አዲስ አበባ፡- የሴቶች ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ምክትል ፕሬዚዳንትና የፌዴራል የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ማቋቋም አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ጠይባ ሐሰን ገለጹ::
ወይዘሮ ጠይባ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፣ በታሪክ የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ ወደ 50 በመቶ የተጠጋበትና እንደ አሁኑ ሴት የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር የሆነችበት ጊዜ ታይቶ አይታወቅም:: ሀብት ከማፍራትና በመምራት ረገድም ሴት ባለሀብቶችን ለማፍራት እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ አበረታች ውጤት ተመዝግቧል::
ቀደም ሲል ከባድ ኃላፊነት ነው በማለት ለወንዶች ብቻ የሚሰጡ እንደ ፕሬዚዳንትነትና ሚኒስትርነት ያሉ አገራዊ ኃላፊነቶች በስፋት ለሴቶች መሰጠታቸውን ያወሱት ወይዘሮ ጠይባ፤ ሴቶቹም በተሰጣቸው ኃላፊነት አበረታች ውጤት ማስመዝገብ መቻላቸውንና ባሉበት የሥራ ኃላፊነት ሚናቸውን በሚገባ እየተወጡ መሆናቸውን አስረድተዋል::
ሴቶች ተሳትፏቸውን በማሳደግ እና ተጠቃሚ እንዲሆኑ መሥራት ያስፈልጋል ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቷ፤ ከዚህ አንጻር በተለይ ሴቶችን ከኢኮኖሚ ጥገኝነት በማላቀቅ በተለያዩ የሥራ መስኮች ለማሳተፍ እየተደረገ ያለው ጥረት የሚያበረታታ መሆኑን አስገንዝበዋል::
ያለብቃት ሴቶችን በሴትነታቸው ብቻ በኮታ ማሳተፍ እንደሌለበት የመከሩት ወይዘሮ ጠይባ፤ ሴቶች ራሳቸውን ችለው በሁሉም የሥራ ኃላፊነት መስኮች ተሳታፊነታቸውን ማሳደግ እና በተለይ ለሴቶች እየተሰጠ ያለውን የትምህርት ዕድል ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል::
እንደ ወይዘሮ ጠይባ ማብራሪያ፣ የአገር ወይም የሥራ መሪ መሆን ማለት የውጤትና የተግባር እንጂ የሥራ መለማመጃ መሆን የለበትም:: ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ መንግሥት በትምህርት ላይ በስፋት ኢንቨስት በማድረጉ በርካታ የተማሩና ብቃት ያላቸው ሴቶች ማፍራት ተችሏል:: እንደከዚህ በፊቱ የተማሩ ወስን ሴቶች በባትሪ የመፈለግ አሊያም ብቁ ያልሆኑትን የማለማመድ ምዕራፍ አይታይም፤ መኖርም የለበትም:: የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግም የሴቶችን አቅም ለማጎልበት የተለያዩ የአቅም ማጎልበቻ ሥራዎችን እየሠራ ነው::
እንደ ስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ማቋቋም አገልግሎትም ከስደት ጋር ተያይዞ ለሚፈጠሩ ችግሮች አብዛኛው ተጋላጭ ሴቶች በመሆናቸው በአገራቸው ሠርተው እንዲለወጡ የተለያዩ ድጋፎች መደረጋቸውን የተናገሩት ወይዘሮ ጠይባ፤ ስደተኞቹን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ማቀላቀል አንዱ የማቋቋም አካል በመሆኑ በርካታ ሴቶች ከቤተሰቦቻቸው ጋር የማቀላቀል ሥራ መሠራቱን አመልክተዋል::
ከሳውዲ ዓረቢያ ብቻ የተመለሱ ዜጎች ወደ አንድ ሚሊዮን ገደማ መሆናቸውን ያብራሩት ወይዘሮ ጠይባ፤ ምንም እንኳ ለዚህ ሁሉ ዜጋ በአንድ ጊዜ የሥራ ዕድል መፍጠር ባይቻልም የተወሰኑትን በተለይ ሴቶቹን ለመደገፍ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ፈንድ የማፈላለግ እና ሥልጠና የመስጠት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል::
ዋቅሹም ፍቃዱ
አዲስ ዘመን መጋቢት 5 ቀን 2015 ዓ.ም