ባሳለፍነው ወር አጋማሽ የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ የፈተና ውጤት ይፋ መደረጉን ተከትሎ በርካታ ሀሳቦች ሲንሸራሸሩ ቆይተዋል።በተለይም ብዙዎችን ያስደነገጠና እንደአገር ወድቀናል ያስባለ እንደነበር ሁሉም ያስታውሰዋል።ማነው ተጠያቂው በሚልም ብዙ ሀሳቦች ተነስተው በየመድረኩ ውይይቶች ተደርጎባቸዋል።በዚህም የመፍትሄ ሀሳብ ናቸው ተብለው ከተጠቆሙት መካከል ለዛሬ ልናነሳው የወደድነው ሀሳብ አንዱ ነው።
ይህም የዩኒቨርሲቲዎች ማህበራዊ ተሳትፎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚል ሲሆን፤ ምን ውጤት አመጣ።በተለይም በዘንድሮው ውጤት ላይ በሚል ሙሉ ለሙሉ ተማሪዎቻቸውን ካሳለፉ ሰባት ትምህርት ቤቶች መካከል ሁለቱን መርጠን አነጋግረናል።ትምህርት ቤቶችና የተደረገላቸውን የዩኒቨርሲቲዎች እገዛ ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር ይዘን ቀርበናል።
ተማሪዎቻቸውን ሙሉ ለሙሉ ካሳለፉ ሰባት ትምህርት ቤቶች መካከል የወላይታ ሊቃ አዳሪ ትምህርት ቤት አንዱ ሲሆን ይህ ትምህርት ቤት በስፋት የሚታገዘው በወላይታ ልማት ማህበር ቢሆንም የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲም እንደ አንደኛው ካምፓሱ ስለሚቆጥረውም በሁሉም ነገር ያግዘዋል።ለአብነት በመምህራን ልማት ዙሪያ የትምህርት ዕድልን ከመስጠት ጀምሮ አጫጭር ስልጠናዎችን ወስደው ተማሪዎቻቸውን በእውቀት እንዲያጎለብቱ ይደግፋል።በተመሳሳይ ለሴቶችና ለወንዶችም የማደሪያና የመጸዳጃ ክፍሎችን በመሥራት ማስረከብ ችሏል።
ቤተ ሙከራና አይሲቲ ክፍሎችን የማደራጀት ሥራም የእሱ ሲሆን ወደሰባት የሚሆኑ የቴክኒካል ድሮይንግ መሣሪያዎችን ለትምህርት ቤቱ ከመስጠት ባለፈ ሊቃ ብቻ ሳይሆን ሌሎቹም ትምህርት ቤቶች በሳይንስ፣ ኢንጅነሪንግና ማትስ በስቲም ሴንተሩ ገብተው ተከታታይ ስልጠና እንዲወስዱም አድርጓል።
ዩኒቨርሲቲው ይህንን ሥራ ለመሥራት ያሰበበት ዋና አላማው የተሻለ ትውልድ፤ ሥራ ፈጣሪ ዜጋ ማፍራት በመሆኑ ሲሆን የፈጠራ ሥራ ሠርተው እገዛ እንፈልጋለን ካሉ በራቸው ክፍት እንደሆነም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንትና የወላይታ ልማት ማህበር ቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ታከለ ታደለ ይናገራሉ።
ዩኒቨርሲቲው አዳሪ ትምህርት ቤቱን የሚያግዘው በትምህርት ቤት ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከዚያም ውጪ ባሉ ለምሳሌ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የተዘጋጁትን ተማሪዎች የትምህርት መስኮችን እንዴት መምረጥ እንዳለባቸው ግንዛቤ በማስጨበጥና በሌሎችም ተሳትፎን ያደርጋል።ዘንድሮም ወደ ዩኒቨርሲቲ ከሚገቡት ተማሪዎች ጋር ለመወያየት እቅድ ይዟል።
