የደቡብ ክልል ሀዲያ ዞና ዋና ከተማ ሆሳዕና ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረች ጉምቱ ከተማ ነች። ከአዲስ አበባ በስተደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ በ230 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ሆሳዕና፣ በአሁኑ ወቅት የሀዲያ ዞን ዋና ከተማ ሆና እያገለገለች ትገኛለች፡፡ የአካባቢው የንግድ ማዕከልም ናት፡፡
ከተማዋ ስፋቷ እየጨመረ እና የሕንፃዎች ብዛት እየተበራከቱባትም መጥታለች፡፡ ይህን የሚመጥን መሠረተ ልማት በማሟላት ረገድ ግን ውስንነት እንዳለባት ነዋሪዎቿ ይጠቁማሉ፡፡ ከከተማዋ ነዋሪዎች አንዱ የሆነው ወጣት ወንደወሰን መንሲዶ ከተማዋ እጅግ በሚያስደስት መልኩ እያደገች መሆኗን ጠቅሶ፣ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የመሠረተ ልማት ችግር እንደሚስተዋልባት ይናገራል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም የወጣቶች መዝናኛ ማዕከላት፣ የመንገድ እና የውሃ ችግሮች ይጠቀሳሉ፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በከተማዋ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች እየታዩ ነው ይላል፡፡
የከተማዋን የመንገድ መሠረተ ልማት ለማሟላት እና የሕዝብ መዝናኛዎችን ለመገንባት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች እጅግ የዘገዩ ናቸው የሚል እምነት አለው፡፡ ከከተማዋ ዕድሜ አንጻር ከብዙ አስርት ዓመታት በፊት መሟላት እንደነበረባቸውም ይጠቁማል፡፡ አሁን የመሠረተ ልማቶቹ ግንባታ መጀመሩም በአድናቆት ይመለከታል፡፡ በተለይም የ‹‹ጀሎ ደቀዬ››የሕዝብ መዝናኛ ፓርክ እና የቤተመጻሕፍት ግንባታ የከተማዋን ወጣቶች የመዝናኛ ችግር የሚቀርፍ መሆኑን ይገልጻል፡፡
ተማሪ ከበቡሽ ኤርሚያስ በከተማዋ በሚገኝ የግል ኮሌጅ ውስጥ ትማራለች፡፡ በ‹‹ጀሎ ደቀዬ›› የሕዝብ መዝናኛ ፓርክ ውስጥ ስታነብ ነው ያገኘኋት፡፡ ከዚህ ቀደም በከተማዋ ውስጥ የቤተመጻሕፍት እጥረት ይታይ ነበር፡፡ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ከሚገኙ አነስተኛ ቤተመጻሕፍቶች ውጪ የሕዝብ ቤተመጻሕፍት ማግኘት ከባድ ነበር የምትለው ተማሪ ከበቡሽ፣ በአሁኑ ወቅት የ‹‹ጀሎ ደቀዬ›› የሕዝብ መዝናኛ ፕሮጀክት አካል ተደርጎ የተገነበው የሕዝብ ቤተመጻሕፍት ለከተማዋ ሕዝብ ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን ተናግራለች፡፡ የንባብ ባህልንም እንደሚያሳድግ ጠቁማለች፡፡
የከተማዋ ከንቲባ አቶ ሊሬ ጀማል እንደሚሉት፤ የከተማዋን የመሠረተ ልማት ጥማት ለማርካት የተለያዩ መሠረተ ልማቶች ግንባታ እየተካሄደ ነው፡፡ ከተማዋ እያደገች እና እየሰፋች ቢሆንም የከተማዋን እድገት የሚመጥኑ የመንገድ፣ የውሃ እና የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች በከተማዋ እድገት ልክ አላደጉም፡፡ የከተማዋን እድገትና መሠረተ ልማት እድገት ለማጣጣም ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡ በከተማዋ እየተከናወኑ ካሉት ለሕዝቡ አገልግሎት ከሚሰጡ የመሠረተ ልማት ሥራዎች መካከል የመንገድ፣ የውሃ ፕሮጀክት፣ የሕዝብ መዝናኛ ፓርክ እንዲሁም የወጣቶች መዝናኛና ቤተመጻሕፍት ግንባታ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የከተማዋን የውሃ ችግር ለመቅረፍም በትኩረት እየተሠራ ይገኛል፡፡ የከተማዋን ውሃ ችግር ለመቅረፍ ከዚህ ቀደም ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ ከነዚህ ጥረቶች መካከል ቀደም ሲል የከተማዋን የውሃ ችግር ይቀርፋል ተብሎ ከ‹‹ሙጎ›› ወደ ሆሳዕና የውሃ መስመር ተዘርግቶ ነበር፡፡ ነገር ግን በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ባለው የሕዝብ ብዛት ምክንያት ከ‹‹ሙጎ›› የመጣው ውሃ የከተማዋ የውሃ ችግር አልተቀረፈም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ወደ ከተማዋ የሚመጡ ሕዝቦች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ የውሃ ፍላጎት እየጨመረ ነው። በመሆኑም የውሃ አቅርቦት መጨመር የግድ አስፈላጊ በመሆኑ ውሃ አቅርቦት ለመጨመር የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተሠሩ ነው፡፡
የከተማዋን የውሃ አቅርቦት ከፍ ለማድረግ ከ‹‹ጀዌ›› እና ከ‹‹ሀይሴ ለሜጃ›› ውሃ ወደ ሆሳዕና ለማስገባት የመስመር ዝርጋታ እና የሪዘርቫይር ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ከንቲባው ጠቅሰው፣ የውሃ ፕሮጀክቱ ከ300 ሚሊዮን በላይ በጀት የተያዘለት መሆኑንም ይናገራሉ፡፡ የሁለቱ የውሃ ማጠራቀሚያዎች /ሪዘርቫይሮች/ ግንባታ እየተጠናቀቀ መሆኑን ጠቅሰው፣ የውሃ መስመር ዝርጋታ ሥራ ወደ ከተማ ውስጥ ገብቷል ይላሉ፡፡
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ከሁለቱ አካባቢዎች ውሃ ወደ ሆሳዕና ለማስገባት እየተሠራ ያለው ሥራ ከ50 በመቶ በላይ ተጠናቋል፡፡ በተለይም የ‹‹ጀዌ›› የውሃ ፕሮጀክት በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ የ‹‹ሀይሴ ለሜጃ›› ፕሮጀክት ደግሞ አራት ጋኖች ያሉት ሲሆን ከአራቱ ጋኖች የሦስቱ ጋኖች ግንባታ በመገባደድ ላይ ነው፡፡ የውሃ መስመሮች ቀበራ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡
በነዚህ አካባቢዎች ከሚገኙ ምንጮች የሚሰበሰበው ውሃ በጋኖቹ ከተከማቸ በኋላ ተገቢው የማከሚያ ሥራ ተሠርቶ ወደ ከተማዋ የሚሠራጭ ይሆናል፡፡ የውሃ ጉድጓዶቹ ግንባታ ተጠናቆ ወደ ሥራ ከተገባ አንድ ሰው መጠቀም አለበት ተብሎ እንደአገር የተቀመጠውን ደረጃ ማድረስ ይቻላል፡፡ የአምቢቾ ጉደራ ፕሮጀክትም የከተማዋን ፍላጎት እየታየ ግንባታው እንደሚካሄድ አንስተዋል፡፡
አቶ ሊሬ ከተማ አስተዳደሩ የከተማዋን የአስፋልት መንገድ እጥረት ለመቅረፍ የከተማው አስተዳደር ከሕዝብ ጋር በመተባበር የመንገዶች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የመጀመሪያ ዙር የመንገድ ግንባታ 14 ነጥብ 14 ኪሎ ሜትር አስፋልት መንገድ እየተገነባ ይገኛል ያሉት ከንቲባው፣ የከተማዋ ሁሉም አካባቢዎች የመሠረተ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እና የሁሉም የከተማዋ አካባቢዎች እድገት እኩል እንዲሄድ 14 ነጥብ 14 ኪሎ ሜትሩ በሰባት የተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች እየተገነባ ነው ሲሉ ያብራራሉ፡፡
እንደ ከንቲባው ገለጻ፤ የአስፋልት መንገዶቹ በሄጦ ትምህርት ቤት አድርጎ ወደ አዲስ አበባ ከሚወስደው አስፋልት ጋር የሚገናኝ፣ ከ18 ማዞሪያ እስከ ማረሚያ ቤት ድረስ የሚዘልቅ፣ ከዋንዛ ፊት ለፊት እስከ ቦቢቾ ቃለሕይወት ቤተክርስቲያን የሚሄድ፣ ከዋስገበታ ማዞሪያ እስከ ቦቢቾ ድልድይ የሚሻገር፣ ከእሌኒ መሐመድ መታሰቢያ ሆስፒታል እስከ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የሚዘልቅ፣ እንዲሁም ከእሌኒ መሐመድ መታሰቢያ ሆስፒታል በሀዲያ ባህል ማዕከል ዞሮ ለማ ኢንተርናሽናል ሆቴል ፊት ለፊት ካለው አስፋልት ጋር የሚያገናኙ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
