ሁሉም ሰው አመል አለው..መኖርን የሚደፍርበት..አለመኖርን የሚሸሽበት፡፡ የእኔም አመሌ እሷ ናት..ቀይዋ ዝምተኛዋ ሴት፡፡ የነፍሴ ነፍስ ናት..በመኖሯ ውስጥ ያለሁ። ከዳናዬ ተጣብቃ፣ ከታሪኬ ተጋምዳ ባለሁበት ያለች፡፡ ፍቅሯን ነው የምተነፍሰው፣ ዝምታዋን ነው፣ ሴትነቷን ነው የማዜመው..
ቀይ ናት..ረጅም..ጠበብ ብሎ ብዙ ነገሮቹ የተስተካከሉለት ፊት አላት፡፡ መስከረም የጠባበት የሚመስል፣ እንደ ፀደይ ወራት ብራ የሆነ ሴትነት፡፡ ጠበብ ባለ ፊቷ ላይ ውበታም አይኖች፣ ሊደፈጠጥ ብሎ ለትንሽ የተረፈ አፍንጫ፣ ጾም የሚያስገድፍ ከንፈር ከየትኛውም ጥበበኛ ስዕሎች በላይ ነፍስ ዘርተው ይታያሉ፡፡ ሁልጊዜ በግንባሯ ግራና ቀኝ ከአናቷ የወረዱ ሁለት የጸጉር ዘለላዎችን አያለሁ፣ በሌላ ቀን ደግሞ ጸጉሯን ወደ ኋላ አሲዛ ሌላ ሆና ነው የማያት፡፡ አይኖቿ ሰው ደፍረው ማየት አይችሉም፡፡ ቅርቧ ካለ ሰው ጋር ካልሆነ ሩቅ ካለ ሰው ጋር መዛመድ አትችልም፡፡
ለሁለት ዓመት አንድ ቢሮ ውስጥ ስንሠራ አውርተን አናውቅም..ግን ነፍሴ የእሷን አንደበት እንደናፈቀች ምንም ናፍቃ አታውቅም፡፡ ዝምተኛ ናት..ከዛ ሁሉ እልፍ የሰው ጫጫታ መሐል የእሷ ዝምታ ነው የሚሰማኝ፡፡ ዝም ብላ ሳያት..ዝም ያለውን እግዜር ትመስለኛለች፡፡ እግዜርን የምቀናበት በዝምታው ነው…እሱን አድርጎ ሠርቷት ይሆን እንዲህ የምቀናባት? ስል ራሴን የእብድ ጥያቄ እጠይቃለሁ፡፡
ስሟን አላውቀውም፡፡አጠገቤ ያለን አንድ ሰው ብጠይቀው ስሟን ሊነግረኝ እንደሚችል አውቃለሁ ግን ስሟን ማወቄ ያን ያክል አስፈላጊ መስሎ ስላልታየኝ ትቼዋለሁ፡፡ አንድ ቀን ምን እንዳሰኛት እንጃ ያለወትሮዋ ጉርድ አድርጋ መጣች፡፡ ነፍሴ በሴት ልጅ ውበት አቅም ያጣችው ያኔ ነው እላለሁ፡፡ ሴት ልጅ መች አደከመችህ ላለኝ ያን ቀን አስታውሰዋለሁ፡፡ ያን ቀንና ያን ጉርድ እንድትለብስ ያሳሰባትን ሀሳቧን አንድ ላይ ረገምኳቸው፡፡ ርግማኔ ደርሶ ይሆን እንጃ ከዛን ቀን በኋላ ያን ጉርድ አልደገመችውም፡፡ በነጋታው ልብሷን ቀይራ በሱሪ አየኋት፡፡ ያን ቀን በጉርድ ያየሁት ሴትነቷ ዛሬም ድረስ ውስጤ አለ፡፡ ለአፍታ ሞቼ የነቃሁበት፣ ላመል የአለመኖርን አዘቅት ያየሁበት ቅጽበት ያ የእሷ በጉርድ ባጠገቤ ማለፍ ነው ስል ጆሮ ላለው ሁሉ አወራዋለሁ፡፡ ድንገት ነው በአጠገቤ እልፍ ያለችው። ያ እልፍታ፣ ያ ሽውታ ነፍሴን አብሮ ከዛ ውብ ገላና ጠረኗ ጋር ወስዶብኛል፡፡ ውብ እግር፣ ውብ ባት ከጸዳ ቆዳ ጋር እንደመስተዋት ዓይኔ ላይ ሲያንጸባርቁብኝ ነበር ከጣለችብኝ የፍቅር ድንዛዜ የነቃሁት፡፡
