‹‹ብዙዎቻችን ልብስ ማጠብ፤ ልጅ መንከባከብና ምግብ ማዘጋጀት ለሴቶች ብቻ ተለይተው የተሰጡ የቤት ውስጥ የሥራ ዘርፎች ይመስሉናል።በቴሌቪዥን መስኮት የምናያቸው ማስታወቂያዎችም እንዲህ ዓይነቶቹን ፍረጃዎችን በማበረታታት የሚያስቀጥሉ ነው የሚመስሉት። ለምሳሌ ኦሞና ዳይፐር እንዲሁም ልጅ ማስከተብና ማሳከምን የሚመለከቱ ማስታወቂያዎች አብዝተው በሴት ነው የሚተዋወቁት።
መኪና መንዳትና ቅንጡ አፓርታማ ማስተዋወቅን ደግሞ ለወንዶች ብቻ የተተወ ይመስላል። ይሄ ልክ ነው ብዬ አላምንም። አሁን ላይ እንደ አገር የጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ ከላይ ከፖለቲካ አመራሩ ጀምሮ ታች እስከ ወረዳ ድረስ እየተሰራ ያለበትን ተግባር ያደናቅፋል። እኩል ተሳትፏችንንም ቀድሞ ማህበረሰቡ ይሄ የሴት፤ያ የወንድ ብሎ በመፈረጅ ወደ ኋለኛው አስተሳሰብ በመመለስ እድገታችንን ይጎትታል።
ይሄም ብቻ ሳይሆን ሴቶች ካለባቸው የኢኮኖሚ ችግር የተነሳ በማስታወቂያ ሲሳተፉ ራሳቸውን እንደሸቀጥ እንዲያቀርቡ የሚገደዱበት ሁኔታ ይስተዋላል።ይሄን እንደጥቃት ነው የማየው።በማስታወቂያ ብቻ ሳይሆን በቃለ ምልልስ ወቅት አንዳንድ ጋዜጠኞች ለሴቶች የሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች ሴቶችን ዝቅ የሚያደርጉ፤ የሴቶች እኩልነትና መብትን ያላገናዘቡም ይመስሉኛል። ለምሳሌ ትልቅ ስልጣን ላይ ያለችና ስኬታማ የሆነችን ሴት ለምን አላገባሽም? ብሎ መጠየቅ ልክ አይደለም›› ትላለች ለረዥም ጊዜ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ስታገለግል የቆየችውና በአሁኑ ሰዓት የኮሚኒኬሽን አማካሪ ሆና በግሏ እየሰራች የምትገኘው አንጋፋዋ ጋዜጠኛ አባይነሽ ብሩ።
አባይነሽ እንደምትመክረው አመራር ላይ ላሉ እና ብዙ ሥራ ለሠሩ እንዲሁም ውጤታማ ለሆኑ ሴቶች ቃለ ምልልስ ሲደረግ በሴትነታቸው ያለፏቸውን ተግዳሮቶች እንዴት አድርገው እንደ ተቋቋሙት ቢዳስሱ ይመረጣል። ጥያቄዎቹ የሚነሱበት አግባብ ወደ ታች ዝቅ በማድረግ ሳይሆን ጥንካሬአቸውን አጉልቶ በማውጣት መሆን አለበት። ማስታወቂያም ዋና ዓላማው ከሽያጭና ገንዘብ ከማግኘት ጋር ቢያያዝም የሴቷን ስብዕና እና ማንነት ያከበረና የስርዓተ ጾታን እኩልነት ያገናዘበ መሆንይኖርበታል። ሥራውም የማስታወቂያ ሕግና ስርዓትን ተከትሎ መሠራት አለበት።
ይሄ የሴት ወገንተኝነትን በማረጋገጥ በሕብረተሰብ ውስጥ የጾታ እኩልነትን ለማምጣት ብቻ ሳይሆን፤ ለአንድ አገር ኢኮኖሚያዊና ሁለንተናዊ ዕድገት በእጅጉ ያስፈልጋል። ሆኖም በእኛ አገር በየትኛውም መንገድ በተለይ መንግስት በሚቆጣጠራቸው ሚዲያዎች ሲተላለፉ የሚስተዋሉ ማስታወቂያዎች ማሟላት የሚገባቸውን አሟልተው የሚሠሩና የሚተላለፉ አይመስሉም።
