ስታወራ፤ ስትጫወት ከአንደበቷ የሚወጡት ቃላት እጅጉን ያስደንቃሉ። ፊቷ ፈገግታ አያጣውም። የተመለከቷት ሁሉ ደስተኛ መሆኗን ያስባሉ። እሷ ግን በፈገግታዋ ውሎዋን፣ በሳቋ ሀዘኗን የምትረሳ ወጣት ናት።
የሕይወቷ ፈተና የጀመረው ገና የአምስት ዓመት ልጅ ሳለች ነበር። እናቷን በሞት ያጣችው በክርስትናዋ ማግስት ነበር። ቤተሰቦቿ አብዮት ይሏታል። አርሶ አደር ናቸው። የተወለደችው በኦሮሚያ ክልል ጫንጮ ከተማ ነው። እድገቷ ግን በአንድ ቦታ ላይ የተወሰነ አልነበረም። ምክንያቱ ደግሞ አካል ጉዳቷ ነው።
አብዮት ሳህሌ አካል ጉዳተኛ የሆነችው ለጨዋታ በወጣችበት ወቅት አተላ በሚደፋበት አካባቢ ላይ በመውደቋ ነው። በዕለቱ በቦታው እንቅልፍ ይዟት ለሰዓታት አሳለፈች። ይህንን የተመለከቱ የአካባቢው ነዋሪዎች ከወደቀችበት ቢያነሷትም በቀላሉ እግሮቿ መቆም አልቻሉም ነበር። ዝልፍልፍ ካለችበት አንስተው ወደቤቷ አደረሷት።
በወቅቱ ‹‹ልክፍት›› ነው በመባሉ ጸበልና መሰል ነገሮች ተሞከረላት። በባህሉ ያላመኑ ደግሞ ሕክምና ያስፈልጋታል ብለው በእርሱም ታየች። ይህ ሁሉ ሙከራ ግን አብዮትን ከመሬት ከፍ አላደረጋትም። እንደትናንቱ በእግሮቿ ለመቆም አልቻለችም። እንደልቧ ከእድሜ ጓደኞቿ ጋር መቦረቅ አልሆነላትም። ከዚያ ይልቅ ከቤት ልትውል ተገደደች። ብዙ ነገሮችን በሞከሩት ቤተሰቦቿ ጫናም አካል ጉዳቷን ተቀብላ መኖር እንዳለባት አመነች። ዓመታትን ከመሬት ሳትነሳ እንደህጻን እየተንፏቀቀች አሳለፈች። የእድሜ እኩዮቿ ትምህርት ቤት ሲሄዱ እርሷ ከቤት እንድትውል ሆነች።
አብዮት በአንድ አጋጣሚ አዲስ አበባ የመምጣት ዕድሉን አገኘች። ይህ አጋጣሚም ወደ ቼሻየር ሰርቪስ ኢትዮጵያ ማዕከል አደረሳት። ቼሻየር የዊልቸር፣ የክራንችና ሰው ሰራሽ አካል ፣ በእግራቸው ቅርጽ የተለያዩ ጫማዎችን በማምረትና ሌሎችንም ድጋፎች በማድረግ አካል ጉዳተኞችን የሚያግዝ ተቋም ነው። በቼሻየር ሰርቪስ የመናገሻ ተሃድሶ ማዕከል እንድትገባ መሆኑ በመጠኑም ቢሆን ተስፋ ሰጥቷታል። ለተወሰኑ ዓመታት ቆይታ መጀመሪያ በዊልቸር ከዚያም በ ‹‹ብሬስ›› ድጋፍ መቆም ቻለች። በክራንች የምትሄድበት እድልም ገጠማት።
በቼሻየር ኢትዮጵያ ማዕከል ብዙ አካል ጉዳተኞች ይስተናገዳሉ። የተሻላቸውና መፍትሄ ያገኙ ለሌሎች ስፍራውን ይለቃሉ። እርሷም ህክምናዋን ጨርሳ ገጠር ወደቤተሰቦቿ እንድትመለስ ሆነች። በቤተሰቦቿ ቤት የተመቻቸ ነገር አልነበረም። የትም ስለማትወጣ ማንንም ማግኘት አትችልም። በዚህም ሁልጊዜ ትናደድ፣ ታዝን ነበር። አንድ ቀን ግን ይህ ታሪክ ሊቀየር ግድ አለ። ይህም ዳግም አዲስ አበባ የተመለሰችበት የጫማ ቅየራው አጋጣሚ ነበር።
