ሀገራት የወጪና ገቢ ንግዳቸውን ለማቀላጠፍና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰታቸውን ለማሳደግ ብሎም አጠቃላይ ምጣኔ ሀብታዊ እድገታቸውን ለማሻሻል ከሚተገብሯቸው አሰራሮች መካከል አንዱ ነፃ የንግድ ቀጠናዎችን (Free Trade Zones) ማቋቋም ነው።
ነፃ የንግድ ቀጠና ‹‹ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና›› (Special Economic Zones) የሚባሉት የንግድና ኢንቨስትመንት መከወኛ ስፍራዎች አካል ሲሆን፣ እሴት የሚጨምሩ የምርት፣ የሎጂስቲክስ፣ የፋይናንስ አቅርቦትና መሰል ተግባራትና አገልግሎቶች የሚከናወንበት ስፍራ ነው። በዚህ ስፍራ ምርቶችን ከማምረት በተጨማሪ አስመጪና ላኪዎች ዕቃዎችን ወደ አገር ውስጥ በማምጣት በቀጠናው ውስጥ የሚያከማቹበት፣ የሚያቀነባብሩበት እንዲሁም መልሰው ለውጭ ገበያዎች የሚያቀርቡበት ሂደትም አለ። በተጨማሪም ሂደቱን ለማሳለጥ ቀልጣፋ የሆነ የሎጂስቲክስ አገልግሎት፣ የተቀናጁ የፋይናንስና የምክር አገልግሎቶችም ይሰጥበታል።
ነፃ የንግድ ቀጠና ኢንቨስትመንትን የሚጨምር፣ አዳዲስ የሥራ ዕድሎች ለመፍጠር የሚያግዝ፣ ቢሮክራሲያዊ የአሰራር ውጣ ውረዶችን የሚቀንስ አማራጭ እንደሆነ ይነገራል። ይህ ቀጠና የንግድ እንቅፋቶች የሌሉበት እንዲሁም ቀረጥና ግብር ያነሰበት የንግድና ኢንቨስትመንት ማሳለጫ አካባቢ እንደሆነም ይገለፃል። በነፃ የንግድ ቀጠናዎች ውስጥ የሚተገበሩ ህጋዊ አሰራሮች በሌሎቹ አካባቢዎች ከሚተገበሩት ጋር ሲነፃፀሩ የላሉና አንፃራዊ ነፃነትንም የሚያጎናጽፉ ናቸው።
ነፃ የንግድ ቀጠናዎች የሚፈጥሩትን የሥራ እድል፣ ለአገር በቀል የሎጂስቲክስ ኢንዱስትሪው መስፋፋት የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግርና የባለሙያዎችንና የሠራተኞችን ክህሎት ለማሳደግ እንዲሁም ለዋጋ ግሽበት መቀነስ ሚናቸው ከፍተኛ ነው። የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግ እንዲሁም የወጪና ገቢ ንግድን ለማቀላጠፍ ያላቸው አበርክቶም አላቸው። ሀገሮች እነዚህን ፋይዳዎች በአጠቃላይ ለሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት መሻሻል የሚኖራቸውን አስተዋጽኦ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነፃ የንግድ ቀጠናዎችን ያቋቁማሉ፤ ያስፋፋሉ።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በዓለም ላይ ከአምስት ሺ በላይ ነፃ የንግድ ቀጠናዎች አሉ። በርካታ ሀገራት የነፃ የንግድ ቀጠና ያላቸው ሲሆን የኢትዮጵያ ጎረቤት የሆኑት ጂቡቲ፣ ኬንያ፣ ሱዳን ተጠቃሽ ናቸው። ዛሬ በምጣኔ ሀብታቸው የበለፀጉት ሀገራትም ይህን የነፃ ንግድ ቀጠና አሰራር ተግባራዊ አድርገዋል፤ እያደረጉም ነው።
ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር እንዲሁም መሬትን ጨምሮ ሌሎች እምቅ ሀብቶች ያላት ኢትዮጵያ ነፃ የንግድ ቀጠናን እስካሁን ድረስ ባለማቋቋሟ ማግኘት የሚገባትን ምጣኔ ሀብታዊ ጥቅም ማጣቷ ተደጋግሞ ሲገለፅ ቆይቷል። የሀገሪቱን የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ እግር ከወርች አስረው የያዙት አንዳንዶቹ መሰናክሎች ነፃ የንግድ ቀጠናዎች በሚያስገኟቸው ጥቅሞች የሚፈቱ ናቸው።
በሀገሪቱ ነፃ የንግድ ቀጠና በማቋቋም የሀገሪቱን ተጠቃሚነት ማሳደግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ልዩ ልዩ የመሰረተ ልማትና ሕግ ማዕቀፍ ዝግጅቶች ሲደረጉ ቆይተው ባለፈው ነሐሴ ወር 2014 ዓ.ም የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ተመርቆ ተከፍቷል። ድሬዳዋ በንግድ የዳበረ ልምድ ያላት፣ ለጅቡቲ ወደብ ቅርብ የሆነች (የ320 ኪሎ ሜትር ርቀት) እና ሦስቱም የመጓጓዣ ዘዴዎች (የየብስ፣ የባቡርና የአየር ትራንስፖርት አማራጮች) ያሏት ከተማ መሆኗ ለነፃ የንግድ ቀጠናው መነኻሪያነት ተመራጭ አድርጓታል።
