የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም ወዳድ ሕዝብ ነው። ለዘመናት አብሮ ተከባብሮ በመኖርና የሰላም ተምሳሌት በመሆን በአርአያነት ሲጠቀስ የኖረ ሕዝብ ነው። ከኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ አኩሪ መገለጫዎች መካከል የብሔር፣ የእምነት፣ የቋንቋ፣ የባሕልና ሌሎች ልዩነቶችን ዕውቅና በመስጠት ተሳስቦና ተከባብሮ መኖር ትልቁ እሴት ነው። በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ሰላም መገለጫቸውና የመጀመሪያ ምርጫቸው ነው። ለሰላም ሲሉ በርካታ መስዋዕትነቶችን ይከፍላሉ።
ሆኖም ይህንን ሰላም ወዳድ ሕዝብ የሚበጠብጡ፤በሀገሩ በሰላም ወጥቶ እንዳይገባ ድንጋይ የሚፈነቅሉ፤ጦር የሚሰብቁና መሣሪያ የሚመዙ የሞት ነጋዴዎች በርካቶች ናቸው። በነዚህ የእኩይ ሰዎች ጦስም ሰዎች ለሞት፤ለሥደት፤ለመፈናቅ፤ለመከራና ሥቃይ ይዳረጋሉ፡፡
የዚህ ሁሉ ሰለባና ገፈት ገማሽ ከሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ዋነኛው ደግሞ ወጣቱ ነው። በመሆኑም ወጣቱ የሰላም ዋጋን ተረድቶ ፊቱን ወደልማት በማዞር ራሱን መጥቀምና ለሌላውም መትረፍ እንዳለበት የአብዛኞች ምኞትና ፍላጎት ነው። ወጣቱ ለሰላም ዘብ ሆኖ በልማት ተጠቃሚ እንዲሆን ታዲያ የየድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን የአማራና የኦሮሚያ ወጣት ማኅበራት ይገልፃሉ።
ወጣት ከፍያለው ማለፉ የአማራ ወጣቶች ማኅበር ዋና ፀሐፊ ነው። እርሱ እንደሚለው ማኅበሩ ከሕግ ማስከበር ዘመቻው ጀምሮ በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል። ከነዚህ ውስጥ ደግሞ ዋናው በሁሉም የክልሉ ከተሞች ላይ ሰርጎ ገቦችን ከመከላከልና ከፀጥታ መዋቅር ጋር በመሆን በየአካባቢው ሰላምና ፀጥታ እንዲረጋገጥ ጥበቃ የማድረግ ሥራ ነው። ለዚህም በጊዜው የግንዛቤ መስጫ መድረኮች ሲያካሂድ ቆይቷል። በተለይ ደግሞ ከባሕርዳር ዩኒቨርስቲ መምህራን ጋር በመሆንና ትላልቅ የግንዛቤ መድረኮችን በመፍጠር ለወጣቶች ሥልጠና በመስጠት ግንዛቤያቸው እንዲሰፋና የክልላቸውን ሰላም እንዲጠብቁና በልማት ሥራዎች ላይ እንዲሳተፉ አድርጓል።
እንደወጣት ከፍያለው ገለፃ፤ የንቅናቄና ግንዛቤ መድረኮቹ 20 ሰዎችን በመመደብ አሥሩ በጎንደር ማዕከል እስከ ሑመራ ድረስ፤ አሥሩ ደግሞ በጎጃም ሰሜን ሸዋ ደሴ ድረስ ሲካሄዱ ቆይተዋል። በዚህም እንደማኅበር የክልሉን ሰላም ከመጠበቅ አንፃር ጥሩ ሥራ ተሠርቷል።
በአሁኑ ግዜም የወልቃይት፣ ራያ፣ አጣዬ እና የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር መሥመር የክልሉ የሰላም ሥጋት ናቸው ብሎ በመለየት የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። በተለይ ደግሞ የአጣዬ መሥመር የውስጥ ኃይሎችም ጭምር የተሳተፉበት ጥቃት በተደጋጋሚ ይከሰታል። ሕዝቡ ወደሰላም እንይመለስና ተረጋግቶ እንዳይኖር፤ ብሎም እርስ በርሱ እንዲጋጭ የማድረግ ሥራዎች ይሠራሉ። ይህም ለመላው የክልሉ ነዋሪና ወጣቱ ኅብረተሰብ ትልቅ ሥጋት ነው።
