ወጣት ዘለቀ ተስፋ ይባላል። ትውልዱም ሆነ እድገቱ ከባህርዳር ከተማ ወጣ ብላ በምትገኘው ጎንጅ ቆለላ ወረዳ ቅዱስ ገብርኤል ቀበሌ ወሸራ ማርያም በምትባል አካባቢ ነው። በትምህርታቸው ጎበዝ ከሚባሉ ተማሪዎች መካከል እንደነበረ የሚናገረው ወጣቱ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሲገባ ህክምና የማጥናት ህልም እንደነበረው ያነሳል። ይሁንና የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ውጤቱ ጥሩ የሚባል ቢሆንም ህክምና ማጥናት የማያስችል በመሆኑ የሚወዳቸውን ፊዚክስና ማትስ ትምህርቶች የበለጠ ተግባራዊ ሊያደርግበት በሚችልበት ዘርፍ መርጦ አዳማ ዩኒቨርሲቲ አመለከተ።
እናም ጥያቄው ተቀባይነት አግኝቶ ከአዳማ ዩኒቨርሲቲ በሜካኒካል ኢንጅነሪንግ ትምህርት ክፍል ገብቶ በ2013 ዓ.ም ተመረቀ። ዩኒቨርሲቲ ቆይታው ከጠበቀው በላይ ጥሩ የሚባል እንደነበር የሚያወሳው ይህ ወጣት በተለይ እንደእሱ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎችን የመስራት ተሰጥኦና ተነሳሽነት ያላቸውን ተማሪዎች በማበረታት ረገድ ይደረግላቸው የነበረው ድጋፍ የሚደነቅ እንደነበረ ያነሳል።
ከእነዚህም መካከል ዩኒቨርሰቲው ከጂአይዜድ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የፈጠራ ሥራ ውድድር አንዱ መሆኑን ጠቅሶ፤ በውድድሩ ላይም ማጨጃ ማሽን በመስራት ከተመረጡ ተፎካካሪዎች መካከል ሰባተኛ ደረጃን በመያዝ እውቅና አግኝቷል። ከተመረቀ በኋላ ግን በተማረበት የሙያ ዘርፍ እንዳሰበው ቶሎ ሥራ ማግኘት አልቻለም። የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ቢያመለክትም በለስ አልቀናውም። በዚህ ግን ተስፋ አልቆረጠም፤ በሙያው ሥራ እስከሚያገኝ ድረስ በሚል አዲስ አበባ በራይድ ሹፌርነት ተቀጥሮ ለአንድ ዓመት ያህል ሠራ።
ይህ ግን ገቢ ከማግኘት ባሻገር ሕይወቱን የሚቀይር ሆኖ አላገኘውም። በመሆኑም ወደ ተወለደበት እና ያደገባት ባህር ዳር ከተማ በመመለስ ከአንድ ጓደኛው ጋር በመሆን የብሎኬት ማምረቻ ከፈተ። ወጣት ዘለቀ ከተማረበት ሙያ ውጪ ሥራ ለመጀመር ምክንያት የሆነውን ነገር ሲያነሳም ‹‹ዩኒቨርሲቲ በነበርንበት ወቅት የተለያዩ ስልጠናዎችን መውሰዴ በየትኛውም ዘርፍ ውጤታማ መሆን የምችልበትን ሥነ-ልቦና በማዳበሬ ነው›› ይላል። የከተማዋን ክፍተት አይቶ በዘርፉ ሥራ መጀመሩ ከወዲሁ ተስፋ ሰጪ ምልክቶች እንዳይ አድርጎኛልም ባይ ነው።
ማምረቻ ቦታ ተከራይተው በ200 ሺ ብር ካፒታል መነሻ ብር በመያዝ እየሠራ መሆኑን የሚገልፀው ወጣት ዘለቀ፤ ግማሽ መንፈቀ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ምርታቸው ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን ይገልፃል። በአሁኑ ወቅት በቀን 1ሺ 200 ብሎኬቶችን የማምረት አቅም ላይ መድረሳቸውንም ይናገራል። ‹‹ምንም