25 ዓመት የአንድ ወጣት እድሜ ነው። አዎ እዚህ ለመድረስ ብዙ ዓመታትን ማለፍ ይጠይቃል። በእነዚህ ዓመታት ደግሞ ውጣ ውረዶችን ማየት ብሎም በእድሜ ሂደቱ የሚያመጡትን በጎና መጥፎ ነገሮችን መጋፈጥም የሚጠይቅ ነው። በሌላ በኩልም 25 ዓመት የሞላው አንድ ወጣት በኖረባቸው ዓመታት ባከናወናቸው ባለፋቸው መንገዶች ብዛት የተነሳ የሚጠበቁበትም በርካታ ውጤቶች መኖራቸው ግልጽ ነው። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ማደግ መማር ማወቅ መስራት አንዳንዴም ቤተሰብ መስርቶ ማስተዳደር ሊኖሩ ይችላሉ። ይህንን ማሳካት የቻለ ደግሞ እድሜውን በአግባቡ የተጠቀመ ወጣት ይባላል።
ለዚህ ሀሳባችን መነሻ የሆነን የ25 ዓመት የስራ ጊዜውን እያከበረ ያለው የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ጉዞ ነው። ማህበሩ ከዛሬ 25 ዓመት በፊት ሲመሰረት መነሻው የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ነው። በእነዚህ ዓመታት ወጣቶች በማህበራዊ በኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ላይ የነቃ ተሳትፎን እንዲያደርጉ ብሎም ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ስራዎችን ለመስራትም ያለመ ነበር ።
እኛም ይህ እቅዱ ምን ያህል ተሳክቷል? ስንል የማህበሩን ዋና ጸሀፊ ወጣት ይሁነኝ መሃመድ አነጋግረናል። ወጣቱ እንደሚለውም የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር የምስረታውን 25ተኛ ዓመት በዓል በማክበር ላይ ይገኛል። ማህበሩ ለመመስረቱ ዋና አላማው ደግሞ የወጣቶችን ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ከመንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ ለመፍታት ነው።
እንደ ወጣት ይሁነኝ ገለጻ ማህበሩ እነዚህን አላማዎቹንም በመላው ከተማዋ የሚገኙ ወጣቶች ተሰባስበው ይወክሉናል የእኛን ጥያቄ ሊያነሱ ይችላሉ ያሏቸውን ወጣቶች በነጻነት መርጠው በኢፌዴሪ በጎ አድራጎትና ማህበራት ኤጀንሲ ዘንድ አስመዝግበውና ፍቃድ አግኝተው ወደ ስራ ገብተዋል። ወደስራ ለመግባቱም ዋና አላማ አድርጎ የተነሳው የወጣቶችን ጥያቄዎች እንዲፈቱ ማድረግ ነበር።
እነዚህን እንቅስቃሴዎች ሲያደርግ በተለይም በወጣቶች ዘንድ ሊታይ የሚችል አበርክቶው ምንድን ነበር? ተብለው ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱም፤ ማህበሩ ከመመስረቱ በፊት በግለሰቦች አነሳሽነት ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እየተባሉ ችግሮች እየተለዩ ይሰራ ነበር እንጂ በትክክል ተለይቶ በመንግስት ደረጃ የወጣቶችን ችግር የሚፈታ ምንም ዓይነት ተቋም አልነበረም፤ በመሆኑም ማህበሩ መቋቋሙ በአገር ደረጃ የወጣቶች ፖሊሲ እንዲረቀቅ የራሱን አበርክቶ ያደረገ ሲሆን ከዛ ባሻገርም ወጣቶችን የሚመለከት እንደ ወጣቶችና ስፖርት߹ ባህልና ቱሪዝም የሚባሉ ተቋማት ወጣቶችን ማዕከል አድርገው እንዲመሰረቱም ያደረገ ስለመሆኑ ያብራራሉ።
ሌላው ወጣቶች ትርፍ ጊዜያቸውን በአልባሌ ቦታ እንዳያባክኑ በአንጻሩ ደግሞ አንድ ቦታ ላይ ቁጭ ብለው እውቀታቸውን ተሞክሮዎቻቸውን እየተለዋወጡ የሚውሉባቸው ቦታዎችን ለማዘጋጀት እቅድ በመያዝና የወጣቶችን ማዕከል ጎተራ አካባቢ በመገንባት ለወጣቶች አስረክቧል። በአሁኑ ወቅትም በመላው ከተማዋ ከ 116 ያላነሱ ማዕከላት ተገንብተው ለወጣቶች የተለያዩ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
