በኢትዮጵያ ውስጥ የተደረጉ አንዳንድ የዳሰሳ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ በማዕድን ልማት ዙሪያ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ ነው። በዚህ ዘርፍ ላይ ጥቂት ሰዎች እውቀቱና መረዳቱ ቢኖራቸውም፣ አብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል ግን ውስን መረጃ እንዳለው ይታመናል። ይህም መንግስትም ሆነ ባለድርሻ አካላት ማህበረሰቡ ስለ ማዕድን ሀብት ልማትና ትግበራ እውቀት፣ ግንዛቤና መረዳት እንዲኖረው ከማድረግ መጀመር እንዳለበት ያስገነዝባል።
ስለ ማዕድን ልማትና አስፈላጊነቱ የተረዳ ማህበረሰብ መፍጠር ከተቻለ የአገሪቱ ሀብት ለግለሰቦች መጠቀሚያ እንዳይውል በመከላከልና በመጠበቅ፣ ዘርፉ ለሀገር ምጣኔ ሀብት እድገት ሊኖረው የሚችለውን ፋይዳ እንደሚያጎላው እንደሚያደርግ ባለሙያዎች ምክረ ሀሳብ ይሰጣሉ፡፡
የአማራ ክልል ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ የበጀት አመት እቅድ ሥራም ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን የቢሮውን የ2015 በጀት አመት የስድስት ወር የእቅድ አፈጻጸም ስንቃኝ ለመረዳት ችለናል። ቢሮው በበጀት አመቱ ስድስት ወር ምን አቅዶ ምን ፈጸመ በሚል የጠየቅናቸው የአማራ ክልል ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ታምራት ደምሴ እንዳሉት፤ ቢሮው ወደ እቅድ ትግበራ ከመግባቱ በፊት የእቅዱ አካል የሆነውን የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል። ቢሮው ዘርፉን ለመምራት የሚያስችለውን አደረጃጀት መፍጠር የቻለው በቅርብ ጊዜ በተለይም የማዕድን ዘርፉ እንደ ሀገር በልዩ ትኩረት እንቅስቃሴ ከጀመረ ወዲህ ነው፡፡
የቢሮ አደረጃጀትና መዋቅሩ ሲጠናከር በዘርፉ የሚያከናወኑ ተግባራትም ውጤት የሚያስገኙ መሆን ስላለባቸው የንቅናቄ ሥራን በማስቀደም ነው ወደ ዋና ትግበራው የገባው። ሀብቱና ከሀብቱ የሚገኘው ገቢ በሀገራዊ ምጣኔ ሀብት ላይ ስላለው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ብቻ ሳይሆን፣ ልማቱ የሚከናወንበት አካባቢ የሚኖረው ማህበረሰብ ተጠቃሚነት እንዲጠበቅም ነው። ልማቱ በቴክኖሎጂ ሲታገዝና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ቀድሞ ግንዛቤ ከተያዘ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመቀነስ ያስችላል ከሚል እሳቤ በመነሳት እንደሆነም አቶ ታምራት ገልጸዋል፡፡
‹‹አልሚው ካልመጣ ልማቱ አይኖርም። እንዲመጣ ደግሞ መርጦ ለማልማት እንዲያስችለው ያለውን ሀብት ቀድሞ ማስተዋወቅና ምቹ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል›› የሚሉት አቶ ታምራት፤ የንቅናቄ መድረኩ ቀድሞ መከናወኑ የሀገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ አልሚውን በመረጠው ዘርፍ ለመሰማራት እንዲሁም የማዕድን ሀብቱና የሚገኝበትን አካባቢ ማሳወቁ አስፈላጊነቱ ጉልህ ሆኖ መገኘቱን ይገልፃሉ። ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ ባለው አመራር እንዲሁም በተለያየ መንገድ የሚመለከተው ባለድርሻ አካልና በማህበረሰብ ዘንድ የማዕድን ዘርፉ ከድህነት መውጫና የብልጽግና መንገድ መሆኑን አጀንዳ እንዲሆን የንቅናቄ መድረኩ ትልቅ ትርጉም እንደነበረው አስታውሰዋል።
