንደነበር ጠቅሰውም፤ አሁን ግን ዘርፉ ከጠቅላላ የሀገሪቱ ምርት ውስጥ የአሥራ ሁለት በመቶ ድርሻ እያበረከተ ነው ብለዋል።
የኡጋንዳ የቲኤስኤ ኮሚቴ ጂም አዮሬኪር በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ ከኢጋድ ቱሪዝም ማስተር ፕላን ጋር የተጣጣመ ብሔራዊ የቱሪዝም ማስተር ፕላን መሆኑን ገልጸው፤ ሂደቱ የቱሪዝም መረጃዎችን ለማግኘት ፣ ሥራን ለመገምገም እና የዘርፉን ቀጥተኛ አስተዋፅዖ ለማሳየት የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።
ሥርዓቱ በተቻለ ፍጥነት ወደ ተግባር እንዲገባ ኤጀንሲዎች፣ ተቋማት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ያሉት ጂም አዮሬኪር፤ በኡጋንዳ የቱሪዝም ዘርፍ አሥር በመቶ የውጭ ምንዛሪ እንደሚያበረክት ሥርዓቱን ተግባራዊ በማድረግ ማወቅ ተችሏል ብለዋል።
የብሔራዊ ኢኮኖሚ ሒሳብና ስታቲስቲክስ ዳይሬክተር አቶ ፈለቀ ደምሲሶን በበኩላቸው፤ የሳተላይት ሥርዓቱ በግል እና በመንግስት ኢንቨስትመንቶች ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ ክፍተቶችን በመለየት የንግድ ሚዛንን ይለካል። ከዚህም ባለፈ ቱሪዝምንና የወጪ ንግድን ለማሳደግ ይረዳል ብለዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10 ቀን 2015 ዓ.ም