ማህበሩ ወጣቶች በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ሰልጥነው ነገር ግን ወደስራ ያልገቡበትና ስራ በማጣት ምክንያት ወደተለያዩ አላስፈላጊ ድርጊቶች ውስጥ ሊገቡ የነበረበትን ሁኔታ ከኮካ ኮላ ጋር በመቀናጀት ኪዎስኮች እንዲከፈቱላቸው በማድረግ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ በማድረግ ተሞክሮ ከቀመረ በኋላ ጥቃቅንና አነስተኛ የሚባለው ተቋም እንዲቋቋም በማድረግ ወጣቶች ሼዶችን አግኝተው በሙያቸው ስራዎችን እንዲሰሩ በዛም እስከ ባለሀብትነት እንዲደርሱ በማስቻልም በኩል ሚናው ከፍ ያለ እንደነበር ይናገራል።
የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር አገራዊ ጉዳዮች ላይም የነቃ ተሳትፎን ያደርጋል ያለው ወጣት ይሁነኝ ለምሳሌ በአክሱም ሀውልት አስመላሽ ኮሚቴ ላይ እንደ አንድ ተቋም አባል ሆኖ ሲንቀሳቀስ የነበረ ነው።
ወጣቶች እንደ አገር የሚመጡ ጥሩም ይሁኑ መጥፎ ነገሮች ተጋላጭ የመሆን እድላቸው ሰፊ መሆኑን የሚናገረው ወጣት ይሁነኝ ማህበሩም በተለይም በ1997 ዓ.ም በነበረው ችግር ምክንያት በወጣቶች ላይ ይደርሱ የነበሩ እስሮችን ባሉበት ቦታ በመሄድ በመመልከት መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮችም እንዲታረሙ ለመንግስት በማመላከት በኩል የበኩሉን ስለመወጣቱ ይናገራል።
ወጣቶች በጤናውም ዘርፍ ላይ ትኩረት ማግኘት አለባቸው በማለትም ኤች አይ ቪ ኤድስ በወጣቱ ላይ የከፋ ጫናን እንዳያደርስ የመከላከያ መንገዶቹን ከማስተማር ጀምሮ እንደ ተስፋ ጎህ ያሉ በጉዳዩ ላይ የሚሰሩ ተቋማት ሲቋቋሙ በማገዝ የበኩሉን ተወጥቷል። በሌላ በኩልም የዛሬ ወጣቶች የነገ አረጋውያን የማይሆኑበት ምክንያት የለምና እንደ መቄዶንያ አይነት የአረጋውያን እንክብካቤ ማዕከላት ሲቋቋሙ ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን ስለመወጣቱ አብራርቷል።
አሁን ላይ በመላው አገራችን ተስፋፍቶ የሚገኘው የበጎ ፍቃድ እንቅስቃሴ አጀማመሩ በዋናነት በማህበሩ ነበር ያለው ወጣት ይሁነኝ በ1995 ዓ.ም ሃሳቡ ሲጠነሰስ ማህበሩ በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የሆኑ ወጣቶች በጋውን ተምረው ክረምት ለእረፍት ወደየመጡበት ሲሄዱ በበጎ ፍቃድ ታናናሾቻቸውን በእውቀት እንዲያግዙ የማድረግ ስራ በአዲስ አበባ ጀምሮ እስከ 2000 ዓ.ም የመሪነት ቦታውን ይዞ ቆይቷል። በነገራችን ላይ ወጣቶች በበጎ ፍቃድ እንዲሰሩ ሲደረግ የነበረው ይህ ብቻ አይደለም ይልቁንም በትራፊክ ማስተባበር߹ በደም ልገሳ በኤች አይ ቪ ትምህርት በመስጠት የአረጋውያንን ቤት በማደስና በሌሎችም ላይ ተሳትፎን እንዲያደርጉ ከፍ ያለ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሷል።
ይህ የማህበሩ ጅምር ደግሞ አሁን ላይ በመላ አገሪቱ ተስፋፍቶ ብዙ ባለቤት አግኝቷል፤ ወጣቶችም ያለማንም ጉትጎታ በሚችሉት አቅም ሁሉ በበጎ ፍቃደኝነት አገራቸውንን ህዝባቸውን ለማገዝ እየሰሩ ነው። ይህ እንግዲህ የማህበሩ የስራ ውጤት ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል በማለት ይገልጻል።