የንግድ ቀጠናው በድሬዳዋ የሚገኘውን የኢንዱስትሪ ፓርክና ደረቅ ወደብን ከዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት፣ ከባቡርና ከመንገድ ትራንስፖርት ጋር በማቀናጀት፣ አስፈላጊ የሆኑ የባንክና የጉምሩክ አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ ወደ አገልግሎት እንዲገባ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት ሲከናወኑለት ቆይቷል።
ቀደም ሲል የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ የነበረው የአሁኑ የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና፣ ከሀገሪቱ የንግድ እንቅስቃሴና የሎጂስቲክስ አቅም መጎልበት ጋር ተያይዞ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ወደ ነፃ ንግድ ቀጠናነት እንዲሸጋገር ተደርጓል። ነፃ የንግድ ቀጠናው በመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታው በ150 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን አራት ሺ ሄክታር መሬት የማስፋፈፊያ ቦታ ተዘጋጅቶለታል።
በአሁኑ ወቅት በርካታ ድርጅቶች ወደ ነፃ የንግድ ቀጠናው ገብተው ለመስራት ፍላጎታቸውን እያሳዩ ይገኛሉ፤ ፍላጎት ማሳየት ብቻ ሳይሆን በነጻ የንግድ ቀጠናው ለመግባት ስምምነት መፈረም ጀምረዋል። በቅርቡም ስምንት ኩባንያዎች በነፃ የንግድ ቀጠናው ውስጥ ለመሰማራት ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነት የፈረሙት ድርጅቶች ‹‹ኢዩፒያ ትሬድ ኤንድ ሎጀስቲክስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር››፣ ‹‹ፐርኪንስ ኢንዱስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር››፣ ‹‹አይ.ኢ ኔትወርክ ሶሉሽንስ››፣ ‹‹ያት ኢንዱስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር››፣ ‹‹አሳምነው አስፋው ጀነራል ኮንትራክተር››፣ ‹‹ማስ ስካይ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር›› እና ‹‹ኦሪዮን አዲስ ኢንጂነሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር›› የተባሉ ሀገር በቀል ኩባንያ እና ‹‹ናይልኮ ኤሌክትሪክ ኢኪዩፕመንት ማኑፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር›› የተሰኘ የውጭ ኩባንያዎች ናቸው።
በምርት፣ በግንባታና በሎጂስቲክስ ዘርፎች የተሰማሩት እነዚህ ድርጅቶች ወደ ሥራ ሲገቡ ከመቶ አስር ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወይም ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ኢንቨስት በማድረግ በመጀመሪያ ዙር ከሁለት ሺ 500 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ።
ከእነዚህ ድርጅቶች በተጨማሪ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ዳሸን ባንክ፣ የኦሮሚያ ኅብረት ስራ ባንክ እና እናት ባንክ ደግሞ ለነፃ የንግድ ቀጠናው የፋይናንስ አቅርቦትን ለማመቻቸት ከኮርፖሬሽኑ ጋር ስምምነት ተፈራርመዋል።
የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ካሚል ኢብራሂም እንደሚሉት፣ ነፃ የንግድ ቀጠናው ከተመረቀ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ወደ ቀጠናው ገብተው በኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ የሚሰማሩ ድርጅቶችን ለማስተናገድ የሚያስችሉ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይቷል። ከእነዚህም መካከል መዋቅር የመዘርጋት፣ በዘርፉ ልምድ ካላቸው ሀገራት ተሞክሮ በመቀመር የታሪፍ መመሪያ እና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የባለሀብቶች መመልመያ መስፈርት እና የውጭ ምንዛሬ አጠቃቀምን ጨምሮ የፋይናንስ መመሪያዎችን የማዘጋጀት ተግባራት ይጠቀሳሉ።