ከጫማ ቅየራው በኋላ አብዮት ረዕቡ ገበያ ወደምትገኘው እህቷ ዘንድ አመራች። ረዕቡ ገበያ አነስተኛ የገጠር ከተማ ናት። በዚህች ስፍራ ትምህርት ቤት ይገኛል። መማር የዘወትር ምኞቷ ነበርና አብዮት መጀመሪያ አባቷን፣ ከዚያም እህቷን እንዲያስተምሯት ደጋግማ ጠየቀቻቸው። ሁለቱም ፈቃደኛ አልሆኑም። እርሷ ግን ይህንን ሀሳብ በፍጹም ለመቀበል አልወደደችምና ሌላ አማራጭ ማፈላለግ ጀመረች።
የአንድ ብር በረከት
አብዮት ሁሌም ቤተሰቦቿን እንደቀደመች ነው፤ አትችይም ያሏትን ችላ ታሳያቸዋለች። ለትምህርቷ ዓላማ የጸጉር ሥራን በመለማመድ በአንድ ሰው አንድ ብር እየተቀበለች አጠራቅማ ደብተርና እስኪርብቶ እንዲሁም አልባሳቷን እያሟላች ቆየች። የአጎቷ ልጅ ከባለቤቷ ተጣልታ ለትምህርት ቤቱ ቅርብ በሆነ ቦታ ተከራይታ ተቀምጣለችና እርሷ ጋር በመሄድ ረዕቡ ገበያ ትምህርት ቤት በመግባት የአንደኛ ክፍል ትምህርቷን አሀዱ አለች።
አብዮት ምንም እንኳን ከአጎቷ ልጅ ጋር ብትኖርም ራሷን ችላ ነው የምትማረው። እግሯን እያመማት በእጅ ሙያዋ እየተጠቀመች ዓመቱን አጠናቃለች። ሁለተኛ ዓመቱን ግን በመካከላቸው አለመግባባት በመፈጠሩ ዳግም እህቷ ቤት መመለስ ግድ ሆነባት። ክረምትን ከእርሷ ጋር አሳለፈች ።
አብዮት ለችግሮች እጅ ሰጥታ አታውቅም። ሁልጊዜ መፍትሄ እንዳለ ታስባለች። ለዚህም ይመስላል የመማር ህልሟን ላለማጨናገፍ ከአንዱ ቤት ወደ አንዱ የዞረችው። ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ ክፍል አጎቷ ከገጠር ወደ አነስተኛዋ ከተማ በመምጣቱ ከእርሱ ጋር ሆና ተማረች።
መማር ለእርሷ መውጫዋም፤ መታያዋም፤ የአዕምሮ ዕረፍቷ ነው። አጎቷ ጋር የምታገኘው ግልጋሎት ሁለት ነገር ብቻ ነበር። የመጀመሪያው መጠለያ ሲሆን፤ ሁለተኛው የእለት ጉርሷ ነው። አጎቷ ሀብታም የሚባል ነው። አምስት ልጆች አሉት፤ ለእነርሱ የፈለጋቸውን ሲያሟላላቸው ለእርሷ አንድም ቀን ለትምህርት ቤት የሚሆን ወጪ እንኳን አግዟት አያውቅም። የራሷ ጥረት ስኬት ላይ እንደሚያደርሳት ታምናለችና የአንድ ብር በረከቷን ተጠቅማ እስከ አምስተኛ ክፍል ዘልቃለች።
የመዳን ጉጉት
