ባህል ሰፊና ጥልቅ የሆኑ የአንድ ማህበረሰብ እውቀቶችን፣ እምነቶችን፣ ኪነ-ጥበቦችን፣ ህጎችን፣ ልማዶችን፣ ወዘተ … ያካተተ በህብረተሰቡ ዘንድ ለረጅም ዘመናት ሲከናወን የነበረ በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለውና በህበረተሰቡ የተፈጠረና የሚያድግ ነው። ባህል የማንነት መገለጫ አስተሳሰብና ባህርይ ሆኖ አንደኛው ከሌሎች የሚማሩበት፣ የሚያዋህዱት ለቀጣይ ትውልድም የሚያስተላልፉት ነው።
ባህል ውርርስ፣ ሽግግር፣ ትውውቅም ነው። ውርርስ ሲባል ደግሞ መቅዳት እና ማስቀዳት ያለበት ነው። ለምሳሌ፡- አንድ ሰው ከአፍ መፍቻ ቋንቋው በተጨማሪ ሌሎች ቋንቋዎችን ሲማር ወይም መናገር ሲጀምር የቋንቋ እውቀቱን ብቻ ሳይሆን ባህሉንም አብሮ ይቀዳል። እውቀት እና ከእውቀት የሚመነጩ ሀሳቦችንም ጭምር ይማራል። ያ ማህበረሰብ ምን ይፈልጋል፣ ምን ይጠላል የሚለውን ጭምር ይለያል። ባህል ማለት ከአንዱ መውሰድ ለሌላው መስጠት ያለበት፤ የተሰጠውም ለሌላ ማቀበልም ነው። ለመሆኑ ስለባህል ይህንን ያህል ለምን አነሳን ከተባለ ዛሬ ልናነሳው የወደድነው ጉዳይ ባህልን በብዙ ትርጉሙ የሚያሳየን ስለሆነ ነው።
ጉዳዩ ወደ ሰሜኑ ክፍል ጎራ ብለን ያገኘነው ሲሆን፤ ዘመናትን በማህበረሰቡ የኖረና አሁንም ያለ ነው። ታሪክም ባህልም ሆኗቸው ይኖሩበታል። ለልጅ ልጃቸውም እያስተላለፉት ማህበራዊ ትስስራቸውን፣ ኢኮኖሚያዊ ከፍታቸውን ይገነቡበታል። ፖለቲካውን ጭምር ዲሞክራሲ ያደረጉበት መርሃቸው ሆኖላቸዋል። ‹‹ አጉማስ ›› እያሉ የሚጠሩት ባህላቸውን። በተለይም በአርሶ አደሩ አካባቢ በብዛት የሚተገበርና የሚኖርበት ሲሆን፤ ከአዲስ ሰብል ስብሰባ ጋር በስፋት ያነሱታል። ይተገበሩታልም።
ይህንን ባህላዊ ትውፊት ኑሯቸው ካደረጉት መካከልም አርሶ አደር ወልዴ ያለው አንዱ ናቸው። በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን በፎገራ ወረዳ ወርቅደሞ ቀበሌ ውስጥ ይኖራሉ። ይህንን ባህል ከልጅነታቸው ጀምሮ ያውቁታል። አሁን ደግሞ ራሳቸውም ደጋሽና አጉራሽ ሆነው ለልጆቻቸው እያስተማሩትም፤ እያወረሱትም ይገኛሉ።
እንደ እርሳቸው አባባል፤ አጉማስ ማለት የውድማ ረድኤት፣ በረከት ማለት ነው። እህሉ ደርሶ በደቦ ሲወቃ አለያም ሲሰበሰብ የደከሙ አካላት እንስሳቱን ጨምሮ አርፈው የሚመገቡት ስርዓትም ነው። ከዚያ ሻገር ሲልም አጉማስ የድግሱ ስያሜ ይሆናል። ማለትም እናቶች ምግብና መጠጡን ሲያዘጋጁ ‹‹ ለአጉማስ የሚሆን ምግብ እያዘጋጀሁ ነው›› ይላሉ። ይህ ምግብ ቅድሚያ ከደረሰው እህል አለያም ከነባሩ እህል መዘጋጀት ይችላል። ጤፍን ግን አይነካም። ምክንያቱም በመጨረሻ የሚደርስ እህል ስለሆነ ለድግሱ አይደርስም። የመሰባሰቢያውና አብሮ የመመገቡ መንስኤም እርሱ እንደሆነ በስፋት ይወሳል።
