ወጣት ሻላሞ እዮብ በሃዋሳ ዙሪያ ሮኬሰ ሱኬ ቀበሌ ነው ተወልዶ ያደገው። እንደብዙዎቹ የሃዋሳ ዙሪያ ወጣቶች እርሱም የግብርና ስራን ከቤተሰቦቹ ተምሯል። በግብርና ብቻ ሳይሆን በቀለም ትምህርቱም ገፍቶ ከአፍሪካ ቤዛ ኮሌጅ በአካውንቲንግ በ2012 ዓ.ም በዲግሪ ተመርቋል። እስከ 2014 ዓ.ም ድረስም በለስ ሳይቀናው ቀርቶ ስራ ሳይዝ ቆይቷል።
ሆኖም የሲዳማ ክልል የስራ፣ ክህሎትና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ በ2014 ዓ.ም ወጣቶችን አደራጅቶ ወደስራ ከማስገባቱ በፊት በአስተሳሰብ ለውጥ ዙሪያ ስልጠናዎችን ሲሰጥ እርሱም ተካፍሎ የሚፈልገውን እውቀት ቀስሟል። ልክ እንደእርሱ ሁሉ እርሱ በተመረቀበት ዓመት ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት የተመረቁ ወጣቶችም ስልጠናውን ተከታትለዋል።
ከስልጠናው በኋላ እርሱን ጨምሮ 19 ወጣቶች ሆነው በሶስት ማህበራት በመደራጀት በግብርና ዘርፍ ስራ ጀምረዋል። የግብርና ስራውን የጀመሩትም አብዛኞቹ ወጣቶች በሚኖሩበት ሮኬሰ ሱኬ ቀበሌ በሚገኝ አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በኪራይ በቀረበላቸው መሬት ላይ በቆሎ በማምረት ነበር። በዚሁ ዓመትም በቆሎ አምርተው እሸቱን ለገበያ አቅርበው 800 ሺ ብር ማግኘት ችለዋል።
በዚሁ ዓመትም በተመሳሳይ በቆሎ በማምረት 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት አቅደው እየተንቀሳቀሱ ሲሆን የማሳ ዝግጅት አድርገዋል፤ ከክልሉ ግብርና ቢሮ የበቆሎ ዘር ለመውሰድም ተዘጋጅተዋል። ከበቆሎው በኋላም ቦሎቄ ወይም ድንች የመዝራት ሃሳብ አላቸው።
‹‹ትምህርቴን አጠናቅቄ ስራ ለማግኘት ብዙ ተቸግሬ ነበር›› የሚለው ወጣት ሻላሞ፤ በማህበር ተደራጅቶ በግብርና ዘርፍ መስራት ከጀመረ ወዲህ የተሻለ ገቢ እያገኘ እንደሚገኝና ለቀጣይ ህይወቱ ጥሩ መሰረት እየጣለ እንደሚገኝ ይገልፃል። በተለይ ደግሞ ግብርና ስራ ብዙም ውጤታማ አያደርግም የሚል አስተሳሰብ እንደነበረውና ገብቶ ሲሰራበት ግን የተሻለ ገቢ የሚያስገኝና ህይወት ሊለውጥ የሚችል መሆኑን እንደተረዳም ነው የሚናገረው።
በተመሳሳይ ተመርቀው ያለስራ የተቀመጡ ሌሎች የክልሉ ወጣቶችም በማህበር ተደራጅተው ስራ ሳይንቁ ቢሰሩ ከራሳቸው አልፈው ቤተሰባ ቸውን፣ አካባቢያቸውንና ክልላቸውን ሊለውጡ እንደሚችሉ ይጠቁማል። ሁሉም ወጣቶች ተቀጥሮ ከመስራት ይልቅ በማህበር ተደራጅቶ የመስራትን ባህል ሊያዳብሩ እንደሚገባም በዚሁ አጋጣሚ ይመክራል።
ወጣት ሳሙኤል ዘለቀም በ2013 ዓ.ም በፐብሊክ አድሚንስትሬሽን የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል። በ2015 ዓ.ም በአስተሳሰብ ለውጥ ዙሪያ የክልሉ የስራ፣ ክህሎትና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ የሰጠውን ሥልጠና ወስዶ ከሌሎች 26 ተመራቂ ተማሪዎች ጋር በግብርና ዘርፍ በማህበር ተደራጅቶ ስራ ጀምሯል።
በተደራጁበት በዚሁ የ2015 ዓ.ም ዘመንም በአርቤጎና ወረዳ ሆሰና ሜቶ ቀበሌ ገብስ ዘርተው ምርት እየሰበሰቡ ይገኛሉ። እስካሁንም ስልሳ ሶስት ኩንታል ገብስ መሰብሰብ ችለዋል። ቀሪውን 10 ኩንታል የመሰብሰብ ስራ እየሰሩ ነው። በሄክታር 200 ኩንታል ገብስ ለመሰብሰብና በአንድ ኩንታል 336 ሺ ብር ገቢ ለማግኘት እቅድ የነበራቸው ቢሆንም መሬቱን ለማከም ኖራ ባለማግኘታቸው የሚጠበቀውን ምርት ሊያገኙ እንዳልቻሉ ይናገራል ወጣት ሳሙኤል።