በአማራ ክልል ከቢሮ አደረጃጀት ጀምሮ ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት እንዲሁም የልማቱም ተጠቃሚነት አነስተኛ እንደነበር የተናገሩት አቶ ታምራት፤ መንግሥት በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የአስር አመት መሪ እቅድ ማዕድንን የሀገር ምጣኔ ሀብት እድገት አንዱ አድርጎ ስለመረጠው ንቅናቄውም አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ገልጸዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የንቅናቄው ዓላማ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ግንዛቤ ፈጥሮ ወደ ሥራ መግባት ነው። ‹‹ማዕድን አዲስ የንጋት ተስፋ ለክልላችን፣ ለሀገራችን›› በሚል መሪ ቃል በተካሄደው የንቅናቄ መድረክ በዞንና በወረዳ ጭምር የተሳካ ተግባር ተከናውኗል። ንቅናቄው አልሚዎችን ጨምሮ ወደ 9ሺህ 807 የሚሆኑ ባለድርሻ አካላትን ተደራሽ ያደረገም ነው።
በዚህ የዝግጅት ምዕራፍ ቢሮው ሌላው ያከናወነው ተግባር ለአሰራር ማነቆ የሆኑ መመሪያዎችን በማሻሻል የዘርፉን የልማት ሥራ የሚመጥኑ ህጎች መተግበር ነው። በክልሉ የሚገኙ የማዕድን አይነቶችና የሚገኙባቸውን አካባቢዎች የሚያመላክት ፍኖተ ካርታ (ማፕ) ከማዘጋጀት ጀምሮ ክልሉ በማዕድን ሀብት የሚገኝበትንም ደረጃ በመረጃ ለማስደገፍ ቢሮው በክልሉ ውስጥ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የተቀናጀ ሥራ በመሥራት ያደረገው ጥረትም ውጤታማ መሆኑ የስድስት ወር ግምገማው ያሳያል። በጥናት የተደገፈ ሥራ መረጃ ሲኖር ሀብትን ለይቶ ለኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረግም ሆነ ከሀብቱ የሚገኘውን ጥቅም ለመከታተልና ለመቆጣጠር የሚያስችል እንደሆነም ቢሮው ከተከናወነው ተግባር መገንዘብ ችሏል፡፡
ክልሉ የማዕድን ልማት ቀጠናውን አንድ በመቶ ሺህ ካሬ ሜትር በሆነ መስፈርት መለየትና መከለል ቢሮው ካከናወናቸው አበይት ተግባራት መካከል ይጠቀሳል ያሉት አቶ ታምራት፣ ለግብርና እና ለሌሎች ልማት ከሚውለው መሬት የማዕድን ልማት ቀጠናዎችን ለይቶ መያዝ አልሚውን በቀላሉ በልማቱ ለማሰማራት ጠቀሜታው የጎላ ሆኖ ተገኝቷል ሲሉ ያብራራሉ። በዚሁ መሠረትም ቢሮው ወደ 20ሺ ካሬ ሜትር መሬት በመለየት ለኢንቨስትመንት ምቹ አድርጓል።
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ በክልሉ አዊ ዞን፣ ጓንጓ ወረዳ፣ ሰሜን ሸዋ አንኮበር፣ ደቡብ ወሎ አምባሰል፣ ዋግ ኽምራ ሰቆጣ ወረዳ፣ ሰሜን ጎንደር ጃንአሞራ አካባቢዎች የርቀት የዳሰሳ ጥናት እንዲካሄድ በማድረግ የመጀመሪያውን ምእራፍ ስራ አጠናቅቋል። በዳሰሳ ጥናቱ መሠረትም ከ40 በላይ የማዕድን አይነቶችን መለየት ተችሏል። ቢሮው በጥናት የተደገፈ ሀብትን ከመለየትና ለኢንቨስትመንት ምቹ ከማድረግ አኳያ ያከናወናቸው ተግባራት በአዲስ ተደራጅቶ ወደ ሥራ የገባ በመሆኑ አፈጻጸሙ ለቀጣይ ስድስት ወራት ሥራው ተሰፋ ሰጪ ሆኖ ተገኝቷል።
