አዲስ አበባ ከተማ የትናንት ታሪካዊነቷን ጠብቃ፣ ዛሬ ለነዋሪዎቿ ምቹ እንድትሆን፣ ነገ ደግሞ ከዛሬ የተሻለች ምቹና ውብ ከተማ ለማድረግ በከተማዋ ቢሊዮን ብሮች የተመደቡላቸው የበርካታ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሄደ ይገኛል። ከፕሮጀክቶቹ መካከል የአንዳንዶቹ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፤ ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል አብርሆት ቤተመጽሐፍት፣ የአንድነት የመኪና ማቆሚያ ፓርክ፣ የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት፣ የአንድነት፣ የእንጦጦ የወዳጅነትና የእንጦጦ ፓርኮች ይጠቀሳሉ፡፡
ከእነዚህ ፕሮጀክቶች አንዳንዶቹ በከተማዋ አስተዳደር የተገነቡ ናቸው። የከተማ አስተዳደሩ አሁንም ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እየገነባ ይገኛል። ክእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል አንዳንዶቹ የተጠናቀቁ ሲሆን ግንባታቸው እየተካሄደ ያለ ፕሮጀክቶችም ብዙ ናቸው።
የከተማ አስተዳደሩ ያልተጠናቀቁትን ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅ እና ለአገልግሎት እንዲበቁ ለማስቻል ርብርብ እየተደረገ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት በግንባታ ላይ ከሚገኙት ትላልቅ ፕሮጀክቶች መካከል የከተማዋ የትራንስፖርት ዘርፍ ዋና መስሪያ ቤት፣ ዓድዋ ሙዚየም፣ የአመራር አካዳሚ፣ የየካ መኪና ማቆሚያ፣ የግብርና ምርቶች ማዕከላት፣ የኢንዱስትሪ ማዕከል፣ የአዲስ አፍሪካ ኤግዚቢሽን እና ኮንቬንሽን ማዕከል፣ የለሚ ኩራ ፓርክ ፕሮጀክቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የዛሬው የመሠረተ ልማት አምዳችን የትራንስፖርት ዘርፍ ዋና መስሪያ ቤት ግንባታ ዙሪያ ላይ የሚያጠነጥን ይሆናል። በትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽሕፈት ቤት ባለቤትነት እየተገነባ ያለው ይህ የትራንስፖርት ዘርፍ ዋና መስሪያ ቤት መገኛ መገናኛ አካባቢ እየተገነባ ነው። በ4 ሺህ 300 ካሬ ሜትር ላይ እየተገነባ የሚገኘው መስሪያ ቤቱ፤ ከ1 ነጥብ 575 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቅ ሲሆን፣ ግንባታው ሲጠናቀቅ አምስት ቢሮዎችን በጋራ እንዲይዝ ታስቧል፡፡
በትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽሕፈት ቤት የትራንስፖርት ዘርፍ ዋና መስሪያ ቤት የባለቤት ተወካይ ኢንጂነር ታደለ ደንደና እንደሚሉት፤ ፕሮጀክቱ ከመሬት በታች ሦስት ወለል፣ ከመሬት በላይ ደግሞ 20 ወለሎች ይኖሩታል። ግንባታው ሲጠናቀቅ መስሪያ ቤቱ የከተማ አስተዳደሩን የትራንስፖርት ዘርፍ ቢሮዎችን አቅፎ ይይዛል። መስሪያ ቤቱ ለሕዝብ ትራንስፖርት ባለስልጣን፣ ለአሽከርካሪዎች እና የተፈቀደላቸው ተሽከርካሪዎች ማረጋገጫ ባለስልጣን፣ ለአዲስ አበባ መንገድ ትራንስፖርት ቢሮ እና ለትራንስፖርት ፕሮግራም አስተዳደር ቢሮ አገልግሎት ይውላል፡፡