ሆኖም ነገሮች ከተስተካከሉ በቀጣይ የተሻለ የገብስ ምርት በማምረትና ለገበያ በማቅረብ ገቢያቸውን ለማሳደግ ብሎም ሌሎች ምርቶችንም በማምረት ተጠቃሚ ለመሆን እየሰሩ እንደሚገኙም ይገልፃል። በማህበር ተደራጅቶ በመስራቱ ደስተኛ መሆኑንና በቀጣይ እርሱና የማህበሩ አባላት ጠንክረው ከሰሩ የተሻለ ምርት የማግኘት እድል እንዳላቸው ይጠቁማል።
አቶ ከፍያለው ከበደ የሲዳማ ክልል ስራ፣ ክህሎትና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የገጠር ስራ እድል ፈጠራ ኃላፊ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት በ2015 ዓ.ም 58 ሺ 146 ለሚሆኑ በክልሉ ለሚገኙ ወጣቶች ቋሚ የስራ እድል ለመፍጠርና 50 ሺ ለሚሆኑት ነባር ኢንተርፕራይዞች የተለያዩ ድጋፎችን ለማድረግ እቅድ ተይዞ ወደስራ ተገብቷል።
በዚሁ እቅድ መሰረት እስከ ሰባተኛው ወር መገባደጃ ድረስ 32 ሺ 262 ለሚሆኑ ወጣቶች በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፍ ቋሚ የስራ እድል መፍጠር ተችሏል። በእያንዳንዱ ዘርፎች በተናጠል ሲታይም በግብርና 6 ሺ 900፣ በኢንዱስትሪ 10ሺ238 እንዲሁም በአገልግሎት ዘርፍ 15 ሺ 124 የስራ እድል ለወጣቶቹ ተፈጥሯል።
በግብርናና ኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ በተለየ መልኩ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ሲሆን በዋናነት በገጠራማው ክፍል የትምህርት ቤት መሬቶችን ጭምር ለወጣቶች በማቅረብና አስፈላጊውን ግብአትና ስለጠናዎች እንዲያገኙ በማድረግ በግብርናው ዘርፍ እንዲሰማሩ ተደርጓል። በኢንዱስትሪ ዘርፍ በተለይ በተፈጥሮና በኢንዱስትሪ ማእድናት እንዲሁም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍም በርካታ የስራ እድሎች ተፈጥረዋል።
መንግስት ለግብርናው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደመሆኑና የሌማት ትሩፋትም ከዚሁ ጋር የሚያያዝ በመሆኑ ክልሉ ደግሞ ገበያ ተኮር ሰብሎች አብቃይና የበርካታ ተፈጥሯዊና የኢንዱስትሪ ማእድናት መገኛ ስለሆነም ጭምር የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራው ይበልጥ በግብርናና በኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ እንዲያተኩር መደረጉን ኃላፊው ያስረዳሉ።
እንደ አቶ ከፍያለው ገለፃ ቢሮው ካስቀመጠው እቅድ አኳያ አፈፃፀሙ ሲታይ የዓመቱን 69 ከመቶ ያህሉን ማሳካት ችሏል። ከሰባት ወሩ አንፃር ሲታይም ወደ 89 ከመቶ ያህሉን መፈፀም ተችሏል። በተለየ መልኩ ቋሚ የስራ እድል ላይ ትኩረት መሰጠቱ እንዲሁም ግዚያዊውን ደግፎ ወደቋሚ የማምጣት ስራ በመሰራቱ ብሎም ለምሩቃን ተማሪዎች የተለየ ትኩረት መሰጠቱ የስራ እድል ፈጠራውን ለየት ያደርገዋል። በተለይ በዲግሪና በዲፕሎማ ከተለያዩ የትምህርት ተቋማትና የቴክኒክና ሞያ ስልጠና ማእከላት ለተመረቁ ተማሪዎች በተለየ መልኩ ትኩረት ተደርጎ ተሰርቷል።
በዚሁ መሰረት 4 ሺ 200 ለሚሆኑ በዲግሪ፣ 10ሺ981 ለሚሆኑ በዲፕሎማ እና 17 ሺ 81 በሰርተፍኬት ለተመረቁና አስረኛና አስራ ሁለተኛ ክፍል ላጠናቀቁ ተማሪዎች ቋሚ የስራ እድል ተፈጥሯል። ለተቀሩት ወጣቶች ደግሞ በግዚያዊነት ስራ በመፍጠርና በመደገፍ ቋሚ የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው ተደርጓል። በገጠሩ አካባቢ ደግሞ በየወረዳው ያሉ ምቹ ሁኔታዎችን በመጠቀም በግብርናው መስክ የራሳቸውን ስራ ፈጥረው እየተንቀሳቀሱ ያሉ ወጣቶችም አሉ።
