ቤርሳቤት በለጠ ትባላለች። ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ውስጥ ቦሌ ሚካኤል አካባቢ ሲሆን ዘንድሮ 19 ዓመቷን ይዛለች። ሳቂታና ደስተኛ ነች። ጥሩ የንባብ ባህል ያዳበረች አንባቢ ስትሆን ቤተ መጽሐፍት ውስጥ ያጠመደ አያጣትም።
እኛም ያገኘናት አብርሆት ቤተ መጽሐፍት ውስጥ ነው። ሰውነትን የሚያጠነክሩና ቅርጹን የሚያስተካክሉ ስፖርቶችን ትወድና አዘወትራ ትሰራለች። በኮሌጅ ትምህርት ባይደገፍም በትምህርት ቤት ሰልጥኖ የወጣ ሰዓሊ ከሚስለው በላይ የስእል ችሎታ አላት።
በእርሳስ የተጀመረ የስዕል ችሎታዋን ጭቃ ከለር፤ ውሃ ቀለም እያለች በየደረጃው በማሳደግ ሙሉ በሙሉ በቀለም ወደ መሳል አሸጋግራዋለች። ገቢም በሚያስገኝላት ደረጃ አድርሳዋለች። አሁን ላይ እንደውም ለኢቢኤስ ቴሌቪዥን ፕሮግራም መክፈቻ የሚሆን ታላቅ ስዕል እየሳለች ትገኛላች።
‹‹ይሄን ማድረግ የረዳኝ ኢንተርኔት ነው። በከፍተኛ ደረጃ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ነኝ›› የምትለው ወጣት ከዚሁ ከኢንተርኔት ባገኘችው ዕውቀት በዓለም ላይ ታዋቂ የሆነችና የኢትዮጵያን ስም የምታስጠራ የኬክ አርቲስት የመሆን ህልም አላት። ህልሟን እውን ለማድረግ እንቅስቃሴ ውስጥ ከገባች ከረምረም ብላለች። ቤርሳቤት እንደምትለው የኢንተርኔት ዕውቀትን መሰረት አድርጋ የባህር ውስጥ ጥናት ወይም ተመራማሪ የመሆንም ዕቅድ በውስጧም ሰንቃለች።
‹‹በአብዛኛው ወጣቶች በመደበኛው ትምህርት ውስጥ የሥራ ፈጣሪ እንድንሆን ሳይሆን የተቀጣሪነትን አስተሳሰብ እንድንይዝ ተደርገን ነው የሰለጠነው። አሁን በተያዘው የትምህርት አቅጣጫ በቀጣዩ ትውልድ ይሄ አካሄድ ይለወጣል የሚል ዕምነት አለኝ›› የምትለው ወጣቷ ሥራ ፈጣሪ በማያደርግ ትምህርት ሥርዓት ያለፈውም ሆነ ለማለፍ የተዘጋጀው ወጣት ለውጡ ዕውን እስኪሆን ጊዜውን በከንቱ ማሳለፍ የለበትም የሚል ዕምነት አላት። ኢንተርኔትና ሌሎች አማራጮችን ተጠቅሞ የራሱን ሥራ መፍጠር ይችላል። ትምህርት, ሙያ ወይም ተጨማሪ ችሎታዎችን ጊዜና ዕድሜ የማይገድበውንም ትምህርት እስከፈለገው ድረስ ባሻው መስክ መቀጠል ይችላልም ባይ ነች።
ቤርሳቤት የ12ኛ ክፍል ትምህርቷን አምና በ2014 ዓ.ም ነው ያጠናቀቀችው። ሆኖም ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የሚያስችላት ነጥብ ለማምጣት ጠንክራ ስትሰራ ብትቆይም ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ ማምጣት አልቻለችም። ይሄን ፍላጎቷን ወላጆቿም ቢሆኑ የሚጠብቁት ነበርና ነጥብ ባለማምጣቷ ደስተኛ አልሆኑም። ቅርም ተሰኝተውባታል።
