በሀገራችን አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ከሚፈታተኑ ችግሮች መካከል የማምረቻ ቦታ እጥረት ዋነኛው ነው። የማምረቻ ቦታ እጥረት የአምራቾቹ የብዙ አመታት ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል።
በአዲስ አበባ ከተማም ይህ ችግር በእጅጉ ሲነሳ ነው የኖረው። የማምረቻና ቦታ ችግር በአነስተኛና መካከለኛ አምራቾች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ በማሳደር ይታወቃል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ይህን የማምረቻ ቦታ ችግር ለመቅረፍ ከዚህ ቀደምም በርካታ የመስሪያ ቦታዎችን ለወጣቶች ያስተላለፈ ቢሆንም ችግሩ አልተቀረፈም።
ከተማ አስተዳደሩ ያለፉትን ድክመቶች በማረም ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት እስከ ዛሬ ከተሰሩት የተለየ ግዙፍ የኢንዱስትሪ ክላስተር እየገነባ ይገኛል። የኢንዱስትሪ ክላስተሩ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ማምረቻነት የሚውል ነው። የኢንዱስትሪ ክላስተሩ ግንባታ እየተካሄደ ያለው የከተማዋ ማስተር ፕላን ለኢንዱስትሪ በለየው አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ውስጥ ነው።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትላልቅ ፕሮጀክቶች ጽሕፈት ቤት የአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ክላስተር ግንባታ አስተባባሪ ኢንጂነር ታደሰ ለማ እንደሚሉት፤ ግንባታው እየተፋጠነ ያለው የአዲስ አበባ ከተማ አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ክላስተር እስከ ዛሬ ከተሰሩት የተለየ፣ ግዙፍና ዘመናዊ ነው። ካላስተሩ በሦስት ሎቶች ተከፍሎ ነው እየተካሄደ የሚገኘው።
በአሁኑ ወቅት የሎት ሁለት እና ሦስት ግንባታ እየተፋጠነ ይገኛል። ለሁለቱ ሎቶች ከሰባት ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተይዞላቸዋል። የሁለቱ ሎቶች ግንባታ ባለፈው ጥቅምት ወር አጋማሽ የተጀመረ ሲሆን፣ በቀጣይ ሁለት ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዶ ነው ወደ ትግበራ የተገባው ፤ ሌሎች ግንባታዎችም በሂደት ይጀመራሉ።
የሎት ሦስት ግንባታ 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ የተበጀለት ሲሆን፣ ግንባታውን ቲ.ኤን.ቲ የተሰኘ ሀገር በቀል ድርጅት እያከናወነው ይገኛል። በሁለት ነጥብ አራት ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፈው ሎቱ ስድስት ህንጻዎችንም ይይዛል። ከስድስቱ ህንጻዎች መካከል ሦስቱ ለእንጨት እና ብረታ ብረት ስራ የሚውሉ ሲሆን፣ ሦስቱ ደግሞ ኬሚካል እና ፕላስቲክ ለማምረት የሚውሉ መሆናቸውን ኢንጂነር ታደሰ ተናግረዋል።
ሎት አንድን ኤም.ሲ.ጂ ኮንስትራሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ ሀገር በቀል ድርጅት እየገነባው መሆኑን የጠቆሙት ኢንጂነር ታደሰ፤ በአንድ ነጥብ ዘጠኝ ሄክታር ላይ የሚያርፍ መሆኑን ጠቁመዋል። ሎቱ ጂ+4 የሆኑ አራት ህንጻዎችን እንደሚያካትት፣ ግንባታቸው ሲጠናቀቅ ለአልባሳት እና ጨርቃ ጨርቅ ማምረቻነት ታሳቢ ተደርገው እየተሰሩ መሆናቸውንም ነው ያብራሩት። በሎት አንድ ውስጥ እየተገነቡ ካሉት አራት ህንጻዎች ውስጥ የሁለቱ ህንጻዎች ግንባታ በጥሩ ፍጥነት እየተካሄደ ነው።
