‹‹ኑሮ ተወደደ›› አድማጭ ያጣ ሕዝባዊ ሙዚቃችን ከሆነ ሰነባበተ። በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የምንታዘበው ደግሞ አያድርስ ነው። ትንሽ ትልቁ ሁሉ በዚሁ ጉዳይ የሚጮህና የሚያማርር ነው። የሽንኩርትና የዘይት ዋጋ ጨመረ ብሎ፣ የቤት አከራዩም የቤት ኪራይ ይጨምራል። የቤት ኪራይዋን ያሰላው ነጋዴም ዞሮ በዕቃ ዋጋ ያካክሰዋል። ታዲያ ማን ማንን ይከሳል? ከአንዱ ጋር በተለኮሰው እሳት ሁሉም የራሱን ቤንዚን እያርከፈከፈበት የሰደድ እሳት ሆኖ ይቀራል።
በዝሆኖች ትግል የሚጎዳው ሳሩ ነውና አንዱን በአንዱ ለማካካስ በሚደርገው ትግል ውስጥ ከምኑም የሌለበት ምስኪኑ፣ ከየአቅጣጫው የሚወረወረውን ድንጋይ ተሸካሚ ሆኖ ይቀራል። የሚሸጠውም ሆነ የሚያከራየው የለውምና ከየቱም ሳይሆን በመሃል ቤት ይታሻል። እንግዲህ የምንታዘበው እውነታ ማንም ማንንም የማይምርበት ዘመን ላይ መድረሳችንን ነው።
በዚህ ጉዳይ ላይ ሌላው የምንታዘበው አንድ ነገር ቢኖር፤ በኑሮ ተወደደ ጩኸት እጅጉን ሲያማርሩ የሚታዩት አንዳንድ የፊት መስመር ተሰላፊና ቀንደኛ የኑሮ ውድነት ተዋናዮች መሆናቸው ነው። ትንሿን የኑሮ ውድነት በሰበብ አስባቡ እያጦዙ ያልተገባቸውን ያህል ትርፍ በሚያግበሰብሱት ዘንድ ጩኸትና ምሬቱ የባሰ ሲሆን እንመለከታለን። ከሆቴል ገብቶ በአንድ ጀንበር አምስትና ስድስት ሺህ ከፍሎ የሚወጣውም፣ በየጉሊቱ እየቸረቸረ ሽሮ መብላት ያቃተውም እኩል ካማረረ ይሄ የኑሮ ውድነት ብቻ ሳይሆን እብደትም ጭምር ነው። አንድም ቀን የኑሮ ውድነትን መራራ ጽዋ ጠጥተን የማናውቅ ሰዎች ከተጎዱት በላይ ስንጮህ ያየ ሰው ብቻ ሳይሆን፣ ፈጣሪም ጭምር ይታዘበናል። የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጣጣ እንዳይሆንብን ቢያንስ ‹‹ተመስገን›› ማለትን እንልመድ።
የኑሮ መወደድ እርግጥ ቢሆንም፣ ነገር ግን ያልተወደደውን ያህል እንዲወደድ፣ ያልጨመረውን ያህልም እንዲጨምር የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች እንዳሉ እንታዘባለን። ኑሮ ተወደደ እያሉ ከሚጮሁት መሃል ሁሉም ባይሆኑም፣ አንዳንዶቹ ነጋዴዎች ራሳቸው በኑሮ መወደድ ውስጥ ቀንደኛ ተዋናይ ናቸው። ጩኸታቸውም የንግዱ ዓለም ፕሮፖጋንዳ መሆኑ ነው። አንድን ዕቃ ሳይጠፋ ጠፋ፣ ሳይወደድ ተወደደ እያሉ ምስኪኑ ሕዝብ አምኖ እንዲቀበል ማድረግ ነው። የዛኔ ታዲያ አማራጭ የለውምና ‹‹አይ ዕድሌ›› በማለት እያማረረም ቢሆን ይገዛታል እንጂ ወዴት አባቱ ይሄዳል።
በኑሮ ውድነት ሰበብ ከየድሃው ኪስ እንደ እንፋሎት እየተነኑ የሚወጡት ገንዞቦች መዳረሻቸው ያው የስግብግቡ ነጋዴ ሆድና ኪስ ናቸው። አንዳንዴ በነጋዴው ላይ አምስት ብር የጨመረ እንደሆን ሕዝቡ ላይ አስር ብር አድርገው ይጭኑበታል። ‹‹በልጅ አመሀኝቶ ይበላል እንኩቶ›› አለ ያገሬ ሰው። ያቺን ጭማሪ አሳቦ በሕዝብ ኑሮ ላይ ቁማር የሚጫወቱ ነጋዴዎችን መታዘብ አሁን አሁን የተለመደ ነገር እየሆነ መጥቷል። አንዳንዱ ቦታ ላይ የሚለጠፉት የዋጋ ዝርዝሮችም ወረቀት ብቻ ናቸው።
