ወጣት አበባው ክንዴ የእጅና የእግር ጉዳተኛ ነው። እጆቹ በተፈጥሮ የተጎዱ ቢሆንም እንደማንኛውም ወጣት በተሽከርካሪ ወንበር ላይ ቁጭ ብሎ ከመጻፍና ያሰበውን ከማሳካት አላገደውም ። በእግሩ ጉዳት ምክንያት ሙሉ በሙሉ ወንበር ላይ ተመቻችቶ መቀመጥ ባይችልም እንግዳ ሲመጣ እመር ብሎ በመነሳት ትህትና በተላበሰ መንገድ መስተንግዶ ሲሰጥ ይውላል ።
አበባው ዕድሜው በወጣትነት ክልል ውስጥ ነው ። አካል ጉዳተኝነቱ ሳይበግረው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከማኔጅመንት ትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ዲግሪውን በ2013 ዓ.ም በመያዝ ወዲያው ምንም ጊዜ ሳያባክን የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቱን ቀጥሎም ዘንድሮ የሚመረቅበትን ፔፐር ሰርቶ አጠናቅቋል ። ወደ ስራ የተሰማራው የመጀመሪያ ዲግሪውን እንደያዘ ሲሆን የሁለተኛ ዲግሪ ማኔጅመንት ፋይናንስ ትምህርቱን ደግሞ ሥራውን እየሰራ በማታው ክፍለ ጊዜ ነው ሲከታተል የቆየው ። በተለይ በመደበኛው የቀን ክፍለ ጊዜ የስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪ በነበረበት ወቅት አንዲት ወጣት ያቀረበችለትን የፍቅር ጥያቄ ተከትሎ ፍቅር ውስጥም የገባበት አጋጣሚ እንደነበር ይናገራል ።
ወጣቱ አሁን ላይ በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን የሰው ሀብት አስተዳደር ኃላፊ ሆኖ በመሥራት ላይ ይገኛል ። ‹‹ምነው እዚህ ደረጃ ላይ ስደርስ በሕይወት በኖረችልኝና የፈለገችውን እያደረኩላት ብንከባከባት›› የሚላቸውና በአካሉ ጉዳት አስታዋሽ አጥቶ ከተደበቀበት ጓዳ አውጥተው ትምህርት ቤት በማስገባት እዚህ ያደረሱት አያቱ ዛሬ በሕይወት ባለመኖራቸው አብዝቶ ቢቆጭም የቀረው የምትወደውንና የሚወዳትን ቆንጆ ልጃገረድ አግብቶ ጎጆ መውጣትና ቤተሰብ መመስረት እንደሆነም በራስ መተማመን መንፈስ ይናገራል ። መጨረሻ የለውም የሚባለውን ትምህርትም ከትዳር ሕይወቱ ጎን ከሁለተኛ ዲግሪ በመቀጠል እስከ ዶክትሬትና በላይ የማዝለቅ ዕቅድ እንዳለውም ይናገራል ።
ወጣቱ አሁን የደረሰበትን ደረጃ ‹‹ስኬታማ ነኝ አካል ጉዳተኛ መሆኔ ከምንም ነገር አልገደበኝ›› ሲል በአንደበቱ ይገልፀዋል ። ‹‹ብዙ ሰዎች አካል ጉዳተኞች ፍቅር የማይዘን፤ቆንጆ የመምረጥ መብት የሌለን ፤ሚስት ማግባትና ልጅ ወልደን ቤተሰብ በመመስረት የምንመራ አይመስላቸውም››የሚለው ወጣቱ፤ ለፍቅርና ለትዳር ከፈቀዳትና ከፈቀደችው ቆንጅዬ ልጃገረድ ጋር ትዳር በመመስረት ልጅ ወልዶ በተመቻቸ ሁኔታ የመኖር ዕቅድ እንዳለውም ያወሳል ።
የስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበርኩበት ወቅት ከአንዲት ተማሪ ድብን ያለ ፍቅር ይዞኝ ነበርም ይላል ወጣት አበባው ። የፍቅር ጥያቄ አቅራቢዋ ልጅቱ በመሆኗ የአካል ጉዳተኞች ጉዳተኛ ባልሆኑ የጾታ አጋሮቻቸው መፈለጋቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ ለማረጋገጥ በቅቶ የነበረበትን እና የልጅቱን ጥያቄ በበጎ ተመልክቶ አፋጣኝ ምላሽ መስጠቱን ያስታውሳል ።
ወጣት አበባው ክንዴ እንዳወጋን ተወልዶ ያደገው በአማራ ክልል ሰከላ በምትባል የገጠር ወረዳ ነው ። የእጅና የእግር አካል ጉዳቱ የስምንት ዓመት ልጀ ሆኖ እንደደደረሰበትም ያወሳል ። እንደነገረን የስምንት ዓመት ልጅ ሳለ ከ12 ዓመት ዕድሜ ጓደኛው ጋር መንገድ ላይ አባሮሽ ይጫወታሉ ። በዚህ ጨዋታ መካከል ከ12 ዓመቱ ጓደኛው ጋር ይጋጫሉ ። በጨዋታ መካከል ልጆች በተደጋጋሚ መጣላታቸው አዲስ ባይሆንም ብድግ አድርጎ ይወረውርና ይጥለዋል ። ‹‹መታው እባላለሁ› ብሎም የወደቀበት ጥሎት እየሮጠ ወደ ቤቱ ይሄዳል ። ወጣት አበባው ለመነሳት ቢሞክርም ይሳነዋል ። መንገድ ላይ መውደቁን ያየ ጎረቤት ለእናቱ እስኪነግሯቸው እስከ 11 ሰዓት ድረስም ከዛው ከወደቀበት ሳይነሳ ይቀራል ።
‹‹11 ሰዓት ላይ እናቴ ጎረቤቶቻችን መንገድ ላይ መውደቄን ነግረዋት እያለቀሰች መጣች›› ይላል ። ይሄንኑም የሰማው በኋላ ላይ ከእናቱ መሆኑን ያከለልን ወጣቱ፤ በወቅቱ ራሱን ስቶና በላብ ተጠምቆ እናቱ ያገኙት መሆኑንም አጫውቶናል ። ሆኖም እናቱ አንስተው በማዘል ወደ ቤት ቢወስዱትም ውሎ ሲያድር እንደ ፊቱ በሁለት እግሩ መሄድና መቆም አልቻለም ። በእጆቹም ከመመገብ ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎችን መሥራት ተሳናቸው ። ይሄ የሆነው የአካል ክፍሎቹ ነርቮች በወደቀበት ወቅት ተጎድተው በመዋላቸው እንደሆነም በኋላ የህክምና ባለሙያዎች እንደነገሩት ያወሳል ። ቀስ በቀስም የእጅና እግሮቹ የመታጠፊያ ሥሮች የመጨማደድ፤እንዲሁም የመሰብሰብ ባህሪ እያመጡ መጡ ። በተለይ ሁለት እጆቹ ላይ የበቀሉት ጣቶቹ ሙሉ በሙሉ ቅርፃቸውን በማጣት ተሰበሰቡ ። ጣቶቹ ብቻ ሳይሆኑ እጆቹም አጠሩ ።
‹‹ይሄ የደረሰብኝ ጉዳት እያሳፈረኝና እያሸማቀቀኝ እንኳን የውጪ ሰው የራሴ ወንድምና እህቶቼ እንዲያዩኝ አልፈቅድም ነበር ። ጓዳ ውስጥ ገብቼ በመደበቅ ለብቻዬ እቀመጥ ነበር››ሲል በጉዳቱ የደረሰበትን መሸማቀቅና በራስ ያለመተማመን ስሜት ሁኔታን ያስታውሰዋል ። ወላጆቹም ሆኑ እህት ወንድሞቹ ፊቱን እንዳያዩት ስለሚፈልግ ጓዳ መግባት ብቻ ሳይሆን አልጋ ስር ገብቶ ተደብቆ የሚቀመጥበት ሁኔታምእንደነበር ያወሳል ።
