ኢትዮጵያ ከመኪና ጋር የተዋወቀችው ከ115 ዓመታት በፊት፣ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ነው።በ1900 ዓ.ም የተጀመረው የኢትዮጵያና የመኪና ትውውቅ፣ብዙ ደረጃዎችን አልፎ ዛሬ ካለበት ደረጃ ደርሷል።መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ ተሽከርካሪዎች ይገኛሉ።
ይሁን እንጂ ከእነዚህ ተሽከርካሪዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት እድሜያቸው የገፋ (አሮጌዎች) እና ከፍተኛ የነዳጅ ፍጆታ ያላቸው ናቸው።
በዓለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ እየጨመረ ነው።ከዚህ በተጨማሪም በነዳጅ ከሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች የሚወጣውና ለአየር ብክለት ከፍተኛ ድርሻ ያለው ጭስ የአካባቢ ሥነ ምሕዳር ትልቅ አደጋ ሆኖ ቀጥሏል።
የነዳጅ ዋጋ መጨመር ያደጉም ሆኑ ታዳጊ ሀገራት አማራጭ የትራንስፖርት ዘርፎችን እንዲያማትሩ እያስገደዳቸው ነው። ከእነዚህ አማራጮች መካከል አንዱ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን መጠቀም ነው። የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በየጊዜው በአዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እየተሻሻሉና ተጠቃሚያቸውም እየጨመረ ይገኛል። የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በነዳጅ ከሚንቀሳቀሱት ተሽከርካሪዎች ጋር ሲነፃፀሩ የራሳቸው የሆኑ ጥቅሞች አሏቸው።ለአብነት ያህል ከወጪ አንፃር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎቹን ባትሪያቸውን ሙሉ (Full) ለማድረግ የሚፈጀው ወጪ የነዳጅ ተሽከርካሪዎች ከሚፈልጉት ወጪ በ24 በመቶ ይቀንሳል።
ተሽከርካሪዎቹ ለመንቀሳቀስ የሚጠቀሙት በሀገር ውስጥ የተመረተ የኤሌክትሪክ ኃይል ነው።የሀገር ውስጥ ኤሌክትሪክ የሚገኘው ደግሞ ከታዳሽ የኃይል ምንጮች ስለሆነ ይህ ዓይነቱ የኃይል አጠቃቀም እንደሀገር ጭምር ለነዳጅ የሚጣውን ወጪ ለመቀነስ ትልቅ ሚና ይኖረዋል። ከዚህ በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ምንም ዓይነት ጭስ ወደ ከባቢ አየር የማይለቁ በመሆናቸው የአየር ብክለትን በማስወገድ የአካባቢ ጥበቃን አስተማማኝ ለማድረግ ያስችላሉ።
ኢትዮጵያም በየዓመቱ ለነዳጅ ግዢ ከፍተኛ ገንዘብ ታወጣለች፤ይህም በውጭ ምንዛሪ ክምችቷ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው። በሀገሪቱ የሚገኙት አብዛኞቹ ተሸከርካሪዎች ከፍተኛ የነዳጅ ፍጆታ ያላቸው በመሆናቸው ከተሸከርካሪዎቹ የሚወጣው ጭስ ለአየር ብክለት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያደረገ ነው። እነዚህን ፈተናዎች ለመቀየር ከተጀመሩት ሥራዎች መካከል አንዱ የማበረታቻ ሥርዓቶችን በመዘርጋት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባትና አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ነው።
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥትም የኤሌክትሪክ ተሽከር ካሪዎች በነዳጅ ከሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ጋር ሲነፃፀሩ ያላቸውን አንፃራዊ ጥቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ኢንቨስትመንት ላይ የሚሰማሩ ኢንዱስትሪዎችንና አስመጪዎችን የሚያበረታታ እንዲሁም ኅብረ ተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ የታክስ ማሻሻያ ተግባራዊ ማድረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል። የታክስ ማሻሻያው ዓላማ በኢትዮጵያ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣውን የተሽከርካሪዎች ቁጥር በፖሊሲ ማዕቀፍ ከአካባቢ ደህንነት ጋር የሚስማማ ለማድረግ፣ በኅብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት የማያስከትል፣ በአየር ንብረትና በብዝኃ ሕይወት ላይ ተጽዕኖ የማያሳርፍ እና ታዳሽ የኃይል ምንጮችን በአግባቡ የሚጠቀም የመጓጓዣ ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ እንዲቀርቡ ለማስቻል እንደሆነም ሚኒስቴሩ ገልጿል።
