ወጣት ሶሽ ፉሪ የቪንቴጅ ቴክኖሎጂስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ነው። ካንፓኒው የሶፍት ዌር ማበልፀግ ሥራ ላይ የተሰማራ ሲሆን ኩባንያውን መመስረትና ወደ ሥራ መግባት ብሎም፤ ለሌሎች ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለው ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ በወጣ በአንድ ወር ዕድሜ ውስጥ ብቻ ነው። ወጣቱ ከዚሁ ጎን ለጎን በሶፍትዌር ማበልፀግ ሙያው ለአገሩም የነፃ በጎ ፈቃድ ሥራዎችን በመስራትም ትልቅ አስተዋጾ አበርክቷል። እያበረከተም ይገኛል። ሶሽ ካበረከታቸው ሥራዎች መካከል በቅርቡ ተመርቆ ወደ ሥራ የገባው “ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አስተዳደር የመረጃ ቋት” ይጠቀሳል።
ወጣት ሶሽ ተወልዶ ያደገው በሻሸመኔ ከተማ ውስጥ ነው። ቤተሰቦቹ ነፃነት የሚሰጥ እና ልጆቻቸው ሀሳብ ሲያመጡና አንድ ነገር የማድረግ ፍላጎት ሲያድርባቸው የማይቃወሙ መሆናቸው አሁን ላለው ማንነቱ ትልቅ መሰረት የጣለለት መሆኑን ይናገራል። ‹‹በእነሱ አቅም መሞከር የሚችሉትን ሁሉ እንዲሞክሩ ይፈቅዳሉ። መሞከር የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥሩና ነፃነቱንም ይሰጣሉ›› ይላል። በተለይ ቢሞክሩት አይጎዱም ብለው የሚያስቧቸው ላይ ሙሉ ፍቃድ ይሰጧቸው እንደነበር ይገልፃል። ወላጆቻቸው ትምህርት ላይና የቤተሰብ ጉዳይ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ቢያደርጉም ከዛ ውጭ ፍጹም ነፃነት የሚሰጡ መሆናቸው በራሱ እንዲተማመንና አዳዲስ ነገሮችን ለመሞከር ተስፋ እንዳይቆርጥ ያገዘው መሆኑን ያስረዳል።
‹‹በተለይ የመንግስት ሠራተኛ የነበረው አባታችን በጣም አንባቢ ነበር›› የሚለው ወጣቱ ሶሽ አባታችዉ ገና የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሳሉ ጀምሮ ለነሱ ዕድሜ የሚመጥኑ መጽሐፍቶችን እንዲያነቡ ዕድሉን ያመቻቹላቸው እንደነበርም ያስታውሳል። ከዚሁ ጎን ለጎንም ኑሮን ለማሻሻል የሚያግዙ የገንዘብ አጠቃቀም ስልቶችን እንዲሁም ከሁሉም ጋር እየተጋገዙና እየተደጋገፉ በሰላም አብሮ መኖር የሚያስችሉ የእርስ በእርስ መስተጋብሮችንና እሴቶችን በአግባቡ እንዲገነዘቡም ያደርጓቸው ነበር።
ወጣቱ የቤተሰብ አስተዳደግ ስርዓቱን ጠቅለል አድርጎ ሲገልፀው ‹‹ቤተሰባችን እኛን በዚህ መልኩ በመቅረጽ በራስ መተማመን ያለው፤ ብዙ ነገር በነፃነት የሚሞክርና ፍርሃት የማያድርበት ዓይነት ሰው ለመፍጠር ሞክሯል ብዬ አስባለሁ›› ይለዋል። ለዛሬ ማንነቱ የጠቀመውና አሁን ላለበት ደረጃ ያበቃው ይሄ ከታች ጀምሮ ሲገነባው የቆየው መልካም ስብዕና እና የአስተዳደግ ስርዓት ድምር እንደሆነም ደጋግሞ ይናራል።
