የኢክራም ሞተር ማኑፋክቸሪንግ ትሬዲንግ ማህበር መሥራችና ባለቤት ናቸው፡፡ ወይዘሮ ኢክራም እድሪስ፡፡ይሄን በስፋት በወንዶች የተያዘ ዘርፍ እሳቸው በዘመናዊ መልኩ በቴክኖሎጂ በተደገፈ ማሽን ይስሩት እንጂ እናታቸውም በባህላዊ አሰራር ተሰማርተውበት ለረዥም ጊዜ ይዘውት ቆይተዋል፡፡ ለወላጆቻቸው ሁለተኛ ልጅ የሆኑት ኢክራም ተወልደው ያደጉት ደሴ ከተማ ውስጥ ነው፡፡የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በደሴ ከተማ፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ሻሸመኔ በሚገኘው ኩየራ አዳሪ ትምህርት ቤት ነው የተማሩት፡፡
አባታቸው ገና በህፃንነታቸው በመኪና አደጋ በመሞታቸው በእናታቸው እጅ ነው ያደጉት፡፡ ከእናታቸው ጋር አብረው ይኖሩ የነበሩት ሴት አያታቸውም በእድገታቸውና በዛሬ ማንነታቸው ቀረፃ ላይ ከወላጅ እናታቸው ያልተናነሰ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ራሳቸው ይናገራሉ፡፡ እንዲያውም ሕብረተሰቡ ለወንድ በሰጠው የጋራዥ ሥራቸው ፀባይ ምክንያት እናታቸው እጃቸው በግራሶ እየተጨማለቀ መኪና ሲገጥሙና ሲፈቱ እንዲሁም ሲያሰማሩና ሲያስጭኑ ውጭ ውጭውን ስለሚሉ እሳቸውን ጨምሮ እህትና ወንድሞቻቸውን ያሳደጓቸው አያታቸው ነበሩ።
ሥራን በፍጥነት ማከናወን ባህላቸው ነው፡፡ አነጋገራቸውም ቢሆን እንደ እርምጃቸውና ሥራቸው ፈጠን ፈጠን ያለ ነው፡፡ ፈጣን አረማመዳቸው አዘወትረው ከሚለብሱትና ለሥራና ለእንቅስቃሴ ምቹ ነው ከሚሉት ጃኬትና ሱሪ ጋር ተዳምሮ ወንዳ ወንድ ያስመስላቸዋል፡፡ ድምፃቸውም ወፈር ጎርነንና ቆጣ ያለ ነው፡፡ በተፈጥሮ ከተሰጠው ውጭ በወንድና ሴት መካከል ባለው በየትኛውም ልዩነት አያምኑም፡፡ ቢሆንም ይሄ እምነታቸውም ሆነ ባህርያቸው ሴትነትን በመጥላት ወንድ ለመምስል ሆን ብለው ያደረጉት አይደለም፡፡
ገና የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ሳሉ የፍቅር ጥያቄዬን አልተቀበልሽም ብሎ ሊያስፈራራቸው የሞከረ ወንድ ተማሪን “በዚህ ሰዓት እዚህ ጋር ጠብቀኝና ይዋጣልን” የሚል ደብዳቤ እንዲደርሰው ካደረጉ በኋላ በሚገጥሙት ጊዜ በውስጣቸው እየተገነባ የመጣ የእኩልነት ማረጋገጫ ነፀብራቅ ተፈጥሮ ነው። በጭንቅላታቸው ላይ የሚጠመጥሙት ሻሽም ውቡንና ሴታ ሴት የፊት ገጽታቸውን ስላደበዘዘው ሴትነታቸውን መለየት የሚቻለው ሲቀርቧቸው ነው።
በተለይ ካምፓኒያቸው ውስጥ ቱታቸውን በመልበስ መኪና ሲፈቱና ሲገጣጥሙ ያየ ሴትነታቸውን ፈጽሞ አይጠረጥርም፡፡ ሥራው በስፋት በወንዶች ሲሰራ መኖሩና መለመዱ ደግሞ ወንድ እንጂ ሴት ወዳለመሆናቸው ድምዳሜ ላይ ከማድረሱም በላይ ለየት ያሉ የሚያስመስላቸው አትኩሮት ያስቸራቸዋል።“እንዴት ሴት እንዲህ ዓይነቱን ከባድ የጉልበት ሥራ ትሰራለች?” ብሎ ራስን ለመጠየቅም ያስገድዳል።