እንደ ኢንጂነር ታደሰ ማብራሪያ፤ በአሁኑ ወቅት ግንባታቸው እየተፋጠነ የሚገኙት ሁለቱ ሼዶች እና በቀጣይ ግንባታቸውን የሚጀመሩት ሼዶች በተለያዩ ሎቶች ተከፍለው የሚሰሩት ሼዶች ለእንጨትና ብረታ ብረት፣ ለኬሚካልና ፕላስቲክ እንዲሁም ለጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ከመዋል ባሻገር ለቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ ለኤሌክትሮኒክስ እና መድኃኒት ፋብሪካ፣ ለአግሮ ፕሮሰሲንግ እንዲሁም ለኮንስትራክሽን ግብዓት ማምረቻነትም ይውላሉ። በከተማዋ ባሉት ኢንዳስትሪያሊስቶች በጥናት የተለዩ የኢንዱስትሪዎች ስብስቦችን ይይዛል። ከኢንዱስትሪ በተጓዳኝ አገልግሎቶችን ሊሰጡ የሚችሉ ማዕከላትን የሚያካትት ነው።
የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ አስፈላጊው ትኩረት ቢሰጠው በፌዴራል መንግሥት ተገንብተው ለሀገሪቱ ከፍተኛ ፋይዳ እያስገኙ ካሉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች የበለጠ ሰፊ የእድገት እድሎችን ማስመዝገብ የሚያስችሉ ናቸው የሚሉት ኢንጂነር ታደሰ፤ ሼዶቹ ሀገራዊና ቀጣናዊ ፋይዳዎችም እንደሚኖራቸው ጠቁመዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኩ ግንባታ በተሻለ ጥራት እና ለወደፊት ለሚሰጠው አገልግሎት ሊረዱ የሚያስችሉ የተለያዩ ማሽነሪዎችን ለመግጠም እንዲያስችል ተደርጎ ከወዲሁ በዲዛይኑ ላይ ተካቶና ታልሞ እየተሰራ መሆኑን ኢንጂነር ታደሰ ያብራራሉ። ይህም ክላስተሩ እንደተጠናቀቀ በፍጥነት አገልግሎት እንዲሰጥ ከማስቻሉም በላይ ለኢንዱስትሪያሊቶቹ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል፣ ተወዳዳሪነታቸውንም ከፍ ያደርጋል ብለዋል።
ክላስተሩ ለኢንተርፕራይዞች ተግዳሮት የነበረውን የማምረቻ ቦታ ችግር የሚፈታ ከመሆኑም ባሻገር የማምረቻ አቅማቸውን ያሳድጋል ያሉት ኢንጂነር ታደሰ፤ በቦታ ችግር ምክንያት የአቅማቸውን ያህል ለማምረት ሲቸገሩ የነበሩትን ኢንተርፕራይዞችን ከችግር የሚያላቅቅ ነው ብለዋል።
ኢንጂነር ታደሰ እንደሚሉት፤ በአሁኑ ወቅት የኑሮ ውድነት እንዲባባስ እያደረጉ ካሉ ምክንያቶች አንዱ የተለያዩ ምርቶች ከውጭ ሀገራት በውጭ ምንዛሬ መግባታቸው ነው። የእነዚህ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ክላስተር ግንባታ ሲጠናቀቅ በርካታ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት እንደሚቻልም ይገልጻሉ፤ ይህም የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር ፋይዳው የላቀ ነው ይላሉ።
ክላስተሩ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የሚያመርቱ አምራቾችን የሚያበረታታ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬን እንድታድን የበኩሉን ሚና እንደሚጫወትም ይጠቁማሉ። በሼዶቹ ውስጥ ለውጭ ገበያ በሚመጥን መልኩ የሚያመርቱ ምርቶችም እንደሚኖሩም ተናግረው፣ በዚህም ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት እንደሚቻል ያመለክታሉ።
