የማዕድን ሀብት በባህሪው አላቂ ነው። ይሁን እንጂ በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋለ ለሌሎች ዘርፎች መልማት የማይተካ ሚና ያለውና በኢኮኖሚው እሴት የሚጨምር አዋጭ ኢንደስትሪ ስለመሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ። ማዕድንን ማልማትና ማበልፀግ ለኢንደስትሪ፣ ለግንባታ፣ለግብርናና ለሌሎችም ግብአት በመሆን ከሚኖረው ድርሻ በተጨማሪ ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠርም የመንግሥትን ጫና በመቀነስ ከፍ ያለ ሚና አለው። በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ በግብርናው ዘርፍ የውጭ ምንዛሪን በማስገኘት የመሪነቱን ሚና የያዘው አረንጓዴው ወርቅ ተብሎ ከሚጠራው ቡና ቀጥሎ የማዕድን ዘርፍ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ስለመሆኑም መረጃዎች ይጠቀማሉ።
ከ2004 እስከ 2005 በነበሩት ዓመታት ከአጠቃላይ የወጪ ንግድ ገቢ ውስጥ በማዕድን ዘርፍ በተለይም ወርቅ 19 በመቶ ድርሻ እንደነበረው ይታወሳል። በተለይ ደግሞ በ2004 በጀት ዓመት 602 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር በማስገኘት ከቡና ቀጥሎ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ለመሆኑ የማዕድን ሚኒስቴር ነሐሴ 2012 ዓ.ም አዘጋጅቶ ከነበረው ረቂቅ የማዕድን ሀብት ልማት ፖሊሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በ2010 ዓ.ም ላይ በዓለም አቀፍ የወርቅ ዋጋ መውረድና በአገር ውስጥ በተፈጠረው አለመረጋጋት ለአገራዊ ምርትና ለወጪ ንግድ የነበረው አስተዋጽኦ ወደ ዜሮ ነጥብ አራት እና ሶስት ነጥብ ስድስት መቀነሱን ከሰነዱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። የማዕድን ዘርፉ ትኩረት እንደሚያስፈልገውም ሰነዱ ጠቁሟል።
የማዕድን ግብይት በዓለም ዋጋ ላይ መሠረት ያደረገ በመሆኑ በዋጋ መዋዠቅ ይፈተናል።ልማቱም ከሰላም ጋር ይያያዛል። በመሆኑም የልማት አካባቢ ከፀጥታ ስጋት ነጻ ካልሆነ፣በቴክኖሎጂ የታገዘ ልማት ለማከናወን ኢንቨስትመንቱ ከፍተኛ በመሆኑ የተለየ ትኩረትና ዋስትና ይጠይቃል። ለዚህም ነው ዘርፉ ልዩ ትኩረት ያስፈልገዋል የሚባለው። ማዕድን ከሌሎች ኢንደስትሪዎች ጋር እንዲተሳሰርና ለአገር ልማትም ተገቢውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ለማስቻል አስፈላጊው ሥራ መሰራት እንዳለበት የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ።
መንግሥት በአገርበቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ውስጥ ማዕድንን አንዱ የልማት ዘርፍ በማድረግ በማዕድን ልማትና ግብይት ላይ የሚስተዋሉ ከፍተቶችና ተግዳሮቶች እንዲፈቱ በማድረግ ዘርፉ በአገር ምጣኔ ሀብት እድገት ላይ ጉልህ ሚና እንዲኖረው ለማስቻል የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል።
