በህብረ ቀለሙና በአንፀባራቂነቱ፣ በውበቱና በተወዳዳሪነቱ የኦፓል ማዕድን በገበያ ላይ ተፈላጊና በዋጋም ውድ መሆኑ ስሙም እንዲገዝፍ አርጎታል። የዚህ ሀብት ባለቤቷ ኢትዮጵያ በዓለም በቡና ስሟ እንደሚጠራው ሁሉ በኦፓል ማዕድንም መታወቅ ችላለች።
የኢትዮጵያን ኦፓል የዓለም ገበያው አሳምሮ እንደሚያውቀውና ለማስተዋወቅም መድከም እንደማያስፈልግ የከበሩ ማዕድናትን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ለ16 አመታት የሰሩት አቶ አብዲአዚዝ መሐመድ የሱፍም ይናገራሉ። በዓለም ገበያ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘትም ከሌሎች የማዕድን አይነቶች ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝም ነው የሚገልጹት።
የኦፓል ማዕድን ሲወሳ የደቡብ ወሎ ደላንታ ወረዳ አካባቢም አብሮ ይነሳል። ኦፓልና ደላንታ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው ማለት ይቻላል። ኦፓል ከአማራ ክልል የማዕድን ልማት አካባቢዎች በስፋት የሚገኘው ደቡብ ወሎ በደላንታ ወረዳ ውስጥ በመሆኑ ነው አካባቢውና ማዕድኑ አብረው እኩል የሚጠቀሱት። በአካባቢው ያለው የኦፓል ማእድን ሀብት ክምችት እንደ ክልል ብቻ ሳይሆን፣እንደ ሀገርም ትልቅ ፋይዳ አለው።
አቶ አብዲአዚዝም እዚህ አካባቢ የሚመረተውን ኦፓል ነው ለዓለም ገበያ የሚያቀርቡት። ሰሞኑንም በአሜሪካ በተካሄደው የማዕድን ኤግዚቢሽን ላይ ተሳትፈዋል። ስለማዕድን ልማቱም ሆነ እርሳቸው ለውጭ ገበያ በማቅረብና ሰሞኑን በአሜሪካ በተካሄደው የማዕድን ኤግዚቢሽን ስለነበራቸው ተሳትፎና ኢትዮጵያም ስለነበራት ቦታ ጠይቀናቸዋል።
መንግሥት በማዕድን ዘርፍ ሶስት የአሰራር ሥርአቶችን ዘርግቷል። አንዱ በማህበር ተደራጅተው የሚያለሙ አምራች ማህበራት፣ሁለተኛው ደግሞ አዘዋዋሪዎች ሶስተኛው ለውጭ ገበያ አቅራቢዎች(ኤክስፖርተሮች) ናቸው። በዚህ መሠረት ላኪው ከአምራች ማህበራትና ከአዘዋዋሪዎች በመቀበል ለዓለም ገበያ ያቀርባል።
የኦፓል ማዕድንን በዓለም ገበያ ተፈላጊ የሚያደርገው ቀለሙ፣መጠኑና ጥራቱ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ኦፓል እነዚህን መሥፈርቶች በሚያሟላ መልኩ በጥንቃቄ መልማት ወይንም መመረት እንዳለበት አቶ አብዲአዚዝ ያስገነዝብሉ። የኦፓል ማእድኑ ሁሉ ገበያ አለው ብሎ ማሰብ ስህተት መሆኑንም የሚገልጹት።
በዘፈቀደ የሚከናወን ልማት ኢኮኖሚያዊ ውጤቱን ዘላቂ እንደማያደርገው የሚናገሩት አቶ አብዲአዚዝ፣ ልማቱ ገበያ ተኮር ካልሆነ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ያመለክታሉ። ማዕድን የሚያስገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ጠንቅቆ መረዳት እንደሚያስፈልግም ይናገራሉ። እሳቸው በኢትዮጵያ የኦፓል ማእድን ልማቱ በዚህ ግንዛቤ ልክ እየተሰራ ነው የሚል እምነት የላቸውም። በአብዛኛው በጊዜያዊ ገቢ ላይ የተመሰረተ ልማትና ግብይት እንደሚስተዋልም ነው የሚጠቁሙት።
