‹‹ዓባይ ለግብጽ ሕይወት ነው›› የሚለው የግብጾች ተደጋጋሚ ትረካ መፈክሩን ዓለም አቀፍ አድርጎታል። ለአንዳንዶች ዓባይ የምርምር የግብጽ ሕይወት ሲመስላቸው አንዳንዶች ደግሞ እውነታውን ውስጣቸው ቢያውቅም ለኢትዮጵያ ባላቸው አሉታዊ አመለካከት ብቻ እውነት አስመስለው ይተርኩላቸዋል። እዚህ ላይ ትልቁ ችግር ዓባይ ለግብጽ ሕይወት ነው መባሉ ብቻ ሳይሆን ፤ ችግሩ ለኢትዮጵያም ከግብጽ በላይ ሕይወት መሆኑን መረዳት አለመፈለጋቸው፤ የዓባይ ባለቤት ግብጽ እስከምትመስል ድረስ የትርክት መዛባት መፍጠራቸው ነው።
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ከስድስት ይሁን አምስት ዓመታት በፊት በዓባይ ጉዳይ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንን ያወያየበት አንድ መድረክ ላይ ታድሜ ነበር። በወቅቱም ምሁራኑ የዓባይን ጉዳይ ከዓለም አቀፍ ሕግ አንፃር፣ ከስምጥ ሸለቆ ካለው ርቀት አንፃር፣ ከታሪካዊ ውዝግቦች አንፃር… አንስተው ትንታኔ ሰጥተውበታል።
ከተሰጡት ትንታኔዎች አንድ ቀልቤን የገዛውና ከዚያ በፊት ሰምቼው የማላውቀው ፤ ግብጽ ሁል ጊዜም ከዓባይ ውጭ ምንም የውሃ አማራጭ የሌላትና ህልውናዋ በዓባይ ላይ ብቻ የተመሰረተ መሆኑን ስትገልጽ ብትኖርም ፤ ከየትኛውም አገር በላይ የከርሰ ምድር ውስጥ ውሃ ያላት አገር መሆኗን ነው።
በእርግጥ እጅጋየሁ ሽባባው(ጂጂ) እንዳለችው ግብጾች የሚበሉትም የሚጠጡትም ውሃ ነው። ዓባይን በዕለት ከዕለት እንቅስቃሴዎቻቸው ውስጥ ሁሉ አስገብተው ሕይወት አድርገውታል። የትምህርት ሥርዓታቸው ሁሉ በዓባይ የታቃኘ መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ። ከመዋዕለ ሕጻናት እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ ዓባይ የአፍ መፍቻቸው እና የጥናትና ምርምር ምንጫቸው ነው።
የዓባይ ባለቤት ወደሆነችው ኢትዮጵያ ስንመጣ ግን የትርክት የበላይነት ተወስዶባታል። ግብጾች ዋሽተው ዓለምን ለማሳመን ሲሞክሩ ኢትዮጵያውያን ግን ተፈጥሯዊና ነባራዊ ሀቁን እንኳን ለመናገር ስንሽኮረመም ረጅም ዘመናት አስቆጥረናል። በወንዙ ውሃ ላይ ትንሽ መነቃቃት የፈጠርነው ከታላቁ ህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ መጣል ወዲህ ነው።
እሱም ቢሆን በቂ አይደለም። በቂ ባለመሆኑም ግብጽ ወቅት እየጠበቀች የዓለምን ቀልብ ይገዛልኛል የምትለውን ሁሉ ይዛ ብቅ የምትለው። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተገቢውን ምላሽ የሰጠባት የሰሞኑ ንግግሯም የዚሁ አካል ነው።
ዓባይ ለኢትዮጵያ ወንዝ ብቻ ሳይሆን ሕይወት ነው። ሕይወት ነው ስንል ከመሬት ተነስተን አይደለም። ይህን ሀቅ ለማወቅ ዓለም አቀፍ ‹‹ጆርናል›› ማገላበጥ ወይም የብራና ታሪኮችን ማፈላለግ አይጠበቅብንም። የኢትዮጵያን ሕዝብ ማህበራዊ ስሪት ማየት በቂ ማስረጃ ነው። በመኖር የምናውቀው ታሪክ ነው። ዛሬም እየተኖረ ያለ ማህበራዊ መስተጋብር ነው።
በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል ያለውን ማህበረሰብ የሕይወት መስተጋብር ካየን ከዓባይ ጋር የተቆረኘ ነው። በየመድረኩ ሲነገር የምንሰማው አንድ ነገር አለ። ‹‹ዓባይ ለዘመናት ለፉከራ እና ለሽለላ ብቻ ስንጠቀመው ኖረናል›› የሚል። ይህ ፉከራና ሽለላ ዝም ብሎ አልመጣም፤ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቁርኝት ስላለው ነው። እንዲያውም በምሁራን ከተሰሩ ጥናቶች በላይ ይህ የሽለላና ፉከራ ትውፊት የኢትዮጵያን ሕዝብና የዓባይን ግንኙነት ያሳያል።
ተረቶች፣ ሐተታ ተፈጥሮዎች፣ አፈ ታሪኮች፣ የሕዝብ ስነ ቃሎች… ከዓባይ ጋር የተያያዙ ናቸው። ዓባይ በዘመናዊው ሥርዓተ ትምህርታችን ውስጥ በቂ ቦታ ባይሰጠውም በልማዳዊ ትምህርቶች ውስጥ ግን ሰፊ ቦታ አለው። በገበሬው ሕይወት ውስጥ ሰፊ ቦታ አለው። ገበሬው መከፋቱን፣ መደሰቱን፣ ማፍቀሩን፣ መጥላቱን… ሁሉ የሚገልጸው በዓባይ አስመስሎ ነው። የስነ ቃሎችን ይዘት በዓይነት በዓይነት ሌላ ጊዜ በሌላ ጽሑፍ የምንመጣባቸው ይሆናል።