ባደገበት አካባቢ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች የሚማሩበት ‹‹ጎለን›› የተሰኘ ትምህርት ቤት ነበር ። ክፉ በጎውን እየለየ ሲመጣ ታድያ ተማሪዎች ስድስት ሰዓት ለምሳ ሲለቀቁና 11 ሰዓት ሲወጡ የሚንጫጩበትን ቤት ውስጥ ተደብቆ ይሰማል ። በውስጡም ደስ የሚል ጥሩ ስሜት ይፈጥርበታል ። ቤተሰቦቹ በሙሉ ቤት ውስጥ በማይኖሩበት ቀንም ቀስ ብሎ ወጥቶ በራፉ ላይ በመቆም እንዲህ በጫጫታ የሚያስደስቱትን ተማሪዎች ያስተውላቸው ገባ ። ሲውል ሲያድር ተማሪዎቹን ማየት ምክንያት ሆነውና እነሱን እየጠበቀ ማየት ብቻ ሳይሆን የአየር ንብረቱን ጨምሮ አካባቢውን ይቃኝም ገባ ። እንዲህም ሆኖ አንድ ሰው ብቅ ሲል ሮጦ ወደ ቤቱ ይገባ እንደነበርም አይዘነጋም ። በሂደትም ‹‹እኔ እስከመቼ ነው ከእናት አባቶቼ እንዲሁም ከእህትና ወንድሞቼ ተደብቄ በአካሌ ጉዳት እያፈርኩና እየተሸማቀቅኩ የምኖረው፤ እንደእኩዮቼስ እኔ መማር የማልችልበት ምክንያት ምንድነው ›› ሲል ራሱን መጠየቁን ያስታውሳል ወጣት አበባው ።
‹‹አንድ ቀንም ድምፅ አውጥቼ መማር አለብኝ፤መውጣት አለብኝ ስል ጮኬ ለራሴ ነገርኩት››ይላል ። የሚገርመው አያቱ ወይዘሮ ትሁኔ ተዋበ ይሄን የሰሙ ይመስል ። የዛኑ ዕለት እየተቻኮሉ ወደ ወላጆቹ ቤት መጡና ‹‹ አንተ ልጅ ሳልሞት እዚህ አካባቢ ያለ ትምህርት ቤት ግባና ተማር ። አንተ ከሌላው በምን ታንሳለህ! አካል ጉዳት በአንተ አልተጀመረም ። ነገ ሌላውም አካል ጉዳተኛ የሚሆንበት ሁኔታ ሊኖር ስለሚችል በአካልህ ጉዳት ምክንያት የበታችነት ሊሰማህ አይገባም ። ራስህን ከእኛም ሆነ ከሌሎች መደበቅ የለብህም›› አሉት ።
‹‹ይሄን ተናግራ ያለ ፈቃዴ በነጠላዋ አዘለችኝና ወደ ትምህርት ቤት ወሰደችኝ››ይላል ወጣቱ ወደ ትምህርት ቤት የገባበትን አጋጣሚ ሰያስታውስ ። በዚህ ወቅት የ10 ዓመት ልጅ ነበር ። አያቱ ርዕሰ መምህሩ ቢሮ ወስደውም አስቀመጡት ።
‹‹ርዕሰ መምህሩ ሲያየኝ የእጅና የእግሬን ጉዳት እንዳያይብኝ ዓይኔን ጨፈንኩ ። ዓይኔን የጨፈንኩት መላ አካላቴን ከርዕሰ መምህሩ ዕይታ የሚደብቅልኝ መስሎኝ ነበር›› ሲልም ሁኔታውን ያስታውሰዋል ። በወቅቱም ርዕሰ መምህሩ ነገ ተነጎድያ ተምሮ አገር ማስተዳደር የሚችል ሰው መሆኑን እሱም እንደማንኛውም ሰው ተምሮ የፈለገው ደረጃ ላይ መድረስ እንደሚችል በልበ ሙሉነት ነገረው ። ይህ ሆኖ እንኳን ዓይኑን አልገለጠም ርዕሰ መምህሩን ቀና ብሎ ማየት አልደፈረም ነበር ። ርእሰ መምህሩ ከብዙ ምክርና ማበረታት በኋላም ስኪሪብቶና ማስታወሻ ደብተር ገዝቶ ሰጠው ። ወዲያውም ትምህርት ጀመረ ። ሆኖም ፈጥኖ ከተማሪዎቹ ጋር መላመድና ትምህርቱን ተረጋግቶ መከታተል ባለመቻሉ አያቱ በኋላም እናቱ ወንበር ይዘው እየመጡ ሦስት ወር ሙሉ አብረውት ተቀምጠው ነበር የተማረው ።
