ነገረ ግዛዋ – የመነሻ ወግ፤
ለመድኃኒትነት ከሚውሉ በርካታ ሀገር በቀል ዕፅዋት መካከል አንዱ ግዛዋ ነው::በአንዳንድ አካባቢዎች ግዛዋ የሚታወቀው “ጊዜዋ” እየተባለ ነው::በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎችም የተለያዩ ስያሜዎች እንዳሉት አንብቤያለሁ::ግዛዋ የትም የሚበቅል ገርና ገራሚ ዕፅ ነው::በግቢ ውስጥ፣ በመስክ ላይ፣ በሸለቆና በተራራ ሳይቀር ሁሌም ወቅት ሳይጠብቅ እንደለመለመ አምሮበት መታየቱ የተለመደ ተፈጥሮው ነው፡፡
እንደ ጓደኞቹ እንደ እነ ዳማከሴ፣ ድንገተኛ፣ ቀበርቾ፣ ፌጦ፣ ኮሶ ወዘተ. “ራሱን በማዋደድ” ርቃችሁ በመጓዝ ፈልጉኝ፣ አጠያይቃችሁ አግኙን በማለት “የሚኮፈስ” ዕፅ አይደለም::የትም ይበቅላል፤ በቀላሉም ይገኛል::ይህ ግዛዋ ዘርፈ ብዙ የመድኃኒትነት ጥቅም ይሰጣሉ ከሚባሉ ሁሉ ገብ መድኃኒቶች መካከል የሚጠቀሰው በሀገር በቀል ዕውቀቶች ብቻ ተመስክሮለት ሳይሆን በሳይንስ የምርምር ዘርፎችም እውቅናን በማግኘቱ ጭምር ነው::የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት በማኅበራዊ ድረ- ገጹ ላይ ያሠፈራቸው የጥናት ውጤቶች የሚጠቁሙትም ይህንኑ እውነታ ነው፡፡
በሳይንሳዊ ስሙ ዊታኒያ ሶምኒፌራ (Withania Somnifera) በእንግሊዘኛ ስያሜው Winter Chery በመባል የሚታወቀው የሀገሬ ግዛዋ ለራሱ ባለሀገሮች ባዕድ ሆኖ ቢታይም በሌሎች የዓለም ሀገራት ዘንድ ግን ተከብሮና ተመስግኖ በሳይንስና ምርምር እየተፈተነ በፈሳሽና በጥጥር መልኩ በፋብሪካዎች ውስጥ በመመረተ የደዌ ከልነቱን ተልዕኮ በሚገባ በመወጣት ላይ ይገኛል::በእኛው ቀዬ ግን “ከሞኝ ደጅ ሞፈር መቆረጡ” ወግና ባህላችንም አይደል፡፡
በተለየ ሁኔታ በህንዶች ዘንድ አሸዋጋንዳ (Ashwagandha) በሚል ስያሜ ዝናን የተጎናጸፈው ይህ ተክል “የመታወቂያ” ስሙን ያገኘው እንደ ፈረስ ጉልበታማ የሆነ መዓዛማ ሽታ ያለው ሁለገብ ፈዋሽ (Horsey Smell) እየተባለ ነው::ምንም እንኳን ይሄው ገራሚ የዕፅዋት ዝርያ በበርካታ የአፍሪካ፣ የሰሜን አሜሪካና የእስያ ሀገራት በስፋት ቢገኝም ህንዶች የተጠቀሙበትን ያህል የትኛውም ሀገር ተግባር ላይ እንዳላዋለው በበርካታ ጥናቶች ውስጥ ተጠቅሷል፡፡
