ወጣት ጌታቸው ድንቅነህ በተማረበት አፕላይድ ኬሚስትሪ ትምህርት ዘርፍ በተለያዩ ፋብሪካዎች ውስጥ አገልግሏል። በዚህም ሰፊ ልምድ ማካበት ችሏል። በፋብሪካ ውስጥ ያሉ ምርቶችን ምስጢርም ጠንቅቆ አውቋል። በተማረበት የትምህርት መስከ አንድ ቀን አዲስ የንግድ ፈጠራ ሃሳብ ይዞ እንደሚመጣም የዘወትር ሃሳቡ ነበር። ታዲያ ምን ያደረጋል ወጣት ጌታቸው የንግድ ሃሳቡን እንዴት እውን ማድረግ ይችላል?
እርሱ የተፈጠረው እንዲህ ዓይነቱን ሃሳብ እምብዛም በማይበረታታበትና ድጋፍ በማይደረግበት አገር ላይ ነው። በሰለጠነው ዓለም የቢዝነስና ንግድ ሃሳብ ከማንኛውም ሸቀጥ በላይ ውድ ነው። ምን ያህል ገንዝብ ሊያስገኝ እንደሚችል በመገንዘብም ለቢዝነስ ወይም ንግድ ሃሳቡ ከፍተኛ ግምት ይሰጣል። እንዲያውም የቢዝነስና ንግድ ሃሳቦችን በመሸጥ የሚተዳደሩና ሕይወታቸውን የለወጡ ጥቂት አይደሉም።
አዎ! በሰለጠነው ዓለም አዳዲስ የቢዝነስና ንግድ ሃሳቦች ዕለት በዕለት ይመነጫሉ፤ ልክ እንደሸቀጥ ለገበያ ይቀርባሉ። ግለሰብንና አገርንም ይለውጣሉ። አዳዲስ የቢዝነስ ሃሳቦችን ጠቀሜታ አስቀድመው የተረዱ አገራትም ሰዎች አዳዲስ የንግድና የቢዝነስ ሃሳቦችን እንዲያመነጩና ሃሳባቸው ተወዳድሮ ገበያ እንዲያገኝ የሚያስችል አሠራር እስከመዘርጋት ደርሰዋል። ይህንኑ አሠራር የሚከውኑ ተቋማትም በሕግ ተቋቁመው የንግድ ሃሳብ ውድድር በማካሄድ የምጡቅ ንግድ ሃሳብ አመንጪ ባለቤቶችን አወዳድረው ይሸልማሉ። ከሽልማት በዘለለም ሃሳባቸው መሬት ወርዶ ወደተግባር እንዲቀየር አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋሉ። ወይም ደግሞ ሌሎች እንዲደግፏቸው ሁኔታዎችን ያመቻቻሉ።
በኢትዮጵያም በአንድ ወቅት የንግድ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ግን ውድድሩ ቆሟል። ጅምሩ ጥሩ ቢሆንም ሊዘልቅ ግን አልቻለም። ከሁለት ዓመት በፊት ግን በቀድሞው የፌዴራል ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን በአሁኑ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አዘጋጅነትና በማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ድጋፍ ‹‹ብሩህ›› የተሰኘ የንግድ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር በተለያዩ ዘርፎች ተካሂዷል።
የውድድሩ ዋነኛ ዓላማም በአገሪቱ የተለያዩ ዘርፎች ቁልፍ ችግሮችን ለመፍታትና የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚችሉ አዳዲስ ሀሳቦች ያሏቸው ወጣቶችን ለማበረታታት መሆኑ ታውቋል። የሦስት ዓመት መርሃግብር መሆኑም ተነግሯል። ይኸው መርሃ ግብርም ነው ወጣት ጌታቸው ድንቅነህን የንግድ ፈጠራ ሃሳቡን ከጓደኞቹ ጋር በመሆን አቅርቦ እውን እንዲሆን ያስቻለው።
በመጀመሪያ ወጣት ጌታቸውና ጓደኞቹ በሚኖሩበት አካባቢ ያለውን ነገር በጥሞና ማየት ጀመሩ። በተለይ በዱራሜ ከተማና አካባቢው ለመስኖ እርሻ የሚመች ሰፊ መሬት እንዳለና ከዓመት እስከ ዓመት የሚፈስሱ ወንዞች መኖራቸውን አረጋገጡ። አካባቢው በስፋት ቲማቲም አብቃይ መሆኑንም ተረዱ።
