አዲስ አበባ፡- የሁለተኛ ደረጃ የእንግሊዘኛ ቋንቋ መማሪያ መጻሕፍትን ወደ ቪዲዮ በመቀየር የኦንላይን ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ::
በትምህርት ሚኒስቴር የአይሲቲና ዲጂታል ትምህርት ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ዘላለም አሰፋ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ያሉ የእንግሊዘኛ ቋንቋ መማሪያ መጻሕፍትን ወደ ቪዲዮ በመቀየርና ዲጂታላይዝ በማድረግ በስርዓተ ትምህርቱ(ካሪኩለሙ) መሰረት የኦንላይን ትምህርት እየተሰጠ ነዉ:: እንዲሁም ከቅድመ መደበኛ እስከ 8ኛ ላሉ ክፍሎች መሰረታዊ ክህሎቶች ላይ በማተኮር የእንግሊዘኛ ቋንቋ የኦንላይን ትምህርት እየተሰጠ ይገኛል::
እንደ ዶክተር ዘላለም ገለጻ፤ ትምህርቱ የሚሰጠው እንደ መደበኛ ሳይሆን ለመደበኛ ትምህርቱ አጋዥ እንዲሆን ነው:: የኦንላይን ትምህርቱ ጥሩ ይዘቶች ያሉት እና በአለምአቀፍ ደረጃ ጥሩ የሚባሉ እንደ ብሪቲሽ ካውንስል ያሉ ተሳትፈውበት የተዘጋጀና የሚተላለፍ ነው::
ለርን ኢንጊሊሽ(learn Engilish)የተሰኘው የኦንላይን ትምህርት ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር እንደሚሰጥ ጠቁመው፤ተማሪዎች ያለምንም ክፍያ በቀላሉ በእጅ ስልክ ወይም በኮምፒውተር ትምህርቱን በነጻ አውርደው መከታተል እንደሚችሉ ገልጸዋል::
በገጠር አካባቢ ለሚኖሩና ኢንተርኔት ማግኘት ለማይችሉ ተማሪዎች የተቀረጹ ትምህርቶችን በሲዲ በማድረግ የሚሰጣቸው ሲሆን፤ በፕላዝማ እና ትምህርት ቤት ውስጥ ባሉ የኮምፒውተር ላብራቶሪዎች በመጠቀም ትምህርቱን መከታተል እንደሚችሉ ገልጸዋል::
የትምህርትን ጥራት ከሚጠብቁ ነገሮች ዋነኛው ትምህርትን በቴክኖሎጂ መደገፍ እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር ዘላለም፤ የኦንላይን ትምህርቱ የተማሪዎችን እንግሊዘኛ ቋንቋ የመናገር ፣የመስማት ፣የማንበብ እና የመጻፍ ክህሎቶችን በማሳደግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ ተማሪዎች https://learnenglish.moe.gov.et የሚለውን ድረገጽ በመጎብኘት ትምህርቱን መከታተል እንደሚችሉ ተናግረዋል::
አጠቃላይ የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ረገድ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ የሚናገሩት ዶክተር ዘላለም፤ ተማሪዎች የሚያጋጥማቸውን የመጽሐፍት እጥረት ለመቅረፍም ሁሉንም የመማሪያ መጻሕፍቶቻቸውን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ካዘጋጀው ዲጂታል ላይብረሪ ማግኘት እንደሚችሉም ጠቁመዋል::
ዲጂታል ላይብረሪው ብዙ ተማሪዎች እየተጠቀሙበት እንደሆነ ገልጸው፤ ሁሉም የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ዲጂታል ላይብረሪውን https://elearn.moe.gov.et ብለው በመግባት በነጻ መጠቀም እንደሚችሉ ጠቁመዋል::
ትምህርትን በቴክኖሎጂ የመደገፍ ሂደት ላይ አሁን ላይ እንደ ችግር ሊነሳ የሚችለው አብዛኛው ተማሪዎች በገጠር አካባቢ የሚኖሩ በመሆኑ የኢንተርኔት ማግኘት ችግር ሊገጥማቸው መቻሉ እንዲሁም የእጅ ስልክ ወይም ታብሌት በማስፈለጉ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ዘላለም፤ በየትምህርት ቤቱ አነስተኛ የኮምፒውተር ላብራቶሪ ቢኖር ችግሩን መቅረፍ እንደሚቻልም ጠቁመዋል::
ባንኮች፣ለትርፍ ያልተቋቋሙ የእርዳታ ድርጅቶች፣ወላጆች፣የልማት ድርጅቶች እና ነጋዴዎች ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣት በሚችሉት አቅም ትምህርት ቤት ድረስ ወርደው ለተማሪዎች ውድ ያልሆኑ ታብሌቶችን በመግዛት እገዛ እንዲያደርጉና ትምህርትን በቴክኖሎጂ ለማገዝ የሚደረገው ጥረት አካል እንዲሆኑ ዶክተር ዘላለም ጥሪ አቅርበዋል::
መዓዛ ማሞ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8 ቀን 2015 ዓ.ም