እንደአገር ማንኛውም ነገር መመራት ያለበት በእውቀት ነው የሚሉት ፕሬዚዳንቱ እውቀት ያልታከለበት ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካም ሆነ ማህበራዊ መስክ ከግብ ሊደርስ አይችልም።ስለሆነም የእውቀት ምንጭ የሆኑ ትምህርት ቤቶች በአግባቡ መገንባትና ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት አለባቸው።ለዚህ ደግሞ በየደረጃው መሥራትና ሁሉም የተሰጠውን ኃላፊነት መወጣት ይኖርበታል፡፡
በተለይም ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው።በዚህም እንደ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በአካባቢያችን ካሉ ትምህርት ቤቶች 30 የሚሆኑትን በመውሰድ መደገፍ አለብን ብለን እየተንቀሳቀስን ነው የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ዩኒቨርሲቲው መንግሥት የማይደርስባቸው አካባቢዎች ላይ ጭምር በመውረድ ትምህርት ቤቶችን ከመገንባት ባሻገር በግብዓት የመደገፍ ሥራ እያከነ እንደሆነ ያነሳሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ይህ ድጋፍና ክትትል ዝም ብሎ በራስ ፈቃድ የተከወነ አይደለም።በሕግና በመመሪያ ጭምር የተቀመጠ ነው።ለዚህም ማሳያው ዩኒቨርሲቲዎች ሲመሠረቱ ሦስት ሥራ ተሰጥቷቸው መሆኑ ነው።የመጀመሪያው መማር ማስተማር ሥራው ነው፤ ሁለተኛ ጥናትና ምርምር ማድረግ ሲሆን፤ ሦስተኛው ደግሞ የማህበረሰብ አገልግሎት መስጠት ነው።ከሁሉም በላይ ደግሞ ሦስተኛው ውስጥ የሚካተት በአዋጅ ደረጃ ተሰጥቷቸዋል።ይህም በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ 11/52/ 2011ዓ.ም ላይ እንደሰፈረው ዩኒቨርሲቲዎች በአካባቢያቸው ያሉትን አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአደረጃጀት፣ በአሠራር፣ በአመራር፣ በግብዓት፣ በክትትልና ድጋፍ ማገዝ አለባቸው ይላል።ይህንን ተግባራዊ ከማድረግ አንጻር ዩኒቨርሲቲዎቻችን ምን ያህል እየሠሩ ነው ከተባለ ሁሉም በራሱ የሚመልሰው ይሆናል።
እንደ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ግን በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነ የሚያነሱት ፕሮፌሰር ታከለ፤ ትምህርት ቤቶችንም ሆነ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በግንባታ፣ በመሠረተ ልማት ማሟላት ለመማር ማስተማሩ የሚያግዙ ግብዓቶችን በመደገፍ እገዛን ይደርጋል።ለምሳሌ፡- ብዙዎቹ ትምህርት ቤቶች የውሃ ችግር ያጋጥማቸዋል።ዩኒቨርሲቲው ደግሞ ውሃ የሚያገኙበትን መንገድ በመፍጠር፤ መንገድ ያስቸገራቸውንም እንዲሁ መንገዶችን በመሥራት፣ መጸዳጃ ቤቶችን ሠርቶ በማስረከብ፣ የትምህርትና የማደሪያ ክፍሎችን ጭምር ገንብቶ በመስጠት ድጋፎች ተደርገዋል።
በቅርቡ ብቻ ዩኒቨርሲቲው 20 ሚሊዮን ብር በመመደብ ድቡላ ፋንጎ አካባቢ አንድ አዳሪ ትምህርት ቤት እየተገነባ ሲሆን፤ ግንባታው ሲጠናቀቅ 1ሺ 500 ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች ተቀብሎ ያስተናግዳል።መንግሥት ባወጣው የትምህርት ቤት አሠራር መስፈርት መሠረት ሁሉንም ነገር ያካተተ ይሆናል።በሚቀጥለው ዓመት ለትምህርት ዝግጁ እንዲሆንም ከአሁኑ በርካታ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው።የትምህርት ግብዓቶችን ሳይቀር ለማስገባት ከኢትዮጵያ ትምህርት መሣሪያዎች ማደራጃ ጋር በመነጋገር የግዢ ሥራ ሂደቱ እየተከናወነ ነው።
