እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ.. የአባቶቼ መልክና ቀለም የቀለመኝ። በኢትዮጵያዊነቴ ውስጥ እውነት ናቸው ብዬ ከተቀበልኳቸውና ባስታወስኳቸው ቁጥር ከሚያስደንቁኝ እውነቶች ውስጥ አንዱ የዓድዋ ታሪክ ነው። ዓድዋ የጋራ መደነቂያችን እንደሆነ ባምንም እንደእኔ የሚደነቅበት ስለመኖሩ ግን እጠራጠራለሁ።
በዓለም ታሪክ፣ በሰው ልጆችም ሥልጣኔ የዓድዋን ያክል እውነት እንደሌለ ፤ ዓድዋ ለዓለምም ለሰው ልጆችም ብቸኛው አስደናቂ እውነት እንደሆነ ይሰማኛል። ይሄ እውነት ደግሞ የእኔና የእናተ እውነት ነው። ይሄ እውነት በአባቶቻችን ሥልጣኔና ዘመናዊነት እንዲሁም ደግሞ ከባድ መሳሪያ የመጣ ሳይሆን በአንድነትና በወንድማማችነት መንፈስ የመጣ ነው።
በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ያ አባቶቻችን በአንድነት የቆሙበት የዓድዋ ዘመን እንደ እኔና እንደእናተ እንደአሁኑ ጊዜ በዘርና በእኔነት የተከፋፈለ አይደለም ፤ ቢሆን ኖሮ ዓድዋ የሚባለውን ታሪክ ውሃ ይበላው ነበር። ዓድዋ ኢትዮጵያዊነትን ባስቀደሙ ኅብረብሄራዊ አባቶቻችን ተጋድሎ የተገኘ ነው።
እኛ ዛሬም ድረስ በአባቶቻችን ታሪክ የምንጠራ ነን። ከመጀመሪያው ዓድዋ እስከ ሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ድረስ ዓርባ ዓመታት አሉ። በአርባ ዓመታት ውስጥ ሁለት ዓይነት ድሎችን መቀዳጀት ትርጉሙ በምን እንደሚለካ ዛሬም ድረስ አልመጣልኝም። እኔና እናተ ግን መቶ ዓመታት አልፈውን እንኳን ዛሬም ድረስ በአባቶቻችን የትናንት ታሪክ የምንጠራ ነን። የእኛ ዓድዋ የታለ? የእኛ ዓድዋ መቼ ነው የሚ ጀምረው?
ከእኔነት መንፈስ እስካልተላቀቅን ድረስ ከፍታችንን አናገኘውም። “መንግሥትህ ትምጣ ብለን እንደምንጸልየው” ቀጣይ ጸሎታችን ኢትዮጵያ ትምጣ ሊሆን ይገባል።
በልባችን ላይ ከትዕቢታችን ቀድማ፣ ከጥላቻችን ቀድማ ኢትዮጵያ ካልመጣች አደጋ ላይ ነን። ከእኔነታችን ቀድሞ በነፍሳችን ላይ ኢትዮጵያዊነት ካልነገሰ ታሪክ ከማውራት ባለፈ ታሪክ መስራት አይቻለንም።
የአባቶቻችን ዓድዋ በኢትዮጵያዊነት ጀምሮ በኢትዮጵያዊነት ያበቃ ነው። የውስጥ ችግሮቻቸው እንኳን ይህን እውነታቸውን አለደበዘዘባቸውም። ጣሊያን ሀገራቸውን ሊወር ሲመጣ የራሳችን/ የውስጥ ጉዳያችን በኋላ ይደርሳል በሚል በአንድነት ወራሪውን ኃይል ለመከላከል የተነሱት።
