‹‹ … ይህ ቀን ለአፍሪካውያን በሙሉ ታላቅና ታሪካዊ ቀን ነው፡፡ ሕዝቦቻችን ከእኛ የሚጠብቁትን ተግባር ለመፈፀምና ክፍለዓለማችን በዓለም አቀፍ ጉባዔ የሚገባትን ትክክለኛ ስፍራ እንድትይዝ ለማድረግ ተሰብስበናል» የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ግንቦት 17 ቀን 1955 ዓ.ም ሲበሰር ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ካደረጉት ንግግር የተወሰደ ነው፡፡
ቀኑ በርግጥም በቅኝ አገዛዝ ስር ለዘመናት ሲማቅቁ ለኖሩ አፍሪካውያን ታላቅና ታሪካዊ ነበር። በተለይ ነፃ የነበሩ የአህጉሪቱ አገራት መሪዎች በአንድ መድረክ ተገናኝተው ስለቀጣይዋ አፍሪካ ዕጣፈንታ መምከር መቻላቸው በወቅቱ ስለነፃነታቸው መራራ ትግል ላይ ለነበሩ የአህጉሪቱ ሕዝቦች ከፍያለ ተስፋ ፈንጣቂ ታሪካዊ ክስተት ነበር።
መሪዎቹ በወቅቱ በአንድ በኩል በነፃነት ትግል ውስጥ ላሉ አፍሪካውያን ያስተላለፉት የትግል አጋርነት፤ በሌላ በኩል ደግሞ የአህጉሪቱ ሕዝቦች በመራራ ትግላቸው የተጎናጸፉትን የፖለቲካ ነፃነት ምሉዕ ለማድረግ የኢኮኖሚ አቅማቸውን አጠናክረው መገኘት እንደሚኖርባቸው የደረሱበት የውሳኔ ሀሳብ ከፍ ያለ አህጉራዊ መነቃቃት መፍጠሩም የሚታወስ ነው፡፡
በአህጉሪቱ አገራት መካከል የተጀመረውን ኅብረት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግም ሆነ መሪዎቹ የደረሱባቸውን የውሳኔ ሀሳቦች ተፈጻሚ ለማድረግ በተቋም ደረጃ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ከብዙ ፈተናዎች በኋላ መስርተው ተንቀሳቅሰዋል። በዚህም የአፍሪካውያን ድምፅ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሻለ ተሰሚነት እንዲኖረውና ሕዝቦቿም ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችለዋል።
ይህ በአባቶቻችን በፈተና የተሞላ የፖለቲካ ሕይወትና መራራ ትግል የተገኘው ስኬት ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ አልፎ አሁን የተሻለ በሚባል የፖለቲካ ቁመና ላይ ቢገኝም፤ አፍሪካውያን አሁንም ቢሆን ፖለቲካዊ ነፃነታቸውን በሁለንተናዊ መልኩ ለመተግበር በሚያስችል የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ አይደሉም።
አፍሪካውያን ከነፃነት ማግስት ጀምሮ የበለጸገች አህጉር ከመፍጠር ይልቅ፤ በብዙ የውጭ ጣልቃ ገብነቶች የግጭት ማዕከል ሆናለች። በዚህም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቿ ለሞት፤ ለስደትና ለከፋ ጉስቁልና ተዳርገዋል። የረሀብና የእርዛት ተምሳሌት፤ የድንቁርናና የኋላቀርነት ማሳያ ሆነዋል።
አህጉሪቱ በተፈጥሮ በታደለቻቸው ጸጋዎች ተረጋግታ እንዳትጠቀም፤ አለመረጋጋት የሚፈጥሩ ውስጣዊና ውጪያዊ ፈተናዎችን በመፍጠር፤ ጸጋዎቿ የእርግማን ያህል ተግዳሮት እንዲሆኑባት ተደርገዋል፤ አሁንም እየተደረጉ ነው። በዚህም ብዙ አምራች ዜጎቿ ለጥፋት ተልዕኮዎች ብረት አንግበው በባሩድ ጪስ ውስጥ ለመኖር ተገደዋል።
በዛሬዪቱ አፍሪካ ያሉ የአህጉሪቱ መሪዎች ይህንን እውነታ በመለወጥ፤ የትናንት አባቶቻችን ብዙ ዋጋ ከፍለው እውን ያደረጉትን የፖለቲካዊ ነፃነት፤ ወደ ተሟላ ሁለንተናዊ ነፃነት ማሻገር ይጠበቅባቸዋል። ይህ በአዳራሽ ውስጥ ስብሰባ በሚደረስ የውሳኔ ሃሳብ ብቻ የሚወጡት ሳይሆን ከፍያለ መስዋዕትነት የሚጠይቅና ብርቱ ትግል የሚሻ ነው።
በተለይም የአህጉሪቱ ሕዝቦችን በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች በማስተሳሰር፤ ጠንካራ የሕዝቦች አንድነት መፍጠር፤ በዚህም የጋራ ራዕይ /ነገዎች እንዲኖራቸው ማስቻል ወሳኝ ነው። የቀደሙት አባቶቻችንም ስለአንድነትና ስለኅብረት ብዙ የሰበኩት የአህጉሪቱ ተስፋ መሠረት የሚያደርገው ይህንኑ እውነታ ስለሆነ ጭምር ነው።
አፍሪካውያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን ተደማጭነት ለማሳደግም ሆነ፤ በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ውስጥ ያላቸውን ተገቢ ስፍራ ለመያዝ ከሁሉም በላይ በመካከላቸው ያሉ አላስፈላጊና ከፋፋይ ልዩነቶችን ማስወገድ ይኖርናቸዋል። ልዩነቶች ሲያጋጥሟቸውም እንደ አንድ የቤተሰብ አባል በሮቻቸውን ዘግተው መምከርና ለችግሮቻቸው የራሳቸውን መፍትሄ ማፈላለግ ይጠበቅባቸዋል። ለዚህ ደግሞ በቂ አቅም እንዳላቸው በቅርቡ ኢትዮጵያ ችግሯን የፈታችበት መንገድ ምስክር ነው፡፡
የአህጉሪቱ መሪዎች ለዚህ የሚሆን በቂ ዝግጅትና ቁርጠኝነት መፍጠር ከቻሉ፤ የውጭ ጣልቃ ገብነቶችን በማስወገድ፤ የአፍሪካ እና ሕዝቦቿን የነገ እጣ ፈንታ ብሩህ ማድረግ ብዙ ፈተና ሊሆንባቸው አይችልም። የዛሬው 36ኛ የኅብረቱ አባል አገራት የመሪዎች ስብሰባም ለዚሁ ግብአት የሚሆን አቅም መፍጠር ያስችላል!
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2015