-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ
የወላጅ ተስፋ ነገ በተባለች በልጆቹ የቀን ሰማይ ላይ ርቃ የተሰቀለች ዳቦ ናት። በአብራኩ ክፋይ መማር ላይ የዛሬን ፈተና የሚሻገር እልፍ ወላጅ አለ። አሳዳጊ ልጅን አስተምሮ ለወግ ለማብቃት የሚወጣው እልፍ ዳገት የሚወርደው የትዬለሌ ቁልቁለት አለው። በለጸግን የሚሉ ሀገራት ከእነሱ ያነሱት ላይ የሚኩራሩት በቁጥራቸው አለያም ባላቸው ጥሪት ሳይሆን በአፈሩዋቸው ምሁራን መሆኑን ማንም አያጣውም፡፡ ለዚህም ነው መማር ከልክ የሚልቅ መለኪያ ነው የሚባለው። ብቸኛ ባይሆንም የሀገርን ልዕልና ያስከብራል፡፡ መሠረት ጣይ ክዋኔም ነው፡፡
በዘመናችን ሰው በመሆን ልኬት ውስጥ መማር የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳልም። መማር በኩራት በአደባባይ አንገትን ቀና አድርጎ መቆሚያ ዘውድ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰው የእውቀት አድማሱን ሲያሰፋ ዓለምን ለእርሱ መኖሪያነት ምቹ ያደርጋታል፡፡ ለዚህ ደግሞ ተፈትኖ ማለፍ ግድ ነው፡፡ በፈተና ላይ ደግሞ ተፈታኝ፣ አላፊና ወዳቂ የማይቀሩ ነገሮች ናቸው። ፈተና ያወቀውን ካላወቀው፤ ብቁውን ካልበቃው አንጥሮ የሚለይ ወንፊትም ነው። በዚህም ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለማለፍ ከወንፊቱ ወጥቶ ማለፍ ግድ ነው፡፡ በተለይም የዘንድሮውን ፈተና ማለፍ እጅግ ብዙ ጥረትን የሚጠይቅ እንደሆነ ማንም ይረዳዋል፡፡ ምክንያቱም ኮሮና እና ጦርነት በብዙ መልኩ ሲያንገላታቸው ነው የቆዩት፡፡ ይህም ሆኖ እጅ ያልሰጡ ተማሪዎች እንደነበሩ በሀገር አቀፍ ሽልማቱ ላይ አይተናል፡፡
ከእነዚህ መካከል ተማሪ ሚኪያስ አዳነ አንዱ ሲሆን፤ የይሁኔ ወልዱ መታሰቢያ ደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪ ነው፡፡ ትምህርት ቤቱ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን ሲወስድ ለመጀመሪያ ጊዜው ሲሆን፤ ለውጤቱ የተማሪዎች ትጋት የመጀመሪያ ነበር። ምክንያቱም ቀጠናው የጦርነት በመሆኑ ለስድስት ወር ያህል ትምህርት መማር አልቻሉም። በኮሮና ምክንያትም እንዲሁ ግማሹን መንፈቀ ትምህርት ( ሴሚስተር ) አልተማሩም። ከዚህ በተጨማሪም ትምህርት ቤቱ ጥቃት ከደረሰባቸው መካከል ነው። እናም በያሉበት ቦታ እየተዟዟሩ ባያነቡ ኖሮ ለዚህ ድል አይበቁም ነበር፡፡
ተማሪ ሚኪያስ፤ መምህራኑና ትምህርት ቤታቸውም እጅግ ይመሰገናል፡፡ ምክንያቱም ጦርነቱ ፋታ ሲኖረው ግብዓቶችን በልመና ጭምር አሟልተው ተማሪዎችን ከያሉበት ሰብስበው ለማስተማር ይጥራሉ፡፡ ትምህርት ቤት እንኳን በማይመስል ውስጥ ተምረውም ለዚህ እንደበቁ ያነሳል፡፡ ሆኖም እውቀት መጨበጥ የአንድ ቀን ስራ ባለመሆኑ ሁሉም ተማሪዎች በከፍተኛ ውጤት እንዲያልፉ ሆነዋልም ይላል፡፡ ተማሪ ሚኪያስ በአመጣው ውጤት እጅግ ደስተኛ ነው፡፡ አሁን በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተገባላቸው ቃልም ከምንም በላይ አስደስቶታል፡፡ እውቅናው በራሱ ልዩ ትርጉም ሰጥቶታል፡፡ እናም የበለጠ ለመሥራት ተነስቷል፡፡ አሁን የገባው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፤ በአስትሮኖሚ ዘርፍ መማር እንደሚፈልግ ነግሮናል፡፡ ሰማይ የተደፋ ያህል ከባድ በመሰለው የውጤት ናዳ መሐል ብቅ ያለችው ሌላኛዋ ተማሪ መቅደላዊት እምሩም ናት፡፡ መቅደላዊት በኮተቤ ሳይንስ ሼር ካምፓስ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ስትሆን፤ ያመጣችው ውጤት ደግሞ 636 ነው፡፡ በዚህም ለሁለተኛ ጊዜ እውቅናን አግኝታለች፡፡ ላፕቶፕም ተሸልማለች። ከዚያ ባሻገር ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የውጪ የትምህርት እድል ከአገኙት መካከል ሆናለች።
እውቅና በሁሉም መልኩ ስኬታማነትን የሚያቀዳጅ ነው፡፡ በተለይም ለተማሪዎች ጥሩ ብርታት የሚሰጥ ነው፡፡ ትውውቅን ያጠነክራል፤ የበለጠ መስራትን ያመጣል፡፡ አሁን ያስመዘገብነው ውጤት ቁጥር ብቻ ሆኖ እንዳይቀርም አደራ የሚሰጠን ነው። አደራው ደግሞ ችግር ፈቺነታችንን እንድንለምድበት ያደርገናል ያለችን ደግሞ በተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት መስክ 645 ያመጣችው፤ ሽልማቱንና እውቅናው ለሁለተኛ ጊዜ ያገኘችው ተማሪ ሄዋን ጥላዬ ነች፡፡ የፈተናው በየጊዜው መራዘም ለውጤታማነቱ እንዳገዘውና በቂ የጥናት ጊዜን እንዳገኘበት የሚናገረው ሌላው ተሸላሚ ደግሞ ሄኖክ ሀብታሙ ነው፡፡ ያመጣው ውጤት 602 ሲሆን፤ ከተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ዘርፍ ነው፡፡ ሽልማቱ እጅግ የሚያነቃቃውና ለበለጠ ሥራ የሚያዘጋጀው እንደሆነ ያነሳል፡፡ ይህ ሽልማት ከሽልማትነቱ ባሻገር የውጪ የትምህርት እድልንም የሰጠኝ በመሆኑ ከምንም በላይ ተደስቼበታለሁ፡፡ በቀጣይ ሀገሬንም የማስጠራ እሆናለሁ፡፡ ማጥናት የምፈልገው የትምህርት ዘርፍ ጤና ላይ ነው፡፡ እናም ችግር ፈቺ እንደምሆን እምነት አለኝም ብሎናል፡፡
በየትኛውም ዘርፍ ላይ ጥሩ ውጤት ያስመዘገበ ማንኛውም አካል መሸለምና እውቅና ማግኘት ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም አርአያነቱና ትርፋማነቱ የትየለሌ ነው፡፡ ተማሪዎች፣ ቤተሰብ ማህበረሰብ ብሎም ሀገር ይኮራበታልና፡፡ በተለይም በዘንድሮው ሀገር አቀፍ ፈተና የመጣው ውጤት ሲታይ እጅግ የሚገርምና የሚያስደነግጥ ነው፡፡ ምክንያቱም እንደሀገር በመደበኛ ደረጃ ካስፈተኑ 2ሺ 959 ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ ያመጡና ተማሪዎቻቸውን ያሳለፉት 1ሺ798 ሲሆኑ፤ ምንም ያላሳለፉት ደግሞ 1ሺ161 ትምህርት ቤቶች ናቸው።ስለሆነም ሙሉ ለሙሉ ተማሪዎቻቸውን ያሳለፉ 20 የሚደርሱ ትምህርት ቤቶች እንደሀገር እውቅናን አግኝተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል ደግሞ የይሁኔ ወልዱ መታሰቢያ ደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት አንዱ ነው።