‹‹ማስታወቂያ የሽያጭ የግዢና የገንዘብ ጉዳይ ስለሆነ አንድ ምርት ለመሸጥ ሲባል በሚሠራ ማስታወቂያ ውስጥ ሴቶች ይሳተፋሉ። የሚሳተፉት ሴቶች ግን በምን መንገድ ነው የሚሳተፉት? ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን›› የምትለው አንጋፋዋ ጋዜጠኛ አንዲት ሴትና አንድ ወንድ ልጅ ያላት እናት ከሴቷ ልጇ በተለየ ሁኔታ ወንድ ልጇ እንዲጠነክር የሚያስችል ገንቢ ምግብ ስትሰራለት የሚያሳይ ማስታወቂያ ለመታዘብ መቻሏንም ለአብነት ትጠቅሳለች።
በማስታወቂያው ለተመልካች የሚተላለፈው መልዕክት የሚያጠነክር ገንቢ ምግብ ለወንድ እንጂ ለሴት እንደማያስፈልግ ዓይነት መሆኑን ታወሳለች። አባይነሽ የስርዓተ ጾታ እኩልነት ላይ እንዲህ ዓይነት ክፍተት የሚፈጥሩ ማስታወቂያዎች በፍጹም መተላለፍ እንደሌለባቸው ታነሳለች።
በርካታ አንጋፋ ሴት ጋዜጠኞች የጋዜጠኛዋን አስተያየት ይጋሩታል። አስተሳሰቡንና አካሄዱን በሀሳብ መዋጋት እንደሚገባም ይመክራሉ። በተደራጀ መልኩ መቀልበስ እንደሚገባም ያነሳሉ። አንጋፋዋን ጋዜጠኛ አባይነሽን ያገኘንበትና ጉዳዩ ሲነሳ የሰማንበት የኢትዮጵያ መገናኛ ባለሙያ ሴቶች ማህበር (ኢትመባሴማ)፤ አንድ ጋዜጠኛ ለአንዲት ከፍተኛ የመንግስት ስልጣን ላይ ላሉ አመራር ቃለ ምልልስ በሚያደርግበት ወቅት ለምን አላገባሽም? የሚል ዓይነት ጥያቄ ማቅረቡን አስመልክቶ ጋዜጠኛው ለሚሰራበት ድርጅት ደብዳቤ መጻፉን ለአብነት ያነሳሉ።
ኢትመባሴማ ጠቅላላ ጉባኤውን ባካሄደበትና ሀሳቡ ተነስቶ በነበረበት መድረክ ላይ ያገኘናት ጋዜጠኛና በአሁኑ ወቅት በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ ሆና በማገልገል ላይ የምትገኘው ዘለዓለም ጌታቸው ከላይ የተነሳውን ሃሳብ አስመልክታ የሚከተለውን ሃሳብ ሰንዝራለች። አንድ ጋዜጠኛ ለአንዲት በከፍተኛ የስልጣን እርከን ላይ ላሉ ሴት ያቀረበው ለምን አላገባሽም? ሳታገቢ እንዴት አመራር ሆንሽ? የሚል እንድምታ ያለው የሚመስለው ቃለ መጠየቅ አሁንም በጋዜጠኞች ጭምር የተዛባ አመለካከት እንዳለ የሚያሳይ ነው። ‹‹ለምን አላገባሽም?›› ዓይነቱ ጥያቄ ‹‹አመራር የሚሆነው ያገባ ነው።›› የሚል ዓይነት መልዕክት የያዘ ነው ትላለች። ጋዜጠኛዋ እንዲህ ዓይነቶቹ የጋዜጠኞች ጥያቄ ለሴቶች ባይቀርቡ እንደምትመርጥና ሆኖም በጋዜጠኛውና በአንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች ሲጠየቁ መስማቷን ታነሳለች።
‹‹ጋዜጠኛው ይህንን ጥያቄ ያነሳው ተጠያቂዋ ሴት ስለሆነች ነው። ወንድ ቢሆን አያነሳውም። እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት አንዳንዴ ሆን ተብሎ የሚደረግ ነው የሚመስለው። ያን ጥያቄ ሳያስበው ነው የጠየቃቸውና ያደረገው ማለት አይቻልም›› ትላለች።