በአጣዬ አካባቢ ያለው ሁኔታ ግን መንግሥት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ችግሩ በተደጋጋሚ የሚከሰትና ማብቂያ ያላገኘ በመሆኑና ድርጊቱም በተቀነባበረና በተጠና ሁኔታ የሚፈፀም በመሆኑ ወጣቶች ለጉዳዩ ምላሽ ሊሰጡበት የሚችሉት ጉዳይ አይደለም። ከፀጥታ መዋቅሩ ጎን ከመቆም፣ አጋዥ ከመሆንና ድርጊቱን ከማውገዝ በዘለለ ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር የለም። ለዛም ነው የመንግሥት ትኩረት የሚያስፈልገው። በአግባቡ ተጠንቶና ፖለቲካዊ ትርጉም ተሰጥቶት ምላሽ ሊሰጠው የሚገባ ስለሆነ የፖለቲካ አመራሩም በደምብ አጥንቶ ምላሽ መስጠት አለበት።
ነገር ግን ወጣት ማኅበሩ እንደክልልም እንደሀገርም ለሰላም ከክልሉ ውጪና ባሻገር ከሌሎች አጎራባች ክልሎች ጋር በጋራ እየሠራ ይገኛል። ለአብነትም ከኦሮሚያ ወጣቶች ማኅበር ጋር በቅርቡ በአዲስ አበባ መድረክ ነበረው። ዋነኛ የውይይቱ አጀንዳም የሚያጠነጥነው፤ እንደ አንድ ሲቪክ ድርጅትና ገለልተኛ ተቋም መንግሥት የሚያጠፋቸውን ጥፋቶች በማሳየት፤ የሚያለማቸውን ደግሞ በመደገፍ ገለልተኛነትን በመጠበቅና አንድ ሆኖ በመቀጠል እንዴት የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንደሚቻል ነበር፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በሀገራዊ ምክክሩ ላይ ወጣቶች ምን ዓይነት ፋይዳ ይኖራቸዋል? የሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ መሆን ለወጣቶች ምን ትሩፋቶችን ይዞ ይመጣል? ውድቀቱ ምን ጉዳት ይዞ ሊመጣ ይችላል? በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያም ውይይት ተደርጓል። የክልሎች ከክልሎች በተለይ ደግሞ በወጣቶች ደረጃ ግንኙነቶችን ለማጠናከርም ከመግባባት ላይ ተደርሷል።
በቀጣይም የአማራና የኦሮሚያ ወጣቶችን የሚያቀራርቡ ተመሳሳይ የአንድነትና የአብሮነት ውይይት መድረኮች በጅማና ጎንደር ከተሞች ይደረጋሉ። ሁለቱ መድረኮች በስኬት የሚጠናቀቁ ከሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሁሉም የየክልሎች ወጣቶች የሚገናኙበት አንድ መድረክ ለማካሄድ በማኅበሩ በኩል ታስቧል። በተጨማሪም የአማራ ምሑራንና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች በተገኙበት አንድ የውይይት መድረክም በቅርቡ በክልል ደረጃ ያካሂዳል።
የመድረኩ ዋነኛ ማጠንጠኛም አሁን የመጣውን ሰላም አስተማማኝ አድርጎ ከማስቀጠል አኳያና ወጣቱ ወደልማት እንዲገባ በማድረግ በኩል የተፅዕኖ ፈጣሪ ወጣቶችና አክቲቪስቶች ሚና ምን ሊሆን ይችላል ነው። በጥቅሉም ክልሉ ሰላም እንዲሆንና ባለፈው ወር የጥምቀት በዓልና ሌሎችም በዓላት በሰላምና በስኬት ተከብረው እንዲጠናቀቁ በሁሉም አካባቢዎች ያሉ የክልሉ ወጣቶች ትልቅ አስተዋፅዖ አድርገዋል። በሕግ ማስከበር ዘመቻው ወቅትም በተለይ በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ሆስፒታሎች ውስጥ በበጎ ፍቃድ ቁስለኞችን የመንከባከብ ሥራዎችን አከናውነዋል።
ወጣት ከፍያለው እንደሚለው፤ በአማራ ክልል በርካታ ሥራ አጥ ወጣቶች አሉ። እስካሁንም መንግሥትም ሆነ ሌሎች የግል ተቋማት በቂ ምላሽ እየሰጡ አይደሉም። ወጣት ማኅበሩ በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ ለመሥራት ያሰበውም የክልሉ ፈተና ሆኖ በቀጠለው የሥራ አጥነት ጉዳይ ላይ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ባለሃብቶችና ሥራ እድል ሊፈጥሩ የሚገባቸው ተቋማት በተለይ ደግሞ መሬት ወስደውና አጥረው የተቀመጡ፣ ትላልቅ ድርጅትም ኖሯቸው የሥራ እድል ያልፈጠሩ በአንፃሩ ደግሞ የሥራ እድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች ዝቅተኛ ተከፋይ ስለሆኑ ኑሯቸውን መግፋት ባለመቻላቸው በዚህ ላይ ማኅበሩ ትኩረት አድርጎ ይሠራል።