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ለ3ሺህ የሴክተር ባለስልጣን ሠራተኞች ቢሮዎች፣ ጂምናዚየም፣ ስፓ፣ ለሕፃናት ማቆያ ቦታ፣ ለትራንስፖርት ዘርፍ ሙዚየም፣ ለምስል ማሳያዎች፣ ለሕዝብ ምግብ ቤት እና ለሠራተኛ ካፊቴሪያ እንደሚኖሩት የጠቆሙት ኢንጂነር ታደለ፤ የመሬት ወለልን ጨምሮ ወደ ታች ያሉት ወለሎች 210 ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ ማቆም እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡
እንደ ኢንጂነር ታደለ ማብራሪያ፤ መስሪያ ቤቱ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የሚገነባ ሲሆን፤ የተለያዩ አገልግሎቶች መስጫዎችንም ያካትታል።ለመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና እርዳታ መስጫ፣ ዲጂታል ቤተመጽሐፍት ለእያንዳንዱ ሴክተር ቢሮ፣ ስድስት ትናንሽ መሰብሰቢያ አዳራሾች እና አራት የስልጠና ማዕከላት፣ አንድ መካከለኛ የኮምፒዩተር ማዕከል እና ለአምስት ሴክተር መስሪያ ቤቶች የጋራ ቦታ ይኖሩታል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከትራንስፖርት ጋር ተያያዥነት ያለው አንድ ጉዳይ ለማስፈጸም የተለያዩ የትራንስፖርት ዘርፍ ቢሮዎች መመላለስ የግድ እንደሆነ የሚጠቅሱት እንጂነር ታደለ፤ አንድ ጉዳይ ለማስጨረስ የተለያዩ ቢሮዎች መመላለስ እና ጉዳይ ማስፈጸም ብዙ ቀናትን ሊወስድ እንደሚችል ጠቁመዋል። እየተገነባ ያለው የዘርፉ ሕንፃ ሲጠናቀቅ ይህን የደንበኞች እንግልት ማስቀረት እና ትክክለኛ አገልግሎት መስጠት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡
ሕንፃው የደንበኞችን እንግልት ከማስቀረት ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውም ከፍ ያለ መሆኑን የሚጠቁሙት ኢንጂነር ታደለ፤ በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ ተቋማት ቢሮዎችን ተከራይተው አገል ግሎት እንደሚሰጡ ተናግረዋል፤ ግንባታው ሲጠናቀቅ ለኪራይ የሚውለውን ወጪ ለሌሎች አገልግሎቶች ማዋል እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡
ቢሮዎቹ በአንድ ላይ መሰብሰባቸው ለመንግሥት ሌላ ራሱን የቻለ ጥቅም እንደሚያስገኝም ይገልጻሉ። ሕዝቡ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ ማግኘት መቻሉ የሕዝብን እርካታ ከፍ እንደሚያደርገው ኢንጂነር ታደለ ጠቁመዋል፡፡
እንደ ኢንጂነር ታደለ ማብራሪያ፤ የፕሮጀክቱ ግንባታ በ2012 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን፣ ይጠናቀቃል ተብሎ ከታሰበው ጊዜ በላይ ፈጅቷል።ፕሮጀክቱ በተለያዩ ምክንያቶች ተጓትቷል። የፕሮጀክቱ ግንባታ ሲጀመር የዲዛይን እና ግንባታ ሥራዎች ቢሮ በባለቤትነት ሲያስገነባ የነበረ ሲሆን፤ በ2012 ዓ.ም ትላልቅ ፕሮጀክቶች ጽሕፈት ቤት ሲቋቋም እና ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የሆኑ ፕሮጀክቶችን የሜጋ ፕሮጀክቶች ጽሕፈት ቤት በባለቤትነት እንዲያስገነባ አቅጣጫ መቀመጡን ተከትሎ ወደ ጽሕፈት ቤቱ ተሸጋግሯል፡፡
