– 24 የጤና ተቋማት የዲጂታል አገልግሎቱን ይጀምራሉ
አዲስ አበባ፡- የዲጂታል ጤና አገልግሎት በሶስት ሆስፒታሎች ተግባራዊ መደረጉን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
በ2015 በጀት ዓመት መጨረሻ ለተገልጋዮች የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት አራት ተጨማሪ ሆስፒታሎች እና 20 ጤና ጣቢያዎች በአጠቃላይ 24 የጤና ተቋማት የዲጂታል ጤና አገልግሎቱን እንደሚጀምሩ ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ጥሩነሽ ቤጂንግ፣ የካቲት 12ና አበበች ጎበና ሆስፒታሎች ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል ጤና አገልግሎት ትግበራ ገብተዋል።
በተጨማሪም በዓመቱ መጨረሻም ራስ ደስታ፣ ጋንዲ መታሰቢያ፣ ዘውዲቱ እና ምኒልክ ሆስፒታሎች በ2015 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ የዲጂታል አገልግሎቱን እንዲጀምሩ ይደረጋል ብለዋል።
እንደ ዶክተር ዮሐንስ ገለጻ፤ በአራቱ ሆስፒታሎች የትግበራ ሥራው ከ50 በመቶ በላይ ተጠናቋል። በመሆኑም ከግብዓት አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮች ቢኖሩም በዚህ ዓመት አስፈላጊ እቃዎችን በማሟላት ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሰራ ነው።
የጤና የመረጃ አያያዝ ሥርዓት መዘመን አለበት ያሉት ኃላፊው፤ የዲጂታል ሥርዓቱ በመረጃ ላይ ተመስርቶ ውሳኔ ለመስጠት፣በጤና ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ጥራት ለማስጠበቅ ጥቅም ላይ ይውላል ሲሉ አስረድተዋል።
ዶክተር ዮሐንስ እንዳስታወቁት፤ ዲጂታል አሰራሩ የወረቀት ወጪን በማስቀረት እና የስራ ቅልጥፍናን በማሳደግ የተገልጋዮችን እርካታ የሚያሳድግ ነው።
ሥርዓቱ በተገልጋዩ በኩልም ይስተዋሉ የነበሩ እንግልቶችን የሚቀንስ ነው ያሉት ዶክተር ዮሐንስ፤ በተለይ ካርድ ሳይዙ ወደጤና ተቋማት የሚመጡ ተገልጋዮችን ለማስተናገድ፣ የተለያዩ የጤና መረጃዎችን ዳግም ይዘው ለማይገኙ ሰዎችና የተመዘገበን መረጃ ከማቅረብ ባለፈ የፋይል መጥፋትን ችግር ለመከላከል ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።
ለዚህ ተግባር በየደረጃው ያሉ ባለሙያዎች ግንዛቤ እየተሰጠ እንደሆነና የሥርዓቱ አስፈላጊነት ላይ ግንዛቤ ከመስጠት ጎን ለጎን አሰራሩ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማስተካከል የሚያስችል ቁጥጥር በጋራ እየተከናወነ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል።
በሆስፒታሎች የተጀመረውን አገልግሎት ወደ ጤና ጣቢያዎች ለማስፋት በተሰራ ሥራ በአሁኑ ጊዜ አራት ጤና ጣቢያዎች ወደ አገልግሎቱ መግባታቸውን ገልጸው፤ በአሁኑ ጊዜ ስምንት ለማድረስ እየተሰራ ነው ብለዋል። በተያዘው ዓመት በ20 ጤና ተቋማት ላይ ተግባራዊ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ኃላፊው አስረድተዋል።
ሶፍትዌር አበልጽጎ የዲጂታል ጤና አገልግሎትን በሆስፒታሎችና በጤና ጣቢያዎች ተደራሽ ለማድረግ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚጠይቅ የገለጹት ዶክተር ዮሀንስ፤ ወጪው ሶፍትዌሩ ተጭኖ ግልጋሎት የሚሰጥበትን ኮምፒውተሮች እንደማይጨምርም ጠቁመዋል።
በአጠቃላይ መሰረተ ልማቱን በ101 ጤና ጣቢያዎችና በሰባት ሆስፒታሎች ተግባራዊ አድርጎ ለማስፋት ብዙ ወጪ የሚጠይቅ መሆኑን ተቁመው፤ የኔትወርኩ ዝርጋታ በሁሉም አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ የሚዘረጋ ይሆናል ሲሉ አብራርተዋል።
በተያዘው ዓመት መጨረሻ በተጨማሪ አራት ሆስፒታሎችና 20 በሚደርሱ ጤና ጣቢያዎች አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ ከተማ አስተዳደሩ በጀት በጅቶ እየሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን የካቲት 21 ቀን 2015 ዓ.ም