ዘርፉ በመንግሥት ትኩረት አግኝቶ የዜጎችንም የአገርንም ተጠቃሚነት ማሳደግ እንዲችል የተለያዩ ሥራዎች ተሰርተዋል። ይሁንና የፀጥታና አለመረጋጋት፣ ህገወጥ ግብይት፣የጌጣጌጥ ማዕድናት ለገበያ የሚቀርብበት መነሻ ዋጋ አለመቀመጥ ከዘርፉ ሊላቀቁ ያልቻሉ ማነቆዎች ናቸው። በጌጣጌጥ ማዕድናት በዓለም ገበያ ተፈላጊና የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ትልቁን ድርሻ የያዘው ኦፓል ማዕድን ለህገወጥ ግብይት መዳረጉና የመሸጫ መነሻ ዋጋ ባለመውጣቱ የአገርን ጥቅም እያሳጣ ስለመሆኑ፣ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ መግባት የነበረበት የወርቅ መጠን እያሽቆለቆለ መምጣት በዘርፉ በስፋት ይነሳል። ለእነዚህ ክፍተቶች መፍትሄ ለመስጠት መንግሥት እርምጃዎችን እየወሰደ ቢሆንም ዘላቂ መፍትሄ እያስገኘ አይደለም።
ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ እርምጃ መውሰድ የመንግሥት ኃላፊነት ቢሆንም ችግሩን የጋራ አድርጎ የጋራ መፍትሄ በመፈለግ ረገድ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ይኖራሉ። ከባለ ድርሻዎች መካከልም ባለሙያዎችን በማፍራትና የምርምር ሥራ በመሥራት ላይ የሚገኙት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት (ዩኒቨርሲቲ) መምህራን ይጠቀሳሉ።እኛም ለዘርፉ ካላቸው ቅርበት አንጻር በማዕድን ዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን እንዴት እየታዘቡት እንደሆነና ችግሩንም የጋራ አድርጎ የመፍትሄ ሀሳብ ላይ ሊኖራቸው ስለሚችለው ድርሻ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በባህርዳር ዩኒቨርሲቱ የሥነምድር ሣይንስ (ጂኦሎጂ) ትምህርት ክፍል መምህራንን አነጋግረናል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ በሚገኘው የሥነምድር ሣይንስ (ጂኦሎጂ) ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ወራሽ ጌታነህ፤ የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ባለድርሻዎች በተለያየ መንገድ መንግሥትን ማገዝ የሚችሉበት ሁኔታ ቢኖርም በህግ የሚፈታውን በመፍታት ረገድ ስልጣንና ኃላፊነቱ የመንግሥት ነው ይላሉ። ከልማት እስከ ገበያ ያለው ሰንሰለት በህግ መመራት እንዳለበትና ህግ ሲጣስም በጠንካራ ህግ መመከት እንዳለበትና አሁን በዘርፉ ላይ እየታየ ላለው ህገወጥነት መስፋፋት ህግ ለማስከበር ካለው ጥንካሬ ጋር ያያይዙታል።መንግሥት ህግ የማስከበር አቅሙን ከፍ ማድረግ ካልቻለም ችግሩ በቀላሉ ይፈታል የሚል እምነት የላቸውም።
‹‹በድንበር በኩል የቁም እንስሳት በህገወጥ እንደሚወጡት ሁሉ የማዕድን ሀብቱም በተመሳሳይ ችግር እየገጠመው ነው›› የሚሉት ዶክተር ወራሽ፤ መንግሥት በሌላ ሥራ በተጠመደበት አጋጣሚ በማዕድን ዘርፉ ላይ የተፈጠረው ህገወጥነት ከአቅም በላይ የሚመስል ሁኔታ ቢኖርም ህግ የማስከበሩ ተግባር ልማቱ በሚከናወንበት እስከ ታች ቀበሌ ድረስ በተዘረጋ አሰራር መታገዝ ከቻለ መከላከል እንደሚቻል አመልክተዋል።
ዶክተር ወራሽ ሌላው ያነሱት ለህገወጥ ተግባር ገፊ የሆኑ ምክንያቶችን መፈተሽ እንደሚያስፈልግ ነው። እርሳቸው እንዳሉት የውጭ ምንዛሪ የማግኘት ጉዳይ በመሆኑ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የሚረከብበት ዋጋና እና በኮንትሮባንድ ወይንም በህገወጥ የሚሸጥበት ዋጋ መካከል ያለውን ልዩነት ማየትና ውሳኔም መስጠት ይፈልጋል። አልሚው ለገበያ የሚያቀርብበት ወይንም የሚያስረክብበት ስፍራም ለህገወጥ ገበያ የተጋለጠ ነው።በልማቱ አቅራቢያ ግብይት የሚከናወንበት ባለመቻቸቱ አልሚው ማዕድኑን ወደ ገበያ ይዞ ሲሄድ በህገወጦች የመነጠቅና እነርሱ በሚፈልጉት ዋጋ እንዲያቀርብላቸው የመገደድ ሁኔታ ይፈጠራል። ህገወጦች አቅራቢያ ላይ ገበያ አለመኖርንና የህግ መላላትን ተጠቅመው የሚፈልጉትን እንዳያደርጉ ማድረግ አንዱ መፍትሄ እንደሆነም ሀሳብ ስጥተዋል። እንዲህ ያለው የዘርፉ ተግዳሮት በሌሎችም አገሮች በተመሳሳይ እንደሚያጋጥም ተሞክሮዎች መኖራቸውንና የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ህገወጥነትን እንደሚከላከሉ ጠቁመዋል።