በአካባቢው ቲማቲም በስፋት ቢበቅልም ወዲያውኑ ጥቅም ላይ ካልዋለ አልያም ለሚፈልገው አካል በቶሎ ካልደረሰ የመበላሸት ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑን ያውቃሉ። በዚህም ቲማቲም ተቀነባብሮ ሳይበላሽ ረጅም ጊዜ እንዲቆይ የሚያስችል አሠራር ባለመኖሩም አገሪቱ ከውጭ አገራት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የተቀነባበሩ የቲማቲም ምርትችን ወደ አገር ውስጥ እንደምታስገባም ተገነዘቡ። ከዚህ ችግር በመነሳትም ወጣት ጌታቸው የሲቪል ኢንጂነሪንግ ባለሞያ ከሆነው አቤል አድማሱና የማርኬቲንግ ባለሞያ ከሆነችው እየሩሳሌም ኃይሉ ጋር በመሆን ቲማቲምን በአገር ውስጥ በማቀነባበር ለአገር ውስጥ ገበያ የማቅረብ ሀሳብ መጣላቸው።
ሃሳቡ ድንቅ ቢሆንም ቲማትምን ሳይበላሽ ለረጅም ጊዜ የሚያቆዩ ‹‹ሚቲየል ፓራብን›› እና ‹‹ሶዲየም ቤንዞይት›› የተባሉ ኬሚካሎችን ከውጭ አገር ማስገባት ግድ ሆነባቸው። የንግድ ሃሳቡን ለመጀመር ለእነርሱም ሆነ ለአገሪቱ ከባድ ፈተና መሆኑን ተረዱ። በይበልጥ ደግሞ ኬሚካሎቹ ለካንሰር፣ ስኳርና የደም ግፊት በሽታዎች የሚያጋልጡ በመሆናቸው ኬሚካሎቹን በተፈጥሯዊ መንገድ ማግኘት እንዳለባቸው ከድምዳሜ ላይ ደረሱ።
በመቀጠል የሁለቱንም ኬሚካሎች ባህሪና ስሪት ካጠኑ በኋላ ኬሚካሎቹን በተቀራራቢነት የሚተኩት አራት የተፈጥሮ ቅመሞች ማለትም የቀረፋ፣ነጭ ሽንኩርት፣ ቁሩንፉድና ዝንጅብል ስብጥሮችን በማቀያየር ተደጋጋሚ ሙከራ አደረጉ። ከ11ኛ ጊዜ ሙከራቸው በኋላም የቲማቲም ማቆያ መድኃኒቱን መስራት ቻሉ። በሂደትም የንግድ ፈጠራ ሃሳቡ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የንብረት ባለቤትነት መብት እንዲኖረው ተደረገ።
በኢትዮጵያ ጥራትና ደረጃዎች ባለስልጣን መፈተሽ ስለነበረበትም በአርተፊል ሲሙሌሽን ፍተሻ ተደርጎለት የባክቴሪያ መፈጠርን ሙሉ በሙሉ እንዳቆመ ተረጋገጠ። በይበልጥ ደግሞ በዚህ ዓይነቱ የማቆያ መንገድ የተቀነባበረው የቲማቲም ምርት ከስኳርና ኬሚካል የፀዳ በመሆኑ ከስኳርና ከካንሰር ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን ሞት የሚቀንስ መሆኑም ታወቀ። ምርቱ ምንም ሳይበላሽ እየተከፈተና እየተዘጋ ለስድስት ወራት እንደሚቆይም በሚመለከተው አካል ተረጋገጠ።
በዚህ መሀል በቀድሞው የፌዴራል ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን በአሁኑ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አዘጋጅነትና በማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ድጋፍ ‹‹ብሩህ›› የተሰኘ የንግድ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር በተለያዩ ዘርፎች ተካሄደ። የውድድሩ ዋነኛ ዓላማም በአገሪቱ የተለያዩ ዘርፎች ቁልፍ ችግሮችን ለመፍታትና የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚችሉ አዳዲስ ሃሳቦች ያሏቸው ወጣቶችን ማበረታታት ነበር። በዚህ ውድድር ከቀረቡ 356 ተወዳዳሪዎች ውስጥ ሰባዎቹ ለመጨረሻው የማጣሪያ ዙር አልፈው ከሰባዎቹ ሃያዎቹ በማሸነፋቸው እያንዳንዳቸው 200 ሺህ ብር ተሸልመዋል። ከውድድሩ አሸናፊዎች ውስጥም ከወላይታ ሶዶ አንድ፣ ከአዲስ አበባ 11፣ ከዱራሜ አንድ እንዲሁም ከደብረ ማርቆስ ሁለት ይገኙበታል።