እንኳን የኮንስራክሽን ሥራ እንደአገር ቢቀዛቀዝም የተሻለ ደንበኞችን የምንቀበልበት ሥርዓት በመፍጠር እና ከደንበኞች የምናገኘውን ምክረ ሃሳብ ላይ በመመርኮዝ ጥራት ያለው ምርት የምናመርት በመሆኑ ተቀባይነታችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው፤ አሁን ላይ ከነባሮቹ አምራቾች ባልተናነሰ ምርታችን ተፈላጊ እየሆነ ነው›› ሲልም አብራርቷል።
በአሁኑ ወቅት ለዘጠኝ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻላቸውን የሚገልፀው ወጣት ዘለቀ በተለይ የምርት ፍላጎት በሚጨምርበት ወቅት የተቀጣሪዎቹ ቁጥርም ከፍ እንደሚልም ያስረዳል። ወደፊት ከአነስተኛ የብሎኬት ማምረቻ ወደ ከፍተኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የመሸጋገር አላማ ሰንቆ እየሠራ መሆኑን ይናገራል። በተለይም በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ኮንክሪት ማምረት ሥራ ለመግባት እቅድ ይዞ እየሠራ መሆኑን አመልክቶ፤ ጎን ለጎንም እንደእሱ በተለያዩ ሙያ ተመርቀው ሥራ ላጡ የከተማዋ ወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ፍላጎት ያለው መሆኑን ነው የጠቆመው። ከዚያ ባሻገርም በተመረቀበት ሙያ በተለይ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ የሚሆኑ የማምረቻ መሣሪያዎችን ዲዛይን የሚያደርግ ኩባንያ ለመክፈትም ህልም እንዳለው አጫውቶናል።
ይሁንና በተለይ አሁን ካለው የዋጋ ንረት ጋር ተያይዞ የማምረቻ ግብዓቶች ዋጋ በየጊዜው የሚጨምር እና እንደልብ ለማግኘት አደጋች ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወደ ኢንዱስትሪ የመሸጋገር ህልማቸው ላይ አሉታዊ የሆነ ጫና እንዳያሳድር ስጋት እንዳለው አልሸሸገም። ‹‹በየጊዜው እየናረ የመጣው የግብዓት ዋጋ እንዲሁም በምንፈልገው መጠን ባለማግኘታችን አሁን እንኳን በምናመርተው ምርት ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ነው ያለው፤ ይህ ችግር በአፋጣኝ የሚወገድበት ሁኔታ ካልተፈጠረ ወደፊት ለያዝነው የማደግ ትልማችንም ስጋት ይሆንብናል የሚል ፍርሃት አለኝ›› ሲል ይገልፃል።
ወጣት ዘለቀ እንደሚለው፤ የራስን ሥራ ፈጥሮ የራስን የገቢ ምንጭ ማሳደግም ሆነ ለአገር ረብ ያለው ሥራ ከመሥራት አኳያ ወጣቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ የቁርጠኝነት ችግር ይስተዋላል። ሁሉ ነገር ተመቻችቶላቸው እና ተደራጅተው ሥራ የጀመሩትም ቢሆኑ በአገሪቱ ከሚፈጠረው ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር ጋር ተያይዞ ቶሎ ተስፋ የመቁረጥ ነገር ይታያል። በሌላ በኩል ደግሞ የራሳቸውንም ሆነ ውጫዊ ተግዳሮቶችን ሰብረው ማለፍ የቻሉ ወጣቶችን የሚያበረታታ ሥርዓት አለመኖሩ የሥራ ፈጣሪዎች ቁጥር በሚፈለገው ደረጃ እንዳያድግ አድርጎታል።