ዕፁ ለየትኞቹ የጤና ችግሮች መፍትሔ እንደሚሰጥ ለመተንተን ጸሐፊውም ሆነ ይህ ጽሑፍ የዕውቀት ሥልጣንም ሆነ ብቃት (Authority) የላቸውም::በአንዳንድ ጽሑፎች ውስጥ እንደተጠቀሰው ግን ለአእምሮ ህመም፣ ለጭንቀት፣ ለድብርት፣ የጡንቻን ብቃት ለመታደግ፣ የልብን ምት ለማስተካከል፣ የቆሰለን አካል ደም ለማስቆም እና ለሌሎች በርካታ ደዌዎች በተጠናና በተስተካከለ ምጣኔ ጥቅም ላይ ከዋለ በፈዋሽነቱ ላይ ጥርጣሬ እንደማይኖር የዘርፉ ተመራማሪዎች መጠቋቆማቸው አልቀረም::ይህ አምደኛ የግዛዋን ዕፅ ለጽሑፉ ማዋዣ እንዲሆን የመረጠው የጽሑፉን ዋና ይዘት ያብራራ እንደሆን ብሎ በማሰብ እንጂ በዕፁ ላይ እንደ ተመራማሪ ሊቆጠርና ለዕፁ ፈዋሽነትም ማረጋገጫ እንደሰጠ ሊቆጠር እንደማይገባ ሊሰመርበት ይገባል፡፡
ወደ መነሻው ጉዳያችን እናቅናና የልጇን ህመም እንደ አዘቦት ቀናት የጤና ማጣት በመቁጠር ቸል ያለችን አንዲት እናት በደጃፏ ተንዠርግጎ ካለው ከዚህን መሰሉ የግዛዋ ተክል ሸምጥጣ ልጇን መታደግ ተስኗት በቸልተኝነት በሞት መነጠቁን ለማመልከትና ለመገሰጽ ስለተፈለገ ይመስላል፡- “ግዛዋ ሳለ ከደጅሽ፤ ለምን ሞተ ልጅሽ” ተብሎ ተተረተ ይባላል::“ግዛዋ ሞልቶ ከዱርሽ፤ ምነው ሞተ ልጅሽ” እየተባለም ይተረታል፡፡
ኢትዮጵያ ሆይ! – እውቀት እያለ ከደጅሽ፤ ስለምን ሞቱ ልጆችሽ?
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እንደ ሀገር የተፈተንባቸውን ሀገራዊ ቀውሶች እንደ መነሻ በማስታወስ ብቻ እየፈከርን ለገደልናቸው ወይንም ላስገደልናቸው፣ እያነባን ለቀበርናቸው ወይንም ወግ ያለው ቀብር እንኳን አጥተው ለአራዊት ሲሳይ ለሆኑት ሙታን ዜጎቻችን “ሀገራዊ የሕዝብ ቆጠራ” እንዲሉ፤ በጦርነትም ሆነ በበርካታ ማሕበራዊ ቀውሶች መንስዔ ደማቸው ደመ ከልብ ሆኖ በከንቱ ወድቀው ለቀሩት ኢትዮጵያዊያን በዝክረ ሙታን ስያሜ የመስዋዕትነት ቆጠራ (“crude` national census) ቢደረግ የአሀዙ ውጤት ምን ያህል ሚሊዮን ሊሆን እንደሚችል ለመገመት ሳያዳግት አይቀርም፡፡
በምሳሌ እናብራራው፡- የጦርነት መዘዝ ያስከተለብን ጥቁር መጋረጃ ለጊዜው እንደተዘጋ በይደር ይተላለፍና ዘርህ ከዘሬ አልተቀዳም፣ ቋንቋህ ከቋንቋዬ አይገጥምም፣ ብሔርህ ከብሔሬ ያነሰ ነው፣ ባህልህ ባህሌ አይደለም፣ ወግህም ከወጌ አይዛመድም በሚል እብሪትና ትምክህት ስንት ንፁሐን ዜጎቻችን እንደረገፉብን ምስክሩ ፀባዖት ብቻ ነው::ሃይማኖቴ ለሃይማኖትህ ባላንጣ ነው፣ እምነቴ ለእምነትህ ባዕድ ነው፣ ዶግማህ ዶግማዬን ተጸይፎታል፣ ቀኖናህም ለቀኖናዬ ፀር ነው በሚል ምክንያትና ሰበብ የምን ያህሉ ወገን እስትንፋስ እንደጨለመ፣ ምን ያህሉ ወገንም ሳይታወቅለት እንዳለፈ ምስክር ልትሰጥ የምትችለው ይህቺ እንደ ጉድ የደም አበላ የጠገበችው “አኬልዳማችን” ኢትዮጵያ ብቻ ነች፡፡
