መሰረተ ልማት ለአገር ብሎም ለከተማ እድገት ምሶሶ ነው። የለውጥና የእድገት ካስማ የሆነውን የመሰረተ ልማት ዝርጋታ በአግባቡ ያከናወኑ አገራት የዓለማችን የለውጥና የብልጽግና አብነት ተደርገው ይወሰዳሉ። በአንጻሩ ደግሞ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ወደ ኋላ የቀሩ አገራት የድህነት እና ኋላቀርነት አብነት ሆነው ይኖራሉ።
ኢትዮጵያ ላለፉት በርካታ ዓመታት በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ረገድ አመርቂ ውጤት ማስመዝገቧ ይታወቃል። በመሰረተ ልማት ግንባታ ረገድ ብዙ ርቀት ብትጓዝም፣ ግንባታዎቹን በተቀናጀ መንገድ የመምራት ልምዷ ግን እምብዛም ነው።
መሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት የመሰረተ ልማት ዝርጋታ በየፊናቸው እያካሄዱ ያለበት ሁኔታ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ በሚፈለገው ፍጥነት እንዳይካሄድ እንቅፋት ሆኗል። ሀብት አላግባብ እንዲባክንም መንስኤ ሆኗል። የአገር ሀብት እንዳይባክን እና የመሰረተ ልማት ዝርጋታን ማፋጠን እንዲቻል የመሰረተ ልማት ዝርጋታን አቀናጅቶ መምራት ለአገርም ሆነ ለከተሞች እድገትም ተኪ የለውም።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ በመሰረተ ልማት ግንባታ፣ ዝርጋታና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች ዙሪያ በዋና ኦዲተር በቀረበለት የክዋኔ ኦዲት ላይ ከወር በፊት ባካሄደው ውይይት፤ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ረገድ ቅንጅታዊ አሰራርን በመተግበር ረገድ የሚመለከታቸው አካላት ብዙ መስራት ቢጠበቅባቸውም፣ የሚጠበቅባቸውን ያህል እንዳልሰሩ ጠቁሟል። በተለይም የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የመሰረተ ልማቶች ግንባታ በተቀናጀ መንገድ እንዲገነባ የሚጠበቅበትን አልሰራም ብሏል። በዚህም ምክንያት አገሪቱ ብዙ ዋጋ እየከፈለች መሆኗን አመልክቷል።
በእርግጥ በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የመሰረተ ልማት በሚያቀርቡ ተቋማት መካከል መናበብ ባለመኖሩ አንዱ የገነባውን ሌላው ሲያፈርስ መመልከት ተለምዷል። አንዳንድ ጊዜ አንዱ የገነባውን መሰረተ ልማት ወር እንኳን ሳያገለግል ሌላኛው አፍርሶ በቦታው የራሱን መሰረተ ልማት ሲዘረጋ ይታያል።
አንዳንድ ጊዜ ተቋማቱ በአንድ መንግሥት የሚመሩ መሆናቸውን እንድንጠራጠር የሚያደርጉ ተግባራት ሲከናወኑ ይስተዋላል። የመንገድ መሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋም መሰረተ ልማቱን ዘርግቶ ካጠናቀቀ ብዙም ሳይቆይ ኢትዮቴሌኮም የራሱን መሰረተ ልማት ዘርግቶ ሲጨርስ፣ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ፍሳሽ ማስወገጃ መስመር ግንባታ ለማካሄድ ይነሳል፤ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር ዝርጋታ ተጠናቀቀ ተብሎ እፎይታ ሊገኝ ነው ሲባል ለኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ አዲስ ቁፋሮ ይጀምራል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኢትዮጵያ በዴቻ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፤ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ በተቀናጀ መንገድ ማካሄድ አለመቻሉ አገሪቱን ብዙ ዋጋ እያስከፈላት ነው። የተቀናጀ አሰራር አለመኖር በአገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ላይ ትልቅ ተግዳሮት ሆኖ ቆይቷል። መሰረተ ልማት የሚገነቡ ተቋማት በአግባቡ ተቀናጅተው ባለመስራታቸው ከፍተኛ የሕዝብ እና የመንግሥት ሀብት እየባከነ ቆይቷል። በቅንጅት እጦት ምክንያት በአገር አቀፍ ደረጃ የባከነውን ሀብት መጠን በእርግጠኝነት መገመት ባይቻልም ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ እንዳለ በተለያዩ አጋጣሚዎች በዘርፉ ባለሙያዎች እና በመሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት ይነሳል።