ጥያቄው ሕብረተሰቡ ሴት ቤቷን መምራት የምትችል ከሆነ የበለጠ ደግሞ ሕዝብንም፤ አገርንም ልትመራ ትችላለች የሚለውን ዕሳቤ የሚያፈርስና ከአመራርነት ጋር የሚያያይዘው ምንም አይነት ሳይንሳዊ መንገድ አለመኖሩን ትናገራለች። ይልቁንም ከጋብቻ ጋር ከማያያዝ ይልቅ ጋዜጠኛው አጉልቶ ማውጣት የነበረበት ኃላፊዋ በሥራቸው ጎልተው የወጡበትን ምስጢር መሆን እንደነበረበት ታወሳለች።
‹‹በተለይ ሴቶች መምራት የምንችለው ገና በህፃንነታችን ከቤታችን ጀምሮ ነው›› ትላለች ጋዜጠኛ ዘለዓለም ጌታቸው። አመራርነት ሴቶች ወላጆቻቸው የሚሰሩትን ሥራ እየሰሩና እህትና ወንድሞቻቸውን እያሳደጉ፤ ትምህርት ቤት አለቃ እየሆኑና እያዳበሩ የሚያመጡት ሂደት እንደሆነም ትናገራለች። በመሆኑም የመሪነት ጉዳይ በዕውቀት ወይም በልምድ የሚመጣ እንጂ የግድ ስላገባችና ስላላገባች የሚመጣ እንዳልሆነም ታነሳለች። አክላም በዚሁ ጥያቄ መነሻነት እንደ ተቋም በቅርቡ ጎንደር ላይ እንዲሁም በተደጋጋሚ በሌሎች ቦታዎች እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች መቅረብ የለባቸውም በሚል ብዙ ስልጠናዎች መውሰዳቸውንም አጫውታናለች።
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ክፍል የመጡ ባለሙያ ጋዜጠኛው ከከፍተኛ አመራሯ ጋር ያደረገውን ቃለ መጠይቅ ቪዲዮ መሰረት በማድረግ ስልጠናው መካሄዱንና እርምት የተወሰደበት መሆኑንም አውስታለች።ጋዜጠኞች ለሴቶች በተለይም ከፍተኛ ስልጣን ላይ ላሉና ትልቅ አገራዊ አበርክቶ ላላቸው ቃለ መጠየቅ ሲያደርጉ እንዴት መሆን አለበት የሚለውም ጥናት እየተካሄደበት መሆኑ መረጃው እንዳላት ነግራናለች።
አንጋፋዋ ጋዜጠኛና ደራሲ እንዲሁም አሁን ላይ ‹‹የሴቶች ይችላሉ›› ማህበር መሥራችና ዳይሬክተር የምወድሽ በቀለ ስለ ሴቶች ሕብረተሰቡ ጋር ብቻ ሳይሆን ጋዜጠኞች ጋር ጭምር የተዛባ አመለካከት እንዳለ ትናገራለች። በሕብረተሰቡ ውስጥ ለሴቶች ያለው አመለካከት ብዙ ሥራና ዕውቀት የሚጠይቅ በመሆኑ አሁን ድረስ ሴቶችን የምናይበት አመለካከት በፍፁም መስተካከል አልቻለም። ‹‹ለዚህም ነው የተለያየን የሴት ማህበራት በየሙያችን ተጠናክረን እየሠራን የምንገኘው›› ትላለች።
አንድ ጋዜጠኛ የሰራው ሥራ ወደ ሕብረተሰብ ከመሄዱ በፊት ኤዲተሮቹም ሊያዩት ግድ ነው። ሆኖም አሁን ላይ የሚወጡ ማስታወቂያዎች እና ጽሑፎች ሁኔታቸው ሲታይ ትክክል አይደሉም። ኤዲተሮች የሚያይዋቸውም አይመስሉም። እንደ ሴት ጋዜጠኞች ማህበር ይሄው ተገምግሟል። ‹‹ተግባራቱ የሴቶችን መብት እየሸረሸሩ ነው ብለን ስለምናስብ እንደ ሴት ጋዜጠኞች ማህበር ይሄ ችግር እንዲቀረፍ ሁላችንም በመነጋገር በጋራ እንሥራ የሚል እሳቤ ላይ ደርሰናልም›› ብላናለች።