ከዛ ቀንና ከዛ ጉርድ በኋላ ላወራት እንደሚገባኝ አሰብኩ፡፡ ይሄን ባሰብኩ በሠልስቱ ሊፍት ውስጥ ተገናኘን። ሳያት ሰማይን ጀርባዬ ላይ ያዘልኩት ያህል ነፍሴ ታውካ ነበር፡፡ ደግሞም የትም ደስ ያላለኝ ደስታ ተዋሕዶኝ ነበር፡፡ ከምትወዳት ሴት ጋር አንድ ሊፍት ውስጥ አብሮ መቆም ደስታው ምን ያክል እንደሆነ አልደረስኩበትም፡፡ የመድረሻ ቁልፌን ልጫን እጄን ወደ ሊፍቱ ስዘረጋ እሷም ስትዘረጋ እጆቻችን ተገናኙ፡፡ነፍሴ ውስጥ የሆነ ኃይል ተሰማኝ፡፡ እግዜር ያቺን ለአስራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈሳት የኖረችውን ሴት በልብሱ ጫፍ ፈውሶ ኃይል ከኔ ወጣ እንዳለው እኔም ስነካት ከእሷ ወደእኔ የተላለፈ ኃይል ጎብኝቶኝ ነበር፡፡ያን ንክኪ፣ ያን መደነቃቀፍ በሕይወቴ ከመጡ ከብዙ መልካም ዕድሎች ጋር አንዱ አድርጌ ቀላቀልኩት፡፡
የፈለገችውን ቁልፍ እንድትጫን እድል ሰጥቼ እጆቼን ሰበሰብኩ፡፡ እኔ ከምሄድበት በአንድ ዝቅ ብላ ቁልፉን ተጫነችው፡፡ ፊት ለፊት መተያየት ስላልቻልን በመስታወቱ ውስጥ አሻግሬ በደንብ አየኋት፡፡ ያልደረስኩበት ሌላም ውበት እንዳላት ተረዳሁ፡፡ በቅርበት ውብ ናት፡፡ እስከዛሬ ያላሸተትኩት ውብ ጠረኗን ያን ቀን ተዋሐድኩት፡፡ለአይኖቼ ሩቅ የሆኑ ቅንድቦቿን፣ የአይኖቿን ሽፋል፣ በአፍንጫዋና በከንፈሯ መሐል ያለውን ጉብታ ሌላም ዋጋ የሌላቸው የሚመስሉ ብዙ ነገሮቿን አየኋቸው፡፡ምንም ነገር አልተቀባባችም ከንፈሯ ራሱ በተፈጥሮ ወዙ ነው፡፡ሁሉ ነገሬን ተረድታ የምትከታተለኝ መሰለኝ፡፡ የሕይወቴ እውነት እኮ እንደእሷ ያለች በሥርዓት ውስጥ ያለችን ሴት መወዳጀት ነው፡፡ ከሕልሜ ትልቁ እኮ እንደ እሷ በዝምታዋ የምታምርን ጨዋ ሴት መቅረብ ነው፡፡ የምፈልገው ነገር ሁሉ ያላት ሴት ናት፡፡ ብዙ ሴቶች ላይ ፈልጌ ባጣሁት ውበትና ልዕልና ልታጠምደኝ የተላከች ወይም ደግሞ ፈጣሪ ጸሎቴን ሰምቶ አፍንጫዬ ስር ጣለልኝ ስጦታዬ መሰለችኝ፡፡ የቱን እንደማምን ግራ ገብቶኝ የሊፍቱ በር ተከፍቶ ቀድማኝ ወረደች፡፡ ጠረኗ ሊፍቱ ውስጥ ቀርቶ የምሄድበት ድረስ አደረሰኝ፡፡ ሴት ልጅ እንደዛ ውብ ውብ ስትሸት እሷንና ጥቂት ሴቶችን ነው የማውቀው፡፡
እንደዛ ቀን ክፉ ምኞት ተመኝቼ አላውቅም፡፡ሊፍቱ ተበላሽቶ ወይም የትኛውም ባለሙያ ባልተረዳው እክል መሄድ አቁሞ እኔና እሷ እዛ ሊፍት ውስጥ ውለን ብናድር ስል ተመኘሁ፡፡ ይሄ በሆነ በሁለተኛው ቀን እኔ ደረጃ ስወርድ እሷ ደረጃ ስትወጣ ተገናኘን፡፡ በአይኔ ሰላም ብያት በአይኗ ሰላም ብላኝ ተላለፍን፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በዛ ሁኔታ ሰላም ተባባልን፡፡ ከሄድኩበት ስመለስ ቀጥታ ወዳለችበት በመሄድ ‹ዮናታን እባላለው› ስል እጄን ለትውውቅ ዘረጋሁላት፡፡
