የምሥራች ዓለሙ ትባላለች። ተወልዳ ያደገችው ከአዲስ አበባ በ76 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሞጆ ከተማ ነው። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷንም በሞጆ ቁጥር አንድ ትምህርት ቤት ተከታትላለች። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ እዚያው ሞጆ ከተማ ላይ ቁጥር ሁለት በሚባለው ተምራለች። ከ12ኛ ክፍል በኋላ ያለውን ትምህርቷን ግን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ገብታ ለመቀጠል አልቻለችም። ለዚህ ደግሞ ምክንያት አላት። ለመኖርና ራሷን በሌላ መንገድ አብቅታ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ለመድረስ መፈለጓ አንዱ ነበር።
ለሕልሟ መሳካት ያግዛት ዘንድ 12ኛ ክፍል ፈተናዋን እንደተፈተነች የጸጉር ሥራ ሙያ ተማረች። በዚህ ትምህርቷም ያገኘችውን እውቀት ይዛ ወደ ተወለደችበት ከተማ አቀናች። ጸጉር ቤት ውስጥ በመቀጠርም ሥራዋን አሀዱ አለች። ተቀጥራ ትሠራባት የነበረችው የጸጉር ቤት ባለቤት መልካም እይታ ያላት ነበረችና የሥራ ብቃታቸውን በማየቷ እርሷን ጨምሮ ሁለት ሴቶችን አዲስ አበባ ሄደው የሚሠሩበትን እድል ሰጠቻቸው። ይህ ሁኔታ ደግሞ ለየምሥራች ብዙ ነገሮቿን ያመቻቸላት ሆነ።
“… አዲስ አበባ በተሰጠኝ እድል ተጠቅሜ የተሳካ ጊዜ እንዳሳልፍ ሆኛለሁ። በሥራውም በኑሮም ጥሩ የሚባል ሁኔታ ውስጥም አስቀምጦኛል። ነገር ግን ሕይወት ሁልጊዜም ቢሆን አዲስ ነገርን ይፈልጋልና እኔም አዲስ አበባ ከተማ ላይ እየሠራሁ ያለሁት የጸጉር ቤት ሥራ ለጊዜው የሚያኖረኝ ቢሆንም ነገን የተሻለ ለማድረግ ግን አያስችለኝምና ሌሎች አማራጮችን ማየት እንዳለብኝ ተሰማኝ።” ትላለች የአዲስ አበባ እድሏንና የሥራ ጉዞዋን ስታነሳ።
የምሥራች ይህ የለውጥ ፍላጎቷ ከእለት እለት እየጨመረ በመምጣቱ ምን ባደርግ ነው በሕይወቴ ላይ ለውጥ የማመጣው ብላ ስታስብ ያገኘችው ምላሽ ወይም አማራጭ ወደ ዓረቡ ሀገር መሄድ ነበር። አደረገችውምና ኩዌት ሄደች። ሆኖም በብዙ ነገር ተፈትና ነበር። ሁኔታውን ስታስረዳ እንዲህ ነበር ያለችው “… ሕይወት ለውጥ ያስፈልጋታል ብዬ በማሰብ ነበር የሄድኩት። እንደ አብዛኞቹ እህቶቼ በቤት ሠራተኝነት ለመሥራት። ሆኖም እዛም ከደረስኩ በኋላ ብዙ ነገሮች ፈተና ሆኑብኝ። ከቋንቋ ችግር ጀምሮ በቀላሉ ነገሮችን ለመልመድ ከባድ ነው። የባዕድነት ስሜቱም ከፍ ያለ ነበር።”
እነዚህ ፈተናዎች ከምታስበው በላይ ቢሆኑባትም ጉዞዋ ዓላማ ያለው ነበርና ራሷን ከሁኔታዎች ጋር በማዛመድ ዓመታትን ቆይታለች። ከሰዎቹ ባሕሪና ከሀገሩ ባሕልና ወግ ጋር ለመግባባት ጥረት አድርጋለች። ይህም ሆኖ ግን መጀመሪያ ከገባችበት ቤት ብዙም ሳትቆይ ነበር የወጣችው። እንደ አብዛኞቹ አሠሪዎች መጀመሪያ የገባችበት ሴት አልተመቻትም። የገባችበት ቤት ባለ አራት ወለል ፎቅ የነበረ ሲሆን፤ አምስት ወንድ ልጆች በቤቱ ውስጥ ይኖራሉ።