‹‹እኔም እንደ አንጋፋ ባለሙያነቴ ይሄ ይሰማኛል። ምክንያቱም ሴቶች መከበር አለብን›› የምትለው ጋዜጠኛ የምወድሽ ሴቶች ስለማግባትና አለማግባታችንና ስለ ግል ሕይወታችን ሳይሆን ሕብረተሰቡን በሙያችን በትክክልና በውጤታማነት እያገለገልን ስለመሆናችን ነው መዘገብ ያለበት ትላለች። አንዲት ሴት መሪ ናት ሲባል የመሪነትን ሚና አሟልታ ምን ሠራች የሚለው ሌሎች ሴት መሪዎች እንዲወጡ ማስተማሪያ በመሆኑ ግላዊና ከባለቤቷ ውጪ ሌሎች ሊሰሟቸው የማይገቡ ጥያቄዎች መቅረባቸው አግባብ አይደለም። ማህበሩ ተግባሩ እንዲታረም ጥያቄ ያቀረበውም ለዚህ ነው።
ጋዜጠኛ የምወድሽ አሁን ላይ ሴቶች በማስታወቂያዎች የሚሳሉበትንም አግባብ ከዚሁ ከተዛባ አመለካከት የፀዳ እንዳልሆነ ታነሳለች። በነዚሁ ማስታወቂያዎች ጉዳይም እንደ ሴት ጋዜጠኞች ማህበርና እንደራሷ ተቋም መወያየታቸውንና ብዙ መልፋታቸውንም ታወሳለች። ሴቶች ላይ የሚደርሱ ችግሮች በመበራከታቸውና ሴቶች በግልም በጋራም ተደራጅተው ሁሌ እነዚህ ችግሮች እንዲቀረፉ በተለያየ መንገድ ሲያነሱ በመስማታቸው አንዳንዶች የዚህ አገር ‹የሴቶች ችግር መቼ ነው የሚቀረፈው› እስከማለት ደርሰዋል። ‹እነዚህ ሴቶች አበዙት› ብለው የሚተቹም አይጠፉም።‹‹ሆኖም ወድደን ሳይሆን መፍትሄ ስላላገኘን ነው። መፍትሄ እስካላገኘን ድረስ መነጋገር፤ ማስተማር፤ እኛም መማር አለብን›› ትላለች።
እንደታዘበችው አሁን ላይ በተለይ ከማስታወቂያ ጋር ተያይዞ የሚሰራው ሥራ ኃይ ባይ ያለው አይመስልም። ሌላው ቀርቶ መንግስት ከሚቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙኃን የሚወጡ ማስታወቂያዎች ብቻ ቢስተዋሉ በጣም ያሸማቅቃሉ። የሴቶችን መብት የሚያከብሩ አይደሉም። በመሆኑም የሚወጡ ማስታወቂያዎች ላይ በደንብ ትኩረት ቢሰጥ ጥሩ ነው። አለበለዚያ ልጆቻችን ይሄን እያዩ ነው የሚያድጉት። ነገ እነሱም ይሄን እንደ ጥሩ ነገር ስለሚወስዱት መዘዙ ለሴቶች ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ለማህበረሰቡና ለአገሪቱም ይተርፋል ትላለች።
‹‹የቀድሞ የጠቅላይ ፍርድቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ ‹በበዓል ቀን ዶሮ ትሰሪያለሽ ተብሎ ለምንድነው የሚጠየቀው› ሲሉ እሰማ ነበር›› ስትል አስተያቷን የጀመረችው በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እያገለገለች የምትገኘው አንጋፋዋ ጋዜጠኛ ዙበይዳ አወል ናት። ዙበይዳ ጋዜጠኞች የተለያዩ ባለስልጣናትን በሚያነጋግሩበት ወቅት ሥራቸው ላይ ትኩረት አለማድረጋቸውንም ታነሳለች። እንዳከለችው በተለይ ውጤታማ ሴቶች ከሆኑ የሄዱበትና ለዚህ የደረሱበትን መንገድ ከማጉላት ይልቅ የግል ሕይወቷን የሚመለከት፤ አግብተሻል ወይ?፤ ፈተሻል አሉ፤ ስንት ልጅ አለሽ? ልጆችሽን እንዴት ነው የምታሳድጊው?፤ አልፈው ተርፈው ሙያ አለሸ ወይ?፤ ዶሮወጥ ትችያለሽ? የሚሉ ጥያቄዎች በብዛት እንደሚጠየቁ ትናገራለች።
