በአገራችን ሰሞነኛ የተለያዩ ከበስተጀርባቸው ጥፋቶችን ያነገቡ ክስተቶች ተከስተዋል፤ ያስከፈሉንም፣ ዋጋ ቀላል ነው ተብሎ የሚጠቀስ አይደለም በእኔ እምነት ነገሮችን በሰከነ መንገድ ማየት ቢቻል እነዚህ ነገሮች ባልተከሰቱ ነበር ብዬ አምናለሁ። የችግሮች ዋነኛ ችግር መስከን አለመቻላችን ነው። መስከን ለበርካታ ነገሮች መፍትሄ ነው። በሰከነ አዕምሮ ውስጥ መፍትሄ አለ። በሰከነ አዕምሮ ውስጥ የተረጋጋ ሥዕብና አለ። በሰከነ መንደር ውስጥ በጥባጮች ቦታ የላቸውም።
‹‹ሠላምን በጉልበት ማስጠበቅ አይቻልም። ሠላምን ማሳካት የሚቻለው በመግባባት ብቻ ነው›› ይላሉ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬገን። እንግዲህ ችግሮች ሲከሰቱ መቋጫው ሠላም ማምጣት ነው። ነገር ግን ነገሮች መፍትሄ አላቸው በሚል እሳቤ ብቻ ችግር መፍጠር ተገቢ አይደለም። አንዳንድ ጊዜ ‹‹ካልደፈረሰ አይጠራም›› የሚለው አገርኛ አባባል ሳይጠናወተን አልቀረም ብዩ ለማሰብ እገደዳለሁ ።
ለመጥራት የግድ መደፍረስ የለበትም። ሳይደፈርስ ገና በጅምሩ መሰረት ማስያዝ ይቻላል። ሰሞኑን የገጠመን ነገር ይህ ነው። ጥቂቶች ሐሳባቸው ነገሩ ይደፍርስ የሚል ይመስላል። የለም! የለም! መደፍረስ ያለበትንና የሌበትን ማወቅ ይገባል። ቀይ መስመሮችን እንዳሻን ከተረማመድንባቸው ውጤታቸው አደገኛ ነው።
ከሁሉም በላይ በሃይማኖት እና በፖለቲካው ጎራ የታየው መደበላለቅ የከፋ እንደነበር ይሰማኛል። ‹‹ሸማ በየፈርጁ ይለበሳል›› እንደተባለው ሁሉም በራሱ አውድ ሲመከርበትና ሲዘከርበት ፍሬያማ ይሆናል። አንዱን ከሌላው እያጋጩና እየበጠበጡ ጥሩ መመኘት ህልም ነው የሚሆነው።
በዚችህ አገር አንድ የበላይ ሌላው የበታች የሚሆንበት አካሄድ መኖር የለበትም። ለአንዱ ህግ የሚከበርለት ለሌላው መብቱ የሚገረሰስበት አግባብም መፈጠር የለበትም። ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ብቻ በአገሪቱ አውድና ህግ መሠረት ሁኔታዎችና ህጎች ሊከበሩና ሊተገበሩ ይገባል።
በመገፋፋት ላይ የተመሰረተች አገር መሆን የለባትም- ኢትዮጵያ። አንዳችን ሌላኛችንን አቅፈን ደግፈን ወደ ተሻለ ምዕራፍ የምንሸጋገርበት፤ ተከባብረን ተቻችለን የምንጓጓዝበት የጋራ ሃዲድ ነው መሆን ያለባት፤ መሆንም ያለበት ይኸው ነው።
ለዚህ ሃሳብ ማጥኛ ይሆን ዘንድም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በበዓለ ሲመታቸው ወቅት ለህዝብ እንደራሴዎች ያደረጉትን ንግግር ማስታወስ ይበጃል። ‹‹ማንነታችንን እንዳይለያይ ሆኖ የተሰናሰለ፣ እንዳትነጣጠል ሆኖ የተገመደ፣ የተዋደደ እና የተዋሀደ ነው። አማራው በካራ-ማራ ለአገሩ ሉዓላዊነት ተሰውቶ የካራ-ማራ አፈር ሆኖ ቀርቷል። ትግራዋይ በመተማ ከአገሬ በፊት አንገቴን ውሰዱ ብሎ የመተማ አፈር ሆኗል።
”ኦሮሞው በአድዋ ተራሮች ላይ ስለአገሩ ደረቱን ሰጥቶ የአገሩን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ከአድዋ አፈር ተቀላቅሏል። ሱማሌው፣ ሲዳማው፣ ቤኒሻንጉል፣ ወላይታ፣ ጋምቤላው፣ ጉራጌው፣ አፋሩ፣ ስልጤው፣ ከምባታው፣ ሀዲያው እና ሌሎቹም የኢትዮጵያ ህዝቦች ሁሉ በባድመ ከአገሬ በፊት እኔን ብለው እንደወደቁ ከባድመ አፈር ጋር ተዋህደዋል።
”አንድ ኢትዮጵያዊ አባት እንዳሉት እኛ ስንኖር ሰዎች፣ ስናልፍ አፈር፣ ስናልፍ አገር እንሆናለን። የየትኛውንም ኢትዮጵያዊ ክቡር ስጋና ደም በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ አፈር ሆኖ ታገኙታላችሁ። ኢትዮጵያውያን ስንኖር ኢትዮጵያ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ እንሆናለን›› ሲሉ ነበር በርካቶቻችን ማንነታችን፣ እምነታችን፣ እሴታችን አንዳችን ከሌላችን ጋር ተሳሰረ ስለመሆኑ አበክረው የተናገሩት።