በዚህ የታክስ ማሻሻያ ከውጭ የሚገቡም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ የኤሌክትሪክ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች፣ የቤት አውቶሞቢሎች እና የእቃ መጫኛ ተሽከርካሪዎች ላይ ዝቅተኛ የጉምሩክ ታሪፍ የሚጣልባቸው ሲሆን ከተጨማሪ እሴት ታክስ፣ከኤክሳይዝ ታክስና ከሱር ታክስ ነፃ ይደረጋሉ። በታክስ ማሻሻያው መሠረት የኤሌክትሪክ የቤት አውቶሞቢሎችን በተመለከተም ሙሉ በሙሉ ተበትነው ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው የሚገጣጠሙ የኤሌክትሪክ የቤት አውቶሞቢሎች ከጉምሩክ ቀረጥ፣ ከኤክሳይዝ ታክስ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስና ከሱር ታክስ ሙሉ በሙሉ ነጻ እንዲሆኑ ተደርጓል።
በከፊል ተበትነው ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው የሚገጣጠሙ የኤሌክትሪክ የቤት አውቶሞቢሎች አምስት በመቶ የጉምሩክ ቀረጥ ብቻ የሚጣልባቸው ሲሆን ከኤክሳይዝ ታክስ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስና ከሱር ታክስ ሙሉ በሙሉ ነጻ እንዲሆኑ ተደርጓል።ሙሉ ለሙሉ ተገጣጥመው ያለቀላቸው የኤሌክትሪክ አውቶሞቢሎች ወደ ሀገር ሲገቡ ደግሞ 15 በመቶ የጉምሩክ ቀረጥ ብቻ የሚጣልባቸው ሲሆን ከኤክሳይዝ ታክስ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስና ከሱር ታክስ ሙሉ በሙሉ ነጻ እንዲሆኑ ተወስኗል፡፡
የታክስ ማሻሻያው ከተደረገ በኋላም ከሰባት ሺ በላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንደገቡ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታውቋል። ከዚህ በተጨማሪም በኤሌክትሪክ የሚሠሩ አንድ ሺ 300 የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ አውቶብሶችን ከውጭ አቅራቢዎች በዱቤ ለመግዛት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጋር መግባባት ላይ መደረሱንም ሚኒስቴሩ መግለፁ ይታወሳል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በርሆ ሁሴን እንደሚሉት፣ በትራንስፖርት ዘርፉ ምክንያት ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀውን በካይ ጋዝ መጠን በመቀነስ ለተፈጥሮ/አካባቢ ተስማሚ የሆነ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት የካርቦን ነዳጅ አጠቃቀምን መቀነስና ለአካባቢ ምቹ የሆኑ የትራንስፖርት አማራጮችን መጠቀም ይገባል።የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የበካይ ጋዝ ልቀትን በመቀነስ ለአካባቢ ምቹ የሆኑ የትራንስፖርት አማራጭን ለማቅረብ የሚያስችሉ ግብዓቶች ናቸው።
‹‹ለአካባቢ ብክለት አስተዋፅዖ ያለው ነዳጅ ዋጋው መጨመሩ፣ የኃይል አማራጭ በማፈላለግ ላይ ለሚገኘው የትራንስፖርት ዘርፍ ተጨማሪ ችግር ነው። አስፈላጊ እርምጃዎች ካልተወሰዱ እ.አ.አ እስከ 2050 ባለው ጊዜ በኢትዮጵያ የሙቀት መጠን ከአንድ ነጥብ ስምንት እስከ ሁለት ነጥብ አንድ ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ እንደሚያድግ ጥናቶች ያመለክታሉ።በዓለም አቀፍ ደረጃ የኤሌክትሪክ አውቶሞቢሎችን የመጠቀም ልምድ እየተስፋፋ መጥቷል።የትራንስፖርት ፖሊሲ ያችን ታዳሽ፣ ተደራሽ፣ የተቀናጀ፣ የደንበኞችን ፍላጎት የሚያረካ፣ ለአካባቢ ተስማሚና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆነ የትራንስፖርት ሥርዓት ተዘርግቶ የማየት ራዕይን ይዞ የተቀረፀ ነው።ዘላቂና ለአካባቢ ተስማሚ የሆነ የትራንስፖርት ሥርዓት መዘርጋት በብሔራዊ የትራንስፖርት ፖሊሲያችን ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው›› ይላሉ።
