ምስክር ጌታነው ሚዲያና ፕሮሞሽን መጋቢት 9 ቀን 2011 ዓ.ም በብሔራዊ ቴአትር ‹‹ኢትዮጵያ ዛሬ እና ነገ›› በሚል ርዕስ ባዘጋጀው የዲስኩር፣ የወግ፣ የግጥም እና የሙዚቃ መርሐ ግብር ላይ ከቀረቡ የአዕምሮ ምግብ ንግግሮች የመጋቢ ሐዲስ እሸቱን እና የዲያቆን ዳንኤል ክብረትን አስነብበናችኋል። በዚሁ ዝግጅት ላይ ከቀረቡት ለዛሬው የአርቲስት ሰርጸ ፍሬስብሐትን እናስነብባችሁ። ትናንት ትዝታ ነው፤ ከዚች ቅፅበት ያለው ወደ ኋላ ያለው በሙሉ ትዝታ ነው። ዛሬ ይኸው እየኖርነው ያለነው የምናሰላስለው ነው።
የሰው ልጅ በሁለት ነገር ብቻ የታደለ ይመስለኛል። አንድ ተስፋውን አርቆ እንዲያይ፤ ሁለት ትዝታን እንዲያሰላስል። ሁለት ተሰጥኦዎች አሉት። ዛሬን መኖር ግን እንስሳትም ይችላሉ። ምንም የሚያቅታቸው አይደለም፤ ሁለቱ ናቸው በጣም ከባዶቹ ለሰው ልጅ ብቻ የተሰጡት። ሁለቱ አቅሞቹ ትዝታና ተስፋ ናቸው። ሰው ዛሬ ዝም ብሎ የሚመሰረት ወይም ከዜሮ የሚገነባ አይደለም። በአጋጣሚ ሆኖ ከኋላው ጋር በእጅጉ የተሳሰረ ፍጥረት ነው። ስለዚህ ወደኋላ መሄዱ የማይቀር ባህሪው ነው። ትምህርት ቤት እንሄዳልን እንላለን፤ ቀለም ለመቁጠር ይመስላል።
ትናንት ከነበረ የተሰበሰበ፣ የተደመረ ነገር ጋር ለመገናኘት ነው የምንሄደው፤ ሌላ ምንም አይደለም። ለምሳሌ ቀላል ነገር ምርምር ልትሠሩ ወይም መመረቂያ ፅሑፍ ልታዘጋጁ መጀመሪያ ጥያቄዎቻችሁን ካደላደላችሁ በኋላ። ሁለተኛው ምዕራፍ ላይ የሚያሠራችሁ ተዛማጅ ጽሑፍ(ሌትሬቸር ሪቪው) የሚባል ክፍል አለ። ይሄ ክፍል ምንም ነገር አይደልም የሚያወራ፤ በዚህ ርዕስ ዙሪያ ያሰላሰሉ ሰዎች ከኔ በፊት ምን ፅፈዋል?፣ ከእኔ በፊት የነበሩ ሰዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ምን አግኝተዋል? የሚለውን ወደኋላ ሄዶ ማጥናትነው። ሌላ ነገር አይደለም። ሄዶ ሄዶ ትምህርት ራሱ ያለፈን ነገር መተንተኛ እና ማገናኛ ድልድይ ሆኖ ነው የሚታሰበው።
ሌላ ነገር የለውም በውስጡ። ኦርቴጋገት እንደሚለን አሁን ባለ ኦራተም በሚባል እንስሳና ድሮ በነበረው ኦራተም እንስሳ መካከል ልዩነት የለም። ለምን ቢባል ከአያቱ ምን አድርጎ ነበር እያለ የሚያሰላስለው ነገር የለውም። ስለዚህ ያም በዋሻ ኖረ ጫካ ውስጥ ገባ ለመኖር የሚሆነውን ነገር እየቀጠፈ በላ ኖረ! ይሄ ኑሮ ይቀጥላል። ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ እንስሳት ዝምድናቸውም ይጠፋቸዋል። ምንም የታሪክ ግንዛቤ የላቸውም። የታሪክ ግንዛቤ የህያዊት፣ የነባቢት የልባዊት ነፍስ ስጦታ ነች።
ይሄ ባይኖረንና ልባውያን ባንሆን ኖሮ ወደኋላ ሄደን ማሰላሰል አንችልም ነበር። በመሬታዊው፣ በእሳታዊው፣ በውሃዊው ተፈጥሯችን አይደለም ይሄን ያገኘነው። በዚህ ሦስት ተብላ በረቂቅ በተፈጠረችልን ነፍስ ምክንያት ያገኘነው ነው። ይሄ ኢትዮጵያ ያላት ትልቅ ዕውቀቷ ነው። ሰውን መርምራ ሰብ ብላ በመጥራቷ ምክንያትነው ከሰባት ነገሮች የተሠራ ከሚለው የፈረንጆቹ ትንታኔ የተለየ ነው። መጀመሪያ ከሰው ለመጀመር የእነዚህ የሦስት ባህሪያት ጥምረት እንጅ የገዛዘፉት መሬትም፣ ውሃም፣ አፈርም፣ እሳትም፣ አንበሳም ያላቸው ይመስለኛል።