ከአጎቷ ጋር መጀመሪያ የወጣችው የአምስተኛ ክፍል ትምህርቷን የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት ፈተናን ልክ እንደጨረሰች ነበር። ለዚህ ያበቃት ደግሞ ጎረቤት የምትኖር ሴት ንግግር ነው። ይህች ሴት ዘወትር ስለ እንጦጦ ማርያም ጸበል ፈዋሽነት ታወራታለች። በዚህም ጉጉቷ ጫፍ ደረሰና ወደስፍራው ለመሄድ ተሰናዳች። አባቷንም ወደዚያ ቦታ እንዲወስዷት ጎተጎተቻቸው ። ምላሻቸው የሚያረካ አልነበረም።
‹‹እናቴ ብትኖር ኖሮ›› ስትላቸው አባት ውስጣቸው ተነካና ፈቃደኝነታቸውን ሰጧት። ፈተናዋን ስትጨርስም ከአጎቷ ልጅ እና ከእህቷ ጋር ወደጸበል ቦታው ላኳት። መጀመሪያ ከወር በኋላ የአጎቷን ልጅ እናቷ መጥታ ወሰደቻት። እህቷም ትምህርት ሊጀመር ሲል ትታት ሄደች። እርሷ ግን አመጣጧ ለድህነት ነውና በጽናት ከዚያው ከረመች።
ቀለብና የቤት ኪራይ እየተላከላት ለስድስት ወር ያህል ተቀመጠች። ይህ ነገር ግን እስከመጨረሻው የዘለቀ አልነበረም። አንድ ቀን በአጎቷ በኩል ምንም እንደማይላክላት ተነገራት። አማራጭ አልነበራትምና ጸበሉን አቋርጣ ወደ አጎቷ ቤት ተመለሰች። ግን የአምስተኛ ክፍል ትምህርቷን እስክትጨርስ ብቻ ነበር የቆየችው። ቤተሰቦቿ ለእርሷ እንዳልተጨነቁ ስለተሰማት ትታቸው በመጥፋት በራሷ ጥረት ያሰበችውን ለማሳካት ቆረጠች፤ አደረገችውም።
አሁን የትም ብትሆን ለፍታ ማደር እንደምትችል ታውቃለችና ማቄን ጨርቄን ሳትል ወደ አዲስ አበባ ዳግም ተመለሰች። ከለመደችው የእንጦጦ አካባቢም ኑሮዋን ቀጠለች። መጀመሪያ ነገሮች እንዳይከብዷት የምታውቀው ሰው የሦስት ወር ኪራይ ከፍሎላት ሄደ።
ኪራዩ ለብቻዋ የምትኖርበት ቤት አልነበረም። ጸበልተኞች በአንድ ቤት አድረው የሚከራዩት ፍራሽ ነው። እናም ለአንድ ፍራሽ በወር 30 ብር እየተከፈለም ይተኛበታል። ሦስት ወሩ ካለቀ በኋላ ደግሞ በአጋጣሚ የተዋወቀቻት ጸበልተኛ ነበረችና ወደ እርሷ ቤት አቀናች። ይህ አጋጣሚ ደግሞ ሌላ ተጨማሪ ዕድል አቀበላት። ጸበል የምትጠመቀው ‹‹ጉስቋም ማርያም›› ነበርና ከአንድ መልካም ሰው ጋር አገናኛት። ይህ ሰው የቤት ኪራዩን ሳያቋረጥ የሚከፍልላት ነበር።
የስም ለውጥ
አብዮት ከቤተሰብ ጠፍታ ሳምንታትን ብታሳልፍም አንድም ቤተሰብ ሊያያት አልመጣም። በዚህም በጣሙን ተበሳጨች። እንዳያገኝዋትም ስሟን ሳይቀር ቀየረች። አሁን ብዙዎቹ ጓደኞቿ የሚያውቋት በአዲሱ ሀና በሚለው ስሟ ነው። ንዴቷ ግን እስከመጨረሻው አልዘለቀም። ምክንያቱም ‹‹አለሁልሽ ›› የሚል ወገን ያስፈልጋታል። አንድ ቀን ቤተሰቦቿ በመጡበት ጊዜ በሯን ከፍታ አስገባቻቸው።