በቅድመ እቅድና ትግበራ ሥራ በተለይም በጥናት በመለየት ለኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረግ በተከናወነው ተግባር ከተመዘገበው ውጤት በቢሮው የማምረት ፈቃድ ተሰጥቷቸው ወደ ሥራ ከገቡት አልሚዎች አንድ የሲሚንቶና አንድ የጂብሰም ቦርድ ፋብሪካዎች ይጠቀሳሉ። 12 ኩባንያዎችም የወርቅ ማዕድን ምርመራ ፍቃድ ከቢሮው የወሰዱ ሲሆን፣ በድንጋይ ከሰል እና በብረት ማዕድን ልማት ላይ በተመሳሳይ ቢሮው ፍቃድ ሰጥቷል፡፡
በመንግሥት ከተቀመጡት የትኩረት አቅጣጫዎች በማዕድን ክፍለ ኢኮኖሚው ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር በመሆኑ ቢሮው በበጀት አመቱ ለ52 ሺህ 858 ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ከያዘው እቅድ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ለ18 ሺህ 228 ዜጎች በዘርፉ የሥራ እድል ፈጥሯል።
በቅድመ እቅድ የተከናወኑት ተግባራት የመጨረሻ ግባቸው ገቢ ማስገኘት በመሆኑ፣ በዚህ ረገድ በተለይም የውጭ ምንዛሬን በማስገኘት የተከናወነውንም ሲገልፁ፤ ክልሉ ከጌጣጌጥ ማዕድናት በኦፓል ማዕድን እንደሚታወቅ አንስተዋል። በመሆኑም በበጀት ዓመቱ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በእቅድ የተያዘው 28ሺህ 531 ኪሎ ግራም ሲሆን፤ በስድስት ወር ክንውን 14ሺህ 268 ኪሎ ግራም ኦፓል ለውጭ ገበያ ቀርቧል። በገቢም ከኦፓል ልማት በበጀት አመቱ አጠቃላይ እቅድ የተያዘው 15 ነጥብ ሁለት ሚሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት እንደሆነና በስድስት ወር አንድ ሚሊየን 692 ሺህ 872 ነጥብ 42 ዶላር ገቢ ከዘርፉ መገኘቱን አቶ ታምራት ገልጸዋል፡፡
ክልሉ በበጀት አመቱ 70 ኪሎ ግራም ወርቅ ለማልማት ታቅዶ እንደነበርም አቶ ታምራት ጠቁመዋል። በዚህም ወደ 84 ነጥብ 98 ኪሎ ግራም በማልማት ከእቅድ በላይ መፈጸም መቻሉን ገልፀው፣ የለማው ወርቅም ለብሄራዊ ባንክ መቅረቡንም አስታውቀዋል። ከዘረፉ አራት ሚሊየን 928ሺህ 840 ዶላር ገቢ እንደተገኘም ይናገራሉ። ከማዕድን ክፍለ ኢኮኖሚው ጋር በተያያዘ በሀገር ውስጥ ገቢን ማሳደግ ተብለው በእቅድ ከተያዙት ከተለያዩ የአገልግሎት ክፍያዎችም ገቢ መገኘቱን ጠቅሰው፣ 100 ሚሊየን 400 ሺህ ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ፣ 16 ሚሊየን 112ሺህ 656ብር መገኘቱን አመልክተዋል፡፡
የውጭ ምንዛሪ ወጪን በማዳን ደረጃም ክልሉ የተለያዩ ተግባራት ማከናወኑን የጠቆሙት አቶ ታምራት፣ በበጀት አመቱ ግምሽ አመት አፈጻፀም ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ግብአት የሚውሉ እንደ ጂብሰም፣ ላይምስቶን፣ ሸክላ አፈር የመሳሰሉ ማዕድናት በማልማት ወደ 27 ሚሊየን ዶላር የሚገመት የውጭ ምንዛሪ ማዳን መቻሉን አስረድተዋል። በበጀት አመቱ በሀገር ውስጥ በማምረት ለመተካት በእቅድ የተያዘው አንድ ሚሊየን 37ሺህ 02 ቶን ማዕድን መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ቢሮው