ከእነዚሁ አሸናፊዎች መካከል ደግሞ አምስቱ ሙሉ በሙሉ በሴቶች የሚመሩ የንግድ ፈጠራ ሃሳብ ውድድሮች ሲሆኑ፤ 14ቱ ሴቶች በከፊል የሚገኙበት ነበሩ። በውድድሩ ቀርበው ሽልማት ካገኙት መካከል ታዲያ የእነጌታቸው ድንቅነህ የከንባታ ጠምባሮ ዞን ዱራሜ ከተማ የራንታ ቲማቲም ማቀነባበሪያ የንግድ ፈጠራ ሃሳብ አንዱ ነበር።
የንግድ ፈጠራ ሃሳቡ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን የተቀነባበረ የቲማቲም ምርት የሚያስቀር፣ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥርና የሚታይ በመሆኑ ከቀረቡት የንግድ ፈጠራ ሃሳቦች ውስጥ አሸናፊ ለመሆን በቅቷል። ተስፋ ከተጣለባቸው የንግድ ሥራ ፈጠራ ሃሳቦች ውስጥም አንዱ ለመሆን ችሏል። በአሁኑ ጊዜም የንግድ ፈጠራ ሃሳቡ ከሃሳብነት በዘለለ ወደ ተግባር ተቀይሮ ጥቅም ላይ መዋል የሚችል መሆኑ በኢፌዴሪ ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ተረጋግጧል።
በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከውጭ አገር የሚገባውን የተቀነባበረ የቲማቲም ምርትም በሁለት ከመቶ እንደሚተካም የንግድ ፈጠራው ሃሳብ አመንጪዎቹ አረጋግጠዋል። ምርቱ ምንም ዓይነት ሰው ሰራሽ ቀለምና ኬሚካል ያልያዘና በአንቲ ኦክሲደንትና ማግኒዢየም የበለፀገ በመሆኑም ከልብ ጋር በተያያዙ የሚከሰቱ በሽታዎችን እንደሚቀንስም ተነግሮለታል። ምርቱ ወደ ገበያ ሲቀርብም መንግሥት፣ ሆቴሎች፣ ልዩ ልዩ ተቋማትና በተለይ ደግሞ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።
በአሁኑ ወቅት ተፈጥሯዊ የቲማቲም ማቆያ መድኃኒቱ የሙከራ ደረጃውን አልፎ ወደትግበራ በመግባት ሂደት ላይ ይገኛል። ከፌዴራል ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ምርቱ ከጀመረ በኋላ የጥሬ ዕቃ እጥረት መፈጠር ስለሌለበት እዚያው ዱራሜና በአካባቢው መስኖ ያለባቸው በርካታ ክፍት መሬቶች ላይ በውሃ መሳቢያ ሞተር በመታገዝና በትራክተር በማረስ ቲማቲምን ዓመቱን ሙሉ የማምረት ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ።
ጌታቸውና ጓደኞቹ ቲማቲሙን በማቀነባበርና የማቆያ መድኃኒቱን በመጠቀም ለገበያ የሚቀርብበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የተለያዩ ሥራዎች ሲሠሩ የቆዩ ሲሆን የዞኑ አስተዳደር ቃል በገባላቸው መሠረት 21 ሄክታር መሬት ሰጥቷቸዋል። በዚሁ መሬት ላይም ለሥራው አመቺ የሆነ የቦታ መረጣ፣ የኢንጂነሪንግ ዲዛይን፣ የውሃ ሪዘርቫይንና ሌሎች መሰል ቴክኒካል ሥራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ።