‹‹እንሂድ›› ሲሏት ግን አልተቀበለችውም። ምክንያቱም መምጣቷ ለፈውስ ነው። እነሱም ብዙ መጫን አልፈለጉም። ከዚያ ይልቅ የአቅማቸውን እየላኩ መደገፉን አመኑበት። የአብዮት ፈተና ዛሬም እንደቀጠለ ነው። አብራት የተከራየችው ሴት እጇ አይፈታም። እሷ እንደምትለው ‹‹ገብጋባ›› የሚሏት አይነት ነች። ቤተሰብ የሚልከውን ብቻ ሳይሆን ጸጉር ሰርታ ያመጣችው ገንዘብ ሳይቀር የቤት ጎዶሎ መሙያ እንዲሆን ትፈልጋለች። ይባስ ብሎም ለአካባቢው ሰው ታሳጣታለች። ይህ ደግሞ አብዮትን ጥገኛ እንደሆነች አስመሰላት። ‹‹እኔ እየቻልኳት ለምን›› በሚል ቁጭትም ትታት ወጣች። እንደቀደመው በ30 ብር የፍራሽ ኪራይም መኖሩን ተያያዘችው ።
ቦታው የጸበል ስለሆነ ምግብ ይሉት አያሳስብም። ማደሪያ ግን ስቃይ ነበር። በዚህ ሳቢያ አብዮት ብዙውን ጊዜ ሳትበላ ትውላለች ፣ ታድራለችም። ይህ እውነት ግን ስሜቷን ነክቶት አያውቅም። ሁልጊዜ የምታዝንበት ጉዳይ ቢኖር ማደሪያ ማጣቷ ነው። ቅዝቃዜው ከእግር ህመሟ ጋር ተዳምሮ ስቃይዋን ያበረታዋል። መውጣት መውረዱና የቤቱ ርቀትም እንዲሁ ፈተና ነው። በተለይም እንጦጦና ክረምት እጅግ አሰቃቂ ሕይወትን እንድታሳልፍ አስገድደዋታል።
አንድ ቀን ግን ይህን ቋጠሮ የሚፈታላት እድል አገኘች። የቤት ኪራይ እየከፈለ ሰዎችን የሚያግዝ ሰው ድንገት ከጸበል ቦታ አጋጠማት። ይህን ሰው ቤት እንዲከራይላት ጠየቀችው። ሰውዬውም ያሰበችውን ሞላላት። የተከራየላት ቤት ግን በሩ የሸራ ነበር። ያም ሆኖ ብዙ አልፈተናትም፤ ይልቁንም ወደዚያ መሄዷ መፍትሄ ሆነላት። በአንድ ወር የእግሯ ብሬስ ወልቆ መንቀሳቀስ ጀመረች። በወቅቱ ወደጸበል ስፍራው የሄደችበት ምክንያት ነበራት። አንደኛው ቅዝቃዜውና ኑሮው ክብደት፣ ሌላው ደግሞ ቃሊቲ ‹‹ጉስቋም ማርያም ›› አካባቢ አዲስ ጸበል ፈልቋል መባልን መስማቷ ነው።
አብዮት ቤተሰቦቿ ከጎኗ ባለመሆናቸው ብዙ ጎድሎባታል። ትምህርቷን አቋርጣለች። እድናለሁ ብላ የሄደችበትና ተስፋ የሰጣትን ጸበልም አቁማለች። ከሁሉም ግን ብቸኝነቷ ያስከፈላትን ዋጋ መቼም አትረሳውም። በአንድ ወቅት እንዲህ ገጠማት።
በአካባቢዋ አንድ የአዕምሮ ህመምተኛ ነበረች። በድንገት ከባሏ ጋር ሊደበድቧት መጡ። እርሷም ለጊዜው ፖሊስ ጠርታ ተረፈች። ሆኖም በዚያ መቆየቷ ስጋት ሆነባት። ቤቱንም አካባቢውንም ለቃ ወጣች። በዚህ ምክንያት የጠላችውን ቦታ ዳግም ተመለሰችበት። ኑሮዋም በዚያ ቀጠለ።