ትምህርት ቤቱ ሙሉ ወጪው ብቻ ሳይሆን የአስተዳደሩ ሥራ ጭምር የሚመራው በዩኒቨርሲቲው ሲሆን፤ ‹‹ከኬጂ ወደ ፒኤችዲ›› የሚል መርህ በመያዝ ለመሥራት የታሰበበት ነው።በተመሳሳይ ዩኒቨርሲቲው ከወላይታ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የነበረው ትምህርት ቤት በአውሮፕላን ማረፊያ መሠራት ምክንያት ተማሪዎች በቀላሉ ሳይረበሹ ለመማር ይቸገራሉ።ስለሆነም ይህ እንዳያጋጥማቸው በማሰብ ትምህርት ቤቱን በማንሳት ወደ ሌላ አካባቢ በመውሰድ 25 ሚሊዮን ብር በመመደብ ለመስራት ወስኗል።አሁን በርካታ ተግባራትን እያከናወነም ይገኛል።ይህንን የማያደርግ ከሆነ ግን ስለ ትምህርት ጥራት፣ ስለ ትምህርት አግባብነት፣ ስለትምህርት ፍታዊነትና ተደራሽነት ማንሳት አይችልም።እናም የራሳችንን ድርሻ እየተወጣን ከሄድን ተጠያቂነትን ከራሳችን እያወረድን እንሄዳለን ብሎ ያምናልና ተግባሩን እየከወነ ነው ይላሉ ፕሮፌሰሩ።
እንደአገር የወደቅንበትን የትምህርት ዘርፍ እንደአገር ለመገንባት ዩኒቨርሲቲዎች ያላቸው አቅም ትልቅ ነው።ምክንያቱም ዩኒቨርሲቲዎች እውቀትም፣ ቴክኖሎጂም፤ ገንዘብም አላቸው።በአግባቡ መጠቀም የሚችሉትም እንዲህ ዓይነት ተግባራትን መከወን ሲችሉ ነው።ኅብረተሰቡን ይዘው አገርን ማሻገር ይችላሉ።ለችግሮች መፍትሄም ይሰጣሉ።ስለሆነም ቆራጥ ሆነው በተሰጣቸው ልክ መሥራት አለባቸው።
እንደአገር የወደቅነውና ያመጣነው ውጤት መታከም ስላለበት መንግሥት በዚህ ሁኔታ አይቀጥልም።እንደአዲስ ፖሊሲና አቅጣጫ ያስቀምጣል።ለዚህ ደግሞ ሁሉም ጋር የሚደርስ ሥራ አለ።እናም ዩኒቨርሲቲዎች ከአሁኑ ቢላመዱትና ወደ ሥራ ቢገቡ ጊዜን መጠቀም እንደሚችሉም ያብራራሉ።ዩኒቨርሲቲው ለወላይታ ዞን በመምህራን ልማት ከ400 በላይ መምህራን ማሰልጠን መቻሉን፤ በዞኑ በነፃ የትምህርት ዕድል (ስኮላር ሺፕ)ም ከ 2ሺ በላይ ሰው ሙሉ ወጪያቸውን ሸፍኖ እያስተማረ እንደሚገኝም ያነሳሉ።
ይህ ዕድል በተለይ የሚያግዘው አቅሙም አማራጩም ለሌላቸው ራቅ ካለ የገጠር ክፍል ለሚመጡ ተማሪዎች ነው።በተለይም ራዕይን የሰነቁ ጎበዝ ተማሪዎች ምቹ ሁኔታ ማግኘት ለማይችሉት ተስፋ ይሰጣል።በተመሳሳይ ትምህርት የማግኘት አማራጫቸው እጅግ ዝቅተኛ ለሆኑ ለአካል ጉዳተኞችና ለሴቶችም ጥቅሙ ቀላል አይደለም።ችሎታው ቢኖራቸውም አጋጣሚዎች ስለማይፈቅድላቸው ቤታቸው ተሸሽገው ይቀራሉ።እናም እነርሱ እንዲወጡና ለአገር ማበርከት ያለባቸውን እንዲያደርጉ ያስችላቸዋል።
ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች እንደ አገር ያሉበት ሁኔታ ቅርብ አይደለም።ቅርብ ያሉ ትምህርት ቤቶች ደግሞ በብዙ አቅም የተደራጁ እንዳልሆኑ ሁሉም ያውቀዋል።እናም ዩኒቨርሲቲዎች እዚህ ላይ መሥራት ተማሪዎችን በብዙ መልኩ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል።አገርም ብትሆን ከውድቀት እንድትላቀቅ ያግዛታል።የተሻለ ተማሪን በማፍራት ሁነኛ መፍትሄ ያመነጫልም።በተለይም ጎበዞቹን አውጥቶ ለአገር ጠቃሚ ማድረግ ላይ ያለው ፋይዳ ቀላል አይሆንም።
