አውሮፓውያን በ18ኛው ክፍለ ዘመን ኢንዱስትሪዎቻቸውን ባስፋፉ ማግስት ጥሬ ሀብት ለመቀራመት እና ለምርቶቻቸው ማራገፊያነት አይናቸውን የጣሉት አፍሪካ ላይ እንደነበር የታሪክ መዛግብት እና ምሑራን ያስረዳሉ። እናም የአውሮፓ አገራት በበርሊኑ ጉባዔያቸው አፍሪካን በቅኝ ግዛት የመያዝ ሴራቸውን ዶለቱ። ለዚህ ቅርምታቸው ፍኖት እንዲሆናቸውም የአፍሪካን ካርታ ከፊታቸው ዘርግተው አገራትን እንደ ቅርጫ ሥጋ በመመደብ አህጉሪቱን ተቀራመቷት።
በዚህ ወቅት ኢትዮጵያም በጣሊያን እጅ እንድትወድቅ የቅርጫው እጣ ወጥቶባት ነበር። በዚሁ ድልድል እና ሃሳባቸው መሠረትም አብዛኛዎቹን የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ግዛት ስር አውለው የተፈጥሮ ሀብታቸውን በዘበዙ ፤ ባርነትንም በሕዝቦች ጫንቃ ላይ ጫኑ። ኢትዮጵያ ግን በልጆችዋ የተባበረ ክንድ ሊወሯት የመጣውን ጠላት ድባቅ መትታ ነጻነቷን አስከበረች። ከራሷ አልፋ ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ሕዝብ ኩራት የሆነ ደማቅ ታሪክ ጻፈች። ይሄው ድልና ገድል ታዲያ በዘመናት የማይደበዝዝ ሕያው የአሸናፊነት አርነት ሆኖ ዛሬም ድረስ ይዘከራል፤ ይጠናል፤ ይተነተናል።
የዓድዋ ድል ታሪክ ብቻ ሳይሆን ሕያው የድል ሐውልት ነውና ከዛሬ የተሻገረ አስተምህሮ እንዲኖረው፤ ለነገው ትውልድ ስንቅና አቅም እንዲሆን በምሑራን በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑም ይገኛሉ። የአዲስ አበባው የዓድዋ ፓርክ ፕሮጀክት የዚህ አንድ ማሳያ ሲሆን፤ በየዩኒቨርሲቲዎች የሚከናወኑ መድረኮችና በምሑራኑም የሚሰጡ አስተያየቶች፤ እንዲሁም የጥናት ሥራዎችም በርካታ ናቸው። የታሪክ ምሑራን እና ተመራማሪዎች ደግሞ ይሄንን ታሪክ በሚገባ አጥንቶና ሰንዶ ከማኖር አኳያ የማይተካ ሚና አላቸው።
በጂማ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ከተቦ አብዲዮ፤ የዓድዋን ጦርነት መንስዔ እና ውጤት እንዲህ ያስረዳሉ። በበርሊኑ ጉባኤ ውሳኔና እጣቸው መሠረት ጣሊያኖች ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ አስበው እኤአ በ1885 በእንግሊዞች ትብብር እግራቸውን ምፅዋ ላይ አሳረፉ። ቀስ በቀስ ከምፅዋ ወደ ዶጋሊ፣ ከዚያም ወደ ሰሐሊን ግዛታቸውን ማስፋፋት ጀመሩ።
ነገር ግን በወቅቱ የነበሩት ንጉሥ አጼ ዮሐንስ ጣሊያኖቹ እንደፈለጉት እንዲሆኑ እድል አልሰጧቸውም ነበር። አጼ ዮሐንስ ከደርቡሾች ጋር ባደረጉት ጦርነት በክብር መሰዋታቸውን ተከትሎ ግን ጣሊያኖች ከሰሜን ወደ ደቡብ ለሚያደርጉት መስፋፋት አመቺ ሁኔታ ተፈጠረላቸው።
ወቅቱ ደግሞ ገና አፄ ምኒልክ ንግሥናቸውን ለዓለም ማኅበረሰብ እያሳወቁ የነበረበት በመሆኑ ጣሊያኖች ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ለአፄ ምኒልክ እውቅናና ድጋፍ እንደሚሰጧቸው በማስመሰል የስምምነት ውል መፈራረም እንዳለባቸው ያሳምኗቸዋል። በውጫሌው ስምምነት የአፄ ምኒልክን መንግሥታዊ መዋቅር ይደግፋሉ በሚል 20 አንቀጾችን ጽፈው ከንጉሡ ጋር ይፈራረማሉ።