በአዲስ መልኩ ከመዋቀሩ ጋር ተያይዞ በበጀት አመቱ ስድስት ወራት አብዛኛው የሥራ እንቅስቃሴ በቅድመ ዝግጅት ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን አቶ ታምራት ገልጸውልናል። ያም ሆኖ ግን የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት፣ በሀገር ውስጥም ከተለያዩ አገልግሎቶች የተገኘው ገቢ ለቀጣይ ሥራ ተስፋ ሰጭ መሆኑና ውጤት መመዝገቡን አመራሩ በግምገማው ማስቀመጡን ያስረዳሉ። በመዋቅር ደረጃ ዘርፉን ብቻ የሚመራ ዘርፍ የተፈጠረበት፣ በክልሉ 13 ዞኖች በመመሪያ ደረጃ መዋቀሩና በ45 ወረዳዎች ውስጥም በተመሳሳይ አደረጃጀቱ መጠናከሩ እንደ አንድ ስኬት መወሰዱን ይገልፃሉ።
ከህገወጥ ንግድ ጋር በተያያዘም የነበረውን ሁኔታ በወርቅ ማዕድን ላይ ክትትልና ቁጥጥሩ የላላ፣ ለሌሎች መጠቀሚያ ሲውል እንደነበር አስታውሰው፤ በተያዘው በጀት አመት በክልሉ በወርቅ ማዕድን የተመዘገበው ውጤት ከዚህ ቀደም ያልተገኘ እና ለብሄራዊ ባንክም የቀረበበት ጊዜ መሆኑን አመልክተዋል።
ውጤቱ በስኬት ቢወሰድም በበጀት አመቱ ካጋጠሙት ተግዳሮቶች መሻገር ያልተቻለው ህገወጥ የማዕድን ንግድን መቆጣጠር አለመቻልን እንደሆነ አቶ ታምራት ይናገራሉ። በአልሚዎች በኩል ለማልማት ፈቃድ ወስደው ቶሎ ወደ ሥራ አለመግባትና መሬት አጥሮ ማስቀመጥ ጉዳይም ሌላው ተግዳሮት እንደሆነም ይጠቅሳሉ። ያለው ሁኔታም በቀጣይ ፍቃድ የመሰረዝ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስገድድ እንደሆነም ነው ያመለከቱት፡፡
የተሟላ መሠረተ ልማት አለመኖርም በማዕድን ልማቱ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እንቅፋት እንደሆነ ቢሮው የለየው ችግር መሆኑን ጠቅሰዋል። በተለይም ልማቱ የሚከናወንበት ሥፍራ የሚያስገባ መንገድ ችግር መቀረፍ እንዳለበት ታምኖበታል። ወደ ማዕድን ልማቱ የሚመላለሱ ተሽከርካሪዎች ጠንካራ መሆን እንዳለባቸው ያለው ነባራዊ ሁኔታ ያስገድዳል ያሉት አቶ ታምራት፣ መንግሥት እነዚህ ተሽከርካሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ የሚፈቀድበትን ሁኔታ ቢያመቻች ባለሀብቱን የበለጠ ያነቃቃዋል ይላሉ።
እንደ ድንጋይ ከሰል ማምረቻ ላሉ ፋበሪካዎች የሚውል የኃይል አቅርቦትም ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመዋል። በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በነበረው ጦርነት ዘርፉ ትልቅ ችግር ውስጥ ወድቆ እንደነበር አስታውሰዋል። የጦርነቱ መቆም አንድ ትልቅ ነገር መሆኑን ጠቅሰው፣ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ እንደልብ ለመሥራት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩ ተስፋ ሰጪ ሆኖ መገኘቱን ገልጸዋል። በክልሉ በዘረፉ መሰማራት ለሚፈልጉ ሁሉ በክልሉ ምቹ ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰው፣ አቶ ታምራት ጥሪ አቅርበዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን የካቲት 3 ቀን 2015 ዓ.ም