እዚህ ጋ ልንማርበት የሚገባ አንድ ትልቅ እውነት አለ.. አባቶቻችን ቅሬታቸውን ከሀገራቸው አላስቀደሙም። ሀገራቸውን ነበር የጉዳያቸው ቀዳማይ ያደረጉት። ይሄ እውነት እኛ ጋ ስንመጣ ሌላ ነው። እኔነታችንን ከኢትዮጵያዊነት አስቀድመን የቆምን ብዙ ነን። የፖለቲካ ልዩነቶቻችንን የሥልጣን መወጣጫ አድርገን ነውጥ የምንፈጥር እዚህም እዛም አለን።
ዓድዋ በዚህ መንገድ አልመጣም። ዓድዋ ኢትዮጵያዊነት ቀድሞ ኢትዮጵያዊነት በተከተለበት የወንድማማችነት መንፈስ የተፈጠረ ነው። እኛም ከልዩነታችን ሀገራችንን ማስቀደም አለብን.. የእኛ ዓድዋ በዚህ መንገድ ካልሆነ በምንም አይፈጠርም።
ዓድዋ ለእኛ ለጥቁሮች ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ ኩራት ነው ። ለመላው ቅኝ ገዢዎች ደግሞ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ የቁጭትና የውርደት ታሪክ ነው። ከዓድዋ በፊትና ከዓድዋ በኋላ ዓለም ሁለት አይነት ናት። ይሄን እውነት ለመረዳት ማስረጃ ማቅረብ አይጠበቅብንም አፍሪካን ማየቱ፣ መላውን ጥቁር ሕዝብ ማየቱ በቂ ነው።
ከዓድዋ በፊት ያለችው ዓለም በጥቁሮች ላይ የበላይ እንደሆነች የምታስብ ነበር። ከዓድዋ በፊት ያለው የነጮች ሥለልቦና ጥቁሮች ሰው እንዳይደሉና ለባርነት እንደተፈጠሩ የሚያስብ ነበር። በዚህም እምነታቸው በጥቁር ሕዝብ ላይ ሁሉንም አይነት ግፍ ሲፈጽሙ ነበር።
ዓድዋ እውን እስከሆነችበት ቀን ድረስ መላውን ጥቁር ሕዝብ ለግዞት ሲገለገሉበት እንደነበር ታሪክ ያስታውሰናል። የሆነ ቀን፣ በሆነ ሕዝቦች፣ የሆነ ቦታ ላይ ዓድዋ ተፈጠረ .. ያ ቀን፣ ያ ቦታ፣ የእነዛ ሕዝቦች ጽናት የነጮች የበላይነት ማብቂያ ሆነ።
ስለ ዓድዋ ሳስብ እየኮራሁ ነው.. ስለዓድዋ ስናገር በአሸናፊነት ውስጥ ቆሜ ነው.. ይሄን ስጽፍ እንኳን ዓለም የሌላትን ታሪክ እየጻፍኩ እንደሆነ በማመን ውስጥ ሆኜ ነው። የእኛ ዓድዋ ለመላው ጥቁር ሕዝብ የነጻነትና የቀና ማለት መለኮት ሆኖ በዓለም አደባባይ የተሰማ ድምጽ ነው።
በጥቁሮች ላይ የበላይ እንደሆኑ የሚያስቡት ቅኝ ገዢዎች ተዋረዱ። መላው አፍሪካ ኢትዮጵያ በምትባለው በምስራቅ አፍሪካዊቷ የነጻነት ታጋይ የነጻነት ተስፋ ሰነቁ። ከዓድዋ በኋላ ዓለም ሌላ መልክን ያዘች። የእኩልነትና የፍትሀዊነትን እሳቤን ማራመድ ጀመረች። የዓለም መልክ በዓድዋ ድል ተቀይሯል። ዓድዋ ለዓለም ጭቁኖች የትንሳኤ ቀን ነው። ዓድዋ ለዓለም ጥቁሮች የአብዮት ማግስት ነው።
ይሄን እውነት፣ ይሄን ታሪክ የጻፉ እጆች ምነኛ አድለኞች ናቸው? አሁን ደጋግመን ከምናወራው የአባቶቻችን ዓድዋ ወጥተን የራሳችንን ዓድዋ የምንሰራበት ጊዜ ነው። ከአባቶቻችን ጽናትንና አንድነትን ኢትዮጵያዊነትንም ወስደን በግለኝነት የጠየመችውን ኢትዮጵያ እንደ አዲስ መማገር አለብን።