የምሥራች ሥራዋ ደግሞ አራቱን ወለል ሕንጻ ማጽዳትና የልጆቹን መኝታ ክፍል ማዘጋጀት ነበር። በዚህም በቀላሉ ለመግባባት ተቸገረች። እናም ከወር በላይ እዚያ ቤት ውስጥ መቆየት አልቻለችም። በአግባቡና በትሕትና ያመጣት አገናኝ (ኤጀንሲ) ጋር እንድታደርሳት አሠሪዋን ለመነቻት። ሴትየዋም በሁኔታው በመናደዷ የቆየችበትን ደመወዝ ከልክላ አገናኙ ጋር አደረሰቻት። የምሥራችም ደመወዟን መከልከሏ ምንም ሳይመስላት ከቤቱ ወጥታ አገናኞቹ ጋር መድረሷ ለእሷ ትልቅ ድል ሆነላት።
ኤጀንሲው ሌላ ሁለተኛ ቤት ፈልጎ አስገባት። ይህኛው ቤት ደግሞ የተለየ ነው። የተፈናቃዮች መንደር አካባቢ የነበረና ራሳቸውን እንኳን በቅጡ ማስተዳደር ያልቻሉ ሰዎች ቤት ነበር።የምሥራች እዚህ ደግሞ ሌላ ፈተና ገጠማት። ሰዎቹ ተፈናቃዮች ከመሆናቸው የተነሳ ገቢያቸውም ያን ያህል አመርቂ አይደለም። እሷ ደግሞ ሠርታ ለማግኘት ከአገሯ የወጣች ናት፤ በዚህ መካከል እነዚህ ሰዎች ደመወዝ ይከፍሉኛል አይከፍሉኝም የሚለው ያሳስባት ጀመር። ይህም ቢሆን ግን ሁሉንም ተቋቁማ ለመሥራት ብትፈልግም ሁኔታው ግን ከአቅሟ በላይ ሆነ። በመጨረሻም ሴትየዋ ያመጣቻት ቦታ የ21 ቀን ደመወዟን ሰጥታ አደረሰቻት። እድል ከእሷ ጋር የሆነችላት የምሥራች እወጣለሁ ባለችባቸው ቤቶች ሁሉ ሰዎች ሳይጣሏት በትሕትና ያመጧት ቦታ መልሰው ያደርሷታል። አሁን ሦስተኛ ቤቷ ላይ ደርሳለች። በልቧ ፈጣሪዋን እየለመነች ወደቤቱ ለሥራ ገባች። ሦስተኛው ቤቷ የተሻለ ሰው ያገኘችበት ነው። ባለቤቷ ሁለት ልጆች አሏት። ከእርሷ በፊት የገባች የፊሊፒንስ ዜጋም አለች፤ ሹፌርም አለ፤ ቤቱም ፎቅ የሌለው ቪላ ቤት ነበር። በዚህም ጥሩና ደስተኛ ሆና መሥራቷን ቀጠለች። የእርሷ የሥራ ድርሻ የምግብ ሥራ ነው። በዚህም ሦስት ያህል ዓመታትን በቤቱ ውስጥ አሳልፋለች። በመካከል ሁለት ዓመት ሲሞላት ለእረፍት ሀገሯ ቤተሰቦቿ ዘንድ ደርሳ ነበር የተመለሰችው።
የምሥራች ሁሌም ለውጥ ናፋቂ ናትና ሀገሯ ደርሳ ስትመለስ አንድ ሃሳብ መጣላት ፤ እሱም ከሰው ቤት ወጥታ ራሷን ችላ መሥራትና ራሷን በበለጠ ሁኔታ መቀየር የሚል ነበር። ይህንን ሃሳቧንም ለአሠሪዋ እንደሄደች ነገረቻት፤ ሴትየዋም የተባረከች ነበረችና ፍላጎቷን አክብራ ነገር ግን ለእሷ የሚሆን ታማኝና ጎበዝ ሰው እንድታመጣላት ነገረቻት። የምሥራችም በሀሳቧ በመስማማት ከኢትዮጵያ የምትተማመንበትን ሰው በማምጣት ሁለት ወር አለማምዳላት ወጣች። ይህም የአሠሪና የሠራተኛ ግንኙነታቸውን ከፍ ወዳለ ወዳጅነት አሸጋገረው። እንደ ቤተሰብ የሚተሳሰቡ የሚጠያየቁ በችግር በደስታ የሚገናኙ አደረጋቸውም።