በታሪክ ትንታኔና አረዳድ መግባባት ተስኖን በተለኮሰ የእሳት ወላፈን ምን ያህሉ ወገን እንደ ቅጠል እንደረገፈ፣ ምን ያህሉ ዜጋ በማያውቀውና በማይገባው የፖለቲካ ወፈፌዎች የእሳት ራት እንደሆነ ዝርዝሩ የሚገለጥልን ወደ ቀልባችን ተመልሰን ከደም ፍላት ስንቀዘቅዝ ወይንም ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚያስተምረን በመጨረሻው የፍርድ ቀን የእያንዳንዳችን ግለ ፋይል በፈራጁ አምላክ ፊት ሲገለጥ ብቻ ይሆናል፡፡
ይህን መሰሉ በሀገሪቱ ላይ እየደረሰ ያለው መከራና አሳር ያነሰን ይመስል በሰንደቅ ዓላማ ቀለምና ትርጉም፣ የትኛው ከፍ ብሎ ይውለብለብ፣ ወዘተ. በሚሉ ሰንካላ ምክንያቶች የተነሳ ምን ያህሉን ነፍስ እንደገበርን ለምን ያህሉ ዜጎች የሥነ ልቦና ቀውስ እንደዳረግን ዛሬ አድበስብሰን ብናልፍ ነግ ተነገ ወዲያ እውነታው በፀሐይ ፊትና በአደባባይ ላይ መሰጣቱ አይቀርም፡፡
ለመሆኑ በሚያግባቡን ተግባብተን፣ በማያግባቡን ተቀባብለን እንዳንኖር አዚም ያደረገብን ምድራዊ ወይንም መንፈሳዊ ኃይል ምን ይሆን? በሥጋዊ ጡንቻችን ሳይቀር እስከ መፋለም ያዙኝ ልቀቁኝ እያልን ለያዥ ለገራዥ ያስቸገርነው በርግጡ የልብ ልብ የሰጠን ትምክህት ምንጩ ምን ይሆን?
ለሰላም ንግግርና ምክክር በየቄያችን ከስሩ የምንጠለልበት ለምለም የዋርካ ዛፍ እያለን፣ “በግዛዋ” የምንመስላቸው አፈርሳታና አውጫጭኝ ባህልና ወጋችን ሆነው እያሉ ስለምን ልጆቻችን በከንቱ እንዲያልቁ እንፈርድባቸዋለን? ስለምንስ የፖለቲካ አታካራዎቻችንን በመነጋገር መፍታት እየተቻለ “ደም ሳይፈስ ሥርዬት የለም” በሚል ብሉያዊ ፍልስፍናና እምነት ታብተን ለመጠፋፋት እንጨካከናለን? በቁጭት ወርዝቶ ከውስጣችን የሚገነፍለው የጥያቄ ወጨፎ ስፍር ቁጥር ስለሌለው እንዲሁ ብቻ ነካክተነው ማለፉ ይበጃል፡፡
ለመሆኑ እንደ እኛ እንደ ኢትዮጵያውያን የፈጣሪን ስም በአንደበቱ ሲያመነዥክ ውሎ የሚያድር ሌላ ሕዝብ ይኖር ይሆን? እንዴት አደርክ/ሽ ሲባል እግዚአብሔር ይመስገን የሚል፣ በጎ ሲደረግለት እግዚአብሔር ይስጥልኝ ብሎ የሚመርቅ፣ ስናቅድ እግዚአብሔር ቢፈቅድ የምንል፣ በህመማችን ወቅት እግዚአብሔር ይማርሽ/ህ ተባብለን የምንጽናና፣ “ስለ እግዚአብሔር ብለህ/ሽ” እየተባባልን ለእርቅ የምንፈቃቀድ፣ “ኢንሽ አላህ” እያልን በቅዱስ ቁርዓን ውስጥ 2699 ያህል ጊዜያት የተጠቀሰውን የፈጣሪ ስም የዚያኑ ያህል በቀን ውስጥ በማንሳትና በመጣል ስንጠራ እየዋልን ስለምን መከባበርና መቀባበል ተሳነን?