ጽሕፈት ቤቱ ፕሮጀክቱን በባለቤትነት ለማስገ ንባት ሲወስደው ከነችግሩ ነው ያሉት ኢንጂነር ታደለ፤ ከችግሮቹ መካከል በዲዛይን እና ስፔሲፊኬሽን ላይ የነበረው የአለመጣጣም ችግር አንዱ ነው ይላሉ። ይህንን ችግር ለመፍታት አራት ወር አካባቢ እንደወሰደ ይገልጻሉ።
እርሳቸው እንዳሉት፤ የዲዛይን እና ስፔሲፊኬሽን ችግር ከተፈታ በኋላም ሥራው አልጋ በአልጋ አልሆነም። እንደገና ሌላ ችግር አጋጥሟል። የግንባታ ዕቃዎች ዋጋ መናር ትልቁ ችግር ሆነ። በዋጋ መናር ምክንያት ኮንትራክተሩ የዋጋ ማሻሻያ እንዲደረግ ሀሳብ አቀረበ። ሀሳብ በማቅረብ ብቻ አላቆመም፤ ግንባታውንም አቆመ። ይህ ችግርም የከተማው ካቢኔ ባስተላለፈው ውሳኔ ተፈታ። ግንባታውም ከተወሰነ ቆይታ በኋላ ዳግም ሊጀምር ችሏል፡፡
ፕሮጀክቱ ለሦስተኛ ጊዜ ችግር አጋጥሞት በቅርቡ ግንባታው ተቋርጦም ነበር። በዋጋ ንረትና የውጭ ምንዛሬ እየጨመረ ከመሄዱ ጋር ተያይዞ ለሦስተኛ ጊዜ ተቋርጦ ግንባታው እንደገና ከተጀመረ በኋላ አሁን ሥራው ከበፊቱ በተሻለ ፍጥነት እየተሠራ ነው። ኮንትራክተሩም ዳግም ግንባታውን ላለማቆም ቃል ገብቷል፡፡
እንደ ኢንጂነር ታደለ ማብራሪያ፤ በተለያዩ ወቅቶች ካጋጠሙት ተደጋጋሚ ችግሮች ተላቆ ፕሮጀክቱ በአሁኑ ወቅት በፍጥነት እየተገነባ ነው።54 ነጥብ 38 በመቶ ላይ ደርሷል። በአሁኑ ወቅት የ12ኛ ወለል ግንባታ በመካሄድ ላይ ይገኛል። እስከ ሐምሌ ድረስ የመዋቅሩ (ስትራክቸራል) ሥራ ያልቃል።ሙሉ በሙሉ የማጠናቀቂያውን ሥራ ጭምር ግን በቀጣይ አንድ ዓመት ተኩል ውስጥ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዟል። ከበላይ አመራር ጀምሮ በየደረጃ ያለው አመራር ለፕሮጀክቱ ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገለት ነው፡፡
ፕሮጀክቱ ሜጋ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ባለቤትነት የሚገነባ እንደመሆኑ በቴክኖሎጂ የታገዘ የግንባታ ሥራ እየተሠራ መሆኑን የሚጠቁሙት ኢንጂነር ታደለ ደንደና፤ በፕሮጀክቱ ላይ የሚሳተፉ ሠራተኞች ልምድ፣ እውቀትና ሙያ እንዲቀስሙ ትልቅ ዕድል እየፈጠረላቸው መሆኑን አስታውቀዋል። ሠራተኞቹ ስልጠናዎችንም እንዲያገኙ እየተደረገ በመሆኑ በቀጣይ የሙያ ባለቤት የሚያደርጋቸው መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡
ይሁን እንጂ አሁንም የሲሚንቶ እጥረት ለፕሮጀክቱ እንቅፋት መሆኑን ቀጥሏል የሚሉት ኢንጂነር ታደለ፣ ችግሩ ሥራዎችን በተያዘው እቅድ መሠረት ለማከናወን እንቅፋት እየሆነ ይገኛል ይላሉ። አንድ ወለል በ15 ቀን ለመሙላት እቅድ ተይዞ እንደነበር አስታውሰው፣ በሲሚንቶ እጥረት ምክንያት በ30 ቀን ለመሙላት እየታሰበ መሆኑን አንስተዋል።
