አዲስ አበባ፡- ዓድዋ ከጭቆና ለመላቀቅ ለሚታገሉ ሁሉ የአንድነትና የአሸናፊነት ተምሳሌት ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።
በመከላከያ ሠራዊት አስተባባሪነት 127ኛው የዓድዋ በዓል በመስቀል አደባባይ ሲከበር ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ እንደገለጹት፤ ዓድዋ የመተባበር ምልክት ሆኖ ለመላው ዓለም ምሳሌ የሆነ ድል የተመዘገበበት አኩሪ ታሪክ ነው።
ዓድዋ ከነፃነት ቀንበር ለመላቀቅ ጥረት ያደረጉ ጥቁሮች እንዲተባበሩ ምክንያት የሆነ ድል ነው። ድሉ ከኢትዮጵያ አልፎ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት
ትግል መሠረት ሆኗል። በዚህም የተነሳ የዓድዋ ድል መዳረሻው ሠፈር ሳይሆን ዓለምአቀፋዊ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በዓለም ደረጃ ትልቅ ክብር የሚሠጠውን የዓድዋ ታሪክ በመጠበቅ ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባል ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፤ ዓለም ያደነቀውን ዓድዋን ከሌላው በበለጠ ማክበርና ማድነቅ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በአባቶች ተጋድሎ የተገኘው ድል ብሔራዊ ስሜትን ለማዳበርና አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ጉልህ ሚና አለው። ቅድመ አያቶቻችን በታላቅ ተጋድሎ ያስረከቡንን አገር ማስቀጠል ደግሞ የትውልድ ኃላፊነታችን ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር ነው ብለዋል።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ እንዳስታወቁት፤ ትውልዱ ከሚያስተሳስረን ጉዳዮች ይልቅ ቁርሾ ላይ ካተኮረ እንደአገሀር ያሉብን ችግሮች እየተባባሱ ይሄዳሉ። በመሆኑም በሚያቀራርቡንና በሚያስተሳስሩን ጉዳዮች ላይ ይበልጥ ተቀራርቦ መስራት ይገባል።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ኤታማዦርሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ዓድዋ የሉዓላዊነት ተጋድሎ የታየበት ድል ነው። ድሉ ከኢትዮጵያ አልፎ ለመላው ጥቁሮችም ትግል ማበብ ምክንያት ሆኗል።
ዓድዋ የኢትዮጵያውያንን ጀግንነት ያሳየና ለመላው ጥቁሮች የትግል ንቅናቄ መነሻ የሆነ ድል በመሆኑ ይበልጥ በደማቅ ሁኔታ እንዲከበር ይደረጋል ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን በብሔር፣ በቋንቋና በሃይማኖት ልዩነት ሳይከፋፈሉ ያስገኙትን የዓድዋ ድል በተገቢው መንገድ መዘከር ይገባል ሲሉ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ገልጸዋል።
127ኛውን የዓድዋ በዓል በመከላከያ ሠራዊት መሪነት እንዲከበር መደረጉ ትክክለኛ ውሳኔ ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ ደረጃውን በሚመጥን መልኩ ለማክበር ጥረት ተደርጓል። ቀጣዩን የዓድዋ በዓል ደግሞ ከአሁኑ በበለጠ ሁኔታ አፍሪካውያን ወንድሞቻችንን በማካተት በደማቅ ሁኔታ እናከብረዋለን ሲሉ ተናግረዋል።
የዓድዋ በዓልን ደረጃ የሚመጥን አኩሪ ዝግጅት ታይቷል ሲሉ የተናገሩት ደግሞ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ ናቸው።
የበዓሉን ድምቀት ያሳደገ ዝግጅት በመከናወኑ በጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ስም ምስጋና አቀርባለሁ ብለዋል።
የአርበኞችን ታሪክና ተጋድሎ በማውሳት ትውልዱ ስለሀገሩ የሚማርበት አውድና ዝግጅቶችን ማጠናከር እንደሚገባም ገልጸዋል።
በመስቀል አደባባይ በተከበረው የዓድዋ ድል በዓል ዝግጅት ላይ ልዩ ልዩ ወታደራዊ ትርዒቶች የታዩ ሲሆን የመከላከያ ሠራዊት አባላትም የእግረኛ ሰልፍ አሳይተዋል። በርካታ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችና ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችም ለዕይታ ቀርበዋል።
በዕለቱ የአየር ኃይል አባላትም በጦር ጄትና በሄሊኮፕተር የታጀበ የአየር ላይ ትርዒት በማሳየት በዓሉን አድምቀዋል።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን የካቲት 24 ቀን 2015 ዓ.ም