ይሁን እንጂ ይህ ስምምነት በውስጡ የኢትዮጵያን ክብርና ሉዓላዊነት የሚጻረር ሃሳብን በውስጡ የያዘ በመርዝ የተለወሰ ማር ዓይነት ነበረ። በተለይም በአንቀጽ 17 ላይ የሰፈረው ሃሳብ የዚህ አብይ ማሳያ፤ ወደማይቀረው ጦርነት የመራ መርዛማ ሃሳብን የያዘ ነበር። ምክንያቱም አንቀጹ በተለይ በኢጣሊያንኛ ትርጉሙ የኢትዮጵያን ክብርና ሉዓላዊነት የሚጻረርና ኢትዮጵያ ለኢጣሊያ ተገዥ መሆኗን የሚገልጽ ነበር።
ሆኖም ይህ እውነት በጥሞና ከተጤነና የትርጉሙ መዛባት ከታወቀ በኋላ በንጉሡና በመኳንንቱ ዘንድ ቁጣን ያስነሳል። ጣሊያኖችም ውሉን ከማስተካከል ይልቅ በኢትዮጵያ ጉዳይ ከእኛ በላይ የሚመለከተው የለም በሚል እንደፈለጋቸው ሊፈነጩ ሞከሩ። በማንአለብኝነት የያዙትን ቦታም ማስፋፋት ጀመሩ፤ መረብ ወንዝን ተሻግረው መቀሌ፣ አምባላጌ ፣ ማይጨው እያሉ ወደ መሐል ሀገር እየተንሰራፉ መጡ። ይሄን የተገነዘቡት ንጉሥ አፄ ምኒልክ እና ሹማምንቶቻቸውም ከመከሩ በኋላ ውሉን ከመሰረዝ ባሻገር የሀገርን ክብር ለማስጠበቅ ወደሚችሉበት ርምጃ መሸጋገር የግድ መሆኑን ወሰኑ።
ጥሪ እና ምላሽ
በወቅቱ የጣሊያኖች ተግባርና ጉዞ የገባቸው ንጉሡ፣ አገር የማስጠበቅ ኃላፊነት አለባቸውና ስለ ወራሪው ባሕሪ በመግለጽ እና ሁሉም ይሄን ወራሪ የመከላከል ሁለንተናዊ ግዴታ እንዳለበት በማሳሰብ አዋጅ አስነገሩ። ‹‹… አገር የሚያጠፋ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሄር የወሰነልንን የባሕር በር አልፎ መጥቷልና እኔም የአገሬን ከብት ማለቅ የሰውን መድከም አይቼ እስከ አሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር….››……‹‹…..አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት ሀገሬን አሳልፌ አልሰጠውም። የሀገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም። አንተም እስከ አሁን አላስቀየምከኝም። ጉልበት ያለህ በጉልብትህ እርዳኝ። ጉልበትም የሌለህ ለልጅህ ለምሽትህ ለሃይማኖትህ ስትል በኅዘን እርዳኝ። ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ አልተውህም። ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም። ዘመቻዬ በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ። ›› (አፄ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት፣ ተክለ ጻዲቅ መኩሪያ፣ ገጽ ፤226)
