ወጣት ተስፋ ወንድሙ ከሁለት አመት ከስድስት ወር በፊት በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ ነበር። ሆኖም በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት ትምህርቱን አቋርጦ ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ ተገዷል። ትምህርቱን አቋርጦ ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በኋላም ከትምህርት ባለፈ በርካታ ነገሮችን የመሞከር ፍላጎት ነበረው።
በርግጥ ታላላቅ ወንድሞቹና እህቶቹ በትምህ ርታቸው ጫፍ የደረሱ በመሆናቸው የእርሱም ዕጣ ፈንታ በትምህርቱ መግፋት እንደሆነ ቢረዳም በቢዝነሱ ዓለም ስኬታማ ለመሆን አጥብቆ ይመኝ ነበር።ለዚህም ሰዎች በቢዝነስ ዓለም እንዴት ስኬታማ መሆን እንደቻሉና ቢዝነስ በራሱ ምን እንደሆነ ለማወቅ ዩቲዩብ ይመለከታል፤ መረጃዎችን ያያል፤ ያገላብጣል፤ይመራመራል። ራሱን ወደ ቢዝነሱ ዓለም የማንደርደር ሃሳብ ውስጥ እያለ ግን አንድ የስልክ ጥሪ ከጓደኛው ደረሰው።
ጓደኛው ሱራፌል ይባላል። የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ጓደኛው ነው።በግል ስብእና ግንባታና አመለካከት ለውጥ ዙሪያ ስልጠናዎችን በመውሰድ ራስን ማብቃት እንደሚቻል መረጃ ሰጠው።አላቅማም። ስልጠናው ወደሚሰጥበት ቦታ ወዲያው አመራ። የሚጠበቅበትን ክፍያ ከፈፀመ በኋላ ስልጠናውን መከታተል ጀመረ። ራስን ስለማበልፀግና የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎችን ለሦስት ወራት ያህል ተከታትሎ አጠናቀቀ።
በዚህም የራሱን ራዕይ ማወቅ ቻለ። ስለ ሕይወቱና ወደዚህ ምድር የመጣበትን ምክንያትም ለመረዳት ችሏል። በተለይ ደግሞ ሲያስባቸው የነበሩና ሊሳኩ አይችሉም ያላቸውን ትላልቅ ህልሞችን ይቻላል በሚል መንፈስ ድጋሚ አድሷቸዋል። ከምንም በላይ ደግሞ ለነገሮች ቸልተኛ የሚባል ሰው የነበረ እንደመሆኑ ስልጠናውን ከተከታተለ በኋላ ይህን ባህሪውን ቀይሯል።
በአሁኑ ጊዜ በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ አንደኛ አመት የማርኬቲንግ ማኔጅመንት ትምህርቱን እየተከታተለ የሚገኘው ወጣት ተስፋ ስልጠናዎችን ለሌሎች ወጣቶች በማካፈልና በማስተዋወቅ ገቢ እያገኘ ነው። እስካሁን ባለው ሂደትም ሰባት ለሚሆኑ ጓደኞቹና ቤተሰቦቹ ስልጠናውን እንዲወስዱ ማድረግ ችሏል። በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉም ስለዚህም ወጣት ተስፋ ገቢ እያገኘም፤ የወጣቶችን አመለካከት እየገነባም ሕይወቱን በመምራት ላይ ይገኛል፡፡
ወጣት ተስፋ ስልጠናዎች ለሌሎች በማካፈልና ስልጠናውን እንዲወስዱ በማድረግ ብሎም ኩባንያውን በማስተዋወቅ ሥራ እስካሁን ባለው ሂደት በመጀመሪያው አንድ አመት ሥራው 200 ሺ ብር ገቢ አግኝቷል። እስካሁን ባለው ሂደትም ባጠቃላይ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ማግኘት ችሏል። በወር ደግሞ ከ150 እስከ 250 ሺ ብር ያገኛል።