በዓለም የሚገኙ ታዋቂ ስም (ብራንድ) ያላቸውን መኪኖች የአካል ክፍሎቻቸውን ዓይነት ስም በየአገራቱ ቋንቋዎች ሲዘረዝሩ ላያቸው በአግራሞት ፍዝዝ ያደርጉና በአድናቆት ያስደምማሉ፡፡“እንደዚች ዓይነቷ ሴት ለታዳጊና ለወጣት ሴቶች አርአያ ያልሆነች ማን ሊሆን ነው?” በሚል ነበር ባለፈው ሳምንት የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ኢክራም የሥራ ተሞክሯቸውን እንዲያካፍሉ ያደረገው።
ምክር ቤቱ የዘንድሮ የዓለም የሴቶች ቀንን አስመልክቶ የራሳቸውን የገቢ ማስገኛ ሥራ በመፍጠር ከስኬት ደረጃ የደረሱ ሴቶችን አስተዋውቋል፡፡ የእውቅና እና የማበረታቻ ሽልማት ሰጥቷል፡፡ “የሴቶች የቢዝነስ አመራር” በሚል በኢንተር ላግዠሪ ሆቴል ባዘጋጀው የፓናል ውይይት ኢክራምን ጨምሮ የሕክምና ክሊኒክ ፈር ቀዳጅና የአከርካሪ አጥንት ሐኪም ዶክተር ሰላም አክሊሉ እንዲሁም አሁን ላይ በመላው አገሪቱ 40 ቅርንጫፎች ያሉት የካልዲስ ኮፊ ዘመናዊ ካፍቴሪያ መስራችና ባለቤት ወይዘሮ ፀደይ አስራት ታድመዋል።
በተጨማሪም የውዳሴ ግሩፕ መሥራችና ባለቤት ወይዘሮ ውዳሴ እንቁስላሴን በድምሩ አራት ስኬታማ ሴቶችን በመጋበዝ የጠንካራ ሥራ ባህል ተሞክሯቸውን በሴትነት ከገጠማቸው ውጣ ውረዱ ጋር እያዋዙ ለታዳሚው እንዲያካፍሉ አድርጎ ነበር፡፡
በአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የ75 ዓመት ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዝዳንት በመሆናቸው ከስኬት ደረጃ ከደረሱት የሚሰለፉት የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጤ ሁሉም ተሞክሯቸውን እንዲያቀርቡ በተጋበዙት መሰረት ወይዘሮ ኢክራምም በመድረኩ ተሞክሯቸውን አቅርበዋል፡፡ እኛም ለዛሬ የኢክራምን ተሞክሮ ልናጋራችሁ ወድደናል፡፡
በስፋት ወንዶች ወደ ተሰማሩበት መኪና የማስዋብና የጋራዥ ዘርፉን ወደ ማዘመን ዘርፍ ሲገቡ ዓላማ አድርገውት የነበረው የቆሸሸውን የጋራዥ ሥራ አካባቢ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ፀአዳ ማድረግም ጭምር ነበር፡፡ “ቀደም ብዬ በሥራው ስላለፍኩ የጋራዥ ሥራ አካባቢን እውቀዋለሁ”የሚሉት ኢክራም እንዳከሉት ልኩስኩስና ዝርክርክ ነው።
ሂደቱም፤ ቅልጥፍና፤ ፍጥነትና ጥራት አልነበረውም፡፡ የፍሬን ዘይትና ግራሶ ልብስና እጅ ያጨማልቅና ያቆሽሻል፡፡ ከዚህ ዓይነቱ ባህላዊ አሰራር መውጣት፤ ሥራውንም በደርዝ በደርዙ በመከፋፈል መለየት አስፈላጊ እንደሆነ ያምኑ ነበር፡፡ ይሄንኑ ሀሳብ ሰንቀው ወደ ዘርፉ ሲገቡ ከእናታቸው የቀሰሙት ልምድና የአስተዳደር ጥበብ መደላድል ስለሆነላቸው አልተቸገሩም፡፡ ምንም እንኳን ለወላጆቻቸው ሁለተኛ ልጅ ቢሆኑም እንደ አብዛኞቹ ኢትዮጵያን ሴት ልጆች በማንኛውም የቤት ውስጥ የሥራ ጫና አላለፉም።
እናታቸው ይልቁኑም ሙሉ በሙሉ ትኩረታቸው ትምህርት ላይ እንዲሆን ስለሚፈልጉም ነበር ኩየራ አዳሪ ትምህርት ቤት ያስገቧቸው፡፡ ሆኖም ለእረፍት በሚመጡበትና በሥራቸው ፀባይ ምክንያት ቤት ውስጥ በማያገኙዋቸውና ለማግኘት ወደ ሥራ ቦታቸው በሚሄዱበት ጊዜ ልክ እንደ ዶሮ ብልት ሁሉ እያንዳንዱን የመኪና አካል ክፍል ደህና አድርገው ያስጠኗቸው ነበር፡፡