ከ127 ዓመት በፊት የታወጀው ይህ የክተት አዋጅ፣ የኢጣሊያ መንግሥት ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለማንበርከክ በሰሜን የሀገራችን ክፍል የያዛቸውን ግዛቶች እያስፋፋ ወደ መሐል ሀገር ሲገሰግስ የኢትዮጵያ ሕዝብ በወራሪው ጠላት ላይ ክንዱን አስተባብሮ የማያዳግም ርምጃ በመውሰድ የሀገሩን ዳር ድንበር እንዲያስከብር አቅም የሆነው ነበር። ይሄ የንጉሡ ሀገር አላስደፍርም የክተት ጥሪ እና ከሕዝቡ የተሰጠው ምላሽ ድምር ውጤትም ዛሬ ኢትዮጵያ በድልና አርነት ከፍ ብላ እንድትገለጥ ያደረጋት ስለመሆኑም፤ ከዚህም በላይ ኢትዮጵያውያን መሪና ተመሪዎች የነበራቸውን ኅብረትና መናበብ በእጅጉ ከፍ አድርጐ ያሳያ እንደነበር ነው በርካቶች የሚመሰክሩት።
ዶክተር ከተቦ፣ ስለ አዋጁ እና ለንጉሡ የክተት የአዋጅ ጥሪ ሕዝቡ የሰጠውን ምላሽ እንዲህ ይገልጻሉ። አጼ ምኒልክ ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት ብለው ሲያውጁ ለጋራ አገራቸው ቀናዒ የሆኑት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጥሪውን ተቀብለው በነቂስ ወጥተዋል። የትግራይ ፣ የበጌምድር፣ የጎጃም ፣ የወሎ፣ የዋግ፣ የሸዋ ፣ የሐረር እና በአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት ያሉ መሳፍንቶችና ሀገረ ገዢዎች በርካታ ተዋጊዎቻቸውን በመያዝ የአጼ ምኒልክን ጥሪ ተቀብለው ወደ ዓድዋ ዘምተዋል።
ከብዙ በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህልም፣ የወላይታው ንጉስ ካዎ ጦና ፣ የጂማው አባጂፋር፣ የወለጋው ኩምሳ ሞረዳ፣ ሼኮ ጄላል ሀሰን፣ የቄለም ወለጋው ጆቴ ቱሉ፣… የመሳሰሉት ተዋጊዎ ቻቸውን በመያዝ ለጥሪው ምላሽ ሰጥተዋል። ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ፣ከሰሜን እስከ ደቡብ ያሉ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ከየአካባቢያቸው በወጡ ጦር መሪዎች ሥር ታቅፈው በጦርነቱ መሳተፋቸውን ዶክተር ከተቦ ይናገራሉ።
እነዚህ ገዢዎችና ነገሥታት የንጉሠ ነገሥቱን ጥሪ ተቀብለውና ጦራቸውን አሰልፈው ለእናት ሃገራቸው ክብር ሲዘምቱ ዘር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ የፖለቲካ አመለካከት አልለያያቸውም። ሌላው ቀርቶ ከንጉሡ ጋር የተኳረፉና የሸፈቱ ሳይቀሩ ንጉሡን ይቅርታ እንዲያደርጉላቸው እየጠየቁ የጋራ ጠላታቸውን ለመዋጋት ተሰልፈው ተዋድቀዋል። ሕዝቡ የመደጋገፍና የአንድነት ስሜቱ ከፍተኛ ስለነበርም፤ ስንቁን እያዘጋጀ ወደ ግንባር ለመትመምም ጊዜ እንዳልፈጀበት ነው የታሪ ክ ምሑሩ ያስረዱት።