በ10 ዓመቱ መሪ የልማት እቅድ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የትራንስፖርት ዘርፍ መገንባት ዋነኛው የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጠቁመው፣ በእቅዱም 4800 አውቶብሶችን እና 148ሺ የኤሌክትሪክ አውቶሞቢሎችን ጥቅም ላይ ለማዋል መታቀዱንም አቶ በርሆ ይናገራሉ።የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሰርቪና የጥገና ወጪን የሚቀንሱ፣ ከድምፅ ብክለት የፀዱ፣ በየጊዜው እየተሻሻለ የመጣ የባትሪ ቴክኖሎጂና ረጅም የአገልግሎት ጊዜ ያላቸው እንዲሁም አካባቢን የማይበክሉ በመሆናቸው በነዳጅ ከሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች የተሻለ ተመራጭ በመሆናቸው የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚያስችሉ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም ይገልፃሉ።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ በበኩላቸው፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን መጠቀም ኢትዮጵያ ለነዳጅ ግዢ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለመቀነስ የምታደርገውን ጥረት ለማሳካት የሚያግዝ አማራጭ የመፍትሔ አቅጣጫ እንደሆነ ይናገራሉ። እንደርሳቸው ገለፃ፣ ኢትዮጵያ ከወጪ ንግድ ከምታገኘው ገቢ አብዛኛውን ለነዳጅ ግዢ ስለምታውለው በውጭ ምንዛሪ ክምችቷ ላይ ጫና እያሳረፈባት ነው። የነዳጅ ዋጋ እየጨመረ በመሄዱ በሀገራዊ ምጣኔ ሀብትና በነዳጅ አቅርቦት ደህንነት ላይ መዛባት እየፈጠረ ነው። ስለሆነም ችግሩን በአጭርና በረጅም ጊዜ የመፍትሔ አማራጮች መፍታት ያስፈልጋል።
በቅርቡ በሥራ ላይ የሚውለው የኢነርጂ ፖሊሲ የኤሌክትሪክ መጓጓዣዎችን ለማስፋፋት መደላድል የሚፈጥር፣ ታዳሽ ኃይል የሚጠቀም የትራንስፖርት መሠረተ ልማት እንዲኖር የሚያስችል እና ኢትዮጵያ ከነዳጅ ጥገኝነት ለመላቀቅ የምታደርገውን ጥረት ለማሳካት የሚያግዝ ይሆናል። የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን አገልግሎት ላይ የማዋል አማራጭ ታዳሽ ኃይልን ለመጠቀም ያስችላል። ታዳሽ ኃይል ደግሞ ሀገሪቱ ለምትከተለው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ትልቅ ሚና ይጫወታል፤ለካርበን ልቀት መቀነስም አስተዋፅዖ ያደርጋል። የኃይል መሙያ ማዕከላትን በግል ባለሀብቶችም ሆነ በመንግሥት መገንባት ተጨማሪ ገቢ ከማስገኘቱ ባሻገር የቴክኖሎጂ ሽግግርና ተጨማሪ የሥራ እድል እድሎችን እንደሚፈጥር የሚናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ሚኒስቴሩ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አቅርቦትና በኃይል መሙያ ጣቢያዎች ግንባታ ለሚሰማሩ ባለሀብቶችና ተቋማት ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ከውጭ በማስመጣት ለገበያ የሚያቀርቡ ድርጅቶች አሉ። ከእነዚህ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው ‹‹ግሪንቴክ ኢትዮጵያ›› ከ500 በላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ አስገብቶ አገልግሎቱን ለሚሰጡ ድርጅቶችና ለግለሰቦች አቅርቧል። የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ፍጹም ዴሬሳ እንደሚናገሩት፣ ‹‹ግሪንቴክ ኢትዮጵያ›› የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ከውጭ አስመጥቶ ለገበያ ከማቅረብ በተጨማሪ በቀጣይ ሦስት ወራት ተሽከርካሪዎቹን በሀገር ውስጥ ገጣጥሞ ለገበያ ለማቅረብ አቅዶ እየሠራ ይገኛል። ይህን እቅዱን ለማሳካትም ሰንዳፋ ላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያ ፋብሪካ እየገነባ ነው።ድርጅቱ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን መገጣጠም በሚጀምርበት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት 300 መኪኖችን የመገጣጠም እቅድ ያለው ሲሆን፣ በቀጣይ ጊዜያት ሥራውን ይበልጥ በማስፋት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በሀገር ውስጥ አምርቶ የመሸጥ እቅድም አለው፡፡
