መቼም ይህን አባባል በሰማን ጊዜ ወደ አዕምሯችን ጓዳ ሰተት ብለው የሚመጡት ሁለት ፍጹም የሚመሳሰሉ ነገሮች ስለመሆናቸው የማይካድ ሃቅ ነው። ይሁንና ዛሬ ይህን አባባል ለጽሁፌ ርዕስ ገላጭ ነው ብዬ ስነሳ ታድያ ያለምክንያት አይደለም። ይልቁንም ከሚመሳሰሉ ነገሮች ይልቅ የማይነጣጠሉ ነገሮችን ላሳይበት ስለወደድኩ ነው።
እነዚህ መመሳሰል ሳይሆን ፍጹም መነጣጠል የማይቻላቸው ‹‹የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች›› እንጀራና ኢትዮጵያውያን ናቸው። ኢትዮጵያውያኑ ከእንጀራ ጋር ባላቸው ጥብቅ ቁርኝት የተነሳ ተነጣጥለው ሊታዩ የማይችሉ ‹‹የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች›› ናቸው።
ኢትዮጵያውያን ዋናውና ቀዳሚው ምግባችን እንጀራ ነው። የእንጀራው ማባያ ወጥ ምንም ይሁን ምን እንጀራ ለኢትዮጵያውያኑ የየዕለት ምግብ በመሆኑ ምክንያት እንጀራ የማይበላ ኢትዮጵያዊ አለ ማለት አይቻል ይሆናል። ቢባልም ከእውነታ መራቅ አይደለም።
ከዚህ በላይ ግን እንጀራ ለኢትዮጵያውያን ከምግብነቱ ባለፈ የብዙ ነገሮቹ መገላጭ ባህልና እሴቱን ማንጸባረቂያም ጭምር ነው። ለአነብነትም ምርቃት የሚመርቅ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ‹‹እንጀራ ይውጣልህ/ሽ›› ብሎ ነው። ይህ ምርቃት ታድያ በኢትዮጵያ ትልቁ ምርቃት ነው።
ዜጎች ሥራ ፍለጋ ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ ሲንቀሳቀሱም እንጀራ ፍለጋ ተሰደደ፣ ሄደ፣ ተንገላታ፣ ደከመ ወዘተ… በማለት እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ከእንጀራ ፍለጋ ጋር ይቆራኛል። በተጨማሪም ኢትዮጵያዊ ፈጣሪውን ሲማጸን በጸሎት ውስጥ የዕለት ጉርሱ የሆነውን እንጀራ ሳይነሳ አይቀርም።
ለአብነትም የክርስትና ዕምነት ተከታዮች በጸሎታቸው መካከል ‹‹…የዕለት እንጀራችንን ስጠን ዛሬ…›› የሚል ሐረግ ይጠቀማሉ የሌሎች ዕምነት ተከታዮችም ይህንኑ ሀሳብ የሚጋሩ እንደሆነ ዕምነት አለኝ፡፤
ለኢትዮጵያውያን ከምግብ በላይ ሆኖ ላይ ታች የሚያባዝነው ይህ እንጀራ ታድያ ከዕለት ጉርስ ባለፈ የጓዳችን ሙላት፤ የገጻችን ወዝ በመሆን ከእኛነታችን ነጥለን የማናየው ‹‹የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ›› ዋና ጉዳያችን ነው። እንጀራን እንጀራ ያደረገው ጤፍ ከኢትዮጵያውያኑ መሬት ብቻ መብቀሉም ቁርኝቱን ይበልጥ ሳያጠነክረው አልቀረም። ‹‹አፍንጫ ሲነካ አይን ያለቅሳል ለካ›› እንደሚባለው ሆነና ከሰሞኑ የእንጀራ ፈጣሪ በሆነው የጤፍ ምርት ላይ መዲናዋ ስትታመስ ሰነባብታለች።
ባለፈው ሰሞን ባልተለመደ ሁኔታ በአዲስ አበባ ከተማ የተስተዋለው የጤፍ ምርት እጥረትና የዋጋ ጭማሪ መነጋገሪያ ሆኖ ሰነባብቷል። ከፍተኛ ጭማሪ ባሳየው የጤፍ ዋጋ ምክንያትም አንድ እንጀራ ከአስር ብር ተነስቶ እስከ 17 እና 20 ብር ድረስ ተሸጧል።
ይህም የኑሮ ውድነቱን አባብሶታል። ‹‹…ደግሞ ባይኔ መጣሽ…›› እንዲል ድምጻዊው ኢትዮጵያዊው የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ሆኖ ከመመሳሰል በላይ ከዕለት ተዕለት ማዕዱ የማይጠፋው እንጀራ ዋጋ በመናሩ የተነሳ የነበረውን ስጋት ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሲገልጽ እንደነበር ይታወሳል።