የመንግሥትን ኃላፊነትና ድርሻ እንዲሁም መፍትሄ ያሉትን እንዲህ ከገለጹልን በኋላ፤ በትምህርት ተቋማትና ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት የሚጠበቀውንም እንደሚከተለው አስረድተዋል፤ ምንም እንኳን ህገወጥነቱ ከግንዛቤ እጥረት በመጣ እየተፈጸመ ነው የሚል እምነት ባይኖርም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ካላቸው የማስተማር ተልእኮ አንጻር የጋራ ሥራ ለመሥራት የሚያስችል የምክክርና ግንዛቤ መፍጠሪያ መድረኮች በማመቻቸት ሚናቸውን ሊወጡ የሚችላባቸው እድሎች አሉ።
የህገወጥነትን ሰንሰለት የሚያሳይና መፍትሄም የሚሆን በጥናትና ምርምር የታገዘ መረጃ ለመንግሥት መስጠት የሚቻልበት እድል፣ ወይንም ችግሩን የጋራ እናድርገው የሚል መነሳሳት የለም ወይ? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም ዶክተር ወራሽ ‹‹በእርግጥ መንግሥት ህገወጥነትን ሊከላከልባቸው የሚችላቸው ዘዴዎች ምን? ምን? ናቸው። የሚለው ላይ በመሥራት ማሳየት እንችላለን። ይገባልም። የህገወጥ ንግድ ሰንሰለት ላይ ጥናት በማድረግ የት ላይ ቢሰራ ውጤታማ የሆነ የሀብት ቁጥጥር ማድረግ እንደሚቻል ማመላከት ይቻላል›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
በአንድ ወቅት ከተማሪያቸው ጋር በአማራ ክልል ወሎ ደላንታ አካባቢ በኦፓል ማዕድን ልማት ላይ ከአልሚዎቹ ጀምሮ ለገበያ እስኪቀርብ ባለው ሂደት፣ ልማቱ በአካባቢ ላይ ሊያሳድር ስለሚችለው ተጽዕኖ፣ የአካባቢ ማህበረሰብንም ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ እየተከናወኑ ስላሉ ተግባራት ላይ ባደረጉት መለስተኛ ጥናት የህገወጥነት ድርጊት በተለያየ ሰንሰለት ውስጥ አልፎ እንደሚፈጸም መለየት ችለዋል። በጥልቀት ለማወቅ የሚያስችል መረጃ ለማግኘት ቀላል ሆኖ ባያገኙትም አልሚው፣ ማዕድን አውጪው ወይንም ቆፋሪው፣አልሚዎችን ቀጥሮ የሚያሰራ፣ ማዕድኑን ተቀብሎ ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚያቀርበው፣ ደላላ እነዚህ ሁሉ ተዋናይ መሆናቸውን በመለስተኛ ጥናታቸው መፈተሽ ችለዋል። አንዳንዴ አልሚዎች ያለሙት ማዕድን ወዴት እንደሚሄድ ተቀባያቸውም ማን እንደሆነ መረጃ የማያገኙበት አጋጣሚ መኖሩንና ይህም ህገወጥነቱ ምን ያህል በጥንቃቄ እንደሚከናወን የሚያሳይ እንደሆነ ጥናቱ አሳይቷል።
የሰንሰለቱ መርዘም ችግሩን ውስብስብ እንደሚያደርገው፣ መካከል ላይ ባለው ሰንሰለት መርዘም ህገወጥ ድርጊቱን የሚፈጽመውን ዋና ተዋናይ ለማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነ መረዳት እንደሚቻል የጠቆሙት ዶክተር ወራሽ፤ ሰንሰለቱን በዚህ መንገድ ለይቶ የት ላይ ሰንሰለቱን መስበር ወይንም መበጠስ ይቻላል የሚለው ሰፊ የጥናት ሥራ እንደሚጠይቅ አመልክተዋል።በቀጥታ ከአልሚዎች ጋር ግንኙነት መፍጠርና እነርሱን የሚያነቃቃ ሥራ መሥራትም ሌላው የህገወጥ ድርጊትን መከላከያ መንገድ ሊሆን እንደሚችልና በህገወጥ ድርጊት ላይ የተሰማሩትንም ቢሆን ወደ መንግሥት የሚሳቡበትን ሁኔታ መፍጠርም ችግሩን ለመቀነስ ይረዳል ብለዋል። እንዲህ ያሉ ሀሳቦችን በማመላከት የትምህርት ተቋማት ሚና ሊኖራቸው እንደሚችል ገልጸዋል።