አባጂፋር፣ ካኦ ጦና እና ኩምሳ ሞሮዳ ወታደሮቻቸውን ይዘው ወደ ዓድዋ እየተንቀሳቀሱ በነበረበት ወቅት፣ አጼ ምኒልክ ሁሉም አገረ ገዢ ተዋጊውን ይዞ ወደ ሰሜን ከሄደ መሐል ሀገሩ ባዶውን እንዳይቀር በሚል ከፊል ወታደሮቻቸውን ብቻ እንዲልኩና እነርሱ ቀሪዎቹን ይዘው አዲስ አበባንና አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ ማድረጋቸውን ዶክተር ከተቦ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ መልኩ የወቅቱን የክተት ጥሪ ጉዞ በተመለከተ በተለያዩ መጽሐፍት እና ሰነዶች ተከትበው ይገኛሉ። ‹‹ ….አጼ ምኒልክ ይህን አዋጅ በመስከረም ወር ካስነገሩ በኋላ እርሳቸው ጥቅምት 2 ቀን 1888 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወደ ዘመቻው ተጓዙ፤… የክተት አዋጁ ከታወቀ ወዲህ የጎጃም የቤጌምድር የወሎና የላስታው ከ300 እስከ 500 ኪሎ ሜትር፤ የሸዋ የሐረር፣ የባሌ፣ የአርሲ፣ የከንባታ፣ የሲዳማ የጂማ የከፋ፣ የወለጋና የኢሉባቦር ጦር ከ600 መቶ እስከ 1000 ወይም እስከ 1500 ኪሎ ሜትር ወደ ጦር ግንባር በእግሩ ተጉዟል፤”(ተክለጻዲቅ መኩሪያ፣ አፄ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት፣ (1983) ገጽ 227)።
ጳውሎስ ኞኞ ፤ አጤ ምኒልክ (1984) በሚለው መጽሐፋቸው ከገጽ 162-163 ፤ የአፄ ምኒልክን ጥሪ ተቀብለው ወደ ዓድዋ የተመሙትን ኢትዮጵያውያን አስመልክቶ ፓውሌቲ የተባለ ጸሐፊ በማሳያነት በማንሳት የውጭ አገር ጸሐፊዎች እንደሚከተለው መግለጻቸውን አስፍረዋል። ‹‹…. ሲጓዙ በደንብ ተመልክቻለሁ ዳገቱን ሲወጡ፣ ቁልቁለቱን ሲወርዱ፣ ሸለቆውን ሞልተው ሲሄዱ፣ እየተጯጯሁ ነው፤ ለወጊያ የሚሄዱ አይመስሉም። ተዋጊዎች ብቻ አይደሉም። ሴቶች፣ ሽማግሌዎች፣ አንካሶች፣ ሕጻናት፣ ቄሶች፣ አልቀሩም፤ በአንድነት ይጓዛሉ። ለጦርነት የሚሄዱ የጦር ወታደሮች አይመስሉም ነበር፤ ሕዝቡ በሙሉ ተነቅሎ ለወረራ የሚሄድ ይመስላል፤›› በማለት ነበር ያሰፈሩት።
ሞልቴዶ የተባለው ጸሐፊ አጣቅሰው ባሰፈሩት መሠረት ደግሞ ‹‹…አህያው፣ በቅሎው፣ ፈረሱ፣ ሰው ሁሉ በአንድነት ይጓዛል፤ መንገዱ ሲጠብ መንገድ ይሠራሉ፤ በአንድ ጊዜ በግራ ወይም በቀኝ ይሠማሩና የጠበበውን መንገድ ይሠራሉ። ሠራዊቱ ባለፈበት መንገድ የእርጥብ ሳር ዘር እንኳን አይገኝም፤ ምክንያቱም በመቶ ሺ የሚቆጠር እግር ረግጦ ስለሚያቦነው ነው፤›› ብለዋል።
ከተጓዦቹ መካከል በሺዎች የሚቆጠሩ መንገድ ሠሪዎች እና አዝማሪዎች ይገኙበታል። አዝማሪዎቹ ግጥም እየገጠሙና እያዜሙ ተጓዡን ያበረታቱት እንደነበር ተጠቅሷል። ለእንጀራ መጋገሪያ የሚሆን የሸክላ ምጣድ እና ለወጥ መሥሪያ የሚሆኑ ድስት የሚሠሩም ነበሩ። ከዚህ የምንረዳው የክተት አዋጁ የጾታ፣ የሙያ፣ የማዕረግ ፣ የብሔር ወዘተ ልዩነት ያልነበረውና ተሳትፎውም በጥሪው ልክ ሁሉንም ያሳተፈ መሆኑን ነው።
ለጥቅም ያልተገዛ ጽኑ ኢትዮጵያዊነት
ኢትዮጵያውያን ጥሪውን ተከትለው በአንድነት መትመም ብቻ ሳይሆን፤ ከጠላት በኩል የሚቀርብን የማታለያና መደለያ ከሀገር ክብርና ፍቅር እንደማይበልጥ ያሳዩበትን ከፍ ያለና የጸና ኢትዮጵያዊነት ያረጋገጡበት ነበር። ይሄን ሐቅ በተመለከተ ዶክተር ከተቦ እንደሚናገሩት፤ ኢጣሊያኖች ከንጉሡ ጋር ቅሬታ አላቸው የሚሏቸውን የተለያዩ አካባቢዎች ሀገረ ገዢዎች ከጎናቸው ለማሰለፍ ጥረት አድርገው ነበር። ሀገር ገዢዎቹ ግን በኢጣሊያኑ ድለላ ሳይታለሉ በዚያ ክፉ ቀን ለሀገራቸው ያላቸውን ጽኑ ታማኝነት ከንጉሡ ጎን በመቆም አረጋግጠዋል።