‹‹እኔ ግን ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት አለማምጣቴን ራሴን በምፈልገው መስክ ለማብቃት እንደሚያስችል መልካም አጋጣሚ ነው የወሰድኩት›› የምትለው ወጣቷ ነጥብ አምጥታ ዩኒቨርሲቲ አለመግባቷን በሰማች ማግስት ምኞቶቿን ለማሳካት ጥረት ማድረጓን ትናገራለች። ወጣቷ ለሌሎች ወጣቶች በተለይም ባለፈው ዓመት የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤት ላልመጣላቸውና ይሄንኑም እንደመጨረሻ ዕድል ቆጥረው በየቤታቸው ለተቀመጡ በኢንተርኔት የሚገኝ ዕውቀትን እንዲጠቀሙና በየመክሊታቸው እንዲሰማሩ መነሳሳት ትሆናቸዋለች በሚል ተሞክሮዋን ማጋራት ወድደናል።
የ19 ዓመቷ ወጣት ቤርሳቤት በለጠ እንዳ ጫወተችን ዩኒቨርሲቲ ገብታ በአንድ ትምህርት እንድትመረቅና ሥራ እንትይዝላቸው በብርቱ ይፈልጉ የነበሩት ወላጆቿ በራሷ እንድትቆም ስለሚፈልጉ አይደግፏትም። አሁን ላይ እሷን ከፍለው ለማስተማር የሚያስችል ገንዘብም የላቸውም። ቤት ገዝቶና ሰርቶ የሚያኖር አቅም ስለሌላቸው በግለሰብ ኪራይ ቤት ነው የሚኖሩት። እንደውም በቅርቡ ዋጋው ቀነስ ያለ ቤት ለማግኘት ቀደም ሲል ይኖሩበት ከነበረው ከቦሌ ሚካኤል ሰፈር ወደ ቡልቡላ ማርያም አካባቢ ለቅቀው ሄደዋል።
‹‹ይሄ ለእኔ በፊት ከነበርንበት ቤት የበለጠ ለትራንስፖርት ወጪ የሚዳርግ ነው። ቢሆንም በአብርሆት የምፈልጋቸውን መጽሐፎች ስለማገኝ ትራንስፖርት ባጣ እንኳን በእግሬ እመጣለሁ እንጂ አልቀርም›› የምትለው ወጣቷ ከመጽሐፍትና ከኢንተርኔት የሚገኝ ዕውቀት ያለምንም ወጪ ምን አልባትም እዚህ ግባ በማይባል ወጪ ሰዎች እራሳቸውን በራሳቸው በማስተማር በዕውቀት ሊበለጽጉባቸው የሚያስችሉ መንገዶች እንደሆኑም ታወሳለች። ከነዚህ በተገኘ ዕውቀት ለገዛ ራስ የሥራ ዕድል መፍጠርና የገቢ ምንጭ ለማግኘት የሚያስችሉ ሥራዎች ላይ መሰማራት እንደሚቻልም ታነሳለች።
እሷ ንባብን ባህሏ ያደረገችውና ኢንተርኔትን የምትጠቀመው ይሄንኑ ታሳቢ አድርጋ እንደሆነም ትናገራለች። ‹‹ወጣቶች አንባቢ እና የኢንተርኔት ተጠቃሚ መሆን ብዙ ጥቅም እንደሚያስገኝ ማወቅ አለብን›› የምትለው ቤርሳቤት ስለኢንተርኔት ጥቅምም ታብራራለች። እንደማብራሪያዋ አሁን ያለንበት ዓለም ዘመናዊ ነው። የዘመናዊነት መገለጫ ደግሞ ቴክኖሎጂ ነው። ቴክኖሎጂ ማለት ሌላ ምንም ሳይሆን ኢንተርኔት ነው። አሁን ላይ በዓለማችን ብዙ ነገሮች የሚከወኑት በኢንተርኔት ነው። ኢንተርኔት የምንፈልገውን መረጃ ማግኘት ያስችለናል።
ኢንተርኔት ገንዘብ ያስተላልፋል። የምንፈ ልገውን ትዕዛዝም ማስተላለፍ ያስችለናል። ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ ሌላ ሩቅ ዓለም ላይ ካሉ ሰዎች ጋር ተግባቦት ማድረግም ያስችላል። የራስ ገቢ ማስገኛ ሥራ መፍጠርና ወደ ተፈለገው ሙያ መግባትና ወደ ምንፈልገው አቅጣጫ ለመሄድም የሚያስችል ነው። በመሆኑም ወጣቶች ዕውቀት፤ ገንዘብ፤ ሥራ፤ የትምህርት ዕድልና ሌሎች አማራጮችን በማያገኙበት ጊዜ እንደሚያግዛቸውና የግድ የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ መሆን እንዳለባቸው መገንዘብ እንዳለባቸው ትመክራለች።