ወጣት ተስፋ የወጣቶችን ስብና በመገንባት ውጤት የኩባንያውን ገፅታ ከገነቡና ከኩባንያው ጋር በመሥራት ውጤት ካስመዘገቡ ወጣቶች መካከል አንዱ በመሆኑ የአፍሪካዊቷ ሲሸልስ ደሴት የደርሶ መልስ ጉብኝት ተጠቃሚ ለመሆን በቅቷል። ወጣቶች ሸቀጥን ብቻ ሳይሆን ሃሳብንም በመሸጥ ከራሳቸው አልፈው ለአገር የሚተርፍ ገቢ ማግኘት እንደሚችሉ ወጣቱ ምክሩን ይለግሳል።
በርግጥ ሥራው በርካታ ውጣውረድ ያለበትና ልፋትን የሚጠይቅ ቢሆንም በትጋትና በብልሃት ከተሠራበት ጥሩ ገቢ የሚገኝበት መሆኑን ይናገራል ወጣት ተስፋ። አሁን ላይ በወር የሚያገኘው ገቢ ቀደም ሲል በአመት የሚያገኘው እንደነበረና ነገር ግን አሁን ላይ ጠንክሮ በመሥራቱ ወርሃዊ ገቢውን ማሻሻል እንደቻለም ነው የሚናገረው። በቀጣይ ደግሞ ዓለም አቀፍ አነቃቂ አሰልጣኝ በመሆን ከሦስት እስከ አምስት ባሉት አመታት ውስጥ ከ30 እስከ 50 ሺ የሚጠጉ ሰዎችን የማሰልጠን ህልም አለው።
ሌሎች ወጣቶችም በቅድሚያ ራዕይ ሊኖራቸው እንደሚገባ ይገልፃል። በመቀጠል ደግሞ ህልም ሊኖራቸው እንደሚገባና ያላቸውን ህልም እውን ማድረግ እንደሚችሉ ማመን ይኖርባቸዋል ይላል። ለህልማቸው እምነት ካላቸው ሁሉንም ነገር ማሳካት እንደሚችሉም ይጠቁማል።
ወጣት ነፃነት ዘነበ በወጣቶች ስብዕና ዙርያ የሚሠራ ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ ነው።እርሱ እንደሚለው ማህበሩ ከተቋቋመ ሦስት አመት ሞልቶታል። ከ300 በላይ የአክሲዮን ባለድርሻዎችንም አፍርቷል። በነዚሁ ሦስት አመታት ውስጥ ለወጣቶች በገፅ ለገፅና በበይነ መረብ የተለያዩ በግለሰብ ስብእና ግንባታ ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎችን ለወጣቶች በመስጠትና በማብቃት ከኩባንያው ጋር አብረው በመሥራትና የራሳቸውን ሥራ በመፍጠር ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል።
እንደ ቦርድ ሰብሳቢው ገለፃ ማህበሩ በዋናነት ደስተኛ፣ ስኬታማና ለሕይወት መሠረት የሚጥሉ አምስት የስልጠና ጥቅሎችን ያቀርባል። እነዚህ የስልጠና ጥቅሎች በሂፕኖ ቴራፒ፣ ኒዩሮ ሊንጉስቲክ ፕሮግራሚንግና ሱዶ ሳይንሶች ላይ መሠረት ያደረጉ ናቸው።እስካሁን ባለው ሂደትም ከ21 ሺ በላይ የሚበልጡ ወጣቶችን በማሰልጠን ዓላማ ያላቸው፣ ዋጋቸውን የሚያውቁ፣ ከደባል ሱስ የፀዱ፣ ለአገር ሰላም የቆሙ፣ ሥራ ፈጠራ ላይ ያተኮሩ ወጣቶችን ለማፍራት ችሏል።
በዚሁ የገፅ ለገፅና በይነ መረብ ስልጠና አማካኝነት ባለራእይና ቀና አስተሳሰብን በወጣቶች ውስጥ አስርጿል። ሰልጣኞችም የራሳቸውን ሥራ እንዲፈጥሩ አስችሏል፤ እያስቻለም ይገኛል። በበይነ መረብ በርግጥም ስልጠና ይገኛል የሚለውን በብዙዎች ዘንድ ያለውን ጥርጣሬ ቢኖርም ምንያህል የገበያው ፍላጎት እንዳለ ኩባንያው ማየት ተችሏል።