ክልሉ ባለፉት ሶስትና አራት ዓመታት የለውጡን መነሻ ተከትሎ በርካታ ስራ አጥ ወጣቶች የሚገኙበት እንደመሆኑ ይበልጥ ምሩቃን ተማሪዎች ላይ ትክሩት ተደርጎ የማይሰራ ከሆነ ጉዳዩ ይበልጥ አሳሳቢ እንደሚሆን ከግምት ውስጥ በማስገባት በዚህ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ተሰርቷል። በየደረጃው ያሉ አካላትም ከተመረቁ ተማሪዎች በታች ባሉት ወጣቶች ላይም በማተኮር የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው ተደርጓል።
ይህ በመደረጉም በክልሉ ያለውን የስራ አጥ ምጣኔ በ2013/14 ዓ.ም በገጠርና በከተማ ከነበረበት 17 ነጥብ 4 ከመቶ በ2015 ዓ.ም ወደ 13 ነጥብ 9 በመቶ ማውረድ ተችሏል። አገር ላይ ካለው የስራ አጥነት ምጣኔ አንፃርም ሲታይ የክልሉ የስራ እድል ፈጠራ ሂደት ፈጣን መሆኑን ያሳያል።
አቶ ከፍያለው እንደሚሉት ለወጣቶቹ የስራ እድል ለመፍጠር በቅድሚያ ልየታ ተደርጎ በአስተሳሰብ ለውጥ ዙሪያ ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል። በዚህም በአብዛኛው ተመራቂ ወጣቶች ዘንድ የነበረውን በመንግስት ተቋማት ውስጥ ተቀጥሬ እሰራለሁ የሚለውን አሰተሳሰብ መቀየር ተችሏል።
ይህንኑ ታሳቢ በማድረግም የክልሉ የሲዳማ ክልል ስራ፣ ክህሎትና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ባለፈው በጀት ዓመት 8 ሺ 900 ለሚሆኑ ወጣቶች የአስተሳሰብ ለውጥ ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል። እነዚህ ሰልጣኝ ወጣቶች የራሳችንን ስራ ፈጥረን የምንሰራ ከሆነ ከራሳችን አልፈን ለሌላም መትረፍ እንችላለን የሚለውን አላማ መሰነቅ ችለዋል።
ቢሮውም ወጣቶቹ የሚሰማሩባቸውን ማዕቀፎችን እንደገና የመከለስ ስራ ሰርቷል። በየአካባቢው ያሉ ፀጋዎችና ምቹ ሁኔታዎች ምን እንደሆኑ፣ የትኞቹ አካባቢዎች ላይ ወጣቶቹ ቢሰማሩ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ በመለየት ወደስራ ተገብቷል። ለአብነትም በሃዋሳ ከተማና ዙሪያ ላይ በኮንስትራክሽን በተለይ ደግሞ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ወጣቶቹ ቢሰማሩ በአጭር ግዜ ውጤታማ ሆነው ለሌሎች ስራ ወጣቶችም በግልም ሆነ በግዚያዊነት በሚሰጡት የስራ እድል መፍጠር እንደሚችሉ ተረጋግጦ በዚሁ ዘርፍ እንዲሰማሩ ተደርጓል።
በሌላ በኩል ደግሞ ለዶሮ ልማት፣ ለወተትና ለከብት ማደለብ የትኞቹ ወረዳዎች ምቹ እንደሆኑ ቀድሞ በመለየት ወደ 41 የሚሆኑ የስራ እድል መፍጠሪያ ማዕቀፎች አሁን ያለውን የገበያ ሁኔታና በየአካባቢው ያለውን እምቅ አቅም ታሳቢ በማድረግ የክለሳና ተጨማሪ ፓኬጆች እንዲጠኑ በማድረግ ለወጣቶቹ የስራ እድል ተፈጥሯል። ምሩቃን ተማሪዎችም ከግዜ ወደ ግዜ የመንግስትን ስራ ከመፈለግ ይልቅ የራሳቸውን ስራ እንዲፈጥሩ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
ለአብነትም በሃዋሳ ዙሪያ ባሉ ወረዳዎች በበቆሎ ሰብል አምና ቁጥራቸው በርከት ያሉና ወደ 380 የሚሆኑ በዲግሪ የተመረቁ ተማሪዎች ተሰማርተው የላቀ ውጤት ማምጣት ችለዋል። እነዚህ ወጣቶችም በመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጥሮ የመስራትን አስተሳሰብ ትተው ሙሉ በሙሉ በራሳቸው ስራ ላይ አተኩረዋል። በሰፋፊ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ያሉ መሬቶችን ተከራይተው ገብስና ስንዴ በማምረትም ጥሩ ውጤት እያስመዘገቡ መጥተዋል።