ባለፈው ዓመት የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ያካሄደው ጥናት እንዳመላከተው በአገር ደረጃ ተቀናጅቶ ባለመስራቱ አገሪቱ ላልተገባ ወጪ እንድትዳረግ ምክንያት እየሆነ መሆኑን አመላክቷል።
በቅንጅት እጦት ምክንያት አገሪቱ እየከፈለች ያለችው ዋጋ ከዚህም የበለጠ ነው። ለአብነት መንገድ ሲሰራ የመንገድ ዝርጋታ እና የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ በሚያካሂድ አካል መካከል ቅንጅታዊ አሰራር ባለመኖሩ የኤሌክትሪክ ፖል መነሳት ባለበት ወቅት ሳይነሳ የሚቀርበት አጋጣሚ አለ። በዚህም ምክንያት የመንገድ ግንባታው ይጓተታል። ግንባታዎች በወቅቱ ሳይጠናቀቁ በሚቀሩበት ወቅት የሚፈጠር የግንባታ እና የግብዓት ዋጋ መናር ይከሰታል። ዘንድሮ መሰራት ያለበት ፕሮጀክት በተቋማት ቅንጅት እጦት ምክንያት ዘንድሮ ሳይጠናቀቅ ሲቀር ለዓመታት እየተጓተተ በሄደ ቁጥር የመሰረተ ልማቶቹ ግንባታ ጥራት እየቀነሰ፣ የግንባታ ግብዓት ዋጋ እየጨመረ ፣ለሰው ኃይል የሚከፈለው ክፍያ እየጨመረ፣ ለካሳ የሚከፈለው ክፍያም እየጨመረ ይሄዳል። ይህም የአገር ሀብት በአላስፈላጊ ሁኔታ እንዲባክን እያደረገ ይገኛል ይላሉ።
እንደ አቶ ኢትዮጵያ ማብራሪያ፤ ይህ የቆየ ችግር ለመፍታት በተለያዩ ጊዜያት ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል። ችግሩን እንደሚፈታ ተስፋ የተጣለበት ተቋም ከስድስት ዓመት በፊት ተቋቁሟል። ተቋሙም የተቀናጀ የመሰረተ ልማት ኤጀንሲ ይሰኛል። ይህ ተቋም እጅግ ትልቅ ተቋም ነው። በመሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት መካከል የሚታየውን የቅንጅት ችግሮችን እንዲፈታ ነው የተቋቋመው። ወደ ስራም ገብቶ ነበር።
ሆኖም የተቋሙ መቋቋም ችግሩን አልፈታም። በመሆኑም የተቋሙ ሙሉ ስራው ወደ ከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር መጥቶ ሚኒስቴሩ ክትትል እያደረገበት የመሰረተ ልማቶች ግንባታ እንዲቀናጅ ጥረት እየተደረገ ነው። የመሰረተ ልማት ዝርጋታ የሚያካሂዱ አገር አቀፍ ተቋማት፤ የቴሌኮም፣ የመንገድ፣ የመብራት፣ የውሃ፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ እና አቪዬሽን ተቋማት በጋራ ተቀናጅተው መስራት የሚችሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር በዋናነት እነዚህ ተቋማት የጋራ እቅድ እንዲያዘጋጁ የመግባቢያ ሰነድ የመፈራረም ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል።
ተቋማቱ እያንዳንዱን ስራ በየፊናቸው ከሚሰሩ ይልቅ አንዱ ከአንዱ ጋር ተናቦ መስራት ቢችል የሚፈጠረውን የገንዘብ፣ የጊዜ እና የቁሳቁስ ብክነት ማዳን እንደሚቻል የጠቆሙት አቶ ኢትዮጵያ፤ ህብረተሰቡም የሚፈልገውን የመሰረተ ልማት ፍላጎት በሚፈልገው ጥራትና ጊዜ ማግኘት የሚችልበት እድል ይፈጠራል ይላሉ። ይህንን በማሰብ የጋራ እቅድ እንዲኖራቸው ለማድረግ የጋራ የስምምነት ሰነድ እንዲፈራረሙ ማድረግ አስፈላጊ ሆኗል። ስምምነቱን መሰረት አድርጎ ለሚሰሩት ስራ የጋራ እቅድ እንዲኖራቸውም ጥረት መደረጉን አብራርተዋል።
እንደ አቶ ኢትዮጵያ ገለጻ፤ በጋራ እቅዳቸው መሰረት ችግሮች እንዲፈቱና በየጊዜው እየተገናኙ ስራዎችን እንዲገመግሙ እየተደረገ ነው። ከማቀድ ባለፈ ስራዎችን ታች ድረስ ወርዶ ለመከታተልና ድጋፍ ለማድረግ እየተሰራ ነው። እነዚህ ስራዎቹ ምን ይመስላሉ፣ እንዴት እየተሰራ ነው የሚለው መመልከት ያስፈልጋል። የመንገድ፣ የኤሌክትሪክ እና የቴሌኮም መሰረተ ልማት ሲሰራ እንዲሁም ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሲገነቡ እና በየቦታው የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ሲስፋፋ የሚሰሩት የቅንጅት ስራዎች በክትትል እና ድጋፍ አንድ የማድረግ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው።