እሳቸው በፊናቸው ልጆቻቸው በዚህ መልኩ ጥርሳቸውን ነቅለው እንዲያድጉ ማድረጋቸውን የሚያወሱት ኢክራም እናታቸው በተለይ ትምህርት ቤት ተዘግቶ ረዘም ላለ የክረምት እረፍት ወደ ቤት መጥተው ወደ ሥራ ቦታቸው በሚሄዱበት ጊዜ ስለ መኪና እና አጠቃላይ ጋራዥ ሥራ እንዲለማመዱ አድርገው ያሰደጓቸው መሆኑን ያስታውሳሉ፡፡
ከመኪና አካል ፈትቶ መገጣጠም ጀምሮ በቅጥቀጣው ረገድ ባሉት የሥራ ሂደቶች ሁሉ ያኔ ገና ነው የተካኑት፡፡ ሁኔታው ራሳቸውን ችለው በዘርፉ በሚሰማሩበት ጊዜ ከባዱን ሥራ አቅሎላቸዋል። ሆኖም ብዙ በመጓዝ ያሰቡበት ዘርፉን የማዘመን ስኬት ማማ ላይ ሳይወጡ ትዳር ውስጥ ገቡ፡፡ “ትዳር መሥርቼ ልጆች በመውለድ ሳሳድግ ከቆየሁ ከ10 ዓመት በኋላ ነው የተመለስኩት” ይላሉ፡፡ ታዲያ እሳቸው ስኬቴ የሚሏቸው በዚህ መልኩ ዋጋ የከፈሉላቸው ልጆቻቸውና ቤተሰባቸው ጭምር ናቸው፡፡ ዋጋ መክፈሉ በሕብረተሰቡ ውስጥ ከግምት ባይገባም እንደ ሴትና እናት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የተለመደ ተግባር ነው፡፡
አገርን የሚመሩ ሰዎች የሚያዘጋጁና የሚያቀርቡትም ሴቶች ከመሆናቸው አንፃር ትዳር መመሥረታቸው ልጆች ወልደው በማሳደግ እስከ 10 ዓመት ሥራውን በይደር ማቆየታቸው ኢክራም ለግል ቤተሰብ ብቻ ሳይሆን ለሕብረተሰብና ለሀገር ሲባልም የሚደረግ በመሆኑ ያምናሉ፡፡ እንደማይቆጩበትም ይናገራሉ፡፡ “ቁም ነገሩ ከዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ መመለሴና ያሰብኩበት መድረሴ ነው” ይላሉ።በእርግጥ ኢክራም አሁን ላይ በወንዶች በተያዘ የሥራ ዘርፍ ሴቶች መሰማራት እንደሚችሉና ውጤታማም እንደሚሆኑ ስኬታማ በሆነ ተግባራቸው አሳይተዋል። ያሳዩት እንዲህ በቀላሉ አይደለም።
ከጋራዡ ዘርፍ ጋር ከእናታቸው ያገኙት ባህላዊ አሰራር ልምድ እንደተጠበቀ ሆኖ ሥራውን በዘመናዊ መንገድ ለመሥራት ልጆቻቸውን ከማሳደጉ ጎን ለጎን በግላቸው ራሳቸውን በተለያየ መንገድ ሲያስተምሩ በመቆየታቸው ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ደግሞ ‹‹በዘርፉም ቢሆን የባከነ ጊዜ የለኝም ማለት እችላለሁ›› የሚሉት ኢክራም የተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ ስልጠናዎችን ሲወስዱ በመቆየት ወደ ዘርፉ መግባታቸውን ይናገራሉ፡፡
በመሰልጠንና በማሰልጠን እንዲሁም ከውጭ ዕቃዎችን በማስመጣት በባለቤታቸው የመኪና ዕቃ መለዋወጫ ውስጥ ተመድበው መሥራታቸውም ጥሩ ልምድ እንዲያገኙ አግዟቸዋል። ዓለም ላይ ቁጥር አንድ ኢንዱስትሪ የሚባለው ሰፊ ገበያ የሚከናወንበት ዘርፍ ይሄ የአውቶሞቲቭ ዘርፍ እንደሆነም ያነሳሉ፡፡ በመሆኑም ከፊላንድና ከተለያዩ የውጭ አገራት ለሥራቸው ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን እንደሚያመጡም ያወሳሉ። በዚህ መልኩ እንዳሰቡት የጋራዥ ዘርፉን ማዘመን ችለዋል። የጋራዡ ሥራ በቴክኖሎጂ በመታገዙ በፍጥነት መከናወን እንዲሁም ጥራቱ መጠበቅ ችሏል። ሥራው የሚከናወንበት ሥፍራ ገጽታው በራሱ ወደ ጽዱና ውብነት ለመቀየር በቅቷል፡፡