እንዳለፈው ጸበል ቦታ አልሄደችም። ሰው ቤት ተጠግታ መኖር ያዘች። የቤቱ ባለቤት ሦስት ልጆች አሉት። ልክ እንደሰራተኛ ነው የሚያዛት፤ አካል ጉዳቷን ሳያስብ የተለያዩ ሥራዎችን ያሠራታል። በዋናነት የምትሰራውም ልጆችን መንከባከብ ነው። እንጀራ ትጋግራለች፤ ምግብ ታበስላለች፤ ልብስም ታጥባለች። ነገር ግን ክፍያ ይሉት የላትም። ቅባት እንኳን አይገዛላትም። መውደቂያ ስለሌላት አምስት ዓመታትን አሳልፋለች።
ቤቱ በርካታ እድሎችን ነፍጓታል። ዛሬ ድረስ የምትቆጭበት ግን አንዱ ነው። የመነጽር ሥራ ሙያ ስልጠናን። ስልጠናው በየምስራች የመነጽር ሥራ ድርጅት የሚሰጥ ነበር። ለሁለት ዓመታትም ሙሉ ወጪ ይሸፈንበታል። አስጠጊዎቿ ግን ይህን ሊፈቅዱላት አልቻሉም። ምክንያቱም እንደሠራተኛ ማን ያገለግላቸዋል። ለጊዜው ምክንያታቸው ‹‹ይርቃታል፣ አካልጉዳተኛም ነች›› የሚል ነበር። ሆኖም እውነታው ርቀቱ ሳይሆን የልጆቻቸው ጉዳይ ነበር።
በጊዜው አብዮት በጣም አዝና ነበር። ድርጊታቸው ግን አስተምሯት አልፏል። ‹‹ለእኔ›› ብላ መስራት እንዳለባትም አስገንዝቧታል ። ቆየት ብለው የመጡ እድሎችን መጠቀም የቻለችውም ከአንዲህ አይነቱ አጋጣሚ በመማሯ ነው።
አዲስ ሥራ በአዲስ ተስፋ
አብዮትና ጓደኞቿ የቆዳ ሙያ ስልጠና አገኙ። ከሥልጠናው በኋላ የሚሰሩበት ብርም በብድር መልክ ተሰጣቸው። ወቅቱ ብዙ እድሎቿን ከነጠቋት ሰዎች ቤት የነበረችበት ጊዜ ነበርና ‹‹ገንዘቡን ስጪን›› ከሚል ንትርክ እንድትገባ አድርጓታል። ወደፊት ከየትም አምጥታ ልትከፍለው ስለማትችል ‹‹እንቢኝ›› አለቻቸው። በዚህ አለመግባባቱ ሰፋና ከቤት ልትወጣ ግድ ሆነ።
ከቤት እንደወጣች አማራጭ አልነበራትም። በተሰጣት ገንዘብ ቤት ተከራየች። ብዙም ሳትቆይ ግን በሰለጠነችበት ሙያ የምትሰራበት አጋጣሚ አገኘች። በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው እንዲሰሩ እድሉ ተመቻቸላቸው። ሁሉም አካል ጉዳተኛ ናቸው። እግራቸው ላይ ጉዳቱ በስፋት የሚታይ። ሆኖም የአዕምሯቸው ጥንካሬ ብርታታቸው ሆነና በስፌት መኪና እስከመስራት ደርሰዋል።
የአብዮት ጉዳት በእግሯ ብቻ ሳይሆን በእጇም ላይ ይስተዋላል። ያም ሆኖ ‹‹አልችልም›› ብላ አታውቅም። ‹‹ካልለፋሁ የትም አልደርስም›› ብላ ስለምታምን ጠዋት ማታ ከእንጦጦ ሥራዋ ድረስ መመላለስ ግድ ይላታል። ሁሌም በአውቶቡስ እስከ አራት ኪሎ ትመጣና ቀሪውን መንገድ ደግሞ በእግሯ ትሄዳለች። የሥራ ቦታዋ በተለምዶ ‹‹ሳንፎርድ›› ከሚባል ትምህርት ቤት አካባቢ ነው።