ወጣቶች በተለይም በመንግስታዊና በትልልቅ ተቋማት ላይ ሊኖራቸው የሚገባውን የመሪነት ስፍራ ላይ መንግስትም ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሊያስቡበት ይገባል በማለት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል፤ ይህ ሁኔታም አሁን ላይ ፍሬ አፍርቶ በርካታ ወጣቶች በትልልቅ የመንግስት የስራ ኃላፊነቶች ላይ እየታዩ ነው ብሏል።
ይህም ቢሰራ ዛሬም ድረስ የወጣቶች ጥያቄ ተፈቶ አላለቀም በርካታ ወጣቶች በአገራቸው ላይ ሰርቶ የመለወጥ ተስፋቸው ተሟጦ ስደትን እንደ ትልቅ አማራጭ እያዩት ነው፤ በዚህ ላይ እንደ ማህበር የተሄደበት ርቀት ምን ያህል ነው? ስል ላነሳሁላቸው ጥያቄ ሲመልሱም፤ “በየዘመኑ የወጣቶች ጥያቄ በተለያየ መልኩ ይነሳል እያደገም ይመጣል፤ አሁንም ያለው ሁኔታ በተለይም ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው ከወጡ በኋላ የስራ እድል የማግኘቱ ሁኔታ የጠበበ ነው፤ በሌላ በኩል የራሳቸው ፈጠራ ኖሯቸው እሱን እንኳን ወደተግባር ቀይረው በመስራትና በመለወጥ ሂደት ላይ እጥረቶች አሉ፤ እኛ እንደ ማህበር ስራን ፈጥረን የምንሰጥበት እድል የለንም ፤ ነገር ግን በወጣቶች በኩል ያሉ ክፍተቶችን ደፍነን ለስራ ዝግጁ የማድረግ ሁኔታ ይሰራል” ይላል።
ወጣት ይሁነኝ አክሎም ማህበሩ በአደረጃጀቱ ውስጥ የአቅም ግንባታና የኢኮኖሚ ዘርፍ አለው፤ በዚህ ውስጥ ደግሞ በዓመት ውስጥ ምን ያህል ወጣቶች የስራ እድል ሊፈጠርላቸው ይገባል? የሚለውን በመያዝ የአመለካከት ቀረጻ ላይ ስልጠና ይሰጣል፤ በፍላጎታቸው ከታችኛው የስራ እርከን ተነስተው ከፍ ወዳለው ደረጃ የሚደርሱበትን ሁኔታ በማስተማር ብቁ አድርገን በተለይም በአካባቢያቸው ያሉ ምቹ ሁኔታዎችን እንዲያዩ ተጨማሪ ነገሮችንም ከአዲስ አበባ ጥቃቅንና አነስተኛ ቢሮ ከአዲስ አበባ የስራ እድል ፈጠራ ተቋም ጋር እያገናኘን ብድር የሚመቻችበትን የመስሪያ ቦታ የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው የድጋፍ ደብዳቤ በመጻፍ ራሳችንም ተገኝተን በማወያየት የወጣቶችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በመደበኛነት የምንሰራው ስራችን ነው።
እንደ ማህበር ወጣቶች ስንል በጠቅላላው ወንዶችንም ሴቶችንም ያጠቃልላል፤ ነገር ግን ሴቶች ደግሞ ከወንድ በተለየ ሁኔታ ትኩረት ሊያገኙ ይገባቸዋል በማለት ከወረዳ ጀምሮ እስከ ከተማ ድረስ ሴቶችን በምን ያህል ደረጃ ተሳታፊ እያደረጋችሁ ነው የሚለውን እናያለን፤ በዚህም የሴቶች ተሳትፎ እንዲጠናከር ውክልናቸውም እንዲጎለብት ጥረት እናደርጋለን፤ በስብሰባዎቻችን በበጎ ፍቃድ በተግባሮቻችን የሴቶች ተሳትፎ እንዲጠናከር ውክልናቸው ከፍ እንዲል እናደርጋለን። እዚህ ላይ ግን ሴቶችን ብቻ ሳይሆን አካል ጉዳተኛ ወጣቶችም እንዲሳተፉ እናደርጋለን።
ይህ የወጣቶች ተሳትፎም ሆነ የማህበሩ ጥረት ግቡን ሊመታ የሚችለው አገር ሰላም ስትሆን ነው። በአገሪቱ ላይ ለአንድ ቀን የሚፈጠር ችግርን ለወጣቱ አንድ ዓመት ከህይወቱ ላይ ያጎላል። በመሆኑ ወጣቱ የአካባቢውን አልፎም የአገሩን ሰላም በመጠበቅ ውስጥ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ሊሆን ይገባል። በመሆኑም በሰላም መደፍረስ ትልቁ ተጎጂ ራሱ መሆኑን ተገንዝቦ ሰላሙን መጠበቅም በእጁ ያለ ነገር ነው እንደ ወጣት ይሁነኝ ገለጻ።