ከሰባት መቶ 666 ያህሉን መመለስ በቻለው በተማሪ ሚኪያስ አዳነ አማካኝነት የዘንድሮውን የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግቢያ ፈተና ትልቁን ውጤት በእጁ ጨብጧል። ከ20 በላይ የሚሆኑት የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ውጤትም ከ600 በላይ እንዲያመጡም አድርጓል፡፡ ስለዚህም እንደሀገር መመስገን ይገበሃል ተብሎ ሽልማቱን ተቀብሏል፡፡ ሀገር አቀፍ ሽልማቱ ላይ በመገኘት እውቅናውንና ሽልማቱን ለተማሪዎቹና ለትምህርት ቤቶቹ ያስረከቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ እናንተ በትምህርት ቆይታቸው የላቀ አድማጭ እና አስቀማጭ ናችሁ፡፡ መምህራኖቻቸው ያስተሟሯችሁን በትክክል ማየት የቻላችሁ፤ በአደመ ጣችሁት ልክ የሰራችሁና ለትምህርታችሁ ትኩረት የሰጣችሁ ናችሁ፡፡ በዚህም ሽልማትና እውቅና ብቻ ሳይሆን ከፍ ያለ ነገር ያስፈልጋቸዋል በማለት ለሁሉም የውጪ የትምህርት እድል መዘጋጀቱን አብስረዋቸዋል።
ለ273 የላቀ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግስት ሙሉ ወጪ የውጪ ትምህርት እድል እንደተሰጣቸው ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ተማሪዎቹ እጅግ ዘመናዊ በሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ ጠቁመዋል፡፡ ለተማሪዎቹ የተሰጣቸውን ፈተና በአግባቡ መስራት በመቻላቸው ኢትዮጵያን የሚያግዙ 273 ተማሪዎች ተገኝተዋል በማለት እርሳቸውም ደስተኛ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ ለኢትዮጵያ እና አፍሪካ የሚደርሱ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የማድመጥና የአስቀማጭነት አቅማችሁን ተጠቅማችሁ ነገሮችን ወደ እውቀት በመቀየር ተጠቀሙበት በማለት ለተማሪዎች የመከሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በቀጣይ በሚኖራችሁ የትምህርት ቆይታም እውቀትን ብቻ ሳይሆን ጥበብን አብዝታችሁ የምትፈልጉ መሆን ይኖርባችኋል። ምክንያቱም ጥበብን የያዘ ሰው ሁልጊዜ ያሸንፋል። የተሻሉትን ያያል፤ ለሌሎችም መትረፍ ይችላል፡፡ ሀገሩን ለመለወጥም ጊዜ አይወስድበትም፡፡ ስለሆነም ለእውነትና ለእውቀት መቆም ይኖርባቸዋል በማለት አሳስበዋል፡፡ “ አሁን ያለነው በትውልዶች ግንባታ ላይ ነው፤ ያለፈው ትውልድ አልፏል፡፡ አሁን ያለው ትውልድም አነሰም በዛም ለሀገሩ እየለፋ ነው፤ እናንተ ግን ገና ከምንጩ ለሀገራችሁ የምትጠቅሙ እንድትሆኑ ከሰፈራችሁ ወጣ ብላችሁ ለሀገር እንድታስቡና ቀድሞ የነበሩ ስመጥር ኢትዮጵያውያን ምሁራን ከእናንተ ውስጥም እንዲወጡ አደራ እንላችኋለን” በማለትም ተማሪዎችም ሆኑ ቤተሰቦች ለሀገራቸው ከዚህ በላይ እንዲለፉ ጠይቀዋል፡፡
እናንተ ስትጠየቁም ከተጠየቀበት አውጥታችሁ ማሳየት የቻላችሁ ናችሁ፡፡ ክፍል ውስጥ ስትሆኑ በዚያ መኖራችሁን፤ መጽሐፍ ስታነቡም እንዲሁ ከመጽሐፉ ጋር ያላችሁና የማትረበሹ መሆናችሁን አረጋግጣችኋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፤ ትምህርት ቤቶቻቸውንም፤ መምህራኖቻቸውንም አመስግነዋል። በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ እንደ መንግስትና ትምህርት ሚኒስቴር የተጀመረው ለውጥ የፈተናዎችን ቅቡልነት ማረጋገጥ ላይ ነው፡፡ ነገር ግን ሥራው መሆን ያለበት በሁሉም መስኮች የሚስተዋሉ የትምህርት ስብራቶችን መጠገንና በሁሉም መመዘኛ ብቁ ማድረግ ነው፡፡ ብቁ የሆኑ ተማሪዎችንና ጠንካራ ዜጎችን መፍጠርም ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዘወትር ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡
የዛሬው የዕውቅና መርሀ ግብር በነበራቸው ያልተቋረጠ ጥረት ውጤታማ የሆኑ ተማሪዎችን በማበረታታት ሌሎች ተማሪዎች ላይ ከፍተኛ መነቃቃትን እና መንፈሳዊ ቅናትን መፍጠር ነው። ለውጤቱ መምጣት ኃላፊነታቸውን ለተወጡ መምህራን ወላጆችና በየደረጃው ለሚገኙ ባለድርሻ አካላት ምስጋናም የሚሰጥ ነው፡፡ ምክንያቱም በዚህ የለውጥ ሂደት ተጠቃሚውም ተጎጂውም ህብረተሰቡ ነው፡፡ ብቁ ተማሪዎችን የመፍጠሩ ሂደትና የትምህርት ጥራትን የማረጋገጥ ስራ ተጠናክሮ ከቀጠለ ተጠቃሚውን ማስፋት ይቻላል፡፡ ማህበረሰቡ በልጆቹ እንዲኮራና ሀገርም እንድታድግ ይሆናል በማለት በፈተናው ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎችን አመስግነዋል፡፡
እውቅና የተሰጣቸው ተማሪዎች በተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት መስክ ከ700 ድምር ውጤት ከ600 በላይ ያመጡ 263 ተማሪዎች እና በማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት ዘርፍ ከ600 ድምር ውጤት ከ500 በላይ ያመጡ 10 ተማሪዎች መሆናቸው በሽልማቱ ወቅት የተጠቀሰ ሲሆን፤ ለሁሉም ተማሪዎች ላፕቶፕ ተበርክቶላቸዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በከተማዋ የላቀ ውጤት ያመጡ ተማሪዎችን በሸለመበት ጊዜ እንዳሉትም፤ በ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከተፈተኑ ተማሪዎች መካከል 20 በመቶ ያህል ተማሪዎች 50 እና ከዚያ በላይ አምጥተዋል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡ 20 ትምህርት ቤቶች መካከል አስሩ አዲስ አበባ የሚገኙ ናቸው፡፡
ህይወት የተሟላ ትርጉም የሚሰጠው መኖራችን በትውልድ ላይ ትርጉም ያለው ተጨባጭ ለውጥ ሲፈጥር ብቻ ነው፡፡ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ ተጨባጭ አስተሳሰብ ፣ የአኗኗርና የአሰራር ስርዓት ለውጥ ደግሞ የሚመጣው እንደነዚህ የነጠሩ ተማሪዎችን ስንፈጥር ነውና ይህ ቅቡልነት ያለው አሰራር የዛሬ ብቻ ሳይሆን የነገም ባለራዕዮች የሚፈጠሩበት ይሁን በማለት ለዛሬ የያዝነውን አበቃን፡፡
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ም