ጳውሎስ ኞኞ፣ አፄ ምኒልክ በሚለው መጽሐፋቸው ገጽ 164 ላይ እንዳሰፈሩትም፣ ‹‹ወራሪውን የጣሊያን ሠራዊት ለመውጋት ወደ ትግራይ ከመዘመቱ በፊት አብዛኛው የኢትዮጵያ መኳንንት በኢጣሊያ ሰርጎ ገብ ሰላዮች ስብከት ተጠምዶ ነበር። አውግስቶ ሳልምቢኒ ጎጃም ውስጥ ተቀምጦ የንጉሥ ተክለሃይማኖት ረዳትና አማካሪ በመምሰል ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ከጣሊያ ጋር ቢያብሩ የኢጣሊያ መንግሥት ባላንጣቸውን ምኒልክን ጥሎ እሳቸውን እንደሚያነግሳቸው እየነገረ ልባቸውን ይጎትት ነበር።…
…በትግራይ በኩል ጂያኮም ናሬቲ እና ሌሎችም በአጤ ዮሐንስ ጊዜ የዮሐንስ ቤተመንግሥት ባለሟል የነበሩትና የምኒልክ ባለሟል የነበረው አንቶሌኒ አጤ ዮሐንስንና ንጉስ ምኒልክን ነገር እየጎነጎኑ ሲያጣሉ እንደነበሩት ሁሉ፤ በአሁኑም ዘመን አጤ ምኒልክ ዙፋኑን የያዙት በግፍ መሆኑን ለራስ መንገሻ በመንገር ራስ መንገሻ ከኢጣሊያ ጋር ቢተባበሩ በግፍ የተወሰደባቸውን የአባታቸውን ዘውድ አስመልሰው በዮሐንስ ዙፋን ላይ እንደሚያስቀምጧቸው ቃል በመግባት እስከ ማስከዳት ደርሰው ነበር።…” የሚለውን ሰፍሮ እናገኘዋለን።
ይሁን እንጂ በዚህ መልኩ ሲሰበኩና የማይጨበጠውን የዙፋን ወራሽነት ቃል ሲገባላቸው የነበሩ እነዚህ አገረ ገዢ ኢትዮጵያውያን ግን፤ በጥቅም ሳይደለሉ ከአፄ ምኒልክ ጋር በመቆም ለዓድዋ ድል ድምቀት የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከታቸው በመጽሐፉ ተጠቅሶ ይገኛል።
ምኒልክ ህዳር 24 ቀን 1888 ዓ.ም መርሳ ላይ ሰፍረው በነበረ ጊዜ፣ ደጃዝማች ጓንጉል የሚባሉና ከአፄ ምኒልክ ጋር ተቀያይመው የሸፈቱ ሰው፤ ከንጉሡ ጎን ቆመው ጣሊያንን ለመዋጋት ተከታዩን መልዕክት ልከው እንደነበር ተጠቅሷል። መልዕክታቸውም፣ ‹‹ጃንሆይ ከእርሶ ተጣልቼ በርሃ ገብቻለሁ። አሁን ግን በሀገሬ ላይ የውጭ ጠላት ስለመጣባት የእርስዎ እና የእኔ ጉዳይ ቀርቶ ይማሩኝና መጥቼ ከእርሰዎ ከጌታዬ ጋር ሆኜ ያገሬን ጠላት ልውጋ” የሚል ነበር። ይሄ መልዕክት የደረሳቸው አፄ ምኒልክም ተደስተው እንዲመጡ አደረጓቸው፤ ደጃዝማች ጓንጉልም መጥተው ከአፄ ምኒልክ ጋር ሲገናኙ ሠራዊቱና መኳንንቱ እጅግ በጣም ደስተኛ እንደሆኑ በመጽሐፉ ተገልጿል።
ችግሮችን በሰላም የመፍታት ጥረቶች
ኢትዮጵያውያን በዚህ መልኩ የተጎናጸፉትን ድል ወዳረጉበት ጦርነት ከመግባታቸው በፊት፤ የተፈጠሩ ችግሮችን በሰላምና በንግግር ለመፍታት ብርቱ ጥረት አድርገው እንደነበር ድርሳናት ይጠቁማሉ። ይሄን በተመለከተ የታሪክ ምሑሩና ተመራማሪው ዶክተር ከተቦ እንደሚያስረዱት፤ አፄ ምኒልክ የክተት አዋጅ ካደረጉ በኋላም ቢሆን ተንደርድረው ወደ ጦርነት ከመግባታቸው በፊት ጣሊያኖች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ሰላማዊ ንግግሮችን ለማድረግ ጥረዋል፤ በዚሁ ጉዳይ ላይም በርካታ ደብዳቤዎችን ተጻጽፈዋል። ጣሊያኖች ግን የታጠቁትን ዘመናዊ የጦር መሣሪያና የሰለጠነ ወታደር ተማምነው ኢትዮጵያን በጉልበት ማንበርከክ ስለፈለጉ አፄ ምኒልክ የሚከተሉትን የዲፕሎማሲ መንገድ እንደፍርሃት ይቆጥሩት ነበር።