እሳቸው እንደሚሉት አልሚውና ለውጭ ገበያ አቅራቢው (ኤክስፖርተሩ) ለአንድ ዓላማ መስራት ይኖርባቸዋል። አንዱ ያለ ሌላኛው መኖር የሚችል ባለመሆኑ የተናበበ ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ለምን ይህን ማድረግ አልተቻለም ብለን መልሰን ላቀረብንላቸው ጥያቄ በምላሻቸው፤ ሁሉም በየራሱ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ የተፈጠረ ችግር እንዳለ ነው ያመለከቱት። በተደጋጋሚ ግንዛቤ መፍጠር ላይ ካልተሰራ በአንድ ወቅት ብቻ በሚሰራ ሥራ ችግሩን ማስወገድ አይቻልም ሲሉም ያስገነዝባሉ።
እሳቸው እንደሚሉት፤ አሁንም አልረፈደም። ማዕድን አላቂ ሀብት መሆኑን ተረድቶ ያለውን በአግባቡ አልምቶ የተሻለ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመሆን መሥራት ይጠበቃል። በተለይም የኢትዮጵያ ሀብት ለኢትዮጵያ እንዲውል በማድረግ ረገድ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
አሁን ባለው የማዕድን ግብይት የውጭ ዜግነት ያላቸው በፈለጉት ዋጋ ገዝተው ለገበያ ማቅረብ የሚችሉበት ሁኔታ በመኖሩ እየተጠቀሙ ያሉትም እነሱው ናቸው ሲሉ ያመለክታሉ። የውጪ ዜጎችና የገንዘብ አቅም ያለው ብቻ በግብይቱ እየተሳተፉ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ይህም አግባብ ነው ብለው እንደማያምኑ ያመለክታሉ። የተናበበ ሥራ በመሥራት ለችግሩ መፍትሄ ማበጀት እንደሚቻልም ነው የተናገሩት።
ሀብትን በሚገባ ማወቅና በጥራት ላይ የሚደረግ ያልተቋረጠ ቁጥጥር ማድረግ ለሀገርም ለህዝብም ይጠቅማል የሚል እምነት ያላቸው አቶ አብዲአዚዝ፣ የከበሩ የድንጋይ ጌጣጌጥ ማዕድናት ከተሰራባቸው ትርፋማ እንደሚያደርጉና በምጣኔ ሀብት እድገት ላይም ሚናቸው ከፍ ያለ እንደሚሆን ተናግረዋል።
እርሳቸውም ስለተሳተፉበትና በቅርቡ በአሜሪካ ስለተካሄደው የማዕድን ኤግዚቢሽንም አቶ አብዲአዚዝ እንደገለጹት፤ ኢግዚቢሽኑ በየአመቱ የሚካሄድ ነው፤ ከተለያዩ ዓለማት የሚመጡ ማእድን ላኪዎች ምርታቸውን ይዘው ይሳተፉበታል። ዓላማውም የገበያ እድል ለመፍጠርና አንዱ ከሌላው ተሞክሮ የሚያገኝበት ነው።
“በጦርነት፣ በኮቪድ ወረርሽኝ እና በተለያዩ ምክንያቶች ዓለም ላይ ያጋጠመው ቀውስ ባሳደረው ተጽእኖ ኤግዚቢሽኑ እንደቀደመው የሚፈለገውን ያህል የገበያ ዕድል አልፈጠረም” የሚሉት አቶ አብዲአዚዝ፣ ቀዝቀዝ ያለ እንደነበር ይናገራሉ።
በኤግዚቢሽኑ ላይ በኢትዮጵያ በኩል 90 በመቶ የቀረበው ኦፓል ማዕድን ነው። ቀሪው 20 በመቶ ሳፋየርና ሩፒ ነው። የኢትዮጵያ ኦፓል በመታወቅ ደረጃ ዓለም አቀፋዊ እውቅና በማግኘቱ በኤግዚቢሽኑ ላይ ይጠበቅ የነበረው ገበያ ማግኘት ብቻ ነበር። ነገር ግን በዓለም ወቅታዊ ሁኔታና ማዕድኑም በስፋት በመቅረቡ የሚጠበቀውን ያህል ሽያጭ ማከናወን አልተቻለም። በዋጋም ቢሆን ወርዷል ሲሉ ያብራራሉ።