እንደ አቶ ካሚል ገለፃ፣ ነፃ የንግድ ቀጠናው በሌሎች ሀገራት ከሚገኙ ብዙ ነፃ የንግድ ቀጠናዎች ያላነሰ የመሰረተ ልማት አቅርቦት አለው። በዚህም ምክንያት በቀጠናው ውስጥ ገብተው በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ባለሀብቶች ቁጥር ጨምሯል። ‹‹ነፃ የንግድ ቀጠናው የንግድ ሂደቱን በማቀላጠፍ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠርና የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ ያግዛል። ኢትዮጵያ ከሌሎች አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነቶች ጋር ተወዳዳሪ እንድትሆንም ያስችላታል። የነፃ የንግድ ቀጠናው መቋቋም ከተሜነትንና ኢንዱስትሪያላይዜሽንን ለማስፋፋትም ይረዳል። ኩባንያዎች ወደ ንግድ ቀጠናው ገብተው ለመስራት ፍላጎት ማሳየታቸው እነዚህን ዓላማዎች ለማሳካት ይረዳል።
‹‹አይኢ ኔትወርክ ሶሉሽንስ›› (IE Network Solutions) በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ውስጥ ለሚሰማሩ ድርጅቶች የመረጃ ማዕከል፣ የኢንተርኔትና ሌሎች የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎቶችን ለመስጠት ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር ስምምነት ተፈራርሟል። የድርጅቱ መስራችና ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መርዕድ በቀለ በነፃ የንግድ ቀጠናው ውስጥ የሚከናወኑ የኢንቨስትመንት ተግባራት ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲሆኑ ብቁ የቴክኖሎጂ እገዛ እንደሚያስፈልጋቸው ይገልፃሉ።
‹‹በአሁኑ ወቅት ቴክኖሎጂ ለሁሉም የሥራ ዘርፎች እጅግ አስፈላጊ ሆኗል። ቴክኖሎጂ ደግሞ መሰረተ ልማት ይፈልጋል። ዋናው መሰረተ ልማት የመረጃ ማዕከል (Data Center) ነው። በነፃ የንግድ ቀጠናው ለሚሰማሩ ድርጅቶች አሰራራቸውን የሚያቀላጥፉበት መንገድ መዘርጋት ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ የእኛ ኃላፊነት የነፃ የንግድ ቀጠናውን ሥራዎች በቴክኖሎጂ በማቀላጠፍ የተሻለ ውጤት እንዲያመጣ ማገዝ ይሆናል›› ሲሉ አቶ መርእድ ያብራራሉ።
‹‹የእኛ ድርጅት ለውጭ ኩባንያዎች ሊከፈል የነበረ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ማስቀረት ችሏል። ሀገሪቱ በራሷ ልጆች ማደግ ለምትችልበት መንገድ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል›› የሚሉት አቶ መርዕድ፣ መንግሥት ሀገር በቀል የሆኑ የግል ድርጅቶችን ማገዝ እንዳለበት ይናራሉ።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ በበኩላቸው፣ ነፃ የንግድ ቀጠናው የሀገሪቱን የንግድ እንቅስቃሴና የሎጂስቲክስ ፍላጎት መጨመርን ታሳቢ አድርጎ የተቋቋመ መሆኑን ያስረዳሉ። ነፃ የንግድ ቀጠናው ድሬዳዋንና አካባቢን የሚያነቃቃ፣ ለነዋሪዎች የሥራ እድል የሚፈጥር እና የወጪና ገቢ ንግድን የሚያሳልጥ ከመሆኑም ባሻገር ማክሮ ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት እና በሀገራዊ ምጣኔ ሀብት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት የሚያግዝ ግብዓት ሆኖ ያገለግላል። ነጻ የንግድ ቀጠናው የውጭ ምንዛሬ እንዲገኝ ከማስቻሉ በተጨማሪ ተኪ ምርቶች እንዲመረቱ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር አገሪቱ ምርቶችን ከውጭ ለማስገባት የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ በማስቀረት ረገድም ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ይሆናል።