ወጣቱ እንዳወጋን መምህሩ ጥያቄ ሲጠይቅ እጁን አውጥቶ ለመመለስ እንኳን ይሸማቀቅና ይሳቀቅ ነበር ። ‹‹እጄን ሳወጣ ተማሪዎች ጣቶቼ የተሰበሰቡ መሆኑን ያዩብኛል ብዬ ስለምፈራ መልስ አልሰጥም ነበር ። እጄን ሳላወጣ ዝም ብዬ መልሱን እናገራለሁ፡፤ በኋላ የገባው መምህሬ አበባው ብሎ ሲጠራኝ እጄን ሳላወጣ መልሱን በፍጥነት እነግረው ነበር›› ሲልም የመጀመሪያዎቹን የትምህርት ቤት ቆይታውን ያስታውሰዋል ።
መምህሩ ጉብዝናውን ደጋግሞ ሲናገርለትና ተማሪዎች እንዲያጨበጭቡለት ሲያደርግ ፍራቻው እየለቀቀው መምጣቱንም ያወሳል ። የክፍል ሥራም ሆነ የቤት ሥራ በመሥራትም ፈጣን ነበር ። በተለይ የክፍል ሥራ ገና ከመሰጠቱ ፈጥኖ በመሥራት የሚያሳይበት ሁኔታ መምህራኖቹ አብዝተው ያሞግሱት ነበር ። በአጠቃላይ የትምህርት አቀባበሉ ፈጣን ስለነበረ የሚወጣውም አንደኛ ሆነ ። መምህራኖቹ ለእሱ ልዩ ፍቅር ነበራቸው ። ከማበረታታት አልፎ በጉብዝናው ባንዲራ ስነስርዓት ላይ እያወጡም በአካል ጉዳተኝነቱ ሳይበገር ይሄን ውጤት ማምጣት ቻለ ሲሉም ይሸልሙት ገቡ ። እንደውም ከተማሪዎች ሁሉ ተመርጦ አርአያ ሆኖ መቅረብ ጀመረ ።
‹‹በትምህርት ቤት የነበረኝ ግንኑነት በዚህ መልኩ ሲሆን፤ እናቴንም ሆነ አያቴን አትምጡ አልኳቸው ። ብቻዬን ትምህርት ቤት ሄጄ መምጣት ጀመርኩ››ይላል ። ስምንተኛ ክፍል ፈተና ተፈትኖም ጥሩ ነጥብ በማምጣቱ ወደ አባይ ምንጭ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተዛውሮ የዘጠነኛ ክፍል ትምህርቱን መከታተል ጀመረ ። ሽልማት ለማግኘት ዓመት አልወሰደበትም ። ዘጠነኛ ክፍል ከመግባቱ በጥሩ ትምህርት አቀባበሉ ‹‹አሁን ድረስ እንደ ሀውልት አስቀምጫታለሁ››የሚላትን የባዮሎጂ መጽሐፍ ተሸለመ ። እንዲሁም ኬምስትሪ ኤክስትሪም የሚባልም መጽሐፍ ተሸለመና ከአጠቃላይ ትምህርት ቤቱ አንደኛ በመውጣት ድል ተቀዳጀ ።
ይሄ ሁሉ ሲሆን ግን ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ በጉልበቱ ነበር የሚራመደውና ረጅም ርቀት ትምህርት ቤት የሚሄደው ። እናቱና እህቶቹ ዝናብ ሲመጣ ጥላ በመያዝና አዝለው በማምጣትና በመውሰድም ሲረዱት ቆይተዋል ። ከመመላለስ ብዛትም ጉልበቱ ደም ይፈሰው እንደነበርም ያወሳል። በዚህም የመዳን ተስፋው የበለጠ ተስፋ አስቆራጭ እየሆነ መጣ ።
‹‹ምንም እንኳን የእጅም ሆነ የእግርና ሌሎች ጉዳቶች ቢኖርብንም ፈጣሪ ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉ አካል ጉዳተኞች ልዩ ተሰጥኦ አለን›› የሚለው ወጣት አበባው፤ የእጅና እግር አካል ጉዳት ቢኖረበትም በተፈጥሮ የተሰጠው በትምህርት ቤት ቆይታው ልዩ ዕውቀት፤ልዩ አስተሳሰብ፤ልዩ አመለካከት እንደነበረው ያወሳል ። እናም በማኔጅመንት ትምህርት ክፍል የጀመረውን የሦስት ዓመት የትምህርት ሂደቱና ዕውቀት የጨበጠበት አግባብ አካሉ ካልተጎዳው ተማሪ እኩል እንደውም የበለጠ በመሆኑ በጥሩ ውጤት ተመርቆ ለመውጣት መብቃቱን ያወሳል ።