አጉማስ ሌላም ትርጉም አለው። ይህም እህሉን ከእብቁ የሚለየው ንፋስ ሲሆን፤ አጉማስ መጣች በማለት ማህበረሰቡ ፈጥኖ ወደስራው የሚገባበት አቅጣጫ ጠቋሚና አመላካች ሲሳይ ተደርጎ ይወሰዳልም። ስለዚህም አጉማስ ማለት እንደ አርሶ አደር ወልዴ ገለጻ፤ ሲሳይ፣ ጸጋ፣ ሀብት፣ በረከት እንደማለት ነው። ታዲያ ይህ ድግስ ምን ይጠቅማል? ከተባለ አሁንም አርሶ አደሩ እንዲህ ያብራሩታል።
የመጀመሪያው ሁሉም የሚያርፍበትና በጋራ የሚመገብበት ሲሆን፤ ማህበራዊ ትስስርን ለማጠናከር ሁነኛ መፍትሄን ይሰጣል። ምክንያቱም በመሰባሰቡ ውስጥ የትናንቱን እያወሳ የዛሬን፣ የነገንና የሚመጣውን እቅዱን ያዘጋጃል። ማን ምን ማድረግ እንዳለበት የሥራ ድርሻን ይከፋፈላል። ከዚያ ሻገር ሲልም የድግሱ ተሳታፊ ሥራ ላይ ተሰማርቶ የነበረው ብቻ ሳይሆን አላፊ አግዳሚውም በመሆኑ ዝምድናን ይፈጥራል። ማለትም በአጉማስ ቅምሻ አበልጅነት ይመጣል። መሃን የሆኑ ጥንዶች ባይወልዱም በድግሱ የተደሰቱ ተሳታፊ እናቶች ወይም አባቶች ለደጋሹ ዝምድናቸውን ለማጠንከር ሲሉ ልጃቸውን በአበልጅነት ይሰጡታል። ከዚያ ባሻገር በኑሮ ዝቅተኛ የሆኑ ወላጆች ከአጋጠሙም አሳድገው ብለው እስከመስጠት ይደርሳሉ።
ይህ አጋጣሚ ደግሞ በስፋት የሚታየውና የሚፈጠረው ለመውለድ የተቃረበች ሴት ወደ ጤና ጣቢያ በምትሄድበት ጊዜ እንዳይሸታት ተብሎ ከምግቡ እንድትቀምስ ስትደረግና ወልዳ ስትመጣ በእንክብካቤ ሲቀበሏት አለያም ደግሞ እዚያው ድግሱ ቤት ስትወልድ ነው። ይህም በአካባቢያቸው በተደጋጋሚ እንደተከሰተ ያነሳሉ። እርሳቸው ጭምር በዚህ አይነት ሁኔታ ዘመድ እንዳፈሩ ይናገራሉ።
ሌላው በአጉማስ ድግስ የሚፈጠረው ‹‹ልጅህን ለልጄ›› የሚለው አይነት የጋብቻ ዝምድና ሲሆን፤ ተግባሩ የሚፈጸመው ግን እንደ ልጆቹ ፈቃደኝነት ነው። ቤተሰቡ የወደደውን ልጆቹ ከተቀበሉት ቤተሰባዊ ዝምድናን ይፈጥሩበታልና አጉማስ ዘር ማብዢያ፣ ቤተሰብ መፍጠሪያ ነው ይላሉ አርሶ አደሩ ወልዴ።
አጉማስ ሰው የማይለይበት ሁሉም በሕብረት የሚቋደስበት ሲሆን፤ ደጋሹ እህሉ በረከት እንዲያገኝ አላፊ አግዳሚውን ብሉልኝ ጠጡልኝ የሚልበት ነው። ያንን የተመገበ ሁሉ ምላሹ ገንዘብ አለያም ሌላ ነገር ሳይሆን ምርቃት ብቻ ነው።
አጉማስ በደቦ የሚከወን ስለሆነ ለቀን ሰራተኛ የሚወጣውን ከፍተኛ ገንዘብ ይቆጥባል። ለማጓጓዣ የሚወጣውንም ወጪ እንዲሁ ይቀንሳል። ምክንያቱም የአካባቢው ጋማ ከብት በሙሉ ተሰብስቦ እህሉን ወደጎተራው እንዲያስገባ ያደርገዋል። አጉማስ ሰዓትም ቢሆን ቆጣቢ ነው። በአጭር ጊዜ ስራውን አከናውኖ ሌላ ስራ ላይ ሰውዬው እንዲሰማራ ያደርገዋል።