አቶ አክሊሉ በተለይም ከፌዴራል መንግሥትና ከሕወሓት የሰላም ስምምነት በኋላ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መሆኑን ጠቁመው፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንም በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠናም ሆነ በሌሎች የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለመሰማራት ጥያቄ የሚያቀርቡ ባለሀብቶችን በፍጥነት ለማስተናገድ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ከዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች መረዳት እንደሚቻለው ነፃ የንግድ ቀጠና አዳዲስና ሰፊ የሆኑ የሥራ እድሎችን ለመፍጠር፣ ተኪ ምርቶችን ለማምረት፣ የእውቀት ሽግግርን ለማሳደግ እንዲሁም ለአገር ውስጥ የቀረቡ ምርቶችን ለማከማቸትና የሎጀስቲክስ ወጪን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል። ይህም ሀገራዊ የሎጂስቲክስ ተወዳዳሪነትን ትርጉም ባለው መልኩ ሊለውጥ የሚችል በመሆኑ የሀገሪቱን የገቢና ወጪ ንግድ ስርዓት ለማቀላጠፍ ያግዛል። አሰራሩ የሚያስገኛቸው ጥቅሞችና የሚፈጥራቸው እድሎች የምርት ወጪን በመቀነስ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋትም ትልቅ ሚና ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
ሀገር በቀል ባለሀብቶች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና አሰራሮችን እንዲለምዱም እድል ይፈጥርላቸዋል። በነፃ የንግድ ቀጠናዎች ውስጥ የሚተገበሩ ህጋዊ አሰራሮች ቀለል ያሉና ቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረዶችን የሚቀንሱ በመሆናቸው ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ለመሰማራት የሚያደርጉትን ጥረት በአንፃራዊነት ቀላል ያደርጉላቸዋል። በነፃ የንግድ ቀጣናው ውስጥ ገብተው የሚሠሩ ባለሀብቶች፣ አስመጪና ላኪዎችም ሆኑ ድርጅቶች የልዩ ልዩ ማበረታቻዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ። ይህ ደግሞ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ጉልህ ሚና ይኖረዋል። እነዚህ ሁሉ ጥቅሞች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለጥቅል አገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት ዓይነተኛ ፋይዳ እንዳላቸውም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ከሚሰጠው ከነፃ የንግድ ቀጠና ስርዓት ርቃ መቆየቷ ብዙ ጥቅሞችን አሳጥቷታል። የእነዚህ ጥቅሞችና እድሎች መታጣት ደግሞ በአጠቃላይ እድገቷ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደረባት አይካድም። ስለሆነም በድሬዳዋ የተቋቋመውን ነፃ የንግድ ቀጣና በሚገባ በመጠቀምና መልካም ተሞክሮችን በመቀመርና በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎችም ተጨማሪ ነፃ የንግድ ቀጠናዎችን በማቋቋም አገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገቱ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲያስመዘግብ ማድረግ ይገባል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን የካቲት 9 ቀን 2015 ዓ.ም