የኦፓል ማዕድን ክምችት በሚገኝበት ደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተካሄደው ጦርነት ምክንያት የኦፓል ልማትና ግብይት ተስተጓጉሎ እንደነበር ይታወሳል። በዚህም ሳቢያ ኑሮው በልማቱ ላይ የተመሰረተው የአካባቢው ማህበረሰብ በተለይም በማህበር ተደራጅተው የሚሰሩ ወጣቶች ተጎድተዋል።
ጦርነቱ ከቆመ ወራት ተቆጥረዋል። ጦርነቱ ከቆመ በኋላ በደላንታ የኦፓል ልማት በምን ሁኔታ ላይ እንደሆነ በደላንታ ወረዳ ማዕድን ሀብት ጽህፈት ቤት ማዕድን ሥራዎች ፍቃድ መስጠትና ማስተዳደር ኃላፊ አቶ በሪሁን አበረን ጠይቀናቸው በሰጡት ምላሽ እንደገለጹት፤ በጦርነቱ የባከነውን ጊዜ ለማካካስ አልሚዎች ኃይላቸውን አጠናክረው ለተሻለ ልማት ወደ ሥራ ገብተዋል። በአሁኑ ጊዜም በማህበር የተደራጁ ወደ አምስት ሺህ (5000) አባላትን የያዙ 27 አምራች የህብረት ሥራ ማህበራት በልማቱ ውጤታማ መሆን ችለዋል።
እንደ አቶ በሪሁን ገለጻ፤ ማህበራቱ በያዝነው 2015 በጀት አመት እስከ ታህሳስ 30 ቀን 13ሺህ 42 ነጥብ 5 ኪሎ ግራም ኦፓል አምርተዋል። የኦፓል ምርቱም በአዘዋዋሪዎችና በሌሎችም ተቀባዮች አማካኝነት ወደ ማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል።
በዚህ በተፈጠረው መነቃቃት በአመቱ ከ25 እስከ 26ሺ ኪሎግራም ኦፓል ይመረታል የሚል እምነት ተጥሏል። የማዕድን ሀብት ልማት ለመንግሥት አንዱ የገቢ መሰብሰቢያ ምንጭ በመሆኑ ከዘርፉ ከሚሰበሰብ ክፍያ(ሮያሊቲ) በሶስት ወራት እንቅስቃሴ 706ሺህ 500 ብር ገቢ ማስገባት ተችሏል። በሌላ በኩል ዘርፉ የሥራ እድል መፍጠሪያም በመሆኑ ለ663 ዜጎች የሥራ እድል ተፈጥሯል።
ለአልሚዎቹ በልማቱ ይበልጥ እንዲሰማሩ በግብይቱም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውም ተጠቁሟል። በቀድሞው አሰራር የተወሰኑ አልሚዎች ብቻ ያመረቱትን ማዕድን ወደ ማእከላዊ ገበያ ይልኩ እንደነበሩ አቶ በሪሁን አስታውሰዋል። በአሁኑ ጊዜ ሁሉም አልሚዎች ወደ ማእከላዊ ገበያ እንዲያቀርቡ፣ የላኪ ፈቃድ በመስጠት ውስን የነበሩ ላኪዎችን ቁጥር በመጨመር በመንግሥት በኩል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ይላሉ።
አቶ በሪሁን ተግዳሮቶችንም አንስተዋል። ልማቱ በሚከናወንበት ሥፍራ ተገኝቶ ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግና ለመከታተል የተሽከርካሪ እጥረት እና ለሥራ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች አለመሟላት እንቅፋት ሆነዋል። ቀደም ሲል የሰው ኃይል እጥረትን ለማሟላት የተሰራው ሥራ ጥሩ ቢሆንም እንደሀገር ከፍተኛ የኦፓል ልማት የሚከናወንበት በመሆኑ በተሻለ ትኩረት በተለያየ መንገድ ሊታገዝ እንደሚገባ ነው አቶ በሪሁን ያመለከቱት። በተለይም ልማቱ እንደ አፈር መቆፈሪያ ያሉ እና ሌሎችም የሥራ መሣሪያዎች በቴክኖሎጂ እንዲታገዙ በማድረግ ረገድ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ነው የገለጹት።
