አዲስ አበባ፡- ባጃጅ ተሽከርካሪዎች በቅርቡ ወደ መደበኛ ስራቸው እንደሚመለሱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ምትኩ አስማረ በቅርቡ በመዲናዋ እየተነሳ ካለው የባጃጅ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ለኢፕድ እንደተናገሩት፤ የከተማ አስተዳደሩ የባጃጅ አገልግሎትን የተሻለ ለማድረግ የአሰራር ማስተካከያ እያደረገ ነው። ይህ እስከሚጠናቀቅ ድረስም የባጃጅ አሽከርካሪዎችና ተጠቃሚዎች በትዕግስት እንዲጠብቁ አሳስበዋል።
የትራንስፖርት ሥርዓቱን ለማዘመን የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ገልፀው፤ ከባጃጅ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የከተማ አስተዳደሩ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ ባጃጆችን በሚመለከት ምንም አይነት ታርጋ ባይሰጥም፣ ከተለያዩ ክልሎች ይዘው የመጧቸውን ታርጋዎችን እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል።
የባጃጅ የትራንስፖርት አገልግሎት መንግሥት የትራንስፖርት አገልግሎት ማድረስ በማይችልበት ቦታዎች ላይ ማለትም የከተማ ዳርቻዎች፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ አገልግሎት መስጠት እንደተጀመረ አስታውሰው፤ አሁን ላይ እየተስፋፋ መጥቶ በከተማይቱ ውስጥ ከሚገኙ 11 ክፍለ ከተሞች መካከል በስምንቱ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
ከተማ አስተዳደሩ አገልግሎቱን ወደ አሰራር ለማስገባት ባደረገው ጥረት 9 ሺህ 950 የባጃጅ አገልግሎት ሰጪዎች በ 123 ማህበራት ተደራጅተው በስምንቱ ክፍለ ከተሞች ላይ እንደሚሰሩ ተናግረው፤ እስካሁን ብዛት ያላቸው የባጃጅ ተሽከርካሪዎች እንዳልተመዘገቡ ጠቁመዋል።
ከባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት ጋር ተያይዞ በኅብረተሰቡ ላይ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እየተከሰቱ ነው። የከተማ አስተዳደሩ ያሉትን ችግሮች በመለየት እየሰራ ነው ያሉት አቶ ምትኩ፤ ከትራፊክ ፍሰት ጋር በተያያዘ ሰፊ መስተጓጐል ይፈጥራሉ፣ ትርፍ በመጫን አደጋዎች እንዲፈጠሩ መንስኤ በመሆንና ከሕግ አስከባሪ አካላት ጋር ግጭት እየፈጠሩ ነው። ሕግን አክብሮ አገልግሎትን ከመስጠት አኳያ ሰፊ ክፍተቶች እየታየባቸው እንደሆነ አቶ ምትኩ አብራርተዋል።
በኅዳር ወር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ፣ የሰላምና ፀጥታ እንዲሁም የከተማው ፖሊስ ኮሚሽን በጋራ በመሆን የባጃጅ ማህበራትን ጠርተው እንዳወያዩና ከተማ አስተዳደሩ በሚወስንላቸው ታሪፍ ሊሰሩ እንደሚገባ፣ በዋና ዋና መንገዶችና አደባባዮች ላይ መስራት እንደማይችሉና የከተማ አስተዳደሩ በሚፈልግበት ጊዜ ከመስመር ላይ ሊያስወጣቸው እንደሚችል ከስምምነት መደረሱን አስታውሰዋል።
የከተማ አስተዳደሩ የትራንስፖርት ቢሮ ይህንን መነሻ በማድረግ የተለያዩ የአሰራር ሥርዓቶችን ዘርግቷል። ከእዚህም መካከልም ታሪፍ የመወሰን፣ የሚመሩበትን መመሪያ የማዘጋጀት፣ የስምሪት ቦታዎችን የመለየት፣ ባለ ንብረቶችን በማኅበር የማደራጀት ስራዎች ተሰርተዋል።
‘’የከተማ አስተዳደሩ በፖሊሲውና በእቅዱ የባጃጅ ትራንስፖርትን የመጠቀምና የማስፋፋት ምንም አይነት ፍላጎት የለውም’’ ያሉት አቶ ምትኩ፤ ባጃጆች መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎት ተደራሽ በማይሆንባቸው የከተማዋ አካባቢዎች ለኅብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጡ ስለሆነ በዛው ይቀጥሉ ተብሎ ተወስኖ እንደነበረና መስመር አንለቅም፣ በሚወጣው ታሪፍ አንሰራም የሚሉና የመደራጀት ፍላጎት አለመኖር ትልቁ ችግር እንደሆነ ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩ አገልግሎት የሚሰጥባቸውን የስምሪት መስመሮች የለየ ሲሆን በከተማዋ ዳርቻዎች፣ በሰፋፊ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ በተመረጡ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎት በሌለባቸው ቦታዎች ላይ የስምሪት መስመሮች ሊሰጡ እንደሚችሉና ተመዝግበው ከተደራጁት ውጭ መስመር የመስጠትም ሆነ የማደራጀት ተግባር ከዚህ በኋላ እንደማይኖር አቶ ምትኩ ጠቁመዋል።
የከተማ አስተዳደሩ በሚያወጣው የታሪፍ ተመን፣ በሚሰጠው ስምሪት፣ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ ሶስት ሰዓት ብቻ መስራት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን መጋቢት 3 ቀን 2015 ዓ.ም