በዋናነት ኩባንያው ስልጠናዎቹን የሚያቀርበው በአካል ብቻ ሳይሆን በኢ- ለርኒንግ ጭምር በአማርኛ፣ በኦሮሚኛ፣ በእንግሊዝኛና፣ በትግርኛ ቋንቋዎች በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል። ይህም ሰዎች በተለይ ደግሞ ወጣቶች ከቤታቸው፤ ከኢትዮጵያ ውጪም ሆነው በቨርችዋል መማሪያ ክፍሎች ውስጥ እየገቡ ስልጠናዎችን በተመቻቸው ሰዓት በቀላሉ መሳተፍ ይችላሉ።
የኩባንያው ዋነኛ አላማም ባለራእይ፣ ቅን፣ ጤናማና ባለፀጋ ትውልድ ማፍራት እንደመሆኑ ይህንኑ ዓላማ ለማሳካት አገር ማለት መሬት ሲደመር ሰው ነው ሰው ደግሞ የሚስለው አስተሳሰቡን በመሆኑ አስተሳሰብም የሚቀረፅና የሚገራ ነው ብሎ ያምናል።ሰው ድሃም ሀብታምም ሆኖ አልተፈጠረም፤ ክፉም ደግም ሆኖ አልተፈጠረም፤ ለዚህም በአገሪቱ ውስጥ ያሉ መድረኮች፣ በቤተሰብና በግል ያለ አስተሳሰብ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው ብሎ ኩባንያው ያስባል።
ጥሬ ዕቃዎችን ብቻ ሳይሆን ስልጠናዎችንም ጭምር ወደ ውጭ አገራት በመላክ ገቢ ማግኘት ይቻላል።የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም የውጭ ምንዛሬ አካውንት ከፍቶ በውጭ አገራት ያሉ ሰዎች በውጭ ምንዛሬ ስልጠናዎችን እየገዙ የውጭ ምንዛሬ ለአገሪቱ ማመንጨት እንዲችሉ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል። በመጪዎቹ ስድስት ወራት ደግሞ በደቡብ ሱዳን፣ ኬንያ እና እሥራኤል ቅርንጫፎችን ከፍቶ በሞያቸውና በትምህርት ደረጃቸው ላቀ ያለ ደረጃ ላይ ላሉት ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠርና የሚጠበቅበትን ግብር ለመንግሥት በማስገባት ለአገሪቱ በየወሩ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ የውጭ ምንዛሬ ለማስገባት እየሠራ ይገኛል።
ኩባንያው ስልጠናዎችን በአምስት ጥቅሎች ለወጣቶች ሲሰጥ በትንሹ ከ3000 ብር አንስቶ እስከ ትልቁ 50 ሺ ብር ድረስ ይጠይቃል። ስልጠናውን ለመስጠት ዝቅተኛው ሦስት ሳምንት፤ ከፍተኛው ደግሞ ስድስት ወር ይፈጃል። ስልጠናዎቹም አነቃቂ አይደሉም። ይልቁንም ወጣቶች ስልጠናውን ወስደው የራሳቸውን ሥራ ፈጥረው እንዲሠሩ ያስችላል።በሌላ በኩል ደግሞ ምንም ገቢ የለኝም ለሚሉ ወጣቶች ከኩባንያው ጋር በጋራ ሆነው በመሥራት በተለይ ደግሞ የሚሰጣቸውን ስልጠናዎችን ለሌሎች በማካፈልና በማስተዋወቅ ከሚገኘው ሽያጭ የኮሚሽን ክፍያ ማግኘት ይችላሉ።
የኩባንያው አሰልጣኞች በወር ለሦስት ቀናት በተለያዩ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ውስጥ በመገኘት ስልጠናዎቹን በነፃ የሚሰጡበትን አሠራር ዘርግቷል። በተለይ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በሚገኙ ከ13 በላይ በሚሆኑ ዞኖች ውስጥ ስልጠናዎችን ሰጥቷል።በመንግሥት መስሪያ ቤቶችም በኩል ለሴት ፓርላማ የካውከስ ተጠሪዎች በመጪዎቹ ሁለት አመት በነፃ ለማሰልጠን እቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። የመጀመሪያውን ጥቅል ስልጠናም ከሦስት ወር በፊት ሰጥቷቸዋል።