ሴቶች በቤተሰብ ጫና፣ በትምህርት ቤቱ ርቀትና በጾታዊ ጥቃት ምክንያት ከትምህርታቸው እንዳያቋርጡ የሚያደርግም ነው።በውጤታቸው ላይም ከፍተኛ ለውጥ እንዲያመጣ ያግዛል።ከሁሉም በላይ አሁን ያየነውን ውጤት ላለመድገም ያስችለናል።መንግሥት የያዘውን 25 በመቶ የማድረስ እቅድም ለማሳካት ሁነኛ መፍትሄ ነው።
መንግሥት ወደ 2ሺ የአዳሪ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት እቅድ ይዟል።በዞን ደረጃ ከልማት ማህበሩ ጋር በመሆን እስከ ስድስት አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ታስቧል።ዩኒቨርሲቲው ደግሞ በራሱ የጀመረው አንድ አዳሪ ትምህርት ቤት አለ።በቀጣይ ዓመትም ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ እየተሠራ ነው።ነገር ግን ሁሉንም በእኩል የጋራ ነገር ያስፈልጋል።በተለይም በክልልና ዞን አካባቢዎች ላይ።የጋራ ነገር ከሌለ ምንም ነገር ስኬታማ አይሆንም።እናም እንደመንግሥት ይህንን ተግባር ለማከናወን የሚያስችል ጠንከር ያለ ህግ ቢወጣ መልካም ነው ይላሉ ፕሬዚዳንቱ ፕሮፌሰር ታከለ።
የዩኒቨርሲቲዎች በዘርፉ ላይ ድርሻ ኖሯቸው ታችኛው ክፍል ላይ ወርደው መሥራታቸው ጠቀሜታው ከግለሰብ አልፎ አገር ላይ የሚያርፍ ነው የሚሉት ደግሞ በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የቀዳማዊ ምኒልክ ሳይንስ ሸርድ ካምፓስ ፕሪኒስፓል አቶ አቤል ጫላ ናቸው።እርሳቸው እንደሚሉት፤ የቀዳማዊ ምኒልክ ሳይንስ ሸርድ ካምፓስን ይዞ በመሥራት ከፍተኛ ውጤት የሚያመጡ ተማሪዎችን እንደአገር ማፍራት የቻለ ተቋም ነው።ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የሚለየው ይህ ባህሪው ይመስለኛል።ሌሎቹ የመምህራን ልማት ላይ፣ ታችኛው ክፍል ወርደው በተለያየ መንገድ የሚደግፉበት ሁኔታ ይኖራል።አንድ ካምፓስ ፈጥረው የሠሩ ግን ያሉ አይመስለኝም።ስለዚህም ቢያሰፉትና ቢሠሩበት ብዙ ጥቅም ያስገኛል።
ይህ ትምህርት ቤት ሲጀመር እንደፕሮጀክት ብቃት ያላቸውን የተለያዩ ተማሪዎች ሰብስቦ ለማስተማር ነበር።ነገር ግን ከሁለት ዓመት ላይ መቀጠል አልቻለም።ስለዚህም ተማሪዎቹ መበተን እንዳለባቸው ሲታመን ይህ ያሳሰበው የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ሁለት ዓመት ተምረው የአስረኛ ክፍል አገራዊ ፈተና ተፈትነው መበተን የለባቸውም በማለት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመነጋገር ከአለው በጀት ላይ ቀንሶ ትምህርቱን አስቀጥሎታል።
እነርሱን መደገፍ አገርን ከፍ ማድረግ እንደሆነ ዩኒቨርሲቲው ያምናል የሚሉት አቶ አቤል፤ ከተለያየ ርቀት ላይ የሚመጡ ተማሪዎች በአቅራቢያቸው ሆነው የተሻለ ትምህርት እንዲያገኙ፣ ከበጀት አንፃርም መጋራትና የተሰጠውን ለሚፈለገው አላማ ለማዋል ይጠቅማል።በተጨማሪም መምህራን ለአገራቸው የሚያደርጉትን አስተዋፅኦ ያሰፋዋል።ምክንያቱም ታች ድረስ ወርደው እንዲያስተምሩ ይሆናሉና የእኔነት ስሜትን ይፈጥራል።መጠቋቆምን ያስቀራል።ትውልድ ቀረጻ ላይም ትልቅ አቅም ይፈጠራል።