‹‹አሁን ላይ ለኔ ተስፋ የሆነኝ ኢንተርኔት ነው። ግን ኢንተርኔት በራሱ ተስፋ ሳይሆን ተስፋ የሚሆነኝን ነገር ሰጥቶኛል ለማለት ነው›› የምትለው ወጣቷ በተለይ በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ ነጥብ ባጣችበት ወቅት የደረሰላት አሌንታዋ እንደሆነም ደጋግማ ትናገራለች። እንደምትለው 12ኛ ክፍል አጠናቃ ውጤት ሳይመጣላት ሲቀር መሥራትና መሆን የምትፈልገውን በቀጥታ ያስመረጣት ኢንተርኔት ነው።
በኢንተርኔት የተለያዩ የኬክ ዓይነቶች መኖራቸውን ተረዳች። አሰራራቸው እንዴት እንደሆነም አየች። ኬክ ለመሥራት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችንም አወቀች። ስለዚሁ የኬክ ሥራ የመሰልጠን ፍላጎትም አደረባት። ኢንተርኔት በዚሁ ላይ ተመስርታ በምትፈልገው የኬክ ሥራ እንድትሰለጥን አስቻላትና በዛው 12ኛ ክፍል ባጠናቀቀችበት ዓመት የኬክ ሥራ ለመግባት ወረቀት ያስፈልግ ነበርና በኢንተርኔት ያገኘችውን ዕውቀት ትምህርት ቤት ገብታ በተግባር በማዳበር ዲፕሎማዋን ያዘች። የኬክ ሥራ ትምህርቱን ከተማረች በኋላ ደግሞ በቅርብ ቀናት የምትመረቅበትን የምግብ ዝግጅት ስራ ትምህርትን ቀጠለች።
ወጣቷ በኬክ ስራ በዓለም ላይ እውቅና አገሯን የምታስጠራ ‹‹ኬክ አርቲስት›› የመሆን ህልሟን ለማሳካት ከኢንተርኔት የቀሰመችውን ዕውቀት በመጠቀም ቀጥላለች። ‹‹ኬክ በሚፈለገው ደረጃ ለማምረት አንድ ኬክ ለመጋገር የሚያስችለውን ሰዓት መጠበቅ ግድ ነው›› የምትለው ወጣቷ ስፖንጅ ኬክ በሦስት ደቂቃ በመሥራት ጀምራ የተለያዩ ኬኮች መጋገር ያስችላትን ብቃት ለማግኘት ስትለማመድ መቆየቷንም ነግራናለች።
ወጣቷ እንደምትለው ኬክ ሲባል ፀጥ ብሎ ክሬም የተቀባ ይመስለናል። አብዛኞቻችንም ይሄንን ነው የምናውቀው። ሆኖም በውጪው ዓለም ሙያው እንዲህ ዓይደለም። ‹‹ኬክ አርቲስት››ማለት የተለያዩ ዕውነት የሚመስሉ ሌሎች በርካታ ኬኮችን መሥራት ማለት ነው›› ትላለች። እንደ ወጣቷ የተለያዩ እንስሳት ዓይነቶችን፤ ቦርሳን፤ ሰውን የሚመስል ግን ደግሞ ዕውነተኛ ኬክ የሆኑ ኬኮችን መሥራት ደረጃ ላይ መድረስ ነው። ለዚህ ግን ጥሩ ስዕል ሰዓሊና ቅርጻ ቅርጽ አዋቂ መሆን ያስፈልጋል።
‹‹እኔ ደግሞ ከህፃንነቴ ጀምሬ እንዲህ ዓይነት ቅርፃ ቅርጾችንና ስዕሎችን እሰራ ነበር። በሁለት ዓመት ከሚበልጠኝ ወንድሜ ጋር እየተፎካከርን እነዚህን የሚመስሉ ስዕሎችን እንሰራ እንደነበር አስታውሳለሁ›› ስትልም ይሄ ከህፃንነት ጀምሮ እያዳበረች የመጣችው ልምዷ ኬክ አርቲስት የመሆን ፍላጎቷን የበለጠ በማሳለጥ ከስኬት ለማድረስ እንደሚረዳት ታወሳለች።
ሙያው በውጭው ዓለም ተፈላጊ የሚያደርግና ዳጎስ ያለ ገቢ የሚያስገኝ ነውም ባይ ነች። ሆኖም አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ በትላልቅ ኢንተርናሽናል ሆቴሎች ኬክ አርቲስቶች ቢኖሩም ጥቂት ናቸው። ብቃታቸውም ቢሆን እንደውጭው ዓለም የመጠቀነው ማለት አይቻልም። የግብዓት አቅርቦት እንደተፈለገው ባለማግኘታቸውም ሆነ አቅርቦቱ የሚጠይቀው ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ የሚሰሩት