የአስፋልት መንገዶቹ ግንባታ በስድስቱም ቀበሌዎች ውስጥ የሚካሄድ ሲሆን የመንገዶቹ አጠቃላይ ግንባታ ከ60 በመቶ በላይ መጠናቀቁን አቶ ሊሬ አስታውቀዋል፡፡ በሁሉም አካባቢዎች፣ የመጀመሪያ አፈር፣ ሁለተኛ አፈር፣ የድንጋይ ሥራ አልቋል፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ጠጠር የማፍሰስ ሥራ አልቆ አስፋልት የማፍሰስ ሥራዎችም ተጀምረዋል፡፡
ጠጠር አድርጎ አስፋልት የማፍሰስ ሥራ በተቀረው አካባቢ ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሰሞኑን በአካባቢው መጣል የጀመረው ዝናብ አስፋልት ለማፍሰስ እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ዝናቡ ፋታ የሚሰጥ ከሆነ አስፋልት የማፍሰስ ሥራውን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እንደሚሠራም አንስተዋል፡፡ አስፋልት ፕሮጀክት ከ450 ሚሊዮን በላይ የተበጀተለት ሲሆን ፕሮጀክቱ የዚህ ዓመት መጨረሻ ድረስ እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል፡፡
በከተማዋ በፊት የተገነቡ መንገዶችም ለረጅም ዘመን አገልግሎት ሲሰጡ በመቆየታቸው አዳዲስ አስፋልቶችን ከመገንባት ጎን ለጎን የአስፋልቶቹን ደረጃ ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ያነሱት አቶ ሊሬ፤ የመንገዶቹን ደረጃ ለማሳደግ ጨረታ ወጥቷል፡፡ የጨረታ ሂደቱ እንደተጠናቀቀ ወደ ማስፋፋት ሥራው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
እንደ አቶ ሊሬ ማብራሪያ፤ የከተማው አስተዳደሩ በራሱ ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን ከዓለም ባንክ በብድር የሚሰጠው ገንዘብ እና የከተማውን ሀብት በማቀናጀት ሌሎች የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ሥራዎችም በትኩረት እየተሠሩ ናቸው፡፡ እየተሠሩ ካሉ ሥራዎች መካከል ወደ 235 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የድሬኔጅ፣ የኮብልስቶን፣ የጠጠር መንገድ ጥገና ሥራ ይጠቀሳሉ። እነዚህ ሥራዎች ከ90 በመቶ በላይ ደርሰዋል፡፡ በዚህ ዓመት ይጠናቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ፕሮጀክቶቹ በተባለለት ጊዜ እንዲጠናቀቁ የከተማው ሕዝብ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡
ሕዝቡ በተለይም ለእግረኛ መንገድ ማስፋፊያ አስፈላጊ የሆነ ቦታ በመልቀቅ ጥሩ ትብብር እያደረገ ነው፡፡ ሕዝቡ እያደረገ ባለው ድጋፍ በከተማዋ መንገድ የማስፋት ሥራ በተሳካ ሁኔታ እየተሠራ ነው፡፡ የከተማው ሕዝብ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመተባበር አመርቂ ሥራ እየሠራ ነው። ሕዝቡ ባሳየው መልካም ፍቃድ ዋና መስመሮች ላይ የእግረኛ መንገድ ከማስፋት ባሻገር ውስጥ ለውስጥ ያሉ መንገዶችንም ለማስፋት የተለያዩ ተግባሮች እየተከናወኑ ናቸው፡፡ የአስፋልት መንገዶችም እጅግ ጠባብ የነበሩ ሲሆን፣ ሕዝቡ ባደረገው ትብብር እንዲሰፋ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡ በርካታ ሰዎች ቤታቸውን ጭምር ለመንገድ ማስፋፊያ በማፍረስ እና ቢሸጥ ብዙ ብር ሊገኝበት የሚችል መሬት በነፃ እየለቀቁ ይገኛሉ፡፡