በዚህ ሂደት ታዲያ አይቀሬው የፍቅር ጣጣ መጣ ። እሱ ባለው የአካል ጉዳተኝነት ለፍቅር ዝግጁ ባይሆንም አንዲት ቆንጆ ተማሪ ወደደችው፤ ለጓደኝነትም ጠየቀችው ። እንደሚያስታውሰውም ወደ ዩኒቨርሲቲ የገባ ሰሞን የአካል ጉዳቱ የብዙ ተማሪዎችን ትኩረት ስቦ ነበር ። እንደልዩ ፍጡር የሚያዩትም ነበሩ ። በጉዳቱ ንቀትም የሚያሳዩት አልጠፉ ። የኋላ ፤የኋላ ታድያ በትምህርት ያለው ጉብዝና በሁሉም ተማሪዎች ዘንድ ታወቀ ። ከመምህራኖቹ ጋር ያለው ግንኙነትና የተለየ የጓደኝነት የሚመስል ቅርበትም ተገልጦ ለተማሪዎች ታየ ። ብዙዎች ቀረቡት ። ቀርበው በትምህርት እንዲያግዛቸው ይጠይቁትም ገቡ ። እና ወጣቷ ተማሪ በፊት ስታየው በአካሉ ጉዳት ብቻ ቦታ ሰጥታው እንዳልነበረ አሁን ግን በትምህርት ያለውን ብቃት ስታይ የበለጠ ቦታ እንደሰጠችውና ነገ ተነጎዲያም ትልቅ ደረጃ ይደርሳል ብላ እንድታስብ አደረጋት ።
በዚህም ምክንያት አካል ጉዳቱን እንደምንም ባለመቁጠርና ነገን አሻግራ በማየት ለወጣት አበባው የፍቅር ጥያቄ ለማቅረብ ተደፋፈረች ። ሁሉንም ግልጽልጽ አድርጋም ነገረችው ። ግልጽነቷና እሱን ለመምረጥ መፈለጓ በራሱ በውስጡ የሆነ ስሜት እንዲፈጠር አደረገው ። ይሄ ስሜት ከዚህ ቀደም በፍፁም ተሰምቶትም ሆነ ገጥሞት የማያውቀው የፍቅር ስሜት እንደነበርም ያወሳል አበባው ።
‹‹አካል ጉዳተኞች ያገባሉ፤ልጅ ይወልዳሉ፤ቤተሰብ ይመሰርታሉ፤ሌላው ቀርቶ ተቃራኒ ጾታ ያፈቅራሉ ተብሎ በማይታሰብበት ማህበረሰብ ውስጥ አድጌ ስለፍቅር ባላስብና አፍቅሬ ባላውቅ አይፈረድብኝም››የሚለው አበባው የቀረበለትንም የፍቅር ጥያቄ ጊዜ ሳይወስድ እንደተቀበለው ይናገራል።
አካል ጉዳተኞች ተመራጭ ለመሆን ራሳቸውን ብቁ አድርጎ መገኘት እንደሆነ መገንዘብ እንደሚገባቸውም ወጣት አበባው ያነሳል ። ይህ ሲሆን አካሉና አካሏ ባልጎደለ ወጣት ሊመረጡ እንደሚችሉም ያነሳል ። እንዲህ አይነቱ የጋብቻ ውህደት የበለጠ ተጋግዞና ተደጋግፎ በጋራ ለመኖር የተሻለ አማራጭ እንደሆነም ይገልፃል ። ‹‹አካል ጉዳተኛ የምንሆነው የሚገባን ማሰብና የተነገረንን ነገር አስታውሰን ምላሽ መስጠት ሳንችል ስንቀር ነው ። እግሬ፤እጄና ሌላ የአካል ጉዳት ስለደረሰብኝ አካል ጉዳተኛ ነኝ ማለት አይደለም››ይላል።
‹‹ቤተሰቦቻችን ሁሌ አብረውንና እያገዙን አይኖሩም ። ነገ ተነጎዲያ ሊሞቱ ይችላሉ ። ይሄኔ ብቻችንን እንቀራለን›› የሚለው ወጣቱ ጭንቅላታችን ጤናማ ከሆነና ጉድለት ከሌለበት እንደማንኛውም ዜጋ መሥራትና ራሳችንን ማስተዳደር ውሃ አጣጫችንንም መምረጥ አለብን ሲል ሃሳቡን አሳርጓል ።
ሠላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2015