የትምህርት ቤቱን ሙሉ ወጪ የሚሸፍነው ራሱ ነው።በዚያ ላይ በዩኒቨርሲቲ መምህራን መስፈርት መምህራንን አወዳድሮ ቀጥሮ ያሠራል።ይህ ሲባል ግን አጋዥ የለውም ማለት አይደለም።ምክንያቱም ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ እና ከአራዳ ክፍለ ከተማ ጋር በመመካከር የተለያዩ ሥራዎች ላይ በጋራ ይተባበራል።ለአብነት የአራዳ ክፍለከተማ ትምህርት ጽሕፈት ቤት የቀዳማዊ ምኒልክ ትምህርትቤትን ሊሰጠው ችሏል።በተጨማሪም ትምህርት ሚኒስቴር ከሌሎች መደበኛ ትምህርት ቤቶች ይልቅ የሚደገፍበትን ሁኔታ አመቻችቶ ያውቃል ይላሉ አቶ አቤል።
እንደኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ሁሉ እነዚህ አዲስ አበባ ላይ ከፍተኛ አቅም ያላቸውና ብዙዎችን መደገፍ የሚችሉ በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች በትምህርቱ ዘርፍ ላይ የተወሰነ አቅማቸውን እንኳን ተጠቅመው ድጋፍና ተሳትፎ ማድረግ ቢችሉ በዘርፉ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ይቻላል።ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ይህንን ያህል በማድረጉ ብዙዎችን ከዘንድሮው ማዕበል መታደግ ችሏል።በተጨማሪም ለቀጣይ አገር ጠቃሚ የሆኑ በእውቀትም በስነምግባርም የተሻሉ ትውልዶችን አፍርቷል።ስለሆነም የእርሱን ፈለግ ቢከተሉና አገርን በዘርፉ የሚታደጉ ዜጎችን ቢፈጥሩ መልካም ነው ሲሉ መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉም።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 6ኪሎ ካምፓስ፣ አራትኪሎና አምስት ኪሎ ካምፓሶች አለፍ ሲል ደግሞ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ካምፓሶች በትምህርት ዘርፍ ትልልቅ ለውጥ ማምጣት የሚችሉ ናቸው።ሆኖም አልሠሩበትም።ስለዚህም እነርሱም የሚሳተፉበትን ምህዳር ቢያሰፉ አዲስ አበባ ላይ ብቻ ብዙ ፈጣሪና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ልጆችን ማፍራት ይቻላል ይላሉ።
ዩኒቨርሲቲዎች የሚያግዟቸው አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መኖራቸው በርካታ ጠቀሜታዎች አለው ለአብነት መምህራን በተሻለ አቅም ሰልጥነው እንዲወጡ ያግዛል፤ ተወዳዳሪ እንዲሆኑም ያስችላል።በተመሳሳይ የትምህርት ዕድሎችን እንዲያገኙም ዕድል ይፈጥራል።ከሁሉም በላይ ደግሞ በትምህርት መስካቸው የተሻለ አቅም ኖሯቸው የተሻለ ተማሪ እንዲያፈሩ ይሆናሉ።በተመረጠ መምህር፣ በተመረጠና በተሻለ የመማር ማስተማር ሥራ የታገዘ ተማሪ ደግሞ አገር ወዳድ ብቻ ሳይሆን ለአገር የሚሠራ መሆኑ አይቀርም።ስለዚህም እንደአገር የወደቅንበት ሁኔታ በቀላሉ መታከም ይቻልም ባይ ናቸው።እኛም ህመሙን ያወቀ መድኃኒት ለማግኘት የሚሳነው ነገር የለምና በአዋጅ የተሰጠን ኃላፊነት መወጣት ይገባል በማለት ለዛሬ አበቃን፡፡
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 6 ቀን 2015 ዓ.ም