አጉማስ የእርቅ ማዕድም ነው። እርቅና ሰላም ይሰፍናል። ደም የተቃባ ሳይቀር ይቅር ይባባልበታል። ምክንያቱም ለአጉማስ የተዘጋጀውን ምግብ ሁሉም መቋደስ ግዴታው ነው። የተጣላ ጎረቤት እንኳን ይህንን ድግስ ማለፍ አይችልም። ካለፈ የእርሱን የሚበላለት የለም። ስለዚህም በድግሱ ተሳትፎ በልቶና ጠጥቶ መርቆ መንገዱን ይቀጥላል። የተጣላውም ሰው ቢሆን አይቶት ዝም አይልም። ይህንን ካደረገ በረከቱ እንደሚነጠቅበት ያውቃል። እናም በረከቴን እንዳታሳጣኝ ሲል ቅመስልኝ ይላል። እናም በአጉማስ ድግስ መቃቃር ሳይሆን መቀራረብ ብቻ ይጎላል። ተሰባስቦ መብላትም ልዩ ቦታ ይሰጠዋል።
ሌላው የአጉማስ ፋይዳ አብሮ ከመብላት ጋር ያለው መልካም ዝምድና ሲሆን፤ ጠብን እስከማብረድ የሚደርስበት ነው። ‹‹አብሮ የበላ ቅዱስ ዮሐንስ አይሽረውም›› እንደሚባለው ምንም ነገር አዲስ ሆኖ ቢመጣ አብሮ የበላን ሰው ሊለውጠው የሚችለው ነገር የለም። አጉማስ ደግሞ አብሮ መብላትና አብሮ መስራት ነው። ስለዚህም ወንድማማችነት ይጠነክርበታል እንጂ መለያየት አይሰፍንበትም። ለፍቅር እንጂ ለመጥፎ ነገር እንዳይተሳሰብ የማድረጊያ መንገድ ነው።
ሳይንስን ወይም ሃይማኖትን መነሻ ያደረጉና ለህብረተሰቡ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ እሴቶች መልካም ዋጋ ያላቸው ልማዳዊ ድርጊቶች ከሚባሉት መካከል አንዱ አጉማስ እንደሆነ የነገረን ደግሞ ቤተሰቦቹ ስሙን አጉማሴ ብለው የጠሩት እንግዳችን ነው። እነርሱ እንደሚለው፤ አጉማስ ለሀገርና ህዝብ ደህንነት፣ ብልፅግናና ማህበራዊ ትስስር ዋነኛና አስፈላጊ ባህል ነው። የአጉማሱን ምግብ የቀመሰ ሁሉ በአስተሳሰብ የቀና፣ አገሩን የሚወድና መልካም ባህሎቻችንን ይዞ ለልጅ ልጁ የሚያስተላልፍ ነው። በባህሉ የሚኮራም ነው።
የአጉማስ ድግስ ጊዜ የማያርፍ ነገር የለም። ሁሉም ድካማቸውን እንዲረሱ ይደረጋሉ። እንስሳት ሳይቀሩ ልክ እንደሰው ሁሉ እየበሉ እንዲቦርቁና እረፍት እንዲያገኙ ይደረጋሉ። ምክንያቱም በደቦው እህል ሲያደርሱ፣ ሲወቁ ቆይተዋል። እናም አጉማስ የእንስሳትን እረፍት አስፈላጊነት የሚያሳይ ባህል ነው። በተጨማሪም አጉማስ የራበው ሰው የሚመገብበት ነው። ምክንያቱም መንገደኛው በጉዞ ደክሞት አረፍ የሚልበት ነው። ገንዘብ ሳያወጣ ረሀቡን አስታግሶ ፀሐይን አሳልፎ መንገዱን የሚቀጥልበት ነውና።
ነደያንም በዚህ ግብዣ ላይ እንደማንኛውም ሰው እስከፈለጋቸው ድረስ እንዲመገቡና እንዲጠጡ ይፈቀድላቸዋል። ምክንያቱም የአጉማስ ድግስ በረከትና ደስታ መፈለጊያ ነው። በጣም የሚገርመው በአጉማስ ድግስ ሰርገኛ ጭምር ይጋበዛል። በአካባቢው ላይ የሚያልፍ ከሆነ ያንን ረግጦ መሄድ አይችልም። ገብቶ ተመግቦና ጠጥቶ መርቆ የመሄድ ግዴታ አለበት።