እንደወጣቱ ገለፃ፤ የቤተሰቦቹ መልካም አስተዳደግ ከአፀደ ህፃናት ጀምሮ እስከ 12ኛ ከፍል ያለውን ትምህርቱን በጥሩ ውጤት እንዲያጠናቅቅ አግዞታል። የ12ኛን የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ከወሰደ በኋላ ባመጣው ጥሩ ውጤት በማምጣቱ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርት ክፍልን መቀላቀል ቻለ። የዩኒቨርሲቲው ቆይታው በልዩ ሁኔታ ያሳለፈው ይህ ወጣት በተለይ የአራተኛ ዓመት ተማሪ ሆኖ አንዳንድ ድርጅቶች ላይ በመስራት ገና ሳይመረቅ ብቃቱን አስመስክሯል።
ተቀጥሮ ለሚሰራባቸው ድርጅቶች ትንንሽ ሶፍትዌሮችን እየሰራ የሚያገኘውም ብር በአግባቡ ያስቀምጥ እንደነበር የሚናገረው ወጣት ሶሽ ልክ በ2008ዓ ዓ.ም በኮምፒውተር ሳይንስ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ እንደወጣ ገንዘቡን የራሱን ድርጅት ለማቋቋም አጋጣሚውን የፈጠረለት መሆኑን ያስረዳል። ይህም ታዲያ ተመርቆ ከዩኒቨርስቲ ከወጣ በኋላ እንደ አብዛኞቹ ተመራቂ ወጣቶች በሥራ ፍለጋ አልተንከራተተም። የራሱን ኩባንያ መስርቶ ወደ ሥራ ለመግባትና ለሌሎች በእሱ ዕድሜ ላሉ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ከአንድ ወር በላይ ጊዜ አልፈጀበትም።
ቪንቴጅ ቴክኖሎጂስ ኃላፊነቱ የተወሰ የግል ማህበር የተሰኘው ኩባንያው ነሐሴ 2008 ዓ.ም ሙሉ ሕጋዊ ዕውቅና አግኝቶ ወደ ሥራ መግባቱን ያስታውሳል። ታዲያ በዚህ ወቅት አንዳንዶች እንደ ተመረቀ ፈጥኖ የራሱን ኩባንያ በማቋቋም ወደ ሥራ የገባው ቤተሰብ የገንዘብ ድጋፍ አድርጎለት ወይም የሆነ ሰው ገንዘብ ሰጥቶት እንደሆነ አድርገው ያስቡ ነበር። በርግጥ እንደተመረቀ ምንም ልምድ ሳይኖረው፤ ገበያውን ሳያውቅ የራሱን ድርጅት ወደማቋቋም መግባት በጣም ከባድ መሆኑን ያውቃል። ይሁንና ሶሽ እንደተመረቀ ወደ ሥራ እንዲገባ ያስቻለው እውነታ የአራተኛ ዓመት ተማሪ ሆኖ ከትምህርት ሰዓት ውጪ በነበረው ትርፍ ጊዜ ውጪ ላይ መሥራቱና የተማረውንና አራት ዓመታት በጥሩ ንባብና በተለያየ ጥረት ሲያዳብረው የቆየውን ዕውቀት ወደ ተግባር ለመለወጥ መቁረጡ እንደሆነ ያምናል።
ሶሽ እንደሚለው፤ አንድ ተማሪ ዩኒቨርሲቲ ሲገባ ብዙ ዕውቀቶችን ይገበያል ተብሎ ይታሰባል። መምህራኖቹ የሰጡትን ሁሉንም ነገር በሙሉ ልቅም አድርጎ ይይዛል። በድምሩ ዩኒቨርሲቲ ፍፁም ያበቃል ተብሎ ይገመታል። በአገሪቱ የትምህርት ፖሊሲ ወይም ነባራዊ ሁኔታ ብዙዎች ዩኒቨርሲቲ ላይ መምህራኖቻችን በሚሰጡን ትምህርት ብቻ ገበያ ውስጥ ገብቶ የሚሰራበት ዓይነት ዕውቀት አይገኝም።