በአካልም ይበልጡናል አዕምሮ አካባቢ የተሰጠን ነገር ግን እንድናስበ አድርጎናል። ወደኋላ እንድንመለስ ማለት ነው። ኋላን መተረክ በተለይ ከ18ኛው ከፍለዘመን በኋላ ያለው የሚያጣላ እየሆነ ነው። ዛሬ ላይ ለመድረስ በጣም ፍርሐት አለን። ዛሬን ለማውራት ምክንያቱም በምን ተረዳኸው ይመጣል። ኋላንም ለመተንተን እንዲሁ ዓይነት በጣም ትልቅ ስቃይ ይሆናል። ለዚህ ነው የታሪክ ሰዎች ሁልጊዜየሚሽኮረመሙት።
አይታችሁ ከሆነ ብዙ የታሪክ ምሁራን ይሄ ሁሉ የታሪክ ተንታኝ መድረክ ላይ እየወጣ ሲዘባርቅ አይታችሁ ለምን ዝም ትላላችሁ? ሲባሉ አይ ታሪክ “ዊንዶ ፔሬድ” አላት ይላሉ። ያስ ጊዜ መቼ ነው የሚያልቀው? ሲባሉ አሁን ሰነድ መሰብሰቢያ ነው፣ ከዚያም መተንተኛ ነው… ከዚያም ከዱሮው ሳይላቀቁ ብዙ የታሪክ ጸሐፍት ዛሬን ይፈሩታል። የኋላውም በጥርጣሬ ውስጥ የተተወ ነው። አንድ ገፅ መጻፍ በጣም ከባድ ነው። ስለዚህ የሚያስፈራው ታሪክ ነው። ግን ደግሞ የሰውልጅ ከታሪክ ሊላቀቅ አይችልም። በምንም ተአምር ሊሆን አይችልም፡፡
አንዱ መሰረት ታሪክ ስለሆነ። ስለዚህ ስልጣኔዎቻችን ምን ቋንቋ ይዘው አናገሩን አልኩኝ። ሦስት እቅድ አወጣሁላቸው ወይም ደግሞ እይታ። አንደኛው የመጀመሪያው አክሱማዊው ዘመናችን ምን ነበር ሊነግርን የፈለገው? ሀውልቱ በተተከለበት አምድ ምን ሊያሳስበንና ምን ሊነገርን ፈለገ የሚለውን ሃሳብ መጣልኝ። በዚያ ውስጥ አንድ ጥሪ አገኘሁ ያንን ሃሳብ የፍልስፍና ምሁሩ ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ ‹‹አንትሮሞርፊክ ሲቪላይዜሽን›› ይለዋል። አክሱም ሰውን መሰረት ያደረገ ስልጣኔ ነው ይላል።
ወደ ላይ የቆመው ያ ሀውልት ደረቱን ቀና አድርጎ ወደላይ እንዲህና እንዲያ ነኝ ብሎ የሚናገር ነው። ተርጓሚና አናጋሪ ቢያግኝ እንደዚያ ብሎ ነበር እራሱን የሚገልጸው። ሰብዓዊነት አንጅ ምንም ዓይነት የሃይ ማኖትም ይሁን የመለከት ጥሪ የሌለው አንድ የሰውነት ትረካ ነው ይለናል። በዚህ ውስጥ አንድ አብረን የምናየው ነገር ‹‹ዲኮሬትድ›› የሆነ ውስጡ በጣም ሀብትን ሊያሳይ የሚችል ቁስ ጥራት ደግሞ እናያለን። ያንን ‹‹ዘኮይቴስት ፎር ማቴሪያል ፐርፌክሽን›› የቁሳዊ ትክክለኛነት ጥሪ ነው ይለናል። እውነት ነው። እውነትም ሀውልቱን አሁን ሄደን ብናናግረው ይሄንን ይነግረናል።
በጊዜው ኢትዮጵያ የነበረችበትን ደረጃ ለትልልቆቹ ከዓለምም ታላላቅ ከነበሩት አክሱም ሦስተኛው ነበረች ብለው ለሚነግሩን እንደነ ማኑ ዓይነት ፀሐፊዎች ትርጉም የሚሰጥ ነው። አክሱም በዓለም መወዳደር ጥሪዋ ነበር። ያንን መስላ ያንን አክላ የቆመች ይመስለኛል። ከዚያ ሁለተኛው ጥሪ ይሰማል። በሀብት ለምልክት ባስቀመጥነው ነገር ብቻ የምንቆም ሰዎች አይደለንም። እምነት መጣ ክርስትና በመሃል ደረሰባት ወይም ደረሰላት አክሱምን። ሁለተኛውን ሃሳቧን ልትቋጭ እያለ ዛጉዌ ይመጣና ያንን የእርሷንና የራሱን ሃሳብ ጨምሮ ‹‹ስፕሪችዋል ፐርፌክሽን›› ይደርሳል።