አፄ ምኒልክ ብቻም ሳይሆኑ፣ራስ መኮንን በግላቸው አላማጣ ላይ ተቀምጠው የኢጣሊያንን መስፋፋት በትኩረት እየተከታተሉ በነበረ ጊዜ፤ በተደጋጋሚ ለጣሊያን የጦር አመራሮች የሰላም ጥሪ ማድረጋቸውን ተክለጻዲቅ መኩሪያ አፄ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት በሚለው መጽሐፍ ገጽ 277 ላይ ጠቅሰዋል።
ይሁን እንጂ ኢጣሊያኖች የሰላም ንግግሩን አሻፈረኝ በማለት አምባላጌ ላይ መሽገው በኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ተኩስ ሲከፍቱ የፊት አውራሪ ገበየሁ ጦር ምሽጋቸውን ሰባብሮ ወደ መቀሌ እንዲያፈገፍጉ አድርጓቸዋል። የኢትዮጵያ ሠራዊት እግር በእግር እየተከታተለ መቀሌ የመሸገውን የኢጣሊያ ጦር ከቦ በንግሥት ጣይቱ ትእዛዝ ሰጪነት ለመጠጥነት የሚጠቀምበትን የምንጭ ውሃ በቁጥጥር ስር ያውለዋል። ይህን ጊዜ የጣሊያን የጦር አዛዦች የተከበበውን ጦራቸውን ለማዳን ሲሉ ሰላማዊ ንግግር የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ይገልጻሉ።
አፄ ምኒልክ ሀሳባቸውን በመቀበል ሰው ሳይጎዳ የተከበበው የኢጣሊያ ጦር በሰላም ወደ ወገኑ እንዲቀላቀል ይፈቅዳሉ። አምባላጌ ላይ የተጀመረው ጦርነት በኢትዮጵያ ሠራዊት ድል አድራጊነት ከተጠናቀቀ እና መቀሌ የመሸገው የጠላት ጦር ከተከበበ በኋላም ቢሆን አፄ ምኒልክ የኢጣሊያ መንግሥት እየተከተለ ያለው አካሄድ ትክክል አለመሆኑን እና አለመግባባቱን በንግግር ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም፤ በተቃራኒው ኢጣሊያኖች በሰላማዊ መንገድ የመነጋገር ፍላጎት ያላቸው በመምሰል የተከበቡ ጦራቸውን ካስለቀቁ በኋላ ጦራቸውን ወደ ዓድዋ ተራሮች በማስጠጋት ኃይላቸውን አደራጅተው ለጦርነት መዘጋጀታቸውን የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።
ለጣፋጭ ድል ያበቃ በኅብር ያጌጠ አንድነት
ይህ ጣፋጭ ድል ኢትዮጵያውያን በተባበረ ክንዳቸው ያስመዘገቡት ታሪክ ነው። ድሉ ከሃገሬው ሰው አልፎ በባርነት ቀንበር ሥር ላሉ ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ተስፋን ፈንጥቋል። የዚህ ታላቅ ድል ምስጢር ምንድን ነው? በሚል ለጠየቀም፤ የታሪክ ተመራማሪዎች ምላሽ፤ በወቅቱ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ያሳዩት አንድነት፣ ጀግንነት፣ ታማኝነት፣ ቆራጥነትና አገር ወዳድነት ስለመሆኑ ያስረዳሉ። የዓድዋ ድል የተገኘው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአፄ ምኒልክ የክተት ጥሪ ምላሽ ለመስጠት በነቂስ በመውጣቱ፣ በአንድነት በመቆሙ፣ በቆራጥነት በመዋደቁ እና በጀግንነት በመሰዋቱ እንደሆነ አስረግጠው ይገልጻሉ።