በአጉማስ የሚሰበሰበው ምርቱ ብቻ አይደለም። ሰውም እንስሳትም ጭምር ነው። ምክንያቱም አንድ ሰው ጤፉን መውቃት ሲያስብ ሊኖረው የሚችለው በዛ ከተባለ ሁለት በሬ ነውና በደቦ ሲሰራ ደግሞ ይህ ብቻ በቂ ስለማይሆን ከአካባቢው ሰው ከብቶችን በመበደር አምጥቶ ይወቃል። ምርቱን ወደቤቱ ሲያስገባም እንዲሁ እንስሳቱን ከየጎረቤቱ ሰብስቦ ነው። በተጨማሪም ውቂያውን ሲያደርግ በህብረት ማለትም በደቦ ሰዎች ተሰብስበው ነው። እናም በመሰባሰብ ውስጥ ያለውን ፋይዳ ያሳያል።
አጉማስ የጎረቤትን ንብረት እንደራስ የመጠቀም ዕድልን ይፈጥራል። ምክንያቱም በአካባቢው አጉማስ ደጋሹ ማን እንደሆነ ይታወቃልና እርሱ ሰብስቦ ወስዷቸው ይሆናል ነው የሚባለው እንጂ ለምን የእኔን የጋማ ከብት ነካህ ብሎ ነገር የለም። እናም በአጉማስ እኛ ኢትዮጵያውያን አብሮ የመብላት ብቻ ሳይሆን አብሮ የመስራት ባህላችንን እናዳብርበታለንም ሲል ይናገራል ወጣቱ አጉማሴ።
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ምግብን በእጁ ይዞ ሳለ እንግዳ ቢመጣ እንብላ ማለት የለመደ ነው። ይህን ባይል ደግሞ “እንብላ አይባልም እንዴ?” ተብሎ በእንግዳው በነገር ሸንቆጥ ይደረጋል። እርሱም ይሉኝታ ይዞት “ይቅርታ ዘንግቼው እኮ ነው” ብሎ እንብላ የሚል ግብዣ ያቀርባል። ይህንን ደግሞ አጉማስ በእጅጉ የሚያረጋግጥና የሚያዳብር ነው። ምክንያቱም በእርሱ ድግስ ዘርቶ እንዳጨደ ከባለቤቱ ይልቅ አላፊ አግዳሚው ነው ጠግቦ ወደቤቱ የሚሄደው። ስለዚህም በአጉማስ ውስጥ የነገ ተስፋን ማለምለም አለ፤ አብሮነትን ማጎልበትም እንዲሁ አንዱ መገለጫው ነው።
ወጣቱ አጉማሴ ይህ ወቅት የሚታለፈው በዚህ አይነት ባህላችን ውስጥ ስንጓዝ ብቻ ነው ባይ ነው። ምክንያቱም ከመሰባሰብ ይልቅ መራራቅን የመረጥንባቸው ረጃጅም ጊዜያትን እንድናሳልፍ የሆነው በባህላችን መመራት ባለመቻላችን ነው።
የእኔ እንጂ የእኛን እየረሳን በመሆናችን ነው። አብሮነታችንን መገንባት ሳይሆን ማፈራረስን እየለመድነው ስለመጣን ነው። ስለሆነም አሁን በቃን ማለት አለብን። እነዚህን ባህሎቻችንን በመጠቀም ለለውጥ መነሳት ይኖርብናል። የሚበታትነንን አዲስ ባህል መቀበል ሳይሆን የሚያጠነክረንን ነባር ባህላዊ እውቀታችንን መጠቀም ይገባናልም ሲል ይመክራል። እኛም የራስ የሆነ ባህል ሀገር አልሚ ነው። ወደ አንድነታችን ይመልሰናል። ገንዘብን ብቻ ሳይሆን ወዳጅነትን ያጠብቅልናል። ስለዚህም አጉማስን የመሰሉ ባህላዊ ስርዓቶች ይጎልብቱ የሚለውን መልዕክት በማስተላለፍ ሃሳባችንን እንቋጫለን። ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 17 ቀን 2015 ዓ.ም