ይሄን ደግሞ ‹‹ሲኦሴንትሪክ ሲቪላይዜሽን ቲዮሎጅካል ሲቪላይዜሽን›› ይለዋል ዶክተር ዳኛቸው። አንድ ትሁት የሆነ መስቀል ከላዩ ላይ የተሸከመ እንደውም ከላይ ቀጥ ብሎ የነበረውን ገልብጦ የለም ከላይ ወደታች ዝቅ የሚል «ሀምብል» የሆነ ‹‹ሲቪላይዜሽን›› ይመጣል። በዚህ ወስጥ ብዙ ማሰላሰል ብዙ መመሰጥ ይልቅ ብዙ ሃሳብ፣ ብዙ ድርሰት፡ ብዙ የአዕምሮ ብቃቶች ታያላችሁ ሁለተኛው ላይ። ተከታይ ይመስላል። በኢትዮጵያ ስልጣኔ ውስጥ ተከታታይነት የላቸው ይላሉ ተችዎች። እኔ ተከታታይ ናቸው ነው የምለው።
እየቋጩ ነው የሚሄዱት። እያስተሳሰሩ ነው የሚሄዱት። እንደውም ወደውጭ የነበረውን ጥሪ ወደ ውስጥ ያደርገዋል የላሊበላውን። ይሄንን ይዘን እንቆያለን። ሁለቱም በመስል የተገለጸ ነገር አላቸው በሀውልት በድንጋይ። ሁለቱም ትዕምርታቸው የተለያየ ትንታኔ ይወጣዋል። ሦስተኛው እንግዲህ በመሃል የራሱን ምልክት ያላስቀመጠው የሸዋው ነው። ወይም የሶሎሞናዊው ስርዎ መንግሥት። እሱ ይመጣና እነዚህን ሃሳቦች በሙሉ ወደ ስነ ፅሑፍ ያሳድ ጋቸዋል። የነበሩትን አርክቴክቸራል ጥበባትበፅሑፍ ሊገልጻቸው ይሞክራል።
ድርሰት እየበዛ ይመጣል። እንደውም ቀለብ እየተሰፈረላቸው ኢትዮጵያዊ የሆነ አስተሳሰብን ከትርጉም ነፃ አውጥተው ከኢትዮጵያ በፈለቀ አተረጓጎም የሚፅፉ ደራሲያንን እንዲፈጠሩ ያደርጋል። ይሄ ሦስተኛው ነው። በዚህም አላበቃም ሄዶ ሄዶ ጎንደር ሁለቱን ያዋህዳል። አንድ መንፈሳዊ የሆነውን ስልጣኔ ሁለት ቅንጡ የነበረውን የአክሱማውያንን የሀብት ምልክት ያመጣና ጎንደር ቤተ መንግሥት ውስጥ ሁለቱን ይመሰርተዋል። ጎንደር የሁለቱ ውሁድ የሆነ ነገር አርክቴ ክቸራል ዓይን ወይም የጥበብ እይታ ያለው ሰው ገብቶ ቢያይ ከመሐል ቤተመንግሥቶቹ፤ ከዳር ዙሪያውን ትልልቆቹ አድባራት ከበውት ያያል። ይሄ መንፈሳዊና ሰብዓዊ የሆነውን ስልጣኔ ሁለቱን የማስታረቅ ቅንጡ ስልጣኔ ነው የምናየው ጎንደር ላይ። ሰብዓዊ የሆነው ስልጣኔ ነው የማየው።
ይሄ ሰዋዊ የሆነው ጨዋታውም እንዳይቀርብን ወደ ዳር ስትሄዱ እነ እንኮይ መስክን የመሰሉ የዛሬውን የከተማ መልክ ያሲያዙ ህይወቶች ደግሞ ታያላችሁ። ስለዚህ ህይወት፣ መንፈስ ስልጣኔ አንድ ላይ ተሳስረው ታገኛላችሁ።
አኔ የአባቶቻችንን ይህን ትልቁን ነገር አይደለም ያየንላቸው። ይሄን የሠሩበትን አዕምሯቸውን አይደለም የመረመርንላቸው። ከዚህ ቤት ነበር የተወለዱት፣ እንዲህ ዓይነት ቋንቋ ነበር የሚናገሩት። በቤተሰባቸው በደንብ ከቆጠርን ቅማንቴ ናቸው። አንዴ እንዲህ ናቸው፤ ሌላ ጊዜ እንዲያ ናቸው እያልን ነው ስንቆጥር የነበረው። እስከአሁን ድረስ የዘር ቆጠራ ላይ ነው እንጅ ሰው በኢትዮጵያ ምድር ላይ የፈጠረውን አንድ ተግባር አይደለም እየመረምርን የነበረው። በተለይም ከ1960ዎቹ ወዲህ የተፈጠረብን አስተሳሰብ የአባቶቻችንን ጥበብ እንዳናይ አድርጎናል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 19/2011