በተለይ ግን የሥራ ፈጠራው ጉዳይ በክልሉ የወጣቱ መሠረታዊ ችግር በመሆኑ ለክልሉ ሰላም እጦት የራሱን አስተዋፅዖ የሚያበረክት በመሆኑ የማኅበሩ ዋነኛና ቀጣይ የሥራ እድል ፈጠራ ላይ ነው። ከዚሁ ጎን ለጎን ግን በክልሉ ሰላም እንዲረጋገጥና ወጣቱ በአመክንዮ የሚታገልና በሀሳብ ትግል ነገሮችን ለመፍታት የሚሞክር እንዲሆን ተከታታይነት ያላቸው መድረኮች በየክልሉ ከተሞች ይካሄዳሉ።
ይህ ወጣት የዚች ሀገር ባለቤት እንደመሆኑ ከአባቶቹ የተረከባትን ሀገር የማስቀጠልና ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነት አለበት። ይህን ማድረግ የሚችለው ደግሞ በተረጋጋ መንፈስ፣ በሀገራዊ አንድነትና ከብሔርተኝነት አስተሳሰብ በፀዳ መልኩ ነው። ወጣቱ ምክንያታዊና ሚዛናዊ ሀሳብ በማንሸራሸር፣ በመተጋገዝና በመደጋገፍም ጭምር እስካልቀጠለ ድረስ አብሮ የመቀጠሉና ችግር ውስጥ የመውደቁ እድል ሰፊ ነው። ስለዚህ ወጣቶች የአብሮነትን ጉዳይ አትኩሮ ሊጠብቀው ይገባል። ለአንድነቱ ጉዳይ መደራደር የለበትም። ለሰላምም ዘብ መቆም ይኖርበታል።
የኦሮሚያ ወጣቶች ማኅበር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወጣት ገዛኸኝ አንዳርጌ በበኩሉ፤ እንደሚለው በክልሉ ያለው የሰላም ሁኔታ ከቦታ ቦታ ይለያያል። ከሸኔ ጋር በተያያዘ በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች በተለይ ደግሞ በምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ በሚገኙ ወረዳዎችና ቀበሌዎች የፀጥታ ችግሮች አሉ። ይህ ችግር ይበልጥ የተባባሰውም ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘና የመንግሥት ሙሉ ኃይል ወደዚያ በመሄዱ ነው።
ይሁንና በአሁኑ ጊዜ የሰሜኑ ጦርነት ስለተቋጨና ሰላም ስለመጣ በሰሜኑ በኩል ያለው ኃይል ወደምዕራብ ኦሮሚያ መጥቶ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። በዚህም ትልቅ ለውጥ እየመጣ ነው። አንዳንድ የሸኔ አባላትም በሰላማዊ መንገድ ገሚሶቹ ለአባገዳዎች ሌሎች ደግሞ ለፀጥታ ኃይሎች እየሰጡ ነው። ይህ ሲባል ግን የተሟላ ሥራ ተሠርቷል ማለት አይደለም። አሁንም ተጨማሪ የፖለቲካና የአደረጃጀት ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡
የክልሉ ወጣት በአብዛኛው ሥራ አጥ በመሆኑ ሰላምን ከማንም በላይ ይፈልገዋል። ለሰላም ሲልም ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሏል። ይሁንና ሰላም እንዳይኖርና ወጣቱም ሥራ እንዳይሠራ፣ ትምህርቱንም እንዳይከታተል የሚያደርጉ ሌላ ተልዕኮ ያላቸው አካላት አሉ። ዓላማው ሳይገባቸው በተሳሳተ መንገድ ከነዚሁ አካላት ጋር ሆነው የሚሠሩ ወጣቶችም አሉ። ሰላምና መረጋጋት ቢኖር ግን ቁጭ ብሎ በመወያየትና ወጣቱም ሥራ ፈጥሮ መሥራትና ራሱን መለወጥ ይችላል። ከዚህ አንፃርም የክልሉ ወጣት በማኅበረሰቡ ውስጥና በበጎ ፍቃድ ሥራዎች ላይ በቀዳሚነት እየተሳተፈ ይገኛል። ሥራ ሳይኖረው ለመለወጥና ለእድገት ያለው ፍላጎትም ከፍተኛ ነው።