የቲማቲም ማቀነባበሪያው የተለያዩ ማሽኖችንና የፋይናንስ ካፒታል የሚጠይቅ ከመሆኑ አኳያ ወደ ትግበራ ለመግባት እነ ጌታቸው ያገኙት የ200 ሺህ ብር ሽልማት እንዳለ ሆኖ ማሽን ከሚሠሩ ሰዎች ጋር በመነጋገር እስከ 250 ሺህ ብር በሚሆን ዋጋ በማይዝግ ብረት በ250 የኤሌክትሪክ ቮልት የሚሠራ ማሽን ለማሠራት ስምምነት አድርገው ነበር። ይሁንና የማምረቻ ቦታ ዘግይተው በማግኘታቸው የማሽን ግዢ አጠቃላይ ዋጋው ወደ 60 ሚሊዮን ብር ከፍ ብሏል።
ከዚህ አንፃር ከአጠቃላዩ የማሽን ግዢ 25 ከመቶው በእነርሱ የሚሸፈን ሲሆን፤ በዚህ መነሻነትም በአሁኑ ጊዜ ፕሮጀክት ፋይናሲንግ በተባለ አሠራር ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድር ወስደው ማሽኑን ለመግዛት በሂደት ላይ ይገኛሉ። የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርም አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገላቸው ይገኛል።
ራንታ የቲማቲም ማቀነባበሪያ በ2022 በአንድ ዓመት ውስጥ 8 ሚሊዮን 500 ሺህ ሁለት መቶ ብር ገቢ እና 5 ሚሊዮን 769 ሺህ 300 ብር ትርፍ እንደሚያስገኝ እቅድ ይዞ ነበር። ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ 50 ከመቶ ያህል ሥራው በመከናወኑ፣ የማሽነሪ ግዢውም ወደመጠናቀቁ እየተቃረበ በመሆኑና ለማሽነሪው የሚያስፈልገው ግብአትን ማምረት የሚያስችል ቦታ በመገኘቱ የማቀነባበሪያው የማምረት አቅም ጨምሯል።
በዚሁ መሠረት ማቀነባበሪያው በዓመት 62 ነጥብ 64 ቶን የቲማቲም ድልህ፣45 ነጥብ 82 ቶን የቲማቲም ከች አፕ፣ 29 ነጥብ 94 ቶን የወጥ ማጣፈጫ ቅመም /puree/ ፣100 ቶን ጥሬ ቲማቲም እንዲሁም ለኮስሞቲክስ ግብአት የሚሆን 8 ነጥብ 2 ቶን የቲማቲም ልጣጭና የሌሎች ተረፈ ምርቶችን የማምረት አቅም አለው። በተጨማሪም በአንድ ዓመት ውስጥ 5 ቶን የተቀነባበረ ነጭ ሽንኩርትና ዝንጅብል የማምረት አቅም ይዟል።
በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ በግብርናው ዘርፍና በገበያው ውስጥ ለሚገኙ እንዲሁም በየደረጃው እስከ ጫኝና አውራጅ ድረስ ላሉ 600 ለሚሆኑ ሰዎችም የሥራ ዕድል ለመፍጠር አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
ጌታቸውና ጓደኞቹ ያለቀለት የቲማቲም ምርት መርካቶ ድረስ ይዘው የመግባት ውጥን አላቸውና ይህንን ለመከወን የሚያስችላቸውን እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው። በቀጣይም የቲማቲም ማቀነባበሪያ ሥራው እንዳለ ሆኖ ከቲማቲም ምርት ወደሚሠሩ የኮስሞቲክስ ምርቶች የመሸጋገር እቅዶችም አሏቸው። ይህም በተለይ በውድ ዋጋ ከውጭ አገር የሚገቡ የፊት ንፅህና መጠበቂያ ሳሙና ምርቶችን ያስቀራል ተብሎ ይታሰባል።
በሃሳብ የተጀመረው የጌታቸውና ጓደኞቹ የንግድ ፈጠራ ሀሳብ እውን ሆኖ ለብዙዎች እንዲተርፉና የአገርም ኩራት እንዲሆን ታዲያ የማያቋርጥና ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ከመንግሥትና ከባለሀብቶች ይፈልጋሉ። የዞኑ አስተዳደርም ተመሳሳይ ድጋፍ እንደሚያደርግ እምነታችን ነው። ሰላም!!
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን የካቲት 10 ቀን 2015 ዓ.ም