ይህንን አላደርግም ብሎ በዋጋው ለመሸጥ የሚወስን ነጋዴ ቢኖር እሱንም ሌሎች ከጨዋታ ውጪ እንዳያደርጉት በመፍራት ተያይዞ ይገባበታል። ‹‹ተስማምተው የፈ… አይሸትም›› እያሉ ለሕዝቡ ምን ያህል እንደሚከረፋ አይረዱትም። ታዲያ የሠሩትን ሠርተው የልባቸውን ካደረሱ በኋላ በኑሮ ተወደደ እሮሮና ዋይታ እነርሱም ከሕዝቡ ጋር ተቀላቅለው ሲጮሁ የሚታዩትን አንዳንድ ነጋዴዎች እንደማየት የሚያናድድ ነገር የለም።
የአንዳንዱ ክፋት ደግሞ ጫፍ የወጣ ነው። ገና የዛሬ አንድ ወር የነዳጅ ዋጋ ይጨምራል መባሉን የሰማ እንደሆን ያለውን ቀብሮ በ‹‹የለም›› አብዮት ባለመኪናውን፣ ከዚያም በላይ ሕዝቡን ያሰቃያል። ሌላው መንግሥት ለሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ ሲያደርግ፣ ተካፍለን እንብላው ይመስል፣ በእያንዳንዱ ዕቃ ስንት ልጨምር እያለ ያለ እንቅልፍ የሚያድረውን ልቡ ይታዘበው። ያገኘውስ እየመረረውም ቢሆን ያካፍለዋል፤ ጭማሪው የማይመለከተው ምስኪንስ? ከየትኛውም ነገር በፊት የነበረንን የመተሳሰብ ባህል ዛሬ በአጉል ስግብግብነት ስንፍቀው መታየት ፍጹም በእኛ አያምርም።
በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ውስጥ ለኑሮ ውድነት መንስኤ የሚሆኑት ሌላኛዎቹ አላባውያን ደግሞ ባለ ገንዘብ የሆኑ ሰዎች መሆናቸው ነው። ገበያው የነፃ ገበያ ሥርዓት ነውና ሻጩ የገዢውን ጀርባ አጥንቶ ሊገዛኝ ይችላል ብሎ የሚያስብበትን ዋጋ ከመጥራት ወደኋላ አይልም። እነርሱም ገንዘብ ስላላቸው ብቻ በተባለው ዋጋ ሁሉ ገዝተው ይመለሳሉ። የሌለው ከአንድ ቡቲክ ቆሞ ላንቃው እስኪደርቅ ለአስርና አስራ አምስት ብር ሲከራከር፣ ያለውና ባለ ገንዘቡ መጥቶ ያለምንም ድርድር የተባለውን መዥረጥ አድርጎ ይከፍላል።
ታዲያ ኑሮ እንዴት ላይወደድ ኖሯል.. ይህን ያየ ነጋዴም ዓይኑን ሳያሽ መደብሩን የጨረታ አዳራሽ ያደርገዋል። የዛኔ ድሃው ዓይኑ እያየ ከጨዋታው ውጪ ይሆናል። ‹‹ከሌለህ የለህም›› የሚለው አባባል በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የእውነትም እየሠራ እንደሆነ እንታዘባለን። ምንም ያህል ገንዘብ ቢኖረን እኛ ቀለል አድርገን የምናደርጋቸው ነገሮች ሌላውን እንደሚጎዳ ማወቅ አለብን። እነዚህ ጥቃቅን ነገሮች እየተበራከቱ፣ ከግለሰቦች አልፎ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ሥርዓት እንደሚያናጋ ቆም ብለን ልናስተውል ይገባል።
በነፃ የገበያ ሥርዓት በጣም ብዙ ተጠቃሚነቶች ቢኖሩም፣ በዚያው ልክ የሚጎዳው ከታች ያለው ምስኪኑ ማኅበረሰብ ለመሆኑ አያጠራጥርም። አገራችን የምትከተለው የነፃ ገበያ ሥርዓት ነው ቢባልም በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ መንግሥት እጁን ሲያስገባ ይታያል። ይህ ጥሩ ነገር ሆኖ ሳለ በነካ እጁ ሌሎች የተንቦረቀቁ ነገሮች ላይም ቁጥጥር ቢያደርግ መልካም ነበር። በአሁኑ ሰዓት በአገራችን ላይ የሚታየው የኑሮ ውድነት ሳይሆን ራስ ወዳድነት ነው። ይህ ራስ ወዳድነት ነው። እንግዲህ በኑሮ ውድነት ቤንዚን ላይ እሳት እየለኮሱ የራሳቸውን ኑሮ ብቻ ከሚያሞቁ ስግብግቦች ይሰውረን!
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2015