‹ፍሬ ሕይወት፡፡ስትል እጄን ጨበጠችው፡፡ ከዛ ሊፍት በኋላ እጆቻችን ዳግም ተገናኙ፡፡ ከእጇ ወደነፍሴ የሆነ ሙቀት፣ የሆነ ትኩሳት፣ የሆነ ንዝረት ተላለፈ፡፡ ‹ግን እኮ እንተዋወቃለን ራሳችንን ማስተዋወቁ ለምን አስፈለገ? ስትል ከአይኔ ሸሽታ ትጽፍበት የነበረውን ኮምፒውተር እያየች ጠየቀችኝ፡፡ ዝምታዋ አይናፋርነት የፈጠረው ከሆነ እጠላታለሁ ጨዋነት የፈጠረው ከሆነ ደግሞ ላልጠላት አፈቅራታለሁ እያልኩ ከራሴ ጋር ስሟገት የሸሸኝን ዓይኗን ወደ እኔ መልሳ መልሴን ትጠብቅ ጀመር፡፡
‹ተግባቦትና ንግግር የሌለበት ትውውቅ ከትውውቅ አይቆጠርም ብዬ ነው› አልኳት፡፡
‹እ..ነው እንዴ..! አለች፡፡
‹አንድ ነገር እሺ በይኝ! አልኳት፡፡
‹ምን?
‹መጀመሪያ ቃል ግቢልኝ..
‹ምን እንደሆነ ሳላውቅ?
‹ቀላል ነገር ነው..
‹እሺ ምንድነው?
‹ነገ ስትመጪ ጉርድ አድርገሽ እንድትመጪ እፈልጋለሁ..› አልኩኝ የምትለውን ለመስማት በመናፈቅ፡፡
‹ማን ስለሆንክ ነው አንተ የእኔን አለባበስ የምትመርጠው? እኔ በራሷ እውነት ውስጥ የቆመች ሴት ነኝ..ማንም ያን አድርጊ ይሄን አድርጊ የሚለኝ ሴት አይደለሁም እሺ› አለችኝ..
በአንድ ጊዜ ኩስስ አልኩ፡፡ በፍቅሯን የበረታ ግርማ ሞገሴ፣ የፍቅሯን ታቦት የተሸከመ ትከሻዬ በተናገረችኝ አንዲት ቃል ምናምንቴ ሆኑብኝ፡፡ ነፍሴ ከስጋዬ ልትለይ ምንም አልቀራት ነበር፡፡ የሆነ ነገር ማለት ስላለብኝ ‹እንደዛ ለማለት ፈልጌ እኮ አይደለም..
‹ምንም ብትል ፊትህ ላለችው ሴት ጉዳይዋ አይደለም።እሷ የራሷ መንገድ ያላት ሴት ናት› አለችኝ ንዴትና ቁጣ በማይታይበት ፊት፡፡እጇን አገጭዋ ላይ አስደግፋ በደንብ አየችኝ፡፡እይታዋን ፈራሁት፡፡ምን ሊያመጣብኝ ይሆን ስል..
ምንም ይሁን ሰው ላለመጨረስ ሰይጣኗን በዝምታዋ ውስጥ ደብቃ የምትኖር ሴት ናት ስል ስም ሰጠኋት፡፡ከዚህ ቀን በኋላ አጠገቧ ላልደርስ በማመን ካለችበት ሸሸሁ፡፡
…….
በነጋታው በትካዜ በወደኩበት የሆነ ረፋድ ላይ የሆነ እጅ ትከሻዬ ላይ አርፎ አባነነኝ፡፡ ስዞር እሷ ናት..በጉርድ ቀሚስ፡፡ እያየኋት ወደማላውቀው ዓለም ሸሸሁ፡፡ ቀይ እግር፣ ቀይ ባት፣ ቀይ ቆዳ ከውብ ጠረን ጋር ፊቴ ቆሞ ሳይ ገነት ከነሙሉ ክብሯ ተጠቃላ ፊቴ የመጣች ነበር የመሰለኝ፡፡
‹ትላንት እንደዛ ያልኩህ ለፈተና ነበር..ስላስቀየምኩህ ምሳ ልጋብዝህ› አለችኝ፡፡
ፈገግ ብቻ ነው ያልኩት..እንቢ የምልበት ምንም አቅም አልነበረኝ፡፡ከእሷ ጋር ምሳ ለመብላት ከሰዓት እስኪሆን ብዙ ዘላለማትን የጠበኩ ይመስለኛል፡፡
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን መጋቢት 22/2015