በራሷ ጥረት እዚህ ደረጃ ላይ መድረሷ የሚያስደስታት አብዮት፤ በታክሲ አልያም በአውቶቡስ ለመጠቀም እጅጉን ትቸገራለች። ሁሌም ለመንቀሳቀስ ብሬሱን በእጇ መስበርና መዘርጋት ይጠበቅባታል። በዚህ ምክንያት ከባድ እቃ ይዛ መንቀሳቀስ አትችልም። እንዲያም ሆኖ ደስታዋን መነጠቅ አትፈልግም። ከአንዳንድ ሰዎች ጋር ሰቆቃ የበዛበትን ወሬ ማውራትና መስማት አትሻም። ሁሌም ‹‹ተመስገንን›› ልታጋራቸው ትፈልጋለች። ይህ ደግሞ መራር ጉዞዋን በደስታ እንድትቀይረው አስችሏታል።
‹‹አካል ጉዳተኝነት አለመቻል አይደለም። አካል ጉዳትን ተቀብሎ ወደፊት መራመድ ነው›› የሚል እምነት ያላት አብዮት፤ አካል ጉዳተኞች ማንነታቸውን ሳይደብቁ አስፈላጊውን የአካል ድጋፍ በመጠቀም ራሳቸውን መለወጥ ይችላሉ። ይህንን ካላደረጉ ደግሞ ከመለመን ውጪ አማራጭ አይኖራቸውም። እናም ተስፋቸው፣ የራሳቸው ጥረት ነውና የተሰጣቸውን እድል ሁሉ ተጠቅመው ከ‹‹አልችልምነት›› ወጥተው ተፈጥሮን ጭምር መገዳደር አለባቸው ስትል መልዕክቷን ታስተላልፋለች።
በሴትነት ላይ አካል ጉዳት ተጨምሮ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ብታልፍም አብዮት ሁሌ የተሻሉ ነገሮችን ታልማለች፤ ተስፈኛም ነች። ነገ ቢሳካላት መሥራት የምትፈልገውም የራሷን ሱቅ ከፍታ በዚሁ በሰለጠነችበት ሙያ ትርፋማ መሆን ነው። እንደምታሳካውም ታምናለች።
አሁን ከጎኗ ‹‹አለሁልሽ›› የሚላትን ትፈልጋለች። ጥንካሬ የሚመጣው ከሰው ጋር አብሮ በመሥራት ነው፤ መደጋገፍና ልምድን ማጋራት ሲኖር ነው። ስለዚህም ለእኔ ልምዶቼ፤ እዚህ ላይ የመድረሴ ምስጢር በተለያዩ አጋጣሚዎች የቀረብኳቸው ሰዎች ናቸው ሁሉም ይህንን ቢያደርግ በማለትም ትመክራለች።
አብዮት በቀን 50 ብር እየተከፈላት ትሰራለች። ምንም ቀን ካልቀረች ደግሞ በወር 1200 ብር ይደርሳታል። ይህን ብር ለቤት ኪራይ፤ ለምግብና ትራንስፖርት ታውላለች። ይህ ገንዘብ ባለመሆኑም የማትበላባቸው ጊዜያት ይበረክታሉ። ይህንን ሀዘኗን ግን ሁሌም በፈገግታ መሸፈን ልምዷ ነው። ይህ እውነታም ግን ለሌሎች ‹‹ድረሱልኝ›› የሚል መልዕክትን ያደርሳል።
አብዮት ቢያንስ ቤት ብታገኝ ብዙ ነገሮች ይቀሉላታል። እናም በዚህ አጋጣሚ አንድ ነገር ማለት እንፈልጋለን። የቀበሌ አመራሮች የቀበሌ ቤት ካላችሁ ከችግሯ ብትታደጓት። ሥራውን አክባሪና የአገር ጫና ላለመሆን የሚጥርን ሰው መደገፍ ደግሞ ሥራ አጥነትን መቀነስ ብቻ ሳይሆን የአገር አበርክቶን ማስፋት ነውና ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2015