ሥራ በኢንተርኔት እንዳየችው ሰርክ ከምናውቀው ኬክ የተለየ፤ ማራኪና ሳቢ፤ እንዲሁም አነጋጋሪ አይደለም። ሆኖም ወጣቷ እነዚህንም ኬክ አርቲስቶች አግኝታ ልትተዋወቃቸውና ከነሱ ልምድ ለማግኘትም ሞክራለች። ከነሱ ከኢንተርኔት ካገኘችው በተጨማሪ ‹‹ኬክ አርቲስት›› መሆን የሚፈልግ ሰው ሊገለገልባቸው የሚችሉ የተለያዩ ዓይነት የኬክ ቀለሞች እንዲሁም ለኬክ መስርያ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን ተጋርታለች።
እነዚህ ግብዓቶች አገር ውስጥ መኖራቸውንና ህልሟን ዕውን ለማድረግ እንደሚያስችሏት ተገንዝባለች። ‹‹ኬክ አርቲስት መሆን የሚፈልግ ሰው ለኬክ ስለተሰሩ የሚበሉና ሰው ላይ ጉዳት የማያስከትሉ ቀለሞች አጠቃቀም ዕውቀቱ ያለው መሆን አለበት። ኬክ ለመሥራት የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች ግንዛቤ ያለው መሆን ይኖርበታል ትላለች። እንዳከለችልን ኬክ አርቲስት ለመሆን የሚፈልግ ሰው በፔይስትሪ (በኬክ ሙያ) መማርና ሰልጥኖ መመረቅ አለበት። በተጨማሪም ስዕል ጎበዝ መሆን አለበት።
እሷ ስዕል ትስላለች። ጎበዝም ናት። የሳለችው ስዕል በቤተሰቧ ዙርያ፤ እንዲሁም በጓደኞቿ የገበያ ዕድል እያገኘ መጥቶ በቅርቡ አንድ ቤተክርስቲያን ባወጣው የጨረታ ማስታወቂያ በመወዳደር ሦስቱ ስዕሎቿ በ11 ሺህ ብር ሊሸጡላት በቅተዋል። አሁን ደግሞ ለኢቢኤስ ቴሌቪዥን የዋናው ቻናል መክፈቻ የሚሆን ድንቅ ስዕል ለማቅረብ እየሰራች ትገኛለች። ይሄ ስዕል ሲደርስ ደግሞ ዳጎስ ያለ ገቢ ሊያስገኝላት እንደሚችል ትገምታለች።
ቤርሳቤት ከኢንተርኔት ባገኘችው ዕውቀት የባህር ውስጥ ጥናት ተመራማሪ የመሆን ዕቅድም አላት። ‹‹የባህር ውስጥ ባዮሎጂስት በባህር ውስጥ የሚኖሩትን ዝርያዎች እንዲሁም ስርጭታቸውን እና የዚህ ክስተት መንስኤ የሆነውን ይለያል። እንደዚሁም በእንስሳዎች መካከል እና በእነሱ እና በአካባቢያቸው መካከል ያለውን መስተጋብር ያጠናል›› ትላለች።
ወጣቷ እንዳወጋችን ይሄ የባህር ባዮሎጂ ጥናት በግሪኩ ጠቢብ በአርስቶትል ነው የተጀመረው። አርስቶትል በርካታ የአናሌል ዝርያ፣ ክሩሴሰንስ፣ ሞለስኮች፣ ኢቺኖዶርምስ እና ዓሳዎችን፤ ዶልፊኖች እና ዌል እንስሳት አጥቢዎች መስተጋብር መገንዘብ ችሏል። ሆኖም ባህር እንደስፋቱ ጥልቅ ምስጥር ያለው በመሆኑ በእሱ ያልተዳሰሱትን በሙሉ በጥናትና ምርምሯ የመሸፈን ዕቅድ አላት። ጥናቱን ካደረኩ በኋላ በዚህ ሙያ ዩኒቨርሲቲ ገብቼ የመመረቅ ዕቅድም አለኝ›› ትላለች።
ጥናቱ ሕይወት ያላቸው የባህር ውስጥ እንስሳት ላይ የሚደረግ ሳይንሳዊ ጥናት ነው ብላናለችም። እንደምትለው ትናንሽ ነፍሳት እንደ ስፖንጅ , ኑዲንጅች ወይም ማይክሮቦች በመመርመር እና ስለ ኒዩሮሳይንስ እና መድሃኒት ለመማርም ይረዳል ስትል ለወጣቶች ያጋራችውን ተመክሮ ቋጭታለች። እኛም የወጣቷ ህልም እውን እንዲሆን በመመኘት ጽሑፋችንን አበቃን።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን መጋቢት 29/2015