አዲስ አበባ፡- ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኦዲት ግኝትን በግብአትነት በማቅረብ ለክትትልና ቁጥጥር ሥራው ክንፍ በመሆን ሃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ እንደሚገኝ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።
የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ አራሬ ሞሲሳ፤ የኦዲት ስራ የአገርን ውስን ሀብትና ንብረት ከብክነት ለማዳን፣ በባለበጀት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ ብልሹ ተቋማዊ አሠራሮችን ለመከላከል እና የተቋቋሙበትን ተልዕኮ በአግባቡ እንዲፈጽሙ ለማስቻል ጉልህ ድርሻ አለው ብለዋል።
ቋሚ ኮሚቴው ሪፖርቶችን ከመስማት ባለፈ የመስክ ምልከታ ማድረጉን በመጠቆምም፤ በመስክ ምልከታ ሂደት አሰራሮች እንዲስተካከሉ መደረጉን አመልክተዋል። የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት የቀረበባቸው መስሪያ ቤቶች አብዛኞቹ ማስተካከያ ማድረጋቸውንም ወይዘሮ አራሬ አመልክተዋል።
ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው፤ ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ ምክር ቤቱ ያጸደቀው በጀት በአግባቡ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን በማረጋገጥ የምስክርነት ቃሉን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመስጠት ለምክር ቤቱ ክንፍ ሆኖ በማገልገል ላይ ነው ብለዋል።
ምክር ቤቱም የቀረበለትን ሪፖርት መነሻ በማድረግ አስፈጻሚ አካላትን የመከታተል እና የመቆጣጠር ስራ እየሰራ ይገኛል ያሉት ወይዘሮ መሰረት፤ የዋና ኦዲተር ጥርስ ምክር ቤቱ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲሰራ እና የቀረበለትን ሪፖርት መነሻ በማድረግ ወደ ተግባር እንዲቀይር ዋና ኦዲተር ግንዛቤ ፈጠራ ላይ ትኩረት ይሰጣል ሲሉም ገልጸዋል።
ተቀባይነት የሚያሳጣ አስተያየት የተሰጣቸው ተቋማት ላይ የነበሩ ችግሮች እየቀነሱ እና ለውጦች እየታዩ እንደሚገኙም ዋና ኦዲተር መሰረት ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የምትከተለው ፓርላሜንታዊ ሥርዓትን በመሆኑ የኦዲት ሪፖርት ሰርተን ለምክር ቤቱ እናቀርባለን። አስፈጻሚዎችን የመቆጣጠር እና የመከታተል ሥልጣን የተሰጠው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደግሞ ተግባራዊ ያደርጋል ሲሉም አክለዋል።
ዋና ኦዲተር ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ ምክር ቤቱ ያጸደቀው በጀት ባግባቡ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን በማረጋገጥ የምስክርነት ቃሉን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እያቀረበ ይገኛል ያሉት ዋና ኦዲተሯ፤ ምክር ቤቱም የቀረበለትን ሪፖርት መሰረት በማድረግ አስፈጻሚዎችን የመቆጣጠር እና የመከታተል ስራ ይሰራል ብለዋል።
እንደ ወይዘሮ መሰረት ገለጻ፤ ምክር ቤቱ በሕግ የተሰጠውን ሥልጣን ተግባራዊ ሲያደርግ ዋናው ኦዲተር ጥርስ አለው ማለት ይቻላል። ምክር ቤቱ በተሰጠው ሥልጣን መሰረት ተግባራዊ ሲያደርግ ዋና ኦዲተር ጥርስ ይኖረዋል።
ዋና ኦዲተር በሰራው ሪፖርት መነሻነት ምክር ቤቱ ተግባራዊ የማያደርገው ከሆነ ‹‹ጥርስ የሌለው አንበሳ›› ማለት ይቻላል። የእኛ ጥርስ ምክር ቤቱ እንደመሆኑ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተጠናከረ እንዲሆን እንፈልጋለን ብለዋል።
ምክር ቤቱ ተጠናክሮ ሃላፊነቱን እንዲወጣም በአስፈጻሚ ተቋማት የወጡ መመሪያዎች፣ ሕጎች፣ ደንቦች እና አሰራሮችን እንዲያውቋቸው የግንዛቤ ፈጠራ ስራ እንደሚሰራም ነው የጠቆሙት። እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ በምክር ቤቱ የመንግሥት ወጭ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስፈጻሚውን ጠርቶ በመገምገምና አቅጣጫ በመስጠት የተወሰነ እርምጃዎች አሉ። ከክፍያ እና ከተሰብሳቢ ክፍያዎች ጋር ተያይዞ መሻሻሎች ታይተዋል።
ገለልተኛ ተብለው ከተቋቋሙ ተቋማት መካከል ዋና ኦዲተር አንዱ መሆኑን ያመለከቱት ሃላፊዋ፤ የሊማና ሜክሲኮ ዲክላሬሽን መርሆዎች ከሕገ መንግሥቱ እስከ አዋጆች መካተት እንዳለባቸው ያስቀምጣል። ይህንን ካካተቱ ጥቂት የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቶች ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት አንዱ መሆኑን አንስተዋል።
‹‹በአደረጃጀት ችግር የለም፣ በአስፈጻሚም በኩል ምንም አይነት ጣልቃ የሚገባበት ሁኔታ የለም፣ ከሥልጣን ገደቡ ጀምሮ አደረጃጀቱ በሕግ የተቀመጠ በመሆኑ መርሁን መሰረት በማድረግ እየተሰራ ይገኛል›› ሲሉም ነው ዋና ኦዲተር መሰረት የተናገሩት።
የኦዲት ጥራትን ከማሳደግ ባለፈ የኦዲት ሥራ ፋይዳን በሚመለከት በየጊዜው የህብረተሰቡን እና የኦዲት ተደራጊ ተቋማትን ግንዛቤ ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች በሰፊው ሊሠራ እንደሚገባም ነው ያመለከቱት።
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2015