እነዚህ አንደኛ ግላዊ ጉዳዮች ናቸው። ሁለተኛ ወንዱ የማይጠየቀው ጥያቄ ነው። የቤተሰብና የቤት ጉዳይ በእኛ ማህበረሰብ በአብዛኛው ለሴቷ ስለተሰጠ ነው እንጂ የወንዱም ኃላፊነት ነው። አሁን ላይ አንዳንድ ባለ ስልጣናት በተለይም ሴት ባለስልጣናት ለቃለ ምልልስ ፈቃደኛ የማይሆኑት ለዚህ ነው። በመሆኑም በቃለመጠይቅ ወቅት ስኬቷን፣ ሥራዋን፣ ኃላፊነቷንና ውጤቷን አጉልቶ ማሳየት ይገባል ትላለች። በተለይ ጋዜጠኞች ላይ ያለው አመለካከት በጣም መቀየር እንዳለበት ትመክራለች።
‹‹ከማስታወቂያ ጋር ተያይዞ ብዙ ጊዜ ሴቶች ቅር የምንሰኝባቸው ችግሮች አሉ›› የምትለው ዙበይዳ ማስታወቂያው ሳቢ እንዲሆን በማሰብ ሴቶች እርቃናቸውን ሆነው ሳይቀር በማስተዋወቅ የሚሳተፉባቸው ሁኔታዎች መስተዋላቸውን ታነሳለች። ለምሳሌ በጣም አጓጉል የሆነ ልብስ ለብሰውና ተኝተው ፍራሽ ማስተዋወቅ ከአኛ ማህበረሰብ፣ ከባህላችን፣ ከሐይማኖታዊ ስርዓታችን አንፃር አይሄዱም ትላለች። ‹‹ለሴት ልጅ ክብር ሊሰጣት ይገባ ነበር›› የምትለው ጋዜጠኛዋ ቆንጆ መልክና ቅርጽ ያላትን ሴት የመምረጥና ውበቷን ቅርጿንና ሴትነቷን ማሻሻጫ አድርጎ ማቅረብ እየተለመደ መምጣቱን ታወሳለች።
ዙበይዳ እንደምትለው በጉዳዩ ከሚተላለፈው መልዕክት ወይም ደግሞ ከምርቱ ሳይሆን ከሴቷ ውበትና ቅርጽ ሽያጭ ጋር የተያያዘ እስኪመስል ድረስ ማስታወቂያዎቻችን በእንዲህ ዓይነቱ ይዘት የተቃኙ ናቸው። ቆንጆ ሴቶችን መርጦ ማስታወቂያዎችን ከማሠራት ባለፈ አንዳንድ እንደ ሳሙና ኦሞ ያሉና ከጽዳት ጋር የተያያዙ የምርት ሸቀጦችን በማስተዋወቅ ሂደት እንዲሁ ሴቷን ብቻ የመጠቀም፤ ልብስ ማጠብ የሴቷ ብቻ ኃላፊነት ማስመሰል፤ መኪናን ማስተዋወቅ ለወንዶቹ የመስጠት ሁኔታዎች እና ልጆቻችንም ሲያይዋቸው በቃ ይሄ ነው የሴቷ ሥራ ብለው እንዲስቡ የሚያደርጉ ማስታወቂያዎች ይስተዋላሉ።
በመሆኑም እኛ አገር ያሉ ማስታወቂያዎች በደንብ መታየትና መፈተሸ አለባቸው። ምርትም ሆነ የትኛውም አገልግሎት ማስታወቂያ ለሕብረተሰቡ የሚሰጠውን ጥቅምና አገልግሎት ነው እንጂ ማስተዋወቅ የሚገባው ሌላ ተግባር አይደለምና ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ በመምከር ዙበይዳ አስተያየቷን ታሳርጋለች።
እኛም እንደታዘብነው ሴቶች በማጀት ብቻ ተከልለው እንዲኖሩ ተፅዕኖ የሚያደርጉ ድርጊቶች በርካታ ናቸው። ድርጊቶቹ በማጀት መከለላቸውን የሚያበረታቱ ብቻ ሳይሆኑ ሴቶችን አሁን ከደረሱበት የዕድገት ማማ ወደ ኋላ የሚጎትቱም ድርጊቶች በርካታ ናቸው። እነዚህ ድርጊቶች ደግሞ በሚዲያ ሲደገፉ ጉዳዩን ይበልጥ ያከብዱታል። ለዛሬ ሃሳባችንን እዚሁ ጋር ገታ እናድርግና በቀጣይ ጽሑፋችን በዚሁ ጉዳይ የሚመለከታቸውን ባለ ድርሻ አካላት አስተያየት ይዘን እንቀርባለን። ቸር ሰንብቱ።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን መጋቢት 19/2015