ኢትዮጵያ ማለት ውሃዊ ስሪት ነው። በውሃ ውስጥ ሃይድሮጂን እና ኦክሲጅን የተሰኙ ንጥረ ነገሮች ስሪት ነው። ነገር ግን ሃይድሮጅን ከኦክስጂን እንለይና ውሃ እናገኛለን ብለን ብንነሳ አስቸጋሪ ነው። ድምዳሜያችንም ሆነ አካሄዳችን ሌላ ውጤት ላይ ይወስደናል።
ይህ ማለት ኢትዮጵያዊ የሆነን አንድ ዜጋ በሃይማኖቱ፣ በብሄሩ ወይንም ደግሞ አንዱ መገለጫው ወስደን ከሌላው አካሉ ከሆነ ኢትዮጵያዊ ለመለየት ብንሞክር ኦክስጂን እና ሃይድሮጂንን ለየብቻ በመለየት ውሃ ለማግኘት እንደመመኘት ነው፤ አይሆንም፤ አይሳካም።
ኢትዮጵያዊነት ማለትም ልክ እንዲሁ ነው። አጋጣሚዎችን በመጠቀምና ሁኔታዎችን በመታከክ ኢትዮጵያዊነት ለመሸርሸር የሚደረጉ ሙከራዎችም ለጊዜያዊ ሆህታ ላይ አዋኪ ድምፅ ይሆናሉ እንጂ ውሃ የሚቋጥር አይሆንም።
የዛሬ ሃሳቤን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአንድ ወቅት የተናገሩትን በማስታወስ ለማቆም እገደዳለሁ። ‹‹ኢትዮጵያ የሁላችን አገር፤ የሁላችን ቤት ናት። በአንድ አገር ውስጥ የሀሳብ ልዩነቶች ይኖራሉ። የሀሳብ ልዩነት እርግማን አይደለም። ልዩነቱ እንዳለ ሆኖ መደማመጥና በመርህ ላይ ተመስርተን መግባባት ስንችል የሀሳብ ልዩነት በረከት ይዞልን ይመጣል። በሀሳብ ፍጭት ውስጥ መፍትሄ ይገኛል።
”በመተባበር ውስጥ ኃይል አለ። ስንደመር እንጠነክራለን። አንድነት የማይፈታው ችግር አይኖርም… አገር ይገነባል። የኔ ሐሳብ ካላሸነፈ ሞቼ እገኛለሁ ማለት ግን እንኳን አገርን ሊያቆም ቤተሰብን ያፈርሳለ። ያለችን ኢትዮጵያ ነች፤ ከየትኛውም የፖለቲካ አመለካከት በላይ አገራዊ አንድነት ይበልጣል። አንድነት ማለት ግን አንድ ዓይነትነት ማለት እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል። አንድነታችን ልዩነቶቻችንን ያቀፈ ብዝሃነታችንን በህብረ- ብሔራዊነት ያደመደቀ መሆን አለበት››
ሲጠቃለል የሰው ልጆች ነንና በአስተሳሰባችን፣ በአስተዳደጋችን፣ በመጣንበት ማህበረሰብ፣ የቀሰምነው እውቀት ብሎም በአነጋገራቻን እና በመሳሰሉት ነገሮች ልንለያይ እንችላለን። ግን ዋና መሠረቱና የሚያመሳስሉንና የሚያስተሳስሩን ነገሮች ላይ በችግሮችም ውስጥ ብንሆንም ኢትዮጵያ ማለት በቃ ኢትዮጵያ ናት። በማንም እና በምንም የማንተካት አገራችን መጠበቅ አለብን። ነገሮችን በተረጋጋ መንገድ መመልከት ይገባል።
እንደ አገር የምንግባባቸው ጉዳዮች የጋራ ጉዳይ ሲሆኑ ህዝባችን የተረጋጋ አገር እንዲኖረው ይፈልጋል። መብቱ እንዲከበር፤ ሉዓላዊነት ተከብሮ አገር ከፍ እንድትል፤ ዕድገት እንዲኖር፣ ፍትህ ማስፈን እና ልማት እንዲፋጠን ብሎም አገርን ተጠቃሚ ለማድረግ ሰላም እና ስክነት ያስፈልጋል።
በአገር ጉዳይ መተማመንና መተባበር ግዴታ ነው። ሠላም፤ አንድነትና የብሄራዊ መግባባት የአንድ አገር የጀርባ አጥንት ናቸው። በዚህ ላይ ፖለቲከኞች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ምዕምናን፣ ምሁራን እና ሌሎች አካላትም የተለያዩ አስተሳሰቦችን የሚያራምዱ ቢሆንም በአገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ይጠበቅባቸዋል። ሠላምን መስበክ፤ መስከን ለነገ ጉዞ መሰረት መጣል ነው። እንስከን።
ስክነት ያስፈልጋል። ስክነት ብስለት ነው፤ ብስለት ደግሞ የነገሮች መቋጫ ወይንም መፍትሄ ማማጫ ነው። ለመፍትሄው በደንብ ማማጥ አለብን። ምጡ የረዘመ ቢሆንም ለበጎ ከሆነ ዋጋ መክፈል ተገቢ ነው። በመሆኑም ነገሮችን በብስለትና ስክነት ማየት እንዲሁም ነገን አሻግሮ መመልከት ይገባል።
ዶክተር ጀኔኑስ
አዲስ ዘመን መጋቢት 2 ቀን 2015 ዓ.ም