ክላስተሩ ከማምረቻ ባሻገር መሸጫ ቦታዎችን ያካትታል። አረንጓዴ ቦታዎችም የሚኖሩት ሲሆን፣ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓቱም በተሻለ ሁኔታ የተሳለጠ እና ከአካባቢ ጋር የሚስማማ እንዲሆን ይደረጋል፤ ይህ መሆኑም የአካባቢ እና የሰው ደህንነትን ከብክለት በመጠበቅ እንዲሁም መሬትን በቁጠባ ለመጠቀም ያስችላል። የከተማ እድገትም በእቅድና ስርዓት እንዲመራ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተጠቁሟል።
የክላስተሩ ግንባታ ጠቀሜታው ዘርፈ ብዙና እጅግ ሰፊ ቦታ የሚይዝ መሆኑን አመልክተው፣ ክላስተሩ በሚገነባበት አዋሳኝ የሚገኝ ከፊል ገጠር አካባቢዎችንም ጭምር የማነቃቃት አቅም እንዳለውም ኢንጂነሩ ጠቁመዋል።
እንደ ኢንጂነር ታደሰ ገለጸ፤ በአሁኑ ወቅት በሎት ሦስትና ሎት አንድ በአማካይ እስከ 500/ አምስት መቶ/ ለሚሆኑ ዜጎች ጊዜያዊና ቋሚ የስራ እድል የተፈጠረ ሲሆን፤ የክላስተሩ ግንባታ ሲጠናቀቅ በማዕከሉ ገብተው የማምረት ስራ የሚሰሩ ኩባንያዎች በስራቸው በመቅጠር ለበርካቶች የስራ እድል ይፈጥራሉ።
ፕሮጀክቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ሲሚንቶ እንደሚፈልግ የጠቆሙት ኢንጂነር ታደሰ፤ ሲሚንቶ አቅርቦት መቆራረጥ ችግርን ለመቅረፍ የግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽህፈት ቤቱ ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች ለፕሮጀክቱ ቅድሚያ እንዲሰጡ የድጋፍ ደብዳቤዎችን እየጻፈ ሲሆን ፋብሪካዎችም ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ግንባታ ቅድሚያ እየሰጡ መሆኑን ጠቁመዋል።
የቢቲ.ኤን.ቲ ኮንስትራክሽንና ትሬዲንግ የአዲስ አበባ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ግንባታ ፕሮጀክት የሎት ሦስት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሰብስቤ በሪሁን እንደተናገሩት፤ በሎት ሦስት የተካተቱ የስድስት ሼዶች ግንባታ በፍጥነት እየተከናወነ ነው። በተያዘለት ጊዜ እና ጥራት የፕሮጀክቱን ግንባታ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።
እንደ ኢንጂነር ሰብሰቤ ገለጻ፤ ለግንባታው የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ሙሉ በሙሉ በማዘጋጀት ነው ወደ ስራ የተገባው። ፕሮጀክቱ ከተጀመረ 81 ቀናት/ መረጃው የተሰጠው ባለፈው እሮብ ነው/ አካባቢ እንደተቆጠረ አንስተዋል። በዚህም ጊዜ ውስጥ የፕሮጀክቱ ግንባታ አምስት በመቶ ተጠናቋል። በኮንስትራክሽን በጣም ጊዜ እና ጉልበት የሚወስድ ከባዱ ስራ ተጠናቋል። በአሁኑ ወቅት የአራቱ ሼዶች የመሰረት ስራዎች አልቀዋል።
ሁለት ብሎኮች በሚገነቡበት ቦታ ላይ የነበረው የጤፍ አዝመራ አለመነሳትና በቦታው አቋርጦ የሚያልፍ የውሃ መስመር በጊዜ ያልተነሳበት ስራውን አስተጓጉለውት እንደነበር አብራርተዋል ።
በተለይም የውሃ መስመሩ ህንጻ በሚገነባበት ቦታ መሃል ለመሃል ሰንጥቆ የሚያልፍ እንደነበር የጠቆሙት ኢንጂነሩ፤ የውሃ መስመሩን ከቦታው አንስቶ ወደ ሌላ ቦታ መውሰድ ጊዜ መውሰዱን ገልጸዋል። አሁን የጤፉ አዝመራም የውሃ መስመሩ መነሳታቸውን አስታውቀው፣ የመሰረተ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት የስድስቱም ሼዶች ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑንና ከተያዘለት የጊዜ ገደብ አስቀድሞ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሀገሪቱ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የግንባታ ስራዎች መስራታቸውን የጠቀሱት ኢንጂነር ሰብስቤ እንደሚሉት፤ በአዲስ አበባ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ክላስተር ግንባታ ላይ ያለው ቅንጅታዊ አሰራር እጅግ የሚያስደስት ነው። የፕሮጀክቱ ባለቤት የሆነው የትላልቅ ፕሮጀክቶች ጽሕፈት ቤት፣ አማካሪ ድርጅቱ እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ያላቸው ቁርጠኝነት፣ ተነሳሽነት እና ፍላጎት ይበል ያሰኛል። የሚያቀርቡ ጥያቄዎች ውለው ሳያድሩ ወዲያው ምላሽ እየተሰጣቸው ነው። ከሲሚንቶ አቅርቦት ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችም በጊዜው መፍትሔ ተሰጥቶታል። አሁን ያለው የቅርብ ክትትል እና ቁርጠኝነት መቀጠል አለበት። ያለው ቁርጠኝነት እና ተነሳሽነት ለሌሎች ፕሮጀክቶችም አርዓያ ይሆናል።
እስካሁን እንዲህ አይነት ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለሀገር በቀል ፕሮጀክቶች የመስጠት ልምድ እምብዛም ነበር የሚሉት ኢንጂነር ሰብስቤ፤ መንግሥት እንዲህ አይነት ትልቅ ፕሮጀክት እንዲገነቡ ለሀገር በቀል ድርጅቶች እድል በመስጠቱና እና እምነት በመጣሉ ትልቅ ኩራት እንደሚሰማቸው ገልጸው፤ መንግሥትን አመስግነዋል። መንግሥት የሰጠውን አደራና እምነት ሳያጎድሉ ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ፣ በጀትና ጥራት በማጠናቀቅ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል በቁርጠኝነት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
የአካባቢው መስተዳድር የሚያደርገው ትብብር እጅግ የሚደነቅ ነው ያሉት ኢንጂነር ሰብስቤ፣ ለግንባታው የሚውል ግብዓት በአካባቢው በብዛት እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ ይህን ግብአት ኮንትራክተሩ እንዲጠቀም ሁኔታዎችን በማመቻቸት ረገድ መልካም ትብብር እያደረገ ነው ብለዋል። በቅድሚያ በተደረሰው ስምምነት መሰረት ቦታዎችን አመቻችተው አቅርበዋል ያሉት ኢንጂነር ሰብስቤ፣መስተዳድሩ በባለቤትነት ስሜት እየተባበሩ መሆኑን ገልጸዋል። ይህ መልካም ግንኙነት እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
ፕሮጀክቱ ግንባታ በተጀመረበት ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፕሮጀክቱ ከተማ አስተዳደሩ ለኢንዱስትሪ የሰጠው ትኩረት ማሳያ ነው ብለው ነበር። በከተማ አስተዳደሩ በጀት እና እቅድ የተገነባ የመጀመሪያው ፕሮጀክት ነው ብለዋል። የፕሮጀክቱ ፋይዳም ዘርፈ ብዙ መሆኑን ጠቁመዋል። ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ወደ አገልግሎት መግባት እንዲችል አስፈላጊው ድጋፍ እና ክትትል እንደሚደረግም ቃል ገብተዋል።
ክላስተሩ የማምረቻ ቦታ ችግርን ከመቅረፍ ጀምሮ የኢንዱስትሪ ልማት ሽግግር፣ የውጭ ምንዛሬ ወጪን ለማስቀረት፣ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለማስገኘት፣ ለዜጎች ሰፊ የስራ እድል ለመፍጠር፣ በዘርፉ ለሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠትና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንደሚኖሩት ተስፋ ተጥሎበታል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2015