ዘርፉ ላይ የሚስተዋለው ክፍተትና ማነቆ ወደፊት በዘርፉ ለመሰማራት በትምህርት ገበታ ላይ ለሚገኙት ተስፋ የሚያስቆርጥ ሊሆን ይችል እንደሆን በስጋት ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር የለም። እንደውም ብዙ ተስፋ ነው ያለው። ለዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር የማዕድን ሀብት ኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛል። በአገሪቱ ውስጥ የተፈጠረው አለመረጋጋት ችግር ህገወጥነቱን ያባባሰው በመሆኑ እንጂ ሰላም ሲፈጠር የሚስተካከል እንደሆነ አስረድተዋል።
ማዕድንን ማንኛውም ሰው በቦርሳውና በኪሱ ይዞ መዘዋወር መቻሉ ለህገወጥ ተጋላጭነቱን እንደሚጨምር የጠቆሙት ዶክተር ወራሽ፤ ይህ በመሆኑም ማዕድን ከሌሎች ዘርፎች በተለየ የሀብት አስተዳደር እንደሚያስፈልገውና መንግሥትም ይህን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ሀብቱን ሊያስተዳድረው ይገባል ብለዋል።
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የሥነምድር ሳይንስ (ጂኦሎጂ) ትምህርት ክፍል ዲን ዶክተር ምንያህል ተፈሪ በበኩላቸው በማዕድን ዘርፍ ለሚስተዋለው የህገወጥነት መስፋፋት የህግ መላላት እንደሆነ ነው የገለጹት። መንግሥትን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት የየራሳቸው ተልእኮና ተግባር እንዳላቸውና በተሰጣቸው ኃላፊነትም የየድርሻቸውን እንደሚወጡም አመልክተዋል። በዚሁ መሠረት ህግን ማስከበርና ህገወጦችንም በህግ መከላከል የመንግሥት ድርሻ እንደሆነና ጠንከር ያለ ህግ በማውጣት ለችግሩ መፍትሄ መስጠት ይጠበቅበታል ብለዋል።
የትምህርት ተቋማት ዋና ተልእኮ ሀብቱ የሚገኝባቸውን አካባቢዎች፣ የሀብት መጠኑንና ጥራቱን በጥናት ለይቶና በሰነድ አዘጋጅቶ ልማቱን ለሚያስተዳድረው አካል መስጠት እንደሆነ በመጠቆም፤ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲም ‹‹የማዕድን ልማት ስትራተጂክ ዶክመንት›› ወይንም ፍኖተካርታ አዘጋጅቶ ለክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ መስጠቱን ገልጸዋል።በዚህ ሰነድ ውስጥም ህገወጥነትን ለመከላከል መሰራት ሥላለበት ሥራ ለማመላከት ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።ማዕድን ላይ የሚፈፀመው ህገወጥነት በሌላ ጉዳይ በሚፈጸም የወንጀል ድርጊት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ሁሉ ማዕድንን ለግል ጥቅማቸው በማዋል የአገርን ጥቅም በሚያሳጡት ላይ ጠበቅ ባለ የህግ ማእቀፍ እርምጃ መውሰድ ይገባል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች ካላቸው ተልእኮዎች አንዱ የማሕበረሰብ አገልግሎት መስጠት እንደሆነ ይታወቃልና ከዚህ አንጻር ልማቱ በሚከናወንበት ስፍራ ላይ ሊሰራ የሚችል ስራ ይኖር እንደሆነም ዶክተር ምንያህል ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ ዩነቨርሲቲው በዚህ ረገድ ከሚሰራቸው ሰፊ ሥራዎች መካከል አንዱ የማዕድን ልማት በሚከናወንበት አካባቢ ነው።ማዕድኑ በህገወጥ ከአገር እንዲወጣ ከመደረጉ በተጨማሪ እሴት ሳይጨመርበት ለውጭ ገበያ መቅረቡ በራሱ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ እንዳይገኝ ያደርጋል። በመሆኑም እነዚህን መሠረት በማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 17 ቀን 2015 ዓ.ም