ጠይቀንና ተጠያይቀን መልስ ከማናገኝላቸውና መልሱ ባይገኝም ደጋግመን መጠየቅን የማናቆምባቸው ሀገራዊ ጉዳዮቻችንና ችግሮቻችን ብዙዎች ናቸው::ብሶት የሚወልዳቸው ችግሮቻችን ገንፍለው ያልተፈለገ ውጤት ከማስከተላቸው አስቀድሞ በሆደ ሰፊነትና በትከሻ ደንዳናነት ተሰባስበን በጥያቄዎቻችንና በፈተናዎቻችን ዙሪያ መፍትሔውን በጋራ ለመፈለግ ዝግጁ እስካልሆንን ድረስ ሥር የሰደደው በሽታችን በነጋ በጠባ እያገረሸ ስናቃስት መኖራችን ግድ መሆኑ አይቀሬ ነው::
አድምጠኝ ላድምጥህ ከመባባል ይልቅ ሻምላ ተማዘን ይለይልን ተባብሎ የደም ሸማ መጣጣሉ የት እንዳደረሰን ስለሚታወቅ ቆም ብለን ልናስብበት ይገባል::ችግሮቻችንን “ድፍን ዕንቁላል” እንደሆነ በማሰብ “ዕንቆቅልሾቻችን” ማወሳሰቡ የት አድርሶ ምን ላይ እንደሚጥለን ቆም ብለን ካላሰብን በስተቀር የእብሪትና የትምክህት ሽክርክሪያችን አዙሮ የሚዘፍቀን ወደ ደም መፋሰስ መሆኑ በጥብቅ ሊታሰብበት ይገባል::ችግሮችን በንግግር መፍታት እየተቻለ ገድሎና ተጋድሎ ያሸነፈ፣ ነፍሱም ተከብራ ኒሻን የተሸለመች “ጻድቅ” ጥንትም ሆነ ዛሬ ኖሮ አያውቅም፤ ለወደፊቱም ይኖራል ተብሎ አይታመንም፡፡
ጠነንና ኮስተር ያለውን ይህንን ጨፍጋጋ ርዕሰ ጉዳይ የሚያለዝብልንን አንድ ሰሞንኛ ዓለም አቀፍ አወዛጋቢ ክስተት ለማዋዣነት እንጥቀስ::ከህንድ የተገኘውን ይህንን የቀደሙን ዜና ተሸቀዳድሞ ለዓለም ያዳረሰው CNN የተባለው አነፍናፊ ሚዲያ ነው::የዜናውን ይዘት እንደሚከተለው አሳጥረን እንጠቅሳለን፡፡
ከህንድ ዜጎች 80% ወይንም 1.3 ቢሊዮን ቁጥር ያላቸው የሂንዱ ጎሳ አባላት ላሞችን የሚመለከቱት እንደ ቅዱስ ፍጡር ስለሆነ አያጎሳቁሏቸውም፣ አያርዷቸውም፣ ተዳፍረው እንኳን ቢነኳቸው ለራሳቸው እንዳይረክሱና ላሞቹንም እንዳያረክሷቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋሉ::ብዙው ድርጊታቸው አነጋጋሪና አወዛጋቢ ስለሆነ ሁሉንም በዝርዝር መተንተኑ እጅግም አስፈላጊ ላይሆን ይችላል፡፡