‹‹መኪና ማስዋብ ራሱን የቻለ አርት ነው›› የሚሉት ወይዘሮ ኢክራም ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ የተሰየመለት የራሱ ዘመናዊ ሂደት እንዳለውም ያብራራሉ፡፡ ተግባሩ መኪናን በቀለም ማስዋብንም እንደሚጨምርም ያወሳሉ።ሥራው በቅብብል የሚሰራ ሲሆን ቅብብሉ አካሉ (ቦዲው) ከአንዱ ወደ ሌላው ቦታ ከተሸጋገር በኋላ ተመልሶ ለሌላ ሥራ እዛው የሥራ ሂደት ላይ የሚመጣበት አጋጣሚ አለ፡፡ ለአብነት የመኪና አካል ከአቧራ ነፃ እንዲሆን ማድረግ የሥራው የመጀመሪያ ክፍል ነው፡፡ ከዛ ደግሞ ጓንት ተደርጎ በእርጥቡ ኬሚካል በእጅ ይታሻል፡፡ ይፈገፈጋል፡፡
ከዛ ላሜራ ይደረጋል (ይቀጠቀጣል) ይሄን የሚሰራ የራሱ የሥራ ሂደት ሲኖረው ላሜራ ተሰርቶ ተመልሶ በመምጣት ይረጋግጣል፡፡ ኢክራም ከቻክ በኋላ ያለውን የጋራዥ ሥራ ነው በተለየ ሁኔታ በቴክኖሎጂ በማዘመን ወደ ገበያ በመግባት በማሽን የሚሰሩት፡፡ እዚህ ታዲያ አካሉ (ቦዲው) ተገጣጥሞ ቀለም በሚቀባበት ጊዜ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ቀለም ተቀብቶ መልሶ ሲመጣ ፊሽ አይስ ተብሎ ከሚጠራውና ቀለም ከሚያነባው ጀምሮ ብዙ ችግሮች ስላሉ እነዚህን ችግሮች በቴክኖሎጂ በመታገዝ ይፈታሉ፡፡
ከብዙ የሥራ ሂደቶች በኋላም በውበት የደመቀና የተንቆጠቆጠ የገጽታ ለውጥ ይመጣል።ይሄ በባህላዊ አሰራር ተልኮስኩሶ በኖረው በጋራዥ ሥራ ሥፍራውም ቀድሞ እንዲጸዳ የተደረገ በመሆኑ በእጅጉ ለዓይን ይማርካል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የመኪና አካል የመግጠም ሥራን ከባህላዊ አሰራር ወደ ዘመናዊ በማሸጋገር ሙሉ በሙሉ በማሽን እንዲሰራ ያደረጉት ኢክራም በዚህ የመኪና አካል ማስዋብ ገበያ ላይ ሴቶች በስፋት እንዲገቡ የማድረግ ሥራቸው አልተቋረጠም፡፡
በመስኩ እየተመረቁ ሴቶች መስኩን ከማመላከት ባለፈ በቋሚና በኮንትራት ቅጥር ሰፊ የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ በተጨማሪም ወደ መስኩ የመግባት ፍላጎቱ ላላቸው ስልጠና በመስጠት እንዲሁም የሌላቸው እንዲሰለጥኑ በማድረግ እያገዙ ይገኛሉ።
ባለፉት ሦስት ዓመታት ይሄንኑ አዲሱን ሥራቸውን በየድርጅቱ ጭምር እየሄዱ በማስተዋወቅ ነው ያሳለፉት፡፡ በአርቲ ቲቪም እንዲሁ የማስተዋወቅ ሥራውን እየሰራ ይገኛል፡፡ የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት (አዲስ ቻምበር) የግሉን ዘርፍ በማጠናከር በሀገሪቱ ንግድና ኢንቨስትመንት ኢንዲስፋፋ የበኩሉን ሚና በመጫወት ላይ እንደሚገኝ የገለፁት የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጤ ‹‹እንዲህ ዓይነት ሴቶች ወደ ላይ እንዲወጡ በየጊዜው ማስታወስ ይፈልጋል›› ባሉት ጽሑፋችንን ደመደምን፡፡
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2015