በዋናነትም በየመንግሥት ተቋማቱ ያለው ኋላቀር ሥርዓትና በቢሮክራሲ የታጠረ አገልግሎት ተጠቃሽ ችግር መሆኑን ያነሳል። ወጣቶች የሥራ እቅድ ወይም ፕሮጀክት ይዘው በሚመጡበት ጊዜ የንግድ ፍቃድ ፤ የፋይናንስ እና የቴክኒክ ድጋፍ በመስጠት ረገድ ሰፊ ክፍተት መኖሩን ይናገራል። የራሱን ተሞክሮ በማንሳት ‹‹እኔ ይህንን ሥራ ለመጀመር የንግድ ፍቃድ ለማውጣት ብቻ ሦስት ወር ነው የፈጀብኝ›› ይላል። ይህም ባሰበው ጊዜ ሥራውን እንዳይጀምር ያደረገው መሆኑንና ለተጨማሪ ወጪ የዳረገው መሆኑን ያመለክታል።
እነዚህን ሁሉ ውጣ ውረዶች አልፎ ሥራ ቢጀምርም የማምረቻ ቦታ በማግኘት እንዲሁም ደግሞ የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው በማገዝ ረገድ በከተማ አስተዳደሩ የሚደረገው ድጋፍ እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ነው ያነሳው። ‹‹ እኔ ሥራ ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ እዚህ እስከምደርስበት ድረስ የሥራ ሂደቴን መጥቶ ያየ፤ የሚጎድለኝን ጠይቆ ድጋፍ ያደረገልኝ አንድም የመንግሥት አካል የለም›› ይላል። ይልቁኑም በመንግሥት ተቋማቱ ያለው ውስብስብ እና ምቹ ያልሆነ አሠራር አምራቹን ተስፋ እያስቆረጠና ከሥራው እንዲወጣ የሚገፋፋ መሆኑን ያመለክታል።
ከዚህም ባሻገር እንደማንኛውም ጀማሪ ሥራ ፈጣሪ ከባንኮች የብድር አቅርቦት ማግኘት ባለመቻላቸው እቅዳቸውን ባሰቡት ልክ ማሳካት እንዳላስቻላቸው ወጣት ዘለቀ ያነሳል። ‹‹የገንዘብ እጥረት ሁሌም ያለ ችግር ነው። አሁን ላይ በእጅ የሚቆይ ገንዘብ ባይኖርም የአንዱን ምርት ገቢ ለቀጣዩ መሥሪያ እንዲሆን እየተደረገ እንጂ ቢዝነስን ይዞ የሚያበድር አንድም ባንክ አላገኘሁም። የምናስይዘው ንብረት ከሌለን በቀር ከባንክ ብድር ማግኘት የማይታሰብ ነው›› ይላል። በተለይ ለሁለት ተደራጅተው ለሚሠሩ ወጣቶች ባንኮች የሚያበድሩበት ሥርዓት ያለመኖሩ እንደእሱ ሥራቸውን ማስፋፋት ለሚፈልጉ ሥራ ፈጣሪዎች ተስፋ አስቆራጭ እንደሆነባቸው ያመለክታል። እስካሁንም ሥራውን ማዝለቅ የቻለው እቁብ በመግባትና ከግለሰቦች በመበደር እንደሆነ ይጠቅሳል።
ባንኮቻችን ቢዝነስን እንደ መያዣ አድርገው ማበደር ቢጀምሩ በጣም ጠቃሚ እንደሚሆንም ያመለክታል። ከዚሁ ጎን ለጎን ማሽን በበድር የሚገዙ ድርጅቶችን ማስፋፋት እንደሚገባ ይናገራል። ‹‹እኔ ለምሳሌ የመስሪያ ማሽኖችን የገዛሁት ዋሊያ ካፒታል ከሚባል የዕቃ ብድር ተቋም ነው። ግን ደግሞ እንደእኔ ይህንን ዕድል ያላገኙና ወደ ሥራ ያልገቡ ብዙ ወጣቶች አሉ፤ በመሆኑም እንዲህ ዓይነት አገልግሎት የሚሰጡ የብድርና ቁጠባ ተቋማትን ማስፋፋት ይገባል›› ሲል አመልክቷል።