በየትኛውም ዓለም ያሉ ወጣቶች ለውጥ ይፈልጋሉ፤ አዲስ ነገር ይመኛሉ፤ የነበረው ነገር የማይጥመው ወይም ደግሞ የማይመቸው ብዙ ወጣት አለ፤ ለውጥ ይጠይቃል፤ ይህንን ተገቢነት ያለውን ጥያቄ በአልባሌ ሁኔታ ሊጠቀሙ የሚችሉ አካላት እንዳሉ ተገንዝቦ መጠቀሚያ እንዳያደርጉት ተጠንቅቆ ጥያቄውን መዝኖ ሁኔታዎችን አጥንቶ ማቅረብ እንዲችል ውይይቶች ይደረጋሉ። ከሚመለከታቸው አካላት ጋርም ወጣቶችን ወክለን ጥያቄዎችን እናቀርባለን። ከዛ ባሻገር ደግሞ የአካባቢው ዘብ ሆኖ እንዲቆም የማድረግ ስራም ይሰራል ይላል ወጣት ይሁነኝ።
“ ወጣቶች የእነሱን ጥያቄ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ሊጠቀሙ የሚችሉ አካላትን ተረድተው በምክንያታዊነት ጥያቄዎችን እንዲያቀርቡ በየጊዜው ውይይቶች ይዘጋጃሉ የሚነሱ ጉዳዮችንም ወጣቶችን በመወከል እንዲቀርቡ እናደርጋለን፤ ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ወጣቱ በንቃት ራሱንም አካባቢውንም እንዲጠብቅ ማድረግ የማህበሩ ትልቅ ስራ ነው። ይህም ባለፉት ጊዜያት አገር ችግር ላይ በነበረችበት ወቅት ተደራጅቶ አካባቢውን በመጠበቅ በኩል ያሳየው ሚና ለዚህ ተጠቃሽ ነው” ይላል ወጣት ይሁነኝ።
ማህበሩ እንደ ተቋም በክፍለ ከተሞች እንዲሁም ወረዳ ላይ ጽህፈት ቤቶችን ከፍቶ እቅድ አውጥቶ በዛ እየተመራ ስራውን የሚያከናውን ነው ያለው ወጣት ይሁነኝ ከዚህ አንጻርም በክፍለ ከተሞች አካባቢ የስራ እድል ተፈጠረ ሲባል በተጨባጭ ለምን ያህል ወጣቶች በምን ዘርፍ ተፈጠረ የሚለውን የምንገመግምበት አሰራር አለ፤ በዚህም በመንግስት ነው ወይስ በግል የሚለውን እናጠራለን ወጣቶቹ በምን መስፈርት ተመለመሉ የሚለውም ይታያል።
“ እንደ አገር የሰላምና ጸጥታ ችግር ሲፈጠር ጉልበት የሚጠይቁ የልማት ስራዎች ሲታሰቡ ወጣቶችን የመፈለግ ቅድሚያ የመስጠት ሁኔታ ይስተዋላል ነገር ግን አብቅቶ ኃላፊነት መስጠት ላይ እንዲሁም ለሚያነሳው ጥያቄ ዘላቂ የሆነ መልስን መስጠት ላይ የሚሰሩ ስራዎች አመርቂ አይደሉም። በሌላ በኩል ደግሞ አሁን ላይ የወጣቶች የስራ እድል ፍላጎት ጥናትን መሰረት አድርጎ የሚሰራ አይደለም። የላስቲክ ሱቅ በመስጠት የስራ እድል ፈጠርን በማለት ሪፖርት ይደረጋል፤ ይህ የተፈጠረው ነገር ግን ቋሚ ነው ጊዜያዊ የሚለው አይታይም፤ ይህ ደግም አሰራሩን ፍትሃዊ አያደርገውም። በመሆኑም መንግስት ማረም የሚገባውን ነገር ማረም የሚመለከታቸው አካላትም የሚሰሩትን ስራ ጥናት የተደገፈ ሊያደርጉት ይገባል” በማለት ወጣት ይሁነኝ ያብራራል።
ማህበሩ እስከ አሁንም ሲያደርግ እንደመጣው የቀጣይ እቅዱም የወጣቱን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው፤ የሚለው ወጣት ይሁነኝ ወጣቱ ሰላማዊ ጤናማ ብቁና ተተኪ በመሆን አገሩን የበለጸጉት አገራት የደረሱበት ደረጃ ላይ የሚያደርስ እንዲሆን አቅደን እንሰራለን።
በሌላ በኩልም የወጣቶችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የሚገባውን ቦታ እውቀትና የትምህርት እድል እንዲያገኝ ማድረግ ደግሞ የእቅዳችን አካል ነው።
“….ወጣቶች አቅሜ ክህሎቴ ምንድን ነው? የሚለውን ማየት ምን ብሰራስ ከራሴ አልፌ ለሌሎች እንዲሁም ለአገር ልጠቅም እችላለሁ ይህንን ለማድረግስ ምን ዓይነት ድጋፍ ከማን ማግኘት አለብኝ የሚለውን ነገር መመርመር ያስፈልገዋል” በማለት ወጣት ይሁነኝ ሀሳቡን አጠቃሏል።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን መጋቢት 1 ቀን 2015 ዓ.ም