ካለፈው ዘመን ፍቅርና ወንድማማችነትን ወርሰን በጥላቻና በመለያየት የቆመችውን ሀገራችንን መሰብሰብ አለብን። ዓድዋን ስንዘክረው መቶ ሃያ ሰባት ዓመት ሆኖናል እርግጥ ዓድዋ እድሜ የለውም እስከ ዓለም ማለቂያ ድረስ መላው የጥቁር ሕዝብ የሚዘክረው ታሪክ ነው።
ግን ደግሞ እኛ ከአባቶቻችን እንደተቀበልነው ሁሉ ለልጆቻችን የምናወርሳቸው ሌላ ዓድዋ ያስፈልገናል። መጪው ትውልድ የአባቶቹንና የአያቶቹን ጥንድ ዓድዋ እንዲያከብር ዛሬ የእኔና የእናተን ዓድዋ መፍጠር አለብን።
ታሪክ ተአምር አይደለም ወይም ደግሞ በጥንቆላና በሆነ አስማት በሚመስል ሁኔታ የሚፈጠር አይደለም። ታሪክ የሚፈጠረው በፍቅር ነው። ታሪክ የሚጻፈው በአንድነት ነው። ፍቅር ውስጥ የቆሙ ነፍሶች ሁሉ ባለታሪክ ናቸው። በአንድነትና በይቅርታ ውስጥ የጸኑ ልቦች እነሱ የታሪክና የተዓምር ባለቤቶች ናቸው።
እድላችንን የደበቅነው ፍቅርን በማያውቅ ጨለማ ልባችን ነው። ዳግማዊ ዓድዋን ለመፍጠር እንደአባቶቻችን መሆን አለብን። ዓላማቸውን ወርሰን፣ ህልማቸውን ተጋርተን በቀናው ጎዳና ላይ መቆም ያዋጣናል። እነሱ የኖሩት ለኢትዮጵያ ነበር የሞቱትም ለኢትዮጵያ ነው።
እነሱ ቋንቋቸው አንድነት ነበር በአንድነትም ዓድዋን ፈጥረው አልፈዋል። የእኛ ቋንቋ ምንድነው?… ቋንቋችን ግለኝነት ነው። እውቀታችን እኔነት ነው። ተነጋግረን መግባባት ተስኖን ወደጦርነት ስንገባ ኖረናል። ለዚህም እኮ ነው ለራሳችን ኖረን ለራሳችን ያልበቃነው። ለዚህ እኮ ነው ዓድዋን መሳይ ታሪክ ያልሰራነው። ለዚህም እኮ ነው የምንናፍቃትን ኢትዮጵያ አምጠን መውለድ ያልቻልነው።
ምኞት ተግባር ካልታከለበት ከንቱ ልፋት ነው። በምኞታችን ውስጥ ሆና ልናያት የምንፈልጋት ኢትዮጵያ አለች። በሃሳባችን ውስጥ ሆኖ እንድናየው የምንፈልገው ሕዝብ አለን። እኔነትና ራስወዳድነትን በቀላቀለ ማህጸን ውስጥ ዓድዋ የለም። ይሄ ማህጸን ምርጧንና ድንቋን ኢትዮጵያ አምጦ መውለድ አይቻለውም።
ማህጸናችን ለኢትዮጵያ ምቹ መሆን አለበት። ማህጸናችን ለድሃ ሕዝባችን የሚስማማ መሆን ይገደዋል። ማህጸን ሃሳብ ነው.. ማህጸን ምግባር ነው። ማህጸን ፍቅርና አንድነት፣ ይቅርታና ወንድማማኝነት ያሉበት ስፍራ ነው። ማህጸን እውነትና ፍትህ፣ እኛነትና ኢትዮጵያዊነት የሚፈጠሩበት ለምለም ቦታ ነው።
በዚህ ማህጸን ካልሆነ ዓድዋንም ሆነ የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ አንደርስባቸውም። ማህጸናችን ጥላቻን ጸንሶ ጥላቻን መውለዱ ይብቃው። ማህጸናችን እልኸኝነትን ጸንሶ እልኸኝነትን መውለዱ ይቁም። ለመነጋገርና ለመግባባት፣ ለመተቃቀፍና አንተ ትብስ አንቺ ለመባባል የሚሆን ማህጸን ያስፈልገናል። ዓድዋና ኢትዮጵያ በዛ ውስጥ ናቸውና።