ከዚያ ባሻገር የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች፣ የመንግሥት ሠራተኞች እና መላው የከተማው ሕዝብ በመነጋገር ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ይገኛል፡፡ የከተማው አመራሮች እና ሠራተኞች የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለከተማው መሠረተ ልማት ግንባታ ለመስጠት ወስነዋል። ከዚህ ወር ጀምሮ ከደመወዛቸው ተቀንሶ ለከተማው ልማት ይውላል፡፡
ከአመራሩና ከመንግሥት ሠራተኛው ባሻገር መላው የከተማው ኅብረተሰብ ድጋፍ ለማድረግ ፍቃደኛ መሆኑንም ተናግረው፣ እያንዳንዱ ቀበሌ 10 ሚሊዮን ብር ለማዋጣት ቃል ገብቷል ብለዋል፡፡ ሕዝቡ ገንዘቡን ማዋጣት ጀምሯል ያሉት ከንቲባው፣ ይህም ሕዝቡ በከተማዋ ውስጥ እየተካሄደ ባለው የመሠረተ ልማት ሥራ ደስተኛ መሆኑን የሚያሳይ ነው ይላሉ፡፡ በቀጣይም ሕዝቡ ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል ከቻለ ብዙ ሥራዎችን መሥራት ይቻላል፡፡ ከተማዋን ከሌሎች ካደጉት ከተማዎች ተርታ ማሰለፍ እንደሚቻል አመላካች ነው ብለዋል፡፡
የ‹‹ጀሎ ደቀዬ››ፕሮጀክትም በዚህ ዓመት ለመሥራት የታቀደውን ሥራ በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቅ ተችሏል፤ ዙሪያው ታጥሯል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፤ የሕዝቡን ባህል የሚያስተዋውቁ ሥራዎች ተሠርተዋል። የጥበቃ ቤቶች ተሠርተዋል፤ ቲኬት መቁረጫ ቢሮዎች ተገንብተዋል፡፡ ውስጥ ፋውንቴይን እና ኳስ መጫወቻዎች ተሠርቷል፡፡ ቤተመጻሕፍት ተገንብቷል። ሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታ ተጀምሯል፡፡ የ‹‹ጀሎ ደቀዬ›› ዘመናትን የተሻገረ ታሪካዊ ቦታ መሆኑን የሚያነሱት አቶ ሊሬ፤ ቦታው ታሪካዊነቱን ይዞ እንዲቀጥል እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡ በቀጣይ አራት ዓመት ተኩል ተሠርቶ ይጠናቀቃል፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡
የሆሳዕና ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ተቋማዊ የመሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ዘነበ ዳኛቸው በበኩላቸው እንዳሉት፤ ከስድስት ኪሎ ሜትር በላይ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ ሥራ በስድስቱም ቀበሌዎች በተለያዩ ሳይቶች በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ አብዛኞቹ ተጠናቀዋል፡፡ ወደ ሰባት ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የጎርፍ መውረጃ መንገድ በ12 ሎቶች ተከፋፍሎ የግንባታ ሥራው እየተሠራ ነው፡፡ የዚህም 70 በመቶ የሚሆን ሥራ ተጠናቋል፡፡ ከዚህ ቀደም ከተማዋው የሚታማበት አንዱ ምክንያት የእግረኛ መንገድ ምቹ አለመሆን ነው፡፡ የውስጥ ለውጥ እና ዋና መንገድ የማስፋት ሥራ ስትራክቸራል ፕላኑን በጠበቀ ሁኔታ እየተሠራ ነው፡፡ የማስፋት ሥራዎች ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ ለከተማው ውበት የሚጨምር ነው፡፡
በፌዴራል መንግሥት በከተማዋ ውስጥ እየተሠራ የነበረው የአምስት ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ሥራም ቆሞ እንደነበር የሚያነሱት አቶ ዘነበ፤ አሁን ግን የመንገዱ ግንባታ ዳግም እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል፡፡ በሆሳዕና ከተማ ውስጥ የሚስተዋለውን የመሠረተ ልማት ችግሮችን ለመቅረፍ እየተደረገ ያለው ጥረት ሊበረታታ የሚገባ እና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
በመላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2015