ትናንት ፌብሯሪ 14 (የካቲት 7) ብዙ ምእራባዊያን ሀገራት የሚያከብሩት የቅዱስ ቫለንታይኑ የፍቅረኞች ቀን በሂንዱዎችም ዘንድ የተከበረው አነጋጋሪ በሆኑ ትዕይንቶች ታጅቦ ነበር::አስገራሚ የተባለለት ይህ የፍቅረኞች ቀን ሲዘከር የዋለው “ከላሞች ጋር በመተቃቀፍ” (Cow hug Day) የሚል መንግሥታዊ ትዕዛዝና መመሪያ ተሰጥቶበት ጭምር ነበር::ይህ መንግሥታዊ መመሪያ ምንም እንኳን በበርካታ የሀገሪቱ ዜጎች ተቃውሞና ትችት ማስተናገዱ ባይቀርም ውሳኔውና ድርጊቱ ግን አንዳች ትምህርት ሳያስተምር አላለፈም፡፡
የሰው ልጅ እንኳንስ በፈጣሪ አምሳል ከተፈጠረው የራሱ ወገን ጋር ቀርቶ ለእንስሳት እንኳን ሳይቀር ከላይ እንደተጠቀሰው “ቅዱስነታቸውን አምኖ” ፍቅሩንና አክብሮቱን ይገልጽላቸዋል::አላግባብም ይሁን በመዳፈር የእንስሳቱን ደም በከንቱ ሊያፈስ ቀርቶ ጠንከር አድርጎ እንኳን ልምጭ አያሳርፍባቸውም::ለቤት እንስሳት ብቻም ሳይሆን ለዱር አራዊትም ሳይቀር “እንስሳዊ መብታቸው” እንዲከበርላቸው “በሕግ አምላክ!” እያሉ የሚሟገቱላቸው ግለሰቦችና ተቋማት ቁጥር ልክና መጠን የለውም፡፡
የእኛ ሀገሩ የሰው ለሰው ጭካኔ ግን ስለምን ከእንስሳት ፍቅር እንኳን አንሶ እርስ በእርስ መገዳደልን ለመጠየፍ እንዳልቻልን ራሳችንን በራሳችን ልንሞግት ይገባል::እርቅ፣ ሽምግልና፣ መነጋገር፣ መወያየት፣ አፈርሳታ፣ አውጫጭኝ ወዘተ. የመሳሰሉና በሀገር በቀል ግዛዋ የሚመሰሉ የሰላም መፍጠሪያና መነጋገሪያ ባህላዊና አካባቢያዊ መድረኮች የሺህ ዘመናት ባህሎቻችን ሆነው እያሉ “ልጆቻችን ሲገዳደሉ እንዴት ዝም ብለን ለማስተዋል የሞራል አቅም አገኘን? ገሎ ማቅራራትስ ስለምን የቁራኛ ያህል ተጣብቶን ባህላችን እስከ መሆን ደረሰ? ።
”የፖለቲካ፣ የብሔርም ሆነ የሃይማኖት ምክንያት እየተሰጠው ኮሽ ባለ ቁጥር ገሎ ለመሞት መሽቀዳደሙ በርግጡ ርእዮተ ዓለማዊ ወለድ ችግር ብቻ ነው ወይንስ ውስጣችን ያልተፈወሰበትና “ግዛዋ” የምንፈልግበት ሥር የሰደደ የሀገራዊ ህመማችን በሽታ ይሆን?” – ኢትዮጵያ ሆይ! አባባሉን ለዛሬው ዐውዳችን እንዋሰውና፤ “ማግባባት ሲቻልሽ በጓዳሽ፤ ስለምን ይተላለቃሉ ልጆችሽ!?” ፈጣሪ አምላክ ድንጋዩን ልባችንን ወደ ሥጋ ልብ ይለውጥልን፤ አሜን! ሰላም ለሕዝባችን፤ በጎ ፈቃድም ለዜጎች!
(በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም