የኢትዮጵያውያን አንድነት መገለጫ እና የኅብረታቸው ልዩ ተምሳሌት ነው፤ የዓድዋ ድል ። ኢትዮጵያውያን የዓድዋን ድል የተቀዳጁት የመሪያቸውን የንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ምኒልክን ጥሪ ተቀብለው በአንድትነት እንደ አንድ ሰው ሆነው በመፋለማቸው ነው።
የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን የቅኝ ግዛት አሳቢዎችን ድል የነሱበት ብቻ አይደለም ። የይቻላል መንፈስን በመላ ዓለም በሚኖሩ ጥቁር ሕዝቦች ዘንድ በማስረጹም ይታወቃል ። አፍሪካውያን ቅኝ አገዛዝን አሻፈረኝ ብለው ይታገሉ በነበረበት ወቅት የዓድዋ ድል ትልቅ አቅም ሆኗቸዋል ። በተለይ በፓንአፍሪካኒዝም ንቀናቄያቸው የበለጠ እንዲንቀሳቀሱ ምቹ ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል ። እናም ድሉ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን በቅኝ ግዛት ስር ሲማቅቁ የነበሩ የአፍሪካ ሕዝቦችም ጭምር ነው፡፡
በኋላ ቀር የጦር መሳሪያዎች ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀን የጣልያን ሰራዊት ድል ማድረግ የተቻለበትና ይህን በመላ ዓለም ጭምር ታላቅ ዜና ሆኖ የወጣበትና ኢትዮጵያ ይበልጥ እንድትታወቅ ያደረገ ድል መሆኑን የታሪክ ድርሳናት ያስገነዝባሉ፡፡
ኢትዮጵያውያን ይህን ታሪክ በየአመቱ በተለያዩ መንገዶች ሲዘክሩት ኖረዋል፤ እየዘከሩትም ይገኛሉ። ድሉ በአደባባይ፣ በውይይት፣ በኤግዚቢሽንና በመሳሰሉት ይዘከራል ። የዓድዋን ድል የሚዘክሩ አንዳንድ ስያሜዎች ቢኖሩን፣ የተለያዩ ወገኖች ዓድዋን የሚዘክሩ ተቋማት፣ መሠረተ ልማቶች፣ ወዘተ በበቂ ሁኔታ እንደሌሉ ሲያመልክቱ፣ ድሉን የሚመጥኑ መዘከሪያዎች መገንባት መሰየም እንዳለባቸው ሲያሳስቡ ኖረዋል ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለእዚህ የዜጎች ጥያቄ መልስ ሊሰጥ፤ የዓድዋን ድልም በሚገባ ይዘክረዋል ያለውን አንድ ግዙፍ ፕሮጀክት በከተማዋ እምብርት ፒያሳ ላይ እየገነባ መሆኑ ይታወቃል። ይህ የዓድዋ ድል እንዲመዘገብ ጉልህ ድርሻ ያበረከተውን የኢትዮጵያውያንን የአንድነት ስሜት፣ ተጋድሎ፣ ጀግኖችንና የመሳሰሉትን ሊዘክር የሚችል ፕሮጀክት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ታላላቅ ፕሮጀክቶች ጽሕፈት ቤት አማካይነት ነው እየተገነባ ያለው። ፕሮጀክቱ የዓድዋ ሙዚየምን ጨምሮ በርካታ አገልግሎቶችን ሊሰጡ የሚችሉ ግንባታዎች የተካተቱበት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ግንባታው 78 ነጥብ 2 በመቶ ደርሷል፡፡
ከፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ የተገኙ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የዓድዋ ሙዚየም ግንባታ ፕሮጀክት በከተማዋ አስተዳደር እየተገነቡ ካሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል ። ፕሮጀክቱ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉና እርስ በእርሳቸው የተሰናሰሉ 11 ሕንፃዎች ተካተውበታል ።
የአዲስ አበባ ከተማ የታላላቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ደቦ ቱንካ እንደሚሉት፤ የፕሮጀክቱ ግንባታ በ2012 ዓ.ም ነው የተጀመረው ። በሦስት ነጥብ ሦስት ሄክታር መሬት ላይ ያረፈና በአራት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር በጀት እየተገነባ ያለው ነው።
ፕሮጀክቱ ‹‹ዓድዋ ዜሮ ዜሮ ሙዚየም ፕሮጀክት›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፤ ሥራ አስኪያጁ ስለስያሜው ሲያብራሩም፡- ፕሮጀክቱ በእዚህ ስያሜ እንዲጠራ የተደረገው ፕሮጀክቱ እየተገነባ ያለበት የመሃል ፒያሳ ስፍራ ወደ ሁሉም ቦታ ለመሄድ መነሻ ነው ። የኢትዮጵያ እምብርት እንደመሆኑ ወደተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚደረጉ ጉዞዎች ከዚህ ቦታ ይጀምራሉ ። የዓድዋ ጉዞም ከዚሁ ቦታ ነው የተጀመረው ። ኢትዮጵያውያን ከየአቅጣጫው በመትመም አሁን ፕሮጀክቱ እየተገነባ ባለበት ቦታ ላይ ተሰባስበው፣ ነጋሪት ተጎስሞ ወደ ጦር ግንባር የዘመቱበት የመነሻ ቦታ በመሆኑም ነው ስያሜው የተሰጠው» ብለዋል ።
ኢንጂነር ደቦ እንዳሉት፤ ግንባታው የተለያዩ ክፍሎችን አካቷል፤ የዓድዋ ተራሮችን የሚያሳዩ ቅርጾች ይኖሩታል፤ በጦርነቱ ወቅት ወደ ዓድዋ የተደረገውን አስቸጋሪ ጉዞ ለማሳየት በፕሮጀክቱ ላይ ረጅም ደረጃዎች እንዲኖሩት ተደርጓል፤ መግቢያ በሩ ላይ የኢትዮጵያውያን ጀግንነት ማሳያ የሆኑት የጋሻና ጦር ምልክቶች እንዲኖሩት ተደርጓል ።
በውስጡ በርካታ ጋላሪዎች፣ መሰብሰቢያ አዳራሾች፣ ቅርስ ማሳያዎች እና የቱሪስት መስህብ ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችም ተካተዋል ። በፕሮጀክቱ ውስጥ ነጋሪት ቅርጽ ያለው ክፍል ያለ ሲሆን፣ ነጋሪቱ ላይ ደግሞ በጦርነት የተሰዉ ሰማዕታት ምስል ይደረግበታል ።
በሌላ በኩል የውሃ ገንዳዎች የሚመስሉ ግንባታዎች ያሉት ሲሆን፤ በዚህም ላይ ጠላትን እንዴት ውሃ በመከላከል ማሸነፍ እንደሚቻል የሚያሳዩ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ይቀመጣሉ ። ይህም በተለይ በጦርነቱ ላይ ለጣሊያኖች ውሃ እንዳይደርስ ውሃውን በማቋረጥ ትልቅ ሚና የተጫወቱትን እቴጌ ጣይቱን የሚያስታውስ ይሆናል ሲሉ ኢንጂነር ደቦ ጠቁመዋል፡፡
‹‹የዓድዋ ድል የጥቁር ሕዝቦች ኩራት ነው፤ በየትኛውም ዓለም ያለ ጥቁር የሚኮራበት ። ጥቁር ማሸነፍ ይችላል፤ የማሸነፍ አቅም አለው ። ጥቁር ብልህ እንደሆነ ያሳየ ድል ነው የሚሉት ኢንጂነር ደቦ፤ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ይበልጥ እንዲቀጣጠልም ሆነ የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ህብረትን የመመስረት እንቅስቃሴዎች እንዲጀመሩ መሠረት የሆነው የዓድዋ ድል መሆኑን ጠቅሰዋል ። ይህንን ትልቅ ታሪክ የሰሩ የጦር መሪዎችን የሚያሳዩ ምስሎች በሙዚየሙ እንደሚካተቱ ጠቁመዋል፡፡
የጽሕፈት ቤቱ የኮንትራት አስተዳደር ዳይሬክተር ኢንጂነር ዳዊት ጥበቡ እንደሚሉት፤ ፕሮጀክቱ በዋናነት የዓድዋ ሙዚየም ሆኖ የሚያገለግል ነው ። በወቅቱ የነበረውን ታሪክ የሚገልጽ፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ያለውን ታሪክ ሊገልጽ እንዲሁም የወደፊት ተስፋን ሊያሳይ በሚችል መልኩ እየተገነባ ይገኛል፡፡