እነዚህ ነገሮች ለምን ሆኑ ከተባለ ዓባይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕይወት ስለሆነ ነው። ምሳሌያዊ ንግግሮች ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲወርዱ ሲወራረዱ የመጡ ናቸው። ዓባይ ከጥንት ዘመን ጀምሮ በሰዎች ሕይወት ውስጥ የነበረውን ቦታ ያሳያል። በዓባይ ተምሳሌትነት ግዝፈትን፣ ኃይለኝነትን፣ አይደፈሬነትን፣ አንዳንዴም ቻይና ታጋሽነትን ሲገልጹበት ኖረዋል።
ስንፍናችን የት ጋ ነው ከተባለ ፕሮጀክቱን ቀድመን አለመጀመራችንና ከተጀመረ በኋላም አለማፋጠናችን ብቻ አይደለም። ስንፍናችን ዓባይ በዚህ ልክ ለኢትዮጵያ ሕይወት መሆኑን አለማሳየታችን ነው። ግብጾች በሰው ሰራሽ መንገድ የፈጠሩትን ትርክት እኛ በተፈጥሮ በተሰጠን ፍጥረታዊ እውነታ ገዝፈን መሸፈን አለመቻላችን ነው።
እንዲያውም ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ እንቅስቃሴዎች ባይጀመሩ ኖሮ በአሁኑ ትውልድ የመታወቅ ዕድሉ ጠባብ ነበር። ምክንያቱም ዓባይ በብዛት ስሙ የሚነሳው በገጠሩ ክፍል ነው፤ ከተሜነት እየተስፋፋ ሲሄድ ከዓባይ ጋር የሚኖረው ቁርኝት እየራቀ ይሄዳል። ስለዚህ የተማረው ክፍል በመገናኛ ብዙኃንና በየመድረኮች ማሳወቅ አለበት። የከተሜው ማህበረሰብ ዓባይን በዕለት ከዕለት እንቅስቃሴው ውስጥ የሚያስታውስባቸው ነገሮች መኖር አለባቸው።
ዓባይን ከሚያስተዋውቁ ነገሮች አንዱ ደግሞ ስያሜዎች ናቸው። የፋይናንስ ተቋማት፣ የተለያዩ ፋብሪካዎች፣ የመገልገያ ንግድ ቤቶች፣ ተሽከርካሪዎች… የመሳሰሉት በየቦታው የመታየት ዕድል ስላላቸው ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው።
ዓባይ እንደ ስሙ ሰፊ ነው የሚባለው ለዚህ ነው። የምንጠቀምበት አጋጣሚ ከውሃ ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም። ዓባይ የሚለው ቃል ከወንዝነት ያለፈ ነው። ትልቅነትን፣ ዘላቂነትን፣ አያልቄነትን… ለመግለጽ የምንጠቀመው ነው። ‹‹ዓባይን ያላየ ምንጭ ያመሰግናል›› የሚባለው አባባልም ትልቅነትንና አያልቄነትን ለመግለጽ ነው።
ወዲህ ደግሞ ወደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ እንምጣ። በየዘመኑ ያለ ትውልድ የሚወደስበት ታሪክ አለው። ለምሳሌ የዓድዋ ትውልድ እነሆ ከመቶ ምናምን ዓመታት በላይ እየተወደሰ ነው፤ በስማቸው እየፎከርን ነው። ይህ የህዳሴ ግድብ ደግሞ የዚህ ትውልድ ሕይወት አካል ነው። ለሺህ ዘመናት ሳይደፈር የኖረውን ዓባይ የደፈረ እና ግድብ የሰራ ነው። ስለዚህ በአባቶቻችን ታሪክ እንደምንኮራው ሁሉ የእኛም የሕይወት ታሪክ ትልቁ ትርክት ነው።
ለጊዜው በፕሮጀክት ስም ይጠራ እንጂ ፤ በዘመናት ውስጥ ከታሪክም በላይ ሕይወት ነው። ሕይወት ነው ሲባል በዚህ ፕሮጀክት የሚድኑ ነፍሶች ይኖራሉ ማለት ነው። እነዚያ በጭስ ዓይናቸው የሚሟሟ እናቶች ሕይወት ይቀየራል ማለት ነው። የሚደርስባቸው የጤና ችግር ይቀረፋል ማለት ነው። አሁን ዘመኑ የኤሌክትሪክ ነው። ቤት ውስጥ መብራት ሲጠፋብን ጾማችንን ልናድር እንችላለን። ስለዚህ ሕይወት ሆኗል ማለት ነው።
ግብጾች ዓባይን ‹‹ሕይወትታችን ነው ›› ያሉት ከዓባይ ወንዝ ላይ በብርጭቆ እየጨለፉ የሚጠጡት ሆኖ አይደለም። በዘመናዊ መንገድ የሚበላም የሚጠጣም ስላደረጉት ነው። ለኢትዮጵያ ደግሞ ከዚህም በላይ ነው፤ ምክንያቱም ከታሪካችንና ከማህበራዊ ስሪታችን ጋር የተቆራኘ ስለሆነ!።
በዚህና ከዚህም በላይ በሆኑ ዛሬ ላይ ባልዘረዘርኳቸው ምክንያቶች ዓባይ ለኢትዮጵያ ወንዝ ብቻ ሳይሆን ሕይወት ነው!
ሚሊዮን ሺበሺ
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2015