አሁን የምሥራች ሌላ ዓለምና ኑሮ ለመመሥረት አሰበች፤ ከዚህ ቀደም እረፍት ስትወጣ የተዋወቀቻቸው ኢትዮጵያውያን እህቶቿ ደግሞ ሥራ እስከምታገኝ ማረፊያዎቿ ሆኑላት። ከዚያም ሥራ ማፈላለግ ጀመረች። እሷ እንኳን ሀገር ቤት በተማረችው የጸጉር ሥራ ለመቀጠር ነበር የፈለገችው። ቢሆንም ጓደኞቿ ግን ሥራው ረጅም ሰዓትን የሚወስድ በመሆኑ እንደ እኛ ሱቆች ላይ ሥሪ ብለው አማከሯት። እሷም በሃሳባቸው ተስማምታ ደመወዙ ዝቅ ያለ ቢሆንም ሱቅ ተቀጥራ እቃ መሸጡን ተያያዘችው። ይህንን እየሠራችም በመኖሪያ ፍቃዱ የሚያኖራት (ስፖንሰር የሚያደርጋት) ማፈላለግ ያዘች። በዚህም ተሳክቶላት በማግኘቷ የሥራ ፈቃዷን በአገኘችው ስፖንሰር በማዞር ሥራዋን በከፍተኛ ሞራል መሥራቷን ቀጠለች።
የምሥራች ሱቅ ቆሞ ከመነገድ ወደ ትልልቅ ካምፓኒዎች የጅምላ ንግድ ማሻሻጥ (ሴልስ) ውስጥ ገባች። ኮሚሽን እያገኘች በማሻሻጥም ጥሩ ገቢን ማግኘት ጀመረች። ነገር ግን ይህንን የሞቀ ሥራዋን የሚያቀዘቅዝ ነገር ተፈጠረ። እሱም ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ነበር። ኮቪድ ባመጣው ችግር ምክንያት ሱቆች ተዘጉ። እንደ ቀድሞው አሻሻጮች (ሴልሶች) የሚያስፈልጉት ነገር ጠፋ። ከዚያ ይልቅ ሰዎች በበይነ መረብ (በኢንተርኔት) ቀጥታ ግብይትን ጀመሩ። ይህ ደግሞ ካምፓኒዎቹ የሠራተኞቻቸውን ቁጥር እንዲቀንሱ አስገደዳቸው፤ ከተቀናሾቹ መካከል ደግሞ የምሥራች አንዷ ሆነች።
ይህ ጊዜ ለየምሥራች አቅጣጫዋን ወደሌላ መንገድ መቀየሪያ ነበር። ማወቅ መቼና እንዴት እንደሚጠቅም አይታወቅምና የምሥራችም ሀገሯ ላይ ተምራው የሄደችው የጸጉር ሥራ ሙያ አሁን ላይ አስፈለጋት፤ ምናልባት ከዘመኑ ጋር ማጣጣም ይገባት ይሆናል እንጂ መሠረታዊው እውቀት ያላት በመሆኑ አልተቸገረችም። በዚህም ትንሽ ዘመናዊ የሆኑ የጸጉር ቤት እቃዎችን አጠቃቀም ማወቅ እንዲሁም አንዳንድ ወቅታዊ የፋሽን ነገሮችን መረዳትን ተማረችና በአነስተኛ ደመወዝ አንድ ጸጉር ቤት ተቀጥራ ጊዜውን ለማለፍ ተጠቀመችበት። ራሷን ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር ለማጣጣም በቤቴ ውስጥ አንዳንድ እቃዎችን ገዝታም በመለማመድ ሥራውን ተቀላቀለች።
“…እኔ ውጪ ስወጣ ምን እንደሚገጥመኝ አላውቅም ነበር፤ ነገር ግን እድለኛ ሆኜ ፈጣሪም አግዞኝ የከፋ ነገር አልገጠመኝም። ስኬታማ ሆኛለሁ ፤ ነገር ግን በርካታ እህቶቼ ስለው የሚመጡት ነገርና ነባራዊው ሁኔታ አልጣጣም ብሏቸው ብዙ ችግር ውስጥ ገብተዋል፤ እየገቡ ያሉም አሉ። ለእነሱ ደግሞ ድምፅ ልሆናቸው በምችለው ሁሉ ሌሎችን አስተባብሬ ላግዛቸው ብዙ እንቅስቃሴዎችን እያደረኩ ነው” የምትለው የምሥራች፤ ዛሬ ላይ በኩዌት ትልቅ የሚባል ጸጉር ቤት ውስጥ ተፈላጊ ሆና ትሠራለች። የዛሬ ሰባትና ስምንት ዓመት ስለእኛ በዓረቡ ዓለም በተለይም በኩዌት ስለሚኖር ዜጎች ግድ የሚለው ምንም ዓይነት ኮሚኒቲ አልነበረንም የምትለው የምሥራች፤ በጊዜው አንድ ሰው ተቸገረ ሲባል እንዲሁ በበጎ ፈቃድ የአቅማችንን ማድረግ ነበር። ይህ ግን ማንም ምንም የሚጠቅም ስላልነበር ሌሎች ነገሮችን ማሰብ ጀመርን በማለት ትናገራለች።