ወጣት ነፃነት እንደሚለው ኩባንያው ከሚያቀርባ ቸው ስልጠናዎች 60 ከመቶ የሚሆነውን ገቢውን ማለትም ከ1 ሺ ብር ላይ 600 ውን እያሰላ ከገፅታ ገንቢ ወጣቶች ጋር አብሮ በመስራትና አብረውት ሰልጥነው በስልጠናው ደስተኛ ለሆኑ ወጣቶች ኮሚሽን ይከፍላል። እስካሁንም እየከፈለ ይገኛል።በዚሁ አሠራር መሠረት ኩባንያው በሦስት አመታት ውስጥ ከ101 ሚሊዮን ብር በላይ ኮሚሽን ለገፅታ ገንቢዎች ከፍሏል።
እነዚህ ገፅታ ገንቢዎች ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት ጀምሮ ያሉ፣ ከኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ያለሥራ የተቀመጡ፣ በተለያዩ ሱስ ውስጥ ተዘፍቀው የነበሩ ወጣቶች ናቸው። ወጣቶቹ በኩባንያው የሚሰጡ በግል ስብእና ግንባታ ዙሪያ ያተኮሩ ስልጠናዎችን ተከታትለው ከኩባንያው ጋር በመሥራት ዛሬ ላይ የስልጠናዎቹን ጠቀሜታ ሌሎች በማካፈልና ወደኩባንያው እንዲመጡና እንዲሰለጥኑ በማድረግ የኩባንያውን ገፅታ ገንብተው በወር ከ50 እስከ 60 ሺ ብር ገቢ በማግኘት ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን መደገፍ ችለዋል።
ኩባንያው በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባና በአዳማ ከተማ ካሉት ቅርንጫፎች በተጨማሪ በመጪዎቹ አምስት አመታት የቅርንጫፍ ስልጠና ማዕከላቱን በመላው አገሪቱ የማስፋፋት እቅድ አለው። የሚሰጣቸውን ስልጠናዎች ከአገር ውስጥ በተጨማሪ ወደተለያዩ የውጭ አገራት ተደራሽ በማድረግና በውጭ አገር የሚሸጠውን ስልጠና በውጭ ምንዛሬ ወደ አገር ውስጥ የማስገባት እቅድም ነድፏል።ከ300 ሺ በላይ ወጣቶችን በማሰልጠን ከፍተኛ ግብር በመክፈል ከ10 ሺ በላይ ገፅታ ገንቢዎችን በየሳምንቱ ኮሚሽን ለመክፈል የሚያስችል አቅም ላይ የመድረስ ውጥንም ይዟል። ከዚህ ባለፈ ኩባንያው በትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ ላይም የመሳተፍ ሃሳብ አለው።
በኢትዮጵያ በየአመቱ በርካታ ወጣቶች በልዩ ልዩ የትምህርት መስኮች ተመርቀው ይወጣሉ።የአብዛኛዎቹ ወጣቶች ፍላጎትም በተማሩበት የትምህርት መስክ ተቀጥሮ መሥራት ነው።ይሁንና በመንግሥትም ሆነ በግል ተቋማት የሚወጡ የሥራ ቅጥር መደቦች ውስንና ከተመራቂው ወጣት ቁጥር ጋር ተመጣጣኝ አይደሉም።ይህንኑ ተከትሎም አብዛኛው ተመራቂ ወጣት ያለ ሥራ ለመቀመጥ ይገደዳል።
ሆኖም እጅን አጣጥፎ ያለ ሥራ ከመቀመጥ ሌሎች አማራጮችን ማማተሩ ከሁሉም ወጣት ይጠበቃል።በተለይ ደግሞ የተዘባ አመለካከትን በማስወገድና የራስን የግል ስብእናን በስልጠና በማዳበር በልዩ ልዩ መስኩ በጋራና በተናጠል ሥራ በመፍጠር ራስንና ቤተሰብን መለወጥ እንደሚቻል ተገንዘበው ዛሬ ነገ ሳይሉ ግራ ቀኝ አይተው ለለውጥ ሊነሱ ይገባል። ሰላም
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን መጋቢት 8 ቀን 2015 ዓ.ም