ፕሮጀክቱ የዓድዋ ድል ታሪክ በሚገባ እንዲዳሰስ እና እንዲታይ አድርጎ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው የገለጹት ኢንጂነር ዳዊት፣ በውስጡ የዓድዋ ታሪክን የሚዘክሩ የተለያዩ እውነቶች እንዲኖሩት መደረጉንም ነው ያመለከቱት። ኢትዮጵያውያን ስለ ታሪካቸው የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ከማስቻሉ ባሻገር፣ ሌሎች አፍሪካውያን ወንድሞች ኢትዮጵያ ለጥቁሮች ነፃነት ያበረከተችውን አስተዋጽኦ የበለጠ እንዲገነዘቡ ለማድረግ ይጠቅማል ብለዋል ።
ኢንጂነሩ ፕሮጀክቱ የሚገነባበት ቦታ ፒያሳ መሆኑን በመጥቀስም፣ የዓድዋን ድል ከመዘከር ባሻገር የፒያሳን መልክ የሚያሳይ እንዲሆን ብዙ ጥረት መደረጉንም ጠቁመዋል ። የፒያሳ መገለጫ የሆኑ የኪነ ሕንፃ ሥራዎች በውስጡ መካተታቸውን፣ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የአዲስ አበባን በተለይም የፒያሳን ውበት በእጅጉ ይጨምራል ተብሎ እንደሚታሰብም ነው ያብራሩት፡፡
በጦርነት ሴቶች ያደረጉትን ተሳትፎ የሚየሳዩ የኪነ ጥበብ ሥራዎች እንደሚኖሩትም ገልጸው፣ ከክተት አዋጁ፣ ከነጋሪት ጉሰማው አንስቶ ጦርነቱ እስኪያበቃ ድረስ የነበረውን ሁኔታ የሚያመላክት እንደሚሆንም ተናግረዋል ። ስንቅ ከማቀበል ጀምሮ እስከ ጦር መምራት ደረጃ ያሉትን የሴቶች ተሳትፎዎች፣ ጀግኖችን፣ ሰማዕታትን የሚዘክር፣ በዓድዋ ድል ወቅት የተከናወኑ የተለያዩ ኩነቶችን የሚገልጽ ፕሮጀክት መሆኑንም አስታውቀዋል ።
ኢንጂነር ዳዊት እንዳብራሩት፤ የተለያየ ሙያ ያላቸው ሰዎች በፕሮጀክቱ እየተሳተፉ ይገኛሉ፤ ሁሉም በእውቀታቸውና በሙያቸው አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ ። የታሪክና የኪነ ሕንፃ ባለሙያዎች፣ የአርክቴክቶች ማህበር፣ የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር በፕሮጀክቱ በመሳተፍ ላይ ናቸው ።
ፕሮጀክቱ በዓድዋ ጦርነት ወቅት ኢትዮጵያውያን ለነፃነታቸው እና ለሉዓላዊነታቸው ያሳዩትን ትብብር በሚያመለክት መልኩ እየተገነባ ይገኛል። ዛሬም ኢትዮጵያ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ናት ። ከችግሮቿ ለመሻገር የሁሉንም ዜጋ ትብብር ትሻለች ። ሁሉም በሙያው፣ በእውቀቱ፣ በገንዘቡ፣ በጉልበቱ ለአገሩ መሥራት አለበት። ሙዚየሙ በዓድዋ ወቅት የነበረውን ዓይነት ትብብር እና ህብረት የሚፈልጉ በርካታ ችግሮችን ለማሸነፍ መልእክት የሚተላለፍበት መሆኑም ተጠቁሟል።
ኢንጂነር ዳዊት እንዳስታወቁት፤ ፕሮጀክቱ አንድ ሺ መኪና ማቆም የሚችል ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ እንዲኖረው ተደርጓል፤ ይህም በአካባቢው የሚስተዋለውን የመኪና ማቆሚያ ችግር ለመቅረፍ ሁነኛ መፍትሄ ይሆናል ። የመኪና ባለቤቶች መኪናቸውን በመንገድ ዳር በማቆም ለትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት እንዳይሆኑ መፍትሄ በመሆን ያገለግላል ። በከተማው ያለውን የትራፊክ ፍሰት ከማሳለጥ ባሻገር ለደንበኞች ንብረት ደህንነት መጠበቅ፤ ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ጉልህ ሚና ይጫወታል ። ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉትና በአጠቃላይ ለከተማዋ ገጽታ ትልቅ ፋይዳ ያለው ፕሮጀክት ነው ።
የፕሮጀክቱ ግንባታ ጃንግ ሱ በተባለ የቻይና ተቋራጭ እየተካሄደ ይገኛል ። የኢትዮጵያ ግንባታ ዲዛይንና ቁጥጥር ድርጅት ደግሞ የማማከር ሥራውን ያካሂዳል ።