የታሪክ ድርሳናቱም ቢሆኑ፤ የንጉሡ የክተት ጥሪ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በቻለው መንገድ የዘመቻው ተባባሪ እንዲሆን የሚጠይቅ ከመሆኑም በላይ፤ በኢትዮጵያውያን ፈጣን ምላሽምና በኅብረት የትግል ውጤት የተገኘን ለወገን የጣፈጠ፣ ለጠላት ግን የመረረ ስለመሆኑ ይመሰክራሉ።
እናም ዓድዋ ሲታሰብ የኢትዮጵያውያን አሸናፊነት ብቻ ሳይሆን፤ የአሸናፊነት ጉዞውና ሥራው ምስጢርም አብሮ ይወሳል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በመደጋገፍና በመተባበር በወራሪው ጠላት ላይ ብርቱ ክንዱን አሳርፎ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አፍሪካን እና መላው ጥቁር ሕዝብን ያኮራ ድል የተጎናጸፈበት ስለመሆኑም ይተረካል። የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን በቋንቋ፣ በዘር፣ በአመለካከት፣ በሃይማኖት፣ በአካባቢ ግዛት ሳይለያዩ በአንድ ሀሳብ በአንድ ልብ ሆነው የጋራ ጠላቶቻቸውን ለማጥፋት የየራሳቸውን አስተዋፅዖ ያበረከቱበት ታላቅ ዐውድ ስለመሆኑ ለዛሬው ትውልድ አስተማሪ ሆኖ ይገለጣል።
ተዋግተው በክብር የተሰዉ እና የቆሰሉ ጀግኖች፣ ምግብ ሲያበስሉ የነበሩ እናቶችና ስንቅ አቀባዮች፣ ቁስለኞችን የሚያነሱና የሚንከባከቡ፣የሞቱትን የሚቀብሩ ደጀኖች፣ መጋዣ የሚያቀርቡና ቀለብ የሚሰፍሩ አርሶ አደሮች፣ የመሐሉን አገር ደህንነትና ሰላም ሲያስጠብቁ የነበሩ ባለ አደራዎች፣ መንገድ ጠራጊዎች፣ በፀሎት ሲራዱ የነበሩ የሃይማኖት አባቶች፣ በዘፈንና በቀረርቶ ሞራል ሲሰጡ የነበሩ ከያኒዎች፣ ሌላው ቀርቶ የመጓጓዣ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ እንስሳት ሳይቀሩ የድሉ ባለቤቶች ናቸው።
ዛሬም ከዓድዋ ዘመን ከእኛ አባቶች ልንማርና ልንወስድ የሚገባን ይሄንን ነው፤ ሳይነጣጠሉ መቆምን፤ ተባብሮ ሊያጠፋና ሊበትን የመጣ ጠላትን መታገልን፤ በኅብር ደምቆ የሀገር ኩራትና ጌጥ መሆንን፤ የትናንት አባቶች ልጆችና የልጅ ልጆች ሆኖ የሀገር አንድነትና ሉዓላዊነትን በማንኛውም ዋጋ ማጽናትን፤ ለግል ጥቅም፣ ለቡድን ፍላጎት፣ ለፖለቲካዊና ሌላም ጉዳዮች ያልተንበረከከ ጽኑ ኢትዮጵያዊ ማንነትን መገንባትን፤… ከዓድዋ ባለቤቶች ልንቀስም፣ ገንዘባችን አድርገንም ልንጠቀምበትና ለኢትዮጵያችን ሁለንተናዊ ብልጽግናና ከፍታ ልናውለው ይገባል። ምክንያቱም ዛሬያችን የትናንቱን በዓድዋ መድረክ የተገለጠ በኅብር የተንቆጠቆጠ የአንድነት ገድልና ድል አብዝቶ ገንዘባችን እንድናደርግ ይሻል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን መጋቢት 8 ቀን 2015 ዓ.ም