ኢትዮጵያውያን በሰው ቤት ሲሠሩ፣ ሳንባቸው ሲታመም። የካንሰር ተጋላጭ ሲሆኑ አንዳንድ ጊዜም ከጫና መብዛት የተነሳ ለአዕምሮ ሕመም ሲጋለጡ አሠሪዎቻቸው ከነደንብ ልብሳቸው አስወጥተው ይጥሏቸዋል። በጣም የተሻሉ ካሉ ደግሞ ሐኪም ቤት አድርሶ የመሄድ ሁኔታዎች ያጋጥማሉ። እናም የምሥራችና ጓደኞቿ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ‹‹በኩዌት የኢትዮጵያውያን ወጣቶች ማኅበር›› በሚል ማኅበር መሠረቱ።
በማኅበራቸው አማካይነትም በዚህ ዓይነት ችግር ውስጥ የገቡ እህቶችን ቫዝሊን። የሴቶች ንጽሕና መጠበቂያዎች። የጥርስ ሳሙናና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን አዋጥቶ በመግዛት በአስራ አምስት ቀን አንድ ጊዜ እየሄዱ መጠየቅ ጀመሩ። ከሁሉም በላይ ደግሞ በኩየት የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሚያሳየው ምንም አይነት ተሳትፎም ሆነ ሥራ ያልነበረ በመሆኑ ኤምባሲው ስለ ዜጎቹ ደህንነት እንዲያስብ የማድረግና የማነቃቃት ሥራንም እንዲሠሩ ሆኑ። ይህ ሥራቸው ደግሞ ብዙ ሰዎችን ተስፋ የሰጠ ወደ ጤናቸውና ሀገራቸው የመለሰ ነበር።
“…በወጣት ማኅበሩ ብዙ ነገሮችን ስንሠራ ቆይተናል። አስር ቤት ያሉ እህት ወንድሞቻችንን እንጠይቃለን። ጉዳያቸውን እንፈጽማለን፤ የታመሙትን እናሳክማለን፤ እንጠይቃለን፤ በሕይወት ሲያልፉም አስከሬናቸው በክብር ወደሀገራቸው እንዲሸኝ እናደርጋለን። ኋላ ላይ ግን ይህ ማኅበር ለምን ወደ ኮሚኒቲ ደረጃ አድጎ ሕጋዊ እውቅናን አያገኝም በማለት ምርጫ ተደርጎ የመተዳደሪያ ሕገ ደንብ ጸድቆ በሥነ ሥርዓት ወደ ሥራ ገብተናል” ትላለች። ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ እውቅና ባገኘው ኮሚኒቲ ውስጥም የምሥራች መሥራች አባል በመሆን በርካታ ሥራዎች እንዲሠሩ ማድረጓን ትገልጻለች።
በዋናነት ኤምባሲው ሕጋዊ መንገድን እንዲከተሉ የሚያደርጉ ደብዳቤዎችን እንዲሰጣቸው ማስቻል ላይ ብዙ ለፍታለች። በተለይም ማረሚያ ቤቶች አካባቢ ሲሄዱ የድጋፍ ደብዳቤ እንዲጽፉላቸው ማድረጉ ላይ ከኤምባሲው ጋር የተጠናከረ ሥራ ከሠሩት መካከል ነች። ‹‹ስለዜጋችን ግድ ይለናል›› በሚል በበጎ ፍቃድ የሚሠሩት ይህ የኮሚኒቲ ሥራቸው ኢትዮጵያውያን ተረጋግተው ሥራቸውን እንዲሠሩ አድርጓቸዋል። በደል ሲኖርባቸው እንዲያወጡት፤ መፈታት የሚችለው እንዲፈታ የማይሆን ከሆነ ደግሞ በአካላቸው እንዲሁም በጤናቸው ላይ ምንም አይነት ጉዳት ሳይደርስ በሰላም ሀገራቸው እንዲገቡ በማድረግ በኩልም ብዙ መፍትሔ የቸራቸው ሆኗል።
አሁን ላይ 20ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በኩዌት ሀገር በተለያዩ የሥራ መስኮች ላይ ተሠማርተው የሚገኙ ሲሆን፤ እነዚህ ዜጎች ደግሞ ትዳር መሥርተው ፤ ልጆች ወልደው ያስተምራሉ። ይሁን እንጂ አንዳንድ ፈተናዎች ይኖራሉ። እናም ይህንን ለመፍታትም ኮሚኒቲው መዋዕለ ሕጻናትን በመክፈት ተጠቃሚ የማድረግ አቅድ ይዟል። በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎች አገሮች እንደሚያደርጉት የሀገራችንን ምርት እዚያ ወስደን ለዜጋውም ለሌላውም ለመሸጥ አንደ ሱፐር ማርኬት አይነት የገበያ ማዕከላትን የመክፈት አቅድ ተይዟል ትላለች የምሥራች።
“…አንድ ለቤት ሠራተኝነት ከአገሯ የምትወጣ ሴት በምን መልኩና ምን ዓይነት ዝግጅት አድርጋ መሄድ እንዳለባት መንግሥትና ኤምባሲዎች እየሠሩ ያለው ሥራ አለ፤ ነገር ግን ይህም ቢሆን ሕገወጥ ደላሎች አሁንም ድረስ ምንም የማያውቁ የገጠር ልጆችን ነው የሚልኩት ፤ ቋንቋ መሞከር እንኳን አይችሉም። ያንን ከባድ የሆነ የዓረቦች ባሕሪም መቋቋም አይችሉም፤ በመሆኑም ምንም ሳያውቁ የሚመጡት እህቶቻችን ከፍ ላለ ችግር እየተጋለጡ ነው” የምትለው የምሥራች፤ በአሜሪካና አውሮፓ ሕግ የበላይ ነው። ማንኛውም ሰው መብቱና ደህንነቱ ይጠበቃል። ዓረብ አገር ላይ ግን ሕጉ ሳይሆን ሰዎቹ ናቸው የበላይ። ይህንን የበላይነታቸውን ለማሳየት ደግሞ የተለያዩ ነገሮችን ይጠቀማሉ። አንድ ነገር እንኳን ሲሆን ‹‹እኔ እኮ ሀገሬ ነው›› በማለት ራሳቸውን ከፍ ያደርጋሉ። በመሆኑም እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ጋር ተግባብቶ ለመኖር ትልቅ ትዕግስት ይጠይቃል። ነገር ግን ከአቅም በላይ ከሆነ ወደ ኤጀንሲ አልያም ኮሚኒቲው ጋር መሄድን መልመድ ያስፈልጋል ስትል ከተሞክሮዋ በመነሳት ትመክራለች።
አሁን በኤምባሲዎች በኩል ብዙ ለውጦች መኖራቸውን የምትጠቁመው የምሥራች፤ ዜጎች ምንም ዓይነት ጉዳት በራሳቸውም በሌሎችም ላይ ከማድረሳቸው በፊት ውሳኔያቸውን ማሳለፍ ይገባቸዋል። ሁሉም ሴቶች ለሥራ ሀገራቸውን ጥለው ከወጡ በኋላ ሊላበሱ የሚገባቸው ነገር ትዕግስት፤ ሆደ ሰፊነት፣ መቻል ከመጠን በላይ ከሆነ ደግሞ ወጥተው ሌላ ቤት የሚቀይሩበትን መንገድ መፈለግ እንጂ ወዳልተገባ ነገር ውስጥ ገብተው የራሳቸውንም የሌላውንም ተስፋ ሊያጨልሙ አይገባቸውም ትላለችም።
በኩዌት የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ከደመወዝ ጋር በተያያዘ የነበሩ ልዩነቶችን በማጥበብ፤ ሌሎች በዜጎች ላይ ይደርሱ የነበሩ ጉዳቶችን በመቀነስ፤ በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት እንደ ዜጋ ለሀገራችን ምን እናድርግ በማለት ብዙ ሠርተናል። ለአብነትም ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ የሚሆን አንድ ሚሊዮን አንድ መቶ ብር አስገብተናል። ከዚያም በጦርነቱ ምክንያት ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ወገኖች አምስት ቤቶችን ለመሥራት ቃል ገብተናል። አሁን ላይ ሦስቱ አልቀዋል፤ ሁለቱም በመሠራት ላይ ናቸው። በሌላ በኩልም ወልዲያ ላይ ለተፈናቀሉ ዜጎች አልባሳትን የመለገስ ሠራ ተሠርቷል ብላናለች።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን መጋቢት 5 ቀን 2015 ዓ.ም