በፕሮጀክቱ ላይ ዘመኑ የደረሰባቸው አዳዲስ የግንባታ ቴክኖሎጂዎች እና ሀሳቦች ተግባራዊ የተደረጉበት ሲሆን፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች እየተሳተፉ ያሉበት እንደመሆኑ የእውቀት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር እንደሚያፋጥን ተስፋ የተጣለበት ሲሉ ኢንጂነር ዳዊት ተናግረዋል ።
የፕሮጀክቱ ግንባታ በአሁኑ ወቅት 78 ነጥብ 2 በመቶ ላይ ደርሷል፤ ይጠናቃቃል ተብሎ ከተቀመጠለት ጊዜ በላይ መፍጀቱም ተጠቁሟል ። የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ደቦ ቱንካ ፕሮጀክቱ ሊጓተት የቻለበትንም ምክንያት ሲያብራሩ፤ «የፕሮጀክቱ ዲዛይን እና ግንባታ ሥራ አንድ ላይ የሚሄድ ነው ። ዲዛይን እና ግንባታው አንድ ላይ በሚሆንበት ጊዜ የዲዛይኑ ሥራ በየጊዜው ተጠንቶና ተቀምሮ አንድ ላይ መቀመጥ አለበት ። በፊት አንድ ፕሮጀክት ግንባታ ከመጀመሩ በፊት ጥናቱና ዲዛይኑ ከተጠናቀቀ በኋላ ነው ወደ ሥራ የሚገባው፤ አሁን ግን ዲዛይኑ የኮንትራቱ አካል ነው ። የፕሮጀክቱ ግንባታ እንዲጓተት አንዱ ምክንያት ይሄ ነው» ብለዋል ፡፡
እንደ ኢንጂነር ደቦ ማብራሪያ፤ ፕሮጀክቱ እንደ ሌሎች የግንባታ ፕሮጀክቶች የሚገነባ አይደለም። መጀመሪያ ዲዛይኑ ላይ መግባባት፣ ዲዛይኖቹ በሚሠሩበት ወቅት የተዛባ ታሪክን እንዳያመጡ ጥንቃቄ ማድረግን ይፈልጋል ። የብዙ ባለድርሻ አካላት ይሁንታን ማግኘት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ ። ከባለድርሻ አካላቱ ይሁንታ ሲያገኝ ነው ዲዛይኑ መሬት ላይ እንዲሠራ የሚደረገው ። በመሆኑም ጥናትና ዲዛይን ብዙ ጊዜ ሊፈጅ ችሏል ።
በጥናትና ዲዛይን ጊዜ ደግሞ ኮቪድ 19 ተጨማሪ ተግዳሮት ሆኖ እንደነበር አስታውሰው፣ በወቅቱ በአብዛኛው እንቅስቃሴ እንዳልነበረም ተናግረዋል። ያ ወቅት ከውጭ የሚገቡ ግብዓቶችን ለማስገባት አስቸጋሪ እንደነበረ፣ ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ ውስጥ የነበረው አጠቃላይ ሁኔታም ግንባታው ላይ የራሱን ጫና ማሳደሩን ጠቅሰው፣ ይህ ሁሉ የፕሮጀክቱ ግንባታ እንዲጓተት ምክንያቶች መሆናቸውን አስታውቀዋል ።
ፕሮጀክቱ የተወሰነ መዘግየት ቢገጥመውም፣ ከባባድ የሚባሉ የኤሌክትሮ መካኒካል፣ የሳኒተሪ፣ እንዲሁም ኤሌክትሪካል ኢንስታሌሽን ሥራዎች ተጠናቀዋል ያሉት ኢንጂነር ደቦ፤ በተለያዩ ምክንያቶች የባከነውን ጊዜ በማካካስ በሚቀጥለው ዓመት ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ እና ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ የሚያስችለው አብዛኛው ዝግጅት ተጠናቋል ። ፕሮጀክትን በጊዜ ለማጠናቀቅ ዋናው ግብዓት ነው፤ ግብዓቶች ተመርተው፣ ተጓጉዘው፤ ለመገጠም ዝግጁ ናቸው። በአሁኑ ወቅት ከ100 በላይ ኮንቴይነሮች ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ይዘው ከውጭ ገብተዋል። ከ50ሺ ካሬ በላይ የሚሸፍን ሴራሚክ ገብቷል። ሙሉ በሙሉ መሥራት የሚቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል ። ፕሮጀክቱን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ከተማ አስተዳደሩ እና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በየጊዜው ጉብኝት እያደረጉ ናቸው ።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን የካቲት 25 ቀን 2015 ዓ.ም