አገሪቱን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለ የሚገኘው ያልተቀናጀ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ መንስኤዎች በርካታ ቢሆኑም፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ማስተር ፕላን አለመኖር፣ ለችግሩ ዋነኛው መንስኤ ነው የሚሉት አቶ ኢትዮጵያ፤ የመሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማትን ለማቀናጀት ከዚህ በፊት ያልነበረ አገራዊ የተቀናጀ የመሰረተ ልማት ማስተር ፕላን አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት፤ የማስተርፕላን ዝግጅት ስራ እየተሰራ ነው ሲሉ ያብራራሉ። ይህንን ማስተር ፕላን ወደ ውጤት ለመቀየር እየተሰራ ነው።
በቅርቡም የማስተር ፕላን ዝግጅቱ ያለበትን ሁኔታ አስመልክቶ በአዳማ ውይይት ተደርጓል። የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ከሚያካሂዱ ዋና ዋና ተቋማት የፕላንና ልማት ሚኒስቴርን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተናበው መስራታቸው አስፈላጊ በመሆኑ የመጀመሪያው ምዕራፍ የማስተር ፕላን ዝግጅት ተጀምሯል።
የማስተር ፕላን ዝግጅት ለውይይት መነሻ የሚሆን በመድረኩ ላይ የመሰረተ ልማት አገራዊ ማስተር ፕላን እንዴት መዘጋጀት እንዳለበት፣ የማስተር ፕላኑ አስፈላጊነት፣ የሌሎች አገራት ተሞክሮ ምን እንደሚመስል፣ የተቀናጀ የመሰረተ ልማት ማስተር ፕላን ያላቸው አገራት ማስተር ፕላን በምን መልኩ አዘጋጁ፣ ማስተር ፕላን በማዘጋጀት ልምድ ያላቸው አገራት የትኞቹ ናቸው፣ እነዚህ አገሮች በማስተር ፕላኑ ምን ማትረፍ እንደቻሉ የሚያሳዩ ጽሁፎች ቀርበው ተቋማት ተናበው በመስራታቸው ምን ውጤት መጣ የሚለው ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጎባቸዋል። በቀጣይ ምን ምን መሰራት እንዳለበት የተመላከተበት ትልቅ መድረክ መካሄዱንም አብራርተዋል።
ማስተር ፕላኑን የማዘጋጀት ስራውን ከየተቋሙ የተወጣጡ ባለሙያዎች እየሰሩት ነው። እነዚህ ተቋማት በቀጣይ ማስተር ፕላኑን ወደ መሬት አውርደው፣ የሚያስፈልገውን በጀት፣ የሰው ኃይል እና የተለያዩ ግብዓቶች በማካተት፣ እነዚህን አሟልቶ በፍጥነት ማስተር ፕላኑ ተዘጋጅቶ በአገር አቀፍ ደረጃ ጸድቆ ወደ ስራ የሚገባበት ይሆናል። ማስተር ፕላኑ በቀጣይ አንድ ዓመት ውስጥ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ኢትዮጵያ ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ኢትዮጵያ ማብራሪያ፤ ማስተር ፕላኑ የቅንጅት ችግር እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለመከላከል በየደረጃው የሚገኙ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት የየራሳቸውን የአጭር እና የረጅም ጊዜ እቅድ ከአገራዊ ራዕይ ጋር በማጣጣም ማስተር ፕላኑን ማዘጋጀት ይቻል ዘንድ በቂ ግብዓት ማሰባሰብ አስፈላጊ በመሆኑ የውይይት መድረኩ ፋይዳው የላቀ መሆኑ ተጠቁሟል።
ማስተር ፕላኑ ተግባራዊ ሲሆን ከአሁን በፊት የተፈጠሩት እና ይፈጠራሉ ተብለው የሚሰጉት ችግሮች እየተቀረፉ የሚሄዱበት ሂደት ይኖራል ያሉት አቶ ኢትዮጵያ፤ በአገር አቀፍ ደረጃ የተለያዩ መሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት መሰረተ ልማቶችን በመዘርጋት ላይ ባሉ ተቋማት መካከል ቅንጅት ሲኖር የሀብት፣ የጊዜ እና የሰው ኃይል ብክነትን ማስቀረት ይቻላል ብለዋል።
በውይይት መድረኩ የፕላንና ልማት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር፣ ኢትዮ ስፔስ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ መብራት ኃይል፣ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን፣ የአዲስ አበባ ፕላን ኮሚሽን እና የአዲስ አበባ ግንባታ ፈቃድ ተቋማት ለአገራዊ ማስተር ፕላኑ ዝግጅት ከየተቋማቸው ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት አስፈላጊውን ግብዓት መስጠታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
አገራዊ የተቀናጀ የመሰረተ ልማት ማስተር ፕላንን በቁርጠኝነት ተግባራዊ ለማድረግ በሚወጡ መመሪያዎች ዙሪያ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው በመስራት የአገርን ሀብት ከብክነት ማዳን ይገባል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን መጋቢት 16/2015