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን መጠቀም ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው የሚናገሩት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ከዋጋ አዋጭነት፣ ከውጭ ምንዛሪ ቁጠባ እና ከአካባቢ ጥበቃ አንፃር ተመራጭ እንደሆኑ ይገልፃሉ፡፡ ‹‹መንግሥት ዘርፉን ለማሳደግ የወሰዳቸው እርምጃው የሚደነቁ ናቸው›› የሚሉት ኢንጂነር ፍፁም፣ የታክስ ማሻሻያው ለዘርፉ እድገት ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳለውና በዘርፉ የተሠማሩ አካላት ተሽከርካሪዎችን ከማስመጣት ባሻገር ገጣጥመው እንዲሸጡና ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ እንደሚያበረታታ ያስረዳሉ።
‹‹ግሪንቴክ ኢትዮጵያ›› የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ፋብሪካውን ከመገንባት ጎን ለጎን የጥገና አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎችን ለማሰልጠን በጀመረው ሥራ ለ25 ወጣቶች የአራት ወር ሙሉ ስልጠና ሰጥቷል፤ቀጣይ ዙር ሰልጣኞችንም እያስተማረ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪም ተሽከርካሪዎቹ አስተ ማማኝ የኃይል ምንጭ እንዲያገኙ የሚያስችሉ 45 የባትሪ መሙያዎችንም (Charging Stations) አዘጋጅቷል።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን አገልግሎት ላይ የማዋሉ ተግባር ስኬታማ እንዲሆን ከሚያስፈልጉ ግብዓቶች መካከል አንዱ ለተሽከርካሪዎቹ ኃይል የሚያቀርቡ የባትሪ መሙያ ጣቢያዎችን መገንባት ነው።‹‹ካርዲናል ኢንዱስትሪ›› የተባለው ኩባንያ ይህን ተግባር ለማከናወን በ25 ሚሊዮን ዶላር የመነሻ በጀት ሥራ ጀምሯል።የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ሊሊያ ኃይሉ እንደሚሉት፣ ኩባንያው በመጀመሪያው ዓመት 500 የባትሪ መሙያ ጣቢያዎችን ለመትከል አቅዷል። የጣቢያዎቹ ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ የሚሄድ ሲሆን፤ የባትሪ መሙያ ጣቢያዎችን የመትከል ሥራውን በቅድሚያ በአዲስ አበባ ከተማ በመጀመር፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን የመጠቀም ልምድ እየዳበረ ሲሄድ ወደ ሌሎች ከተሞች ለማስፋፋት ጥረት እንደሚደረግም ተናግረዋል።‹‹ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ መገንዘብ እንደሚቻለው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን የመጠቀም ልምድ እንዲጨምር አስተዋፅዖ ከሚያደርጉት ነገሮች ዋነኞቹ የኃይል አቅርቦት እና የባትሪ መሙያ መሠረተ ልማት አቅርቦት ናቸው። የጣቢያዎቹ ቁጥር ሲጨምር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን የመጠቀም ልምድም እየዳበረ ይሄዳል ተብሎ ይጠበቃል›› ይላሉ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በበኩሉ ለሥራው ስኬት ኃይል እና መሠረተ ልማት ያቀርባል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን እንደሚናገሩት፣ መሠረተ ልማቶቹ የሚገነቡት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች ነው።ይህም ሰፊ የተደራሽነት እድልን ይፈጥራል።ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ኃይል የሚያቀርብ ራሱን የቻለ የኃይል መስመር በማዘጋጀትና ተጨማሪ ኃይል ለማምረት የሚያስችል አቅም በመጠቀም ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሚቀርበው ኃይል አሁን ባለው የኃይል አቅርቦት ላይ ተፅዕኖ ማሳረፍ እንዳይችል ዝግጅት ተደርጓል።አሁን ባለው ኃይል የማመንጨት አቅም በዓመት እስከ አንድ ሺ ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ማቅረብ የሚቻልበት አቅም አለ። በመጀመሪያው ዓመት ሊተከሉ ከታቀዱ የባትሪ መሙያ ጣቢያዎችም በዓመት እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዷል፡፡
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን መጋቢት 7 ቀን 2015 ዓ.ም