እርግጥ ነው የኑሮ ውድነት በየጊዜው አናት አናቱን ለሚለው ሸማች የጤፍ ዋጋ መጨመር አዲስ ነገር አይደለም ይሆናል። ነገር ግን የጤፍ ዋጋ ለማሰብ በሚከብድ መልኩ ድንገት ተነስቶ ሽምጥ መጋለቡና ዋጋው አልቀመስ ማለቱ ሸማቹን ግራ ከማጋባት በላይ መንግሥትም ጉዳዩን ቆም ብሎ እንዲያስብና እንዲያጤን አድርጎታል። መንግሥት ለጉዳዩ በሰጠው ትኩረትም በአሁን ወቅት ያለአግባብ የተሰቀለው የጤፍ ዋጋ እየወረደ መምጣቱን መመልከት ችለናል።
አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከጊዜ ጋር እሽቅድምድም የያዘ የሚመስለው የጤፍ ዋጋ ዕለት ተዕለት እያሻቀበ ሸማቹን ለምሬት ስለዳረገው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳር የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች የጋራ መፍትሄ ለማምጣትና ለሰው ሰራሽ እጥረት ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን ለመፍታት መፍትሄ አምጪ እንቅስቃሴዎች ማድረግ ጀምረዋል። አገሪቷ የጤፍ ምርትን በገፍ እንዳመረተችና የማምረት ዕምቅ አቅም እንዳላት ስለሚታወቅም ሰው ሰራሽ ሆኑ ችግሮችን መፍታት ከተቻለና የገበያ ስርዓቱ መስመር ከያዘ ለችግሩ ዘለቄታዊ መፍትሄ እንደሚመጣ የሚያጠራጥር አይሆንም።
በከተማዋ የታየው የጤፍ ዋጋ ንረትም በኬላዎች አካባቢ በተፈጠሩ አላስፈላጊና ሕገወጥ ተግባራት ምክንያት እንደሆነ መረጃዎች አመላክተዋል። እርግጥ ነው ሕገወጥ ተግባራት በአገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች እዚህም እዚያም የሚስተዋሉ ቁልፍ ችግሮቻችን ናቸው። እነዚህን ሥር የሰደዱና የገነገኑ ችግሮችን ታድያ በአንድ ጀንበር ነቅሎ መጣል የማይቻል ቢሆንም በጊዜ ሂደት መፍታት እንዲቻል ግን የቤት ሥራውን ከዛሬ መጀመር ያስፈልጋል።
ከኢትዮጵያውያን ገበታ የማይነጠለው ጤፍ ዋጋው በከፍተኛ መጠን በመናሩ ምክንያት ሸማቹ ስጋት ውስጥ ከመግባቱም ባለፈ የኑሮ ውድነቱ ይበልጥ እንዲሰማውም አድርጓል። ይሁንና በአሁን ወቅት ጤፍን ጨምሮ የምግብ ፍጆታ እቃዎች ገበያን መንግሥት ለማረጋጋት ከላይ ታች እያለ ይገኛል። በመሆኑም መሰረታዊ የህብረት ሥራ ማህበራት አንድ ኪሎ ግራም ጤፍን እንደየደረጃው ከ55 እስከ 68 ብር መሸጥ እንዲችል እየሠሩ መሆኑን እያስረዱ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ በበኩሉም ሰሞኑን በአስደንጋጭ ሁኔታ የናረውን የጤፍ ዋጋን ከረፈደም ቢሆን ገበያውን ለማረጋጋት በአገሪቱ በበቂ ሁኔታ ተመርቷል ያለውን ምርት ወደ መዲናዋ ማስገባት መጀመሩን እየገለጸ ይገኛል። በተለይም በከተማዋ የተፈጠረውን የገበያ ንረት ለማረጋጋት 300 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ምርቶች ለገበያ መቅረባቸው ተገልጿል።
ማንኛውም ችግር የራሱ የሆነ መፍትሔ እንዳለው ሁሉ በገበያው አለመረጋጋትም የተፈጠረውን ችግር ለመቆጣጠር እየተደረገ ያለውን ጥረት ይበል የሚያሰኝና የሚያበረታታ ነው። ይሁንና ‹‹ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ›› የሚለውን የአበው ተረት በአግባቡና በወቅቱ መጠቀም ችግሮችን ከማቅለል ባለፈ ችግሮች የሚፈጠሩበትን ዕድልም የሚያጠብ በመሆኑ ትኩረታችን ዘላቂ መፍትሔዎች ላይ ይሁን። ሰላም!
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን መጋቢት 17 ቀን 2015 ዓ.ም