መንግሥት ለፕሮጀክቶቹ ሲሚንቶ ለማቅረብ የሚያደርገውን ጥረት በማጠናከር ግንባታው እንዲፋጠን ሊያደርግ ይገባል ሲሉ አስታውቀው፣ ሲሚንቶ የማይቀርብ ከሆነ ፕሮጀክቱ ተጨማሪ ጊዜ እና ተጨማሪ ሀብት ሊጠይቅ እንደሚችል ጠቁመዋል። ሲሚንቶ አምራች ፋብሪካዎችን ማገዝ የሚያስፈልግ ከሆነም አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጎ በብዛት እንዲያመርቱ እና በአቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለው ክፍተት እንዲጠብ ሊደረግ ይገባል ይላሉ፡፡
የሲሚንቶ ችግር የምርት እጥረት ብቻ እንዳልሆነም ጠቅሰው፣ የሲሚንቶ ዋጋ እንዲንር ብሎም የሲሚንቶ እጥረት እንዲከሰት የሚያደርጉ ደላሎች መኖራቸውን ጠቁመዋል። ደላሎችን ከገበያው ለማስወጣት አስፈላጊው እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱን የማማከር ሥራ የኢትዮጵያ ኮንስት ራክሽን ዲዛይን፣ ሱፐርቪዥን ሥራዎች ኮርፖሬሽን በማከናወን ላይ ነው። ኢንጂነር እናውጋው አለማየሁ አማካሪ ተቋሙ የመደባቸው የፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ መሐንዲስ ናቸው። ኢንጂነሩ ሥራው ሁለት ሦስት ጊዜ በመቋረጡ እና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት መዘግየት ያጋጠመ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ፕሮጀክቱ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ነው። በተለይም ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ መልካም የሚባል እንቅስቃሴ እየታየ ነው ይላሉ።
ጥራት ላይ አንዳች ችግር እንዳይፈጠር ከፍተኛ ጥንቃቄ እየተደረገ ነው የሚሉት ኢንጂነር እናውጋው፤ ከብረት እና ሲሚንቶ ጋር የሚገናኙ እያንዳንዱ ዕቃዎች በገቡ ቁጥር ምርመራ እየተደረገ ጥቅም ላይ እንደሚውል አስታውቀዋል። በግንባታ ዘርፍ ሥራ ላይ ጫና የሚያሳድሩ የተለያዩ ውጫዊ ነገሮች እንደተጠበቁ ሆነው ፕሮጀክቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያሳየ ባለው መሻሻል መሠረት በአንድ ዓመት ተኩል ውስጥ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
ፕሮጀክቱን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ ባለቤት ተቋሙ፣ ኮንትራክተሩ እና አማካሪው በጋራ ርብርብ እያደረጉ ናቸው የሚሉት ኢንጂነር እናውጋው፤ በባለድርሻ አካላት መካከል ያለው መናበብ ፕሮጀክቱ ከነበረበት ችግር ወጥቶ ግንባታው በፍጥነት እንዲከናወን እያስቻለ ነው ብለዋል። ተቋማቸውን ወክለው እንደአማካሪ ተቋም ኮንትራክተሩን እና ባለቤት ተቋሙን የማማከር እና ሥራው ጥራቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከናወን ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ሦስቱ ተቋማት እጅና ጓንት ሆነው እየሠሩ ነው። በራሳቸው አቅም የሚፈቱ ችግሮች ወዲያው እንዲፈቱ በማድረግ እና ከአቅማቸው በላይ የሆኑ ችግሮች ደግሞ በበላይ አመራሩ እንዲፈቱ እያደረጉ መሆናቸውን ነው የጠቆሙት፡፡
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን መጋቢት 9 ቀን 2015 ዓ.ም