‹‹ዩኒቨርሲቲ ለእኛ ለወደፊት እድገትና የተቃና ስኬታማ ሕይወት መሰረት ነው የሚጥልልን። ሌላውን በራሳችን ጥረት እየሞከርን ነው ማግኘት ያለብን›› የሚለው ወጣቱ የራሱን ተሞክሮም በማሳያነት ይጠቅሳል። ሆኖም በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዘንድ ያለው ምልከታ በተሳሳተ መልኩ መሆኑን ያስረዳል። ዩኒቨርሲቲ ፍፁም አድርጎ ያበቃኛል ወይም በተማርኩት ብቻ ገበያ ውስጥ ገብቼ እሰራለሁ የሚል እንደሆነ ይገልፃል። ነገር ግን ይሄ አይነቱ ምልከታ ትክክል አለመሆኑን ይናራል። ከዚያ ይልቅም ገበያ ውስጥ ገብቶ ለመሥራት የሚያበቃው የራስ ጥረት እንደሆነ እና ተጨማሪ ዕውቀትና ንባብ አስፈላጊ መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ ማሰግባት እንዳለባቸው ያመለክታል።
‹‹ዩኒቨርሲቲዎች በተጨባጭ መሰረት ነው የሚሰጡን። መምህራኖቻችን ደግሞ መስመሩን ያሳዩናል። ከዚያ በኋላ ያለውን እኛ ነን በንባብና በተለያየ መንገድ የምናጎለብተው›› ብሏል ወጣቱ ገበያ ውስጥ ገብቶ ለመሥራትና ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችለውንና እሱ ስኬታማ የሆነበትን መንገድ ለዕድሜ አቻዎቹ ሲያመላክት።
የራሱን ኩባንያ ካቋቋመ በኋላ ሁለት ቦታ ይሰራ እንደነበር የሚገልፀው ወጣቱ የራሱ ኩባንያ ካማቋቋም ባለፈ በሌሎች ተቋማት ተቀጥሮ ይሰራ የነበረውም ልምድ ለማግኘትና በመስኩ ላይ ያለውን የገበያ ሁኔታ ለማወቅ እንደሆነም ይናገራል። ‹‹ምን ዓይነት ስትራቴጂዎችን እንደሚከተሉ ለማወቅ እንዲሁም በዘርፉ ልምዴን እንዳዳብር አግዞኛል›› ሲልም ያስረዳል። ወጣቱ የራሱን ኩባንያ ሥራ ከማስኬድ ጎን ለጎን በቅጥር ይሰራ የነበረውን ሥራ አቁሞ ሙሉ በሙሉ ወደ ራሱ ድርጅት የተመለሰው በራሱ ለመቆም የሚያስችለው አቅም መገንባቱን ካረጋገጠ በኋላ እንደሆነም ነው የጠቆመው።
እንደወጣት ሶሽ ገለፃ፤ በራሱ የመቆም አቅም መገንባቱን ካረጋገጠ በኋላ በአጠቃላይ ኩባንያውን በመሰረተ በስድስት ዓመታት ውስጥ በርካታ ወጣቶችን መቅጠር ችሏል። ያሳተፈው ደግሞ በቋሚ እና በኮንትራት ቅጥር እንዲሁም የተማሪዎች የስራ ላይ ልምምድ ነው። በስራ ላይ ልምምድ ብቻ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ 40 ተማሪዎችን አስተናግዷል። ከነዚህ ውስጥም የራሳቸውን ሥራ እንዲፈጥሩና ተቀጥረው እንዲሰሩ ዕድል ያመቻችላቸው ተማሪዎችም ነበሩ።
‹‹ከአዲስ አበባ፤ ከባህር ዳር፣ ከአዳማ፣ ከዲላ፣ ከድሬደዋ፣ ከአምቦ፣ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመጡ ተማሪዎች የራሳቸውን ሥራ እንዲፈጥሩና ተቀጥረው እንዲሰሩ ካደረግናቸው ውስጥ ይጠቀሳሉ›› ይላል። በነዚህ ወጣቶች ስኬታማም ስራ መሰራት መቻሉን ጠቅሶ፤ በእሱ ፕሮግራም ውስጥ ከነበሩ ተለማማጅ ተማሪዎች ከፊሎቹ የራሳቸውን ስራ መጀመራቸውን፤ ቀሪዎቹ ደግሞ የተሻለ ደሞዝ ተከፋይ መሆናቸውንም ነው ያመለከተው። በተጨማሪም የውጭ አገር የትምህርት ዕድል ያገኙም፤ እየሞከሩ የሚገኙም እንዳሉ ተናግሯል።