የማዕድን ልማቱ የመጨረሻው ግብ ለገበያ ቀርቦ ገቢ ማስገኘት መሆኑን ጠቅሰው፣ ገበያው ግን እንደሚዋዥቅ ጠቁመዋል። እንደ ርሳቸው ማብራሪያ፤ ኦፓል በኪሎ ግራም የመሸጫ ዋጋ የወጣለት ባለመሆኑ ግብይቱ በገዥና በሻጭ ነው የሚወሰነው። ይህ ደግሞ ዋጋው አንዴ ከፍ ሌላ ጊዜ ደግሞ ዝቅ እንዲል አድርጎታል። በሀገር ውስጥ በግብይቱ ፍቃድ የተሰጣቸው ቁጥር መጨመሩ ማዕድኑ በወረደ ዋጋ እንዲሸጥ አንድ ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ ይጠቅሳሉ።
የዋጋ መውረድ ደግሞ አልሚው ከልፋቱ ጋር በማነፃፀር ቅሬታ የሚያነሳበት ጉዳይ ነው። ጥያቄው ከድካማቸው ጋር የሚመጣጠን ገቢ ከማግኘት ጋር ብቻ የተያያዘ እንዳልሆነም ከተጨማሪ ሀሳቦች መረዳት ይቻላል። አልሚው በሚያገኘው ገቢ ኑሮውን መለወጥ አንዱ ፍላጎቱ በመሆኑ ገቢ ለእርሱ ወሳኝ ነው። ውድ እና ተፈላጊ የሆነ ማዕድን በወረዳ ዋጋ መሸጥ የለበትም። የሀገር ኢኮኖሚ ጥቅምን ያሳጣል። የሚለው ሌላው ተቆርቋሪነት ነው። ልማቱ በኩባንያ ደረጃ ቢለማ በጥራትና ከፍተኛ መጠን ያለው ኦፓል እንደሚገኝ ቢታመንም ልማቱ ከዋና ዓላማዎቹ አንዱ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርበት በመሆኑ ኩባንያዎችን ወይንም ኢንቨስትመንት በመሳብ ረገድ በትኩረት አልተኬደበትም።
የኦፓል ልማትና ግብይትን በማጣመር በአካባቢው በሚከናወነው እንቅስቃሴ በተለይም ግብይት ላይ እሴት የተጨመረበት ምርት ለገበያ እየቀረበ መሆኑን ነው አቶ በሪሁን የነገሩን።በሶስት ወር ውስጥ ከተመረተው 13ሺህ 42 ነጥብ አምስት ኪሎግራም ኦፓል ውስጥ ወደ 313 ነጥብ 5 ኪሎግራም እሴት ተጨምሮበት ለገበያ መቅረቡን ነው አቶ በሪሁን የገለጹት።እሴት ጨምረው የሚያቀርቡ ከ105 በላይ ኢንተርፕራይዞች መኖራቸውንም አመልክተዋል።
ለቁጥጥርና ክትትል እንዲያመች ግብይቱ በአንድ ማዕከል ውስጥ እንዲከናወን በአንድ ወቅት ተይዞ ስለነበረው የማዕከል ግንባታ ሥራ እቅድም አቶ በሪሁን ላነሳንላቸው ጥያቄ በምላሻቸው፤ ከ2011 በጀት አመት ጀምሮ የተያዘ እቅድ ነበር። ይሁን እንጂ ዓለም ላይ የተከሰተው ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ፣ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የነበረው ጦርነት መባባስ እቅዱ ስኬታማ እንዳይሆን እክል ፈጥሯል። ማዕከላቱ ለግብይት ብቻ ሳይሆን ማሰልጠኛ ጭምርም ሆነው አገልግሎት እንዲሰጡም ታሳቢ ያደረገ እቅድ ነው። በእቅዱ መሠረት ተገንብተው የነበሩ ማዕከላትም በጦርነቱ ለወታደሮች ካምፕ ሆነው እንዲያገለግሉ መደረጉንም አስታውሰዋል። ከጉዳት የተረፉ ማዕከላት ቢኖሩም የተሟላ አገልግሎት በሚሰጡበት ሁኔታ ምቹ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ዘርፉን የሚመራው የክልሉ አመራር በቅርቡ እንደተመለከተውና ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ሥራ ይሰራል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን የካቲት 10 ቀን 2015 ዓ.ም