በሌላ በኩል ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ እንዲሁም የውሃ እጥረት ለሥራቸው መጓተት ዋናው ምክንያት እንደሆነባቸው ያነሳል። ‹‹የመብራት መቆራረጥ ምንም ሊያሠራን አልቻለም፤ በተለይ የመስሪያ ውሃ ማግኘት ትልቅ ፈተና ነው የሆነብን። በዚህ ምክንያት የአንድ ቀን ምርት ዋጋ ማጣት ማለት በጣም ከባድ ነው። በተዋዋልንበት ጊዜ ማድረስም ይጠበቅብናል። ባለን አቅም ደግሞ ውሃም ሆነ ለመብራቱ ጄነሬተር ተገዝቶ በየጊዜው ነዳጅ እየተሞላ የሚሠራው ሥራ ትርፋማ አያደርገንም። የቱንም ያህል ደንበኞች ብናፈራም የምንሠራው ሥራ ትርፉ ወጪ ከሆነ ሥራችን ቀጣይነት አይኖረውም›› ሲል አብራርቷል። በመሆኑም መንግሥት ይህንን ዓይነት የመሠረተ ልማት ፍላጎቶችን የማመቻቸት ኃላፊነቱን ሊወጣና የዘርፉን ተዋናዮች ሸክም ሊቀንስ እንደሚገባ ነው ያስገነዘበው።
ዝግጅት ክፍላችንም የወጣቱን የሥራ ትጋትና ለመለወጥ ያለውን ትልም በማየት የሚመለከታቸው የሥራ አካላት በዘርፉ የሚነሱትን ቁልፍ ችግሮች ለመፍታት ቁርጠኛ መሆን እንዳለበት ማሳሰብ ይወዳል። በተለይ እንደወጣት ዘላቀ ዓይነት ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው ሥራ ሳይንቁ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የተረፉ ወጣቶችን መደገፍ እና ማገዝ ይገባል የሚል መልዕክት ማስተላለፍ ይወዳል።
‹‹እነዚህ ሁሉ ችግሮች ቢኖሩብኝም ፤ የሚያጋጥሙኝ ፈተናዎች በፅናት በማለፍ ለሌሎችም የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሌ ግን ከምንም በላይ ያስደስተኛል›› የሚለው ወጣት ዘለቀ፤ በተለይ እንደእሱ በተለያዩ ሙያዎች ሰልጥነው ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የወጡ ሥራአጥ ወጣቶች ከእሱ ተሞክሮ በመነሳት ሥራ ሳይንቁ ራሳቸውን ከጥገኝነት ሊያወጡ እንደሚገባቸው ይናገራል። በተለይ በተማሩበት ሙያ ብቻ ሥራ ለማግኘት በሚል ጊዜያቸውን በከንቱ እያቃጠሉ ያሉ ወጣቶች ያሉበት አገራዊ ነባራዊ ሁኔታ መረዳት እንደሚገባቸው፤ በአሁኑ ወቅት ምን ብሠራ ያወጣኛል የሚለውን ነገር ማጤንና አዋጭና ቶሎ ገቢ የሚያገኙበትን ዘርፍ መቀላቀል እንዳለባቸው ይመክራል።
ነገሮች የሚሳኩት መውደቅ የማንፈራ ከሆነ ነው። በተለይ ወጣት መቁረጥ የለበትም ! ጤናም ጉልበትም እውቀትም የሚኖረው በወጣትነት ዕድሜ ስለሆነ መሮጥ ያለብን ይሄኔ ነው። ብንወድቅም ደግሞ ራሳችንን አንስተን ድጋሜ መሮጥ ነው እንጂ ተስፋ መቁረጥ በፍፁም አያስፈልግም። በቃ ሕይወት ይቀጥላል፡፡’’
በዚህ ረገድ መንግሥትም እና የሚመለከታቸው አካላት አዳዲስ ምሩቃንንም ሆነ ሥራ ሳይንቁ ተደራጅተው መስራት የጀመሩ ወጣቶችን በተጨባጭ ውጤታማ ሊያደርጓቸው የሚችሉ ሥልጠናዎች በተከታታይነት የሚያገኙበትን ሁኔታ መፍጠር እንዳለባቸው ያስገነዝባል። ከዚህም በተጨማሪ ለመነሻ የሚሆን የፋይናንስ ድጋፍ፤ የማምረቻ ቦታ እና የገበያ ትስስር የሚፈጠርበት ሁኔታ ማመቻቸትም ወሳኝ መሆኑን ይገልፃል።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6/2015