በካፒታል የሚሰሩ ፕሮጀክቶችም ለወጣቶች ብቻ እንዲሰጡ በመደረጉ የሚጠገኑና አዳዲስ መንገዶችን በዚሁ ዘርፍ የተደራጁ ወጣቶች እንዲሰሯቸው ተደርጓል። በ2013/14 በጀት ዓመት 3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘት ችለዋል። በዚሁ ዓመትም የተሻሉ ኢንተርፕራይዞች ተመልምለው ከ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እንዲገኙ ተደርገዋል። በሀዋሳ ከተማ አምና ከ1 ሺ 200 በላይ የሚሆኑ በዲግሪ የተመረቁ ወጣቶች በኮብል ስቶን ንጣፍ ስራ እንዲሰማሩ ተደርጓል።
አቶ ከፍያለው እንደሚናገሩት ከመንግስታዊ ድጋፎች ውስጥ ብድር፣ ቁጠባ፣ መሬትና ሼድ አቅርቦት ይገኙበታል። በዚህ ዓመት 556 ሄክታር መሬት ለወጣቶች ለማቅረብ ታቅዶ እስከ ሰባተኛው ወር መገባደጃ ድረስ 326 ሄክታሩን ማቅረብ ተችሏል። ይህም ከዚህ በፊት ቀድመው የተሰጡ መሬቶች እንዲመለሱ በማድረግ አሁን እንደገና ለወጣቶቹ የተሰጣቸውን ሳይጨምር በአዲስ መልክ ለወጣቶች እንዲሰጥ የተደረገ መሬት ነው። አምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ሆኖ ተገኝቷል።
ብድር አቅርቦትን በሚመለከት ክልሉ በዚህ ዓመት ለወጣቶች ስራ እድል ፈጠራ 100 ሚሊዮን ብር መድቧል። ከዚህ ውስጥ በመጀመሪያው ዙር 30 ሚሊዮን ብር ለወጣቶቹ ተላልፎ ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ። ከብድር የሚመለሰው ገንዘብም በድጋሚ ለአዳዲስ ስራ ፈጠራ እንዲውል ለወጣቶቹ ተሰጥቷል። 198 ሚሊዮን ብር ብድር ለማስመለስ ታቅዶም እስከ ሰባተኛ ወር ድረስ 75 ሚሊዮን ብር ያህሉን ማስመለስ ተችሏል። ከእቅዱ አንፃር ግን በቀጣይ ቢሮው ብዙ ነገር መስራት እንዳለበት ይጠቁማል። እንዲያም ሆኖ ግን ከፌደራል መንግስት የተመደበውን ጨምሮ እስከ ሰባተኛ ወር ድረስ 82 ሚሊዮን ብር ለወጣቶቹ የብድር ስርጭት ተደርጓል።
ወጣቶች ወደስራ ከተሰማሩ በኋላና ተሰማርተው ያገኙትን ውጤት መነሻ በማድረግ ገንዘብ እንዲቆጥቡ ተደርጓል። በዚሁ በጀት ዓመትም 89 ሚሊዮን ብር ለማስቆጠብ እቅድ ተይዞ እስከ ሰባተኛ ወር ድረስ 73 ሚሊዮን ብር ማስቆጠብ ተችሏል። ይህም ወጣቶቹ በተሰማሩበት ስራ ውጤታማ መሆናቸውን ያሳያል። ከስልጠና ጋር በተያያዘም 39 ሺ የሚሆኑ ወጣቶችን ለማሰልጠን ታቅዶ እስከ ሰባተኛ ወር ድረስ 19 ሺ 300 ወጣቶችን ስልጠና በመስጠት ወደስራ ማሰማራት ተችሏል። ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲታይ የተሻለ ነው።
ክልሉ በዚህ ደረጃ ለወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር ከስራ አጥነት እያላቀቀ ቢሆንም አሁን ካለው የስራ አጥነት ምጣኔ አንፃር ገና ብዙ መሰራት ያስፈልጋል። ለዚህም ነው ስራ አጥነት ላይ የተለየ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ያለው። በተለይ በተመራቂ ተማሪዎች ላይ እየተሰራ ያለው ስራ በወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ዙሪያ መሬት ላይ በትክክል እየተሰራ ያለውን ስራ ይጠቁማል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/2015