በአሁኑ ወቅት አስር ቋሚ ወጣት ሠራተኞችና ሌሎችም የኮንትራት ሠራተኞች እንዳሉት የሚናገረው ወጣቱ በአገሩ ውስጥ ኩባንያ መስርቶ ገንዘብ ከማግኘት ጎን ለጎንም በርካታ ነፃ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን ከወጣቶች ጋር በመቀናጀት እየሰራ ስለመሆኑም ያስረዳል። ወጣቱ በዚህ በኩል ከአቻዎቹ ጋር እየሰራቸው ያሉት ነፃ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች በርካታ ቢሆኑም በቅርቡ ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው “ብሄራዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አስተዳደር የመረጃ ቋት” ሳይጠቀስ የሚያልፍ አይደለም።
ወጣቱ ይሄን የመረጃ ቋት መሥራት ያስቻለው አንድ ዕለት ማለዳ በቴሌቪዥን የተመለከተው ዜና እንደሆነ ይጠቅሳል። ‹‹ከውጭ አገር የመጣ የህክምና ባለሙያ በእረፍት ጊዜው በሙያው አገሩን በበጎ ፈቃደኝነት ለማገልገል ቢፈልግም የሚሄድበትን ቦታ ባለማወቅ መቸገሩን ሲናገር ሰማሁ›› ሲል መነሻውን ያስታውሳል። ይሄንኑ በቴሌቪዥን ያየውን ቅሬታም መሰረት አድርጎ ‹‹አገራችን ላይ ነው፤ ገንዘብ እየሰራን ነው ያለነው። ሁሌ ከአገር ብቻ አይወሰድም፤ ለአገራችንም መስጠት አለብን›› ሲልም የመረጃ ቋቱን በመሥራት በሙያው ለአገሩ ነፃ አስተዋጾ ማበርከቱን ይናገራል።
ሶሽ እንደሚለው እንደኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ ወጣቶች ብዙ ጥያቄዎችን ሲጠይቁ ይታያል። ብዙ የጎደሉንና ሊሟሉ የሚገቡ ነገሮች በመኖራቸው ጥያቄ መጠየቃቸው ትክክል ነው። ይሁንና ጥያቄውን ሲጠይቁ የአቅማቸውን አበርክተው ቢጠይቁ የተሻለ ነው። በተለይም ወጣቱ በተሰማራበት ሙያ ራሱን ማብቃት ይጠበቅበታል። በተሰማሩበት መስክ ተወዳዳሪ ሊያደርገኝ የሚችል ክህሎቱ አለኝ ወይ? ብለው ራሱን መጠየቅ አለባቸው።
ተመርቀው በሚወጡበት ዘርፍ ‹‹የስራ ዕድል ቢሰጠኝ መሰረታዊ የሆኑትን ስራዎችን እንኳን መስራት እችላለሁ ወይ?›› ብሎ ራስን መጠየቅም እንደሚገባ ይጠቅሳል። ‹‹ከዩኒቨርሲቲ ዲግሪውን ይዤ በመውጣቴ ብቻ ብቁ ነኝ ማለት አይገባም። አስቀድሞ እኔ ተወዳዳሪ የሚያደርገኝ ብቃት ላይ ደርሻለሁ የሚለው ጥያቄ ውስጥ መግባት አለበት›› ሲል አበክሮ ይናገራል።
አክሎም ‹‹ ብዙ ወጣቶች ሰቅለው ደህና ውጤት በማምጣት መውጣትን ብቻ ነው የሚፈልጉት። ስለዚህም ድርጅቶች ሲቀጥሩ ብቃታችውን እንጂ ሰቅለው የተመረቁትን ውጤት አይተው ቀጥሮ አያውቅም›› በማለት ይገልፃል።
ወረቀቱ ሊጠቅማቸው የሚችልበት ቦታ ሊኖር በመቻሉ መስማማቱን የሚናገረው ሶሽ ገበያው የሚፈልገው የሚሰጣቸውን ሥራ የሚወጡበት አቅም ላይ የደረሱ ሰዎችን እንደሆነ ያሰምርበታል። በመሆኑም ወጣቶች ከዩኒቨርሲቲ ሲወጡ ዲግሪያቸውን የሚመጥን ብቃት ይዘው መውጣት አለባቸው›› ሲልም መልክቱን አስተላልፏል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 17 ቀን 2015 ዓ.ም