ዓድዋ አጥቢያ ነው.. የኢትዮጵያዊነት የአንድነትና የነጻነት ዜማ የሚደመጥበት። የጽናት፣ የሉዓላዊነት ቅኔ መወድስ የሚሰማበት.. የክብር፣ የህብር.. ደብር። ዓድዋ ኢትዮጵያዊነት የተቀረጸበት የብኩርና ጽላት ነው። ሞት የዋጀው፣ ጉስቁልና ያልረታው የማንነት አውድ። ዓድዋ ዋርካ ነው የኩራት፣ የክብርና የትህትና የነጻነትም የመምሬ አድባር። ዓድዋ ተራራ ነው.. ትልቅና ጥልቅ የኢትዮጵያዊነት ስጋና ደም። ጽናት እምነትና አሸናፊነት የከተቡት።
ዓድዋ ጌጥ ነው.. የመቶ ሃያ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን አሸንክታብ። የሰማንያና ከዛ በላይ ብሄረሰብ የኩራትና የልዕልና ምንጭ። የመላው ጥቁር ሕዝብ መታበያ.. መመጻደቂያ። ዓድዋ ይሄን ሁሉ ነው.. እኛም ይሄን ሁሉ ነን።
ዓድዋን የፈጠሩ ክብር ይግባቸው እነዛ ሻካራ እጆች። ክብር ይግባቸው እነዛ ባዶ እግሮች። ክብር ይግባቸው እነዛ ከፍቅር ውጪ ምንም የማያውቁ ነፍሶች.. በነሱ ነው ዛሬን እንዲህ ደምቆ ያየነው። እነዛ ሻካራ እጆች፣ እነዛ ባዶ እግሮች፣ እነዛ ክቡር ነፍሶች ባይሞቱልንና ባይጎሳቆሉልን ኖሮ እኔም እኔን እናተም እናተን ባልሆንን ነበር።
ምኒልክ ሲጠራን ወይ ባንለው ኖሮ.. እቴጌ ስትጠራን እመይት ባንላት ኖሮ ዛሬ እኛን ባልሆንን ነበር። ክብር ይገባቸው ሞተው ያቆሙን እነዛ ነፍሶች። ዓድዋ የኢትዮጵያዊነት ቀለም ነው.. እንደ አፍሪካ ከፊት የቆምነው፣ እንደ ጥቁር ፊተኝነትን ያገኘነው በዚህ እውነት ላይ ተረማምደን ነው። ኢትዮጵያዊነት አፍሪካን አምጦ የወለደ ማህጸን ነው። ኢትዮጵያዊነት የዓለምን ታሪክ የቀየረ፣ የነጮችን የበላይነት ያዋረደ የልዕልና ጥግ ነው። በዚህ ስም ስም መጠራት ክብሩ የት ድረስ እንደሆነ መመዘን ቀላል ቀላል አይደለም ።
ዓድዋ በየትኛውም ዘመን ለሚፈጠር ነጭና ጥቁር መደነቂያና መገረሚያ ነው። ወጣቱ ትውልድ የአባቶቹን ዓድዋ እያስቀጠለ የራሱን ዓድዋ ለመፍጠር ከመቼውም ጊዜ በላይ አሁን መነቃቃት አለበት። በአባቶቻችን ዓድዋ ውስጥ የእኛን ዓድዋ ለማየት እንደአባቶቻችን ያለ አእምሮና ነፍስ ያስፈልገናል። እኔነት ያልጎበኘው አእምሮና ነፍስ። ግለኝነት ያልነካው፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ያሻናል። በኢትዮጵያዊነት ጀምሮ በኢትዮጵያዊነት ያበቃ ንጹህ ሰውነት የዚህኛው ትውልድ ዓድዋን መፍጠሪያ ጥበብ ነው።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2015