«ችግሩ በሁለት ወራት ውስጥ ይፈታል»የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሲዳማ ሪጅን
አዲስ አበባ፡- ለአራት ዓመታት የዘለቀው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ለበርካታ ችግሮች መዳረጋቸውን በሲዳማ ክልል የዳዬ ከተማ ነዋሪዎች ቅሬታ አቀረቡ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሲዳማ ሪጅን በበኩሉ ችግሩን ለመቅረፍ እየሠራ መሆኑንና በሁለት ወራት ውስጥ መፍትሄ እንደሚሰጥ አስታውቋል።
የዳዬ ከተማ ነዋሪ አቶ የሱፍ አሊ ከአራት ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ ወደከተማዋ የሚለቀቀው የኤሌክትሪክ ኃይል በሰዓታት ልዩነት ይቆራረጣል። ለረጅም ሰዓትም ይጠፋል ሲል ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አስተያየቱን ሰጥቷል።
በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ በአማካኝ ከአራት ጊዜ በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ያጋጥማል ያለው አቶ የሱፍ፤ በዚህም ምክንያት ማህበረሰቡ በከፍተኛ ምሬትና ችግር ውስጥ ገብቷል። ችግሩ ምግብ ለማብሰልም ሆነ በኤሌክትሪክ የሚከናወኑ ሥራዎችን ለመፈጸም አዳጋች ሆኗል ብሏል።
አሁን ላይ በሚቀርበው የተቆራረጠ ኃይል የተነሳ የከተማዋ ነዋሪ ኤሌክትሪክ እያገኘ ነው ማለት አይቻልም። ለረጅም ሰዓታት ጠፍቶ የሚመጣ በመሆኑ ችግሩን የሚመለከተው አካል መፍትሄ ሊሰጥበት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
ሌላኛው የዳዬ ከተማ ነዋሪ ወጣት መልካሙ ማርቆስ በበኩሉ፤ ወጥ የሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል ባለመኖሩ ምክንያት የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ አገልግሎት ለማግኘት ተቸግረናል ብሏል።
የግል ንግድ የሚሰሩ ግለሰቦች ሥራቸውን ላለማቋረጥ ሲሉ ጄኔሬተር ገዝተው እየሠሩ ቢሆንም የቤንዚል መግዣ ገንዘብ ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ ሥራቸውን ለማቆም እየተገደዱ መሆኑን ወጣት መልካሙ አስታውቋል።
ፀጉር ቤቶች፣ ስቴሽነሪና ጎሚስታ እንዲሁም በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ የንግድ ቤቶች በኃይል መቆራረጡ የተነሳ ለኪሳራ መዳረጋቸውንና ችግሩ ከፍተኛ የሕዝብ ምሬት መፍጠሩን ተናግሯል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሲዳማ ሪጅን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አበበ ዕድሉ በበኩላቸው፤ በክልሉ ካሉ 15 የኤሌክትሪክ ማዕከላት ከፍተኛ የሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ያለው የዳዬ ማዕከል ላይ መሆኑን ገልጸው፤ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ችግሩ በሁለት ወራት ውስጥ እንደሚፈታ ገልጸዋል።
የዳዬ ከተማ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ መሠረታዊ ችግር የኤሌክትሪክ መስመሩ ከይርጋለም ሰብስቴሽን ከወጣ በኋላ ዳዬ ከተማ እስከሚደርስ 110 ኪሎ ሜትር ርቀት ስለሚጓዝና በመሃል የሚያጋጥሙ መበላሸቶች ስለሚፈትኑት ነው ብለዋል።
ሌላኛው ምክንያት የሰብስቴሽን እጥረት በመፈጠሩ ነው ያሉት ኃላፊው፤ ከዳዬ ከተማ በተጨማሪ አለታ ወንዶ፣ ሀገረ ሰላምና ጭኮ ከተሞች እና ዙሪያቸው የሚገኙ 86 የገጠር ቀበሌዎች የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የሚያገኙት ከይርጋለም ሰብስቴሽን በመሆኑ ችግሩ መከሰቱን አስረድተዋል።
በ 86ቱ ቀበሌዎች የተዘረጋው የኤሌክትሪክ መስመር ዳዬ ከተማ እስኪደርስ በአንዱ ቀበሌ ላይ በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሠራሽ ምክንያት ብልሽት ሲያጋጥመው የኃይል መቆራረጡ ይከሰታል ብለዋል።
የችግሩን አንገብጋቢነት በመረዳት ለዳዬ ከተማ እራሱን የቻለ የተለየ የኤሌክትሪክ መስመር በ100 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተዘረጋ መሆኑን አቶ አበበ ገልጸዋል።
አቶ አበበ እንዳስታወቁት፤ የመስመር ዝርጋታው ሥራ በወሰን ማስከበር ምክንያት የተጓተተ ቢሆንም በሁለት ወራት ውስጥ የዳዬ ከተማ ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ችግር ይፈታል።
ኅብረተሰቡ የመስመር ዝርጋታው ሥራ እስኪጠናቀቅ ድረስ በትዕግስት እንዲጠብቅ አቶ አበበ መልዕከታቸውን አስተላልፈዋል።
አማን ረሺድ
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2015