እንደ ወጣት ገዛኸኝ ገለፃ፤ የሰላም ችግር የሚመጣው ካለመረጋጋትና በፖለቲካ ሽኩቻ በሚመጡ ችግሮች ነው። የክልሉ ወጣት ማኅበር ሥጋትም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው የፖለቲካ ፍላጎት ከብሔር ጋር መገናኘት ነው። ለአብነትም የተረኝነት ነገሮችና ሌሎችም ከብሔር ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ይነሳሉ። እንደዚህ አይነት ነገሮች ደግሞ ወጣቱን ስሜታዊ በማድረግ ወደተሳሳተ አቅጣጫ ይመሩታል። ስለሆነም መከባበርና መተሳሰብ ያስፈልጋል።
ከዚህ አንፃር ሰው ተረጋግቶ እኔ ብቻ ከሚለው አስተሳሰብ ወጥቶ እኛ ወደሚለው ከመጣ ሰላምና አንድነትን ማረጋገጥ ይቻላል። ማኅበሩም ወጣቱ በሰከነ መንገድ ነገሮችን በማየትና በማመዛዘን ወደፊት እንዲሄድ እየሠራ ይገኛል። በዚህም በርካታ ለውጦች እየመጡ ነው። ነገር ግን ይህ ብቻውን በቂ ባለመሆኑ በተለይ ይህን በማጉላት ረገድ ሚዲያዎች ትኩረት አድርገው ሊሠሩ ይገባል። መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት በወጣቱ ስብዕና ግንባታ ላይ ብዙ መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ይህን ማድረግ ከተቻለም የተሻለች ኢትዮጵያን ማየት ይቻላል።
በክልሉም ሆነ በሀገሪቱ የተሻለ ሰላም እንዲመጣ በወጣቱ ላይ መሥራት ያስፈልጋል። በተለይ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች በመኖራቸው ብሔርን ከብሔር ጋር ለማጋጨት የሚሠሩ አካላት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል። ከዚህም ባሻገር ታች ወርዶ የሕዝቡን በዋናነት ደግሞ ወጣቱ ፍላጎት ምን እንደሆነ ለማወቅ ማወያየት ያስፈልጋል።
ወጣት ማኅበሩም በክልሉ ምንም ዓይነት የሰላም ችግር እንዳይፈጠር ይሠራል። ሰላምን ለማስጠበቅ ደግሞ እንደወጣት አደረጃጀትና እንደክልሉ ብሔር ብሔረሰቦች ወጣቶች ሰፊ ርብርብ እያደረገ ይገኛል። ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። ወጣቱ ለሰላም በነፃ እየሠራ ያለውም ለሕዝቡና ለሀገሩ ሲል ነው።
ይሁንና ራሳቸው ሳይነኩ ወጣቱ በተለያዩ ነገሮች ሰለባ እንዲሆን የሚሠሩና ብሔርን ከብሔር ጋር ለማጋጨት የሚጥሩ ሰዎች ከዚህ ሥራቸው መቆጠብ አለባቸው። ከዚህ ይልቅ ቁጭ ብሎ መወያያትና መነጋገር አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። ማኅበሩም ከዚህ ወዲያ በእንዲህ አይነቱ ድርጊት ውስጥ በሚሳተፉ አካላት ላይ የራሱን አቋም ይወስዳል። ምንም ዓይነት የፀጥታ ችግር እንዲፈጠርም አይፈልግም።
ወጣቱ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር ነው። ነገር ግን ደግሞ ወጣቱ እስከዛሬ ድረስ በተለያዩ ነገሮች ሰለባ ሆኗል። ይህ ነገር ደግሞ አሁንም መቀጠል የለበትም። ሥራውን ተረጋግቶ መሥራት አለበት። ራሱንና ሀገሩንም መለወጥ ይጠበቅበታል። ለዚህ ታዲያ የሰላም ዋጋ ምን ያህል ውድ መሆኑን ተረድቶ ፊቱን ወደሰላም ማዞር ይኖርበታል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን የካቲት 3 ቀን 2015 ዓ.ም