ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ዘርፍ እምቅ አቅም ያላት ሀገር ናት:: አገሪቱ ግዙፍ አምራች ኃይል፣ ወሳኝ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ፣ ምቹ ሕጋዊ ማዕቀፎችና ለዘርፉ እድገት አወንታዊ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ ሌሎች መልካም አጋጣሚዎችና አስቻይ ሁኔታዎች አሏት:: በኢንዱስትሪ ያላትን ይህን እምቅ አቅም በመጠቀምና ከዚሁ ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የምታደርገውን መዋቅራዊ ሽግግር እውን ለማድረግም ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ጥረት አድርጋለች::
የዘርፉ ችግሮች፤ የመንግሥትን፣ የግሉን ዘርፍና በአጠቃላይ የሕዝቡን የተቀናጀ ጥረት የሚፈልጉ እንደሆኑ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል:: ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ብዙ ሙከራዎች ተደርገው የማይናቁ ውጤቶች ቢመዘገቡም፣ ከአገሪቱ አቅምና ከችግሮቹ ስፋት አንፃር ግን መፍትሄዎቹ የሚፈለገውን ያህል ውጤት ሊያስገኙ እንዳልቻሉ በተደጋጋሚ ተገልጿል::
ዘርፉ በግብዓት (ጥሬ ዕቃ)፣ በሰው ኃይል፣ በማምረቻ ቦታ፣ በኃይል፣ በፋይናንስና በውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ችግሮች የተተበተበ ነው:: በዚህም ምክንያት ኢንዱስትሪዎች እያመረቱ ያሉት የአቅማቸውን ግማሽ ያህል ብቻ እንደሆነ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃዎች ያሳያሉ::
የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከአጠቃላይ ጥቅል አገራዊ ምርት ያለው ድርሻ ከሰባት በመቶ ያልበለጠ መሆኑን ቅርብ ጊዜ የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ:: ይህን ድርሻ ወደ 17 ነጥብ ሁለት በመቶ ለማሳደግ ታቅዷል:: ከዚህ በተጨማሪም አሁን ያለውን 50 በመቶ የኢንዱስትሪዎች የምርታማነት አቅም ወደ 85 በመቶ የማድረስ እቅድም ተይዟል::
የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ መጠናከር ሌሎቹን የኢኮኖሚ ዘርፎች የሚያሳድግ ግብዓት ነው:: ለአብነት ያህል የግብርና ምርታማነትን ለመጨመር ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎችን እንዲሁም የአገልግሎት ዘርፉን ውጤታማነት ለማሻሻል ደግሞ የዘርፉን የስራ እንቅስቃሴ የሚያሳልጡ ግብዓቶችን (መሳሪያዎችን) በብዛት፣ በጥራትና በፍጥነት የሚያመርት አምራች ዘርፍ ያስፈልጋል:: አምራች ዘርፉ ከሚጠናከርባቸው መንገዶች መካከል አንዱ በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ማድረግ ነው::
ፖሊሲዎችን ጨምሮ ምቹ ሕጋዊ ማዕቀፎችን ማዘጋጀት፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦቶችን ማስፋፋት፣ የብድር አቅርቦትን ማመቻቸት እና ተደራሽ፣ ቀልጣፋና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት ከድጋፎቹ መካከል ይጠቀሳሉ:: በኢትዮጵያም አምራች ዘርፉ የግብርናውን ሚና ተክቶ ምጣኔ ሀብቱን እንዲመራና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት እንዲመዘገብ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል::
መንግሥት የኢንዱስትሪው ዘርፍ ችግሮችን ለማቃለል እየተገበራቸው ከሚገኙ የመፍትሄ እርምጃዎች መካከል እየተተገበረ ያለው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገራዊ ንቅናቄ ተጠቃሽ ነው:: የንቅናቄው ዋና ዋና ዓላማዎች የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግሮች በጋራ በመፍታት ለዘርፉ ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ዘርፉ ለኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ ማስቻል እንዲሁም በዘርፉ ያለውን የሥራ ባህል ማሻሻልና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ጥራትና ተወዳዳሪነት በማሳደግ ገቢ ምርቶችን የመተካት ሽፋንን ማሳደግ ናቸው::
በንቅናቄው የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ምርትና ምርታማነት ለመጨመር ብሎም የዘርፉን ልማት ለመደገፍ እንዲሁም አምራች ኢንዱስትሪዎችን በጥራትና በቁጥር ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት ይከናወናሉ:: ይህም የኢንዱስትሪ ዘርፉን ከተለመደው አሰራር በማሻገር ምርታማነትን ለመጨመር እንደሚያግዝ ታምኖበታል::
‹‹የኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ የኢንዱስትሪ ምርቶችን አምርታ ለመሸጥ እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት
ያስችላታል:: ይህም የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመቅረፍ የምታደርገውን ጥረት ወደ ወሳኝ ምዕራፍ የሚያሻግር ይሆናል:: አገሪቷ ያላትን የዘርፉን እምቅ ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም ይቻል ዘንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ተሞክሮዎችን በመቀመር ንቅናቄውን አጠናክሮ በማስቀጠል የተፈለገው ውጤት እንዲመጣ ባለድርሻ አካላትን ማሳተፍ፣ ዘርፉን በጥናትና ምርምር መደገፍ፣ ለዘርፉ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ማድረግ እና የሀገር በቀል ምርቶችንና አመራረትን ማሳደግ ያስፈልጋል::
በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ አስቻይ ሁኔታዎችን በመፍጠር የዘርፉን የማምረት አቅም ማሳደግ፣ ለዜጎች ተጨማሪ የስራ ዕድል መፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ እና ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሬን ማዳን ከ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› መርሃ ግብር የሚጠበቁ ውጤቶች ናቸው::
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ዓመት በንቅናቄው ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማሳደግ በሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ፣ የሀገር ውስጥ ምርቶችን መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነና በ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ የኢንዱስትሪ ዘርፉን ምርታማነት ለመጨመር እየተሰራ እንደሚገኝ መናገራቸው ይታወሳል::
በሁሉም አካባቢዎች አመራሩም ሆነ ባለሃብቱ ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ ወስዶ ወደ ሥራ በመግባቱ፤ አዳዲስ ኢንቨስመንቶችን በመሳብ፣ የወጪ ንግድን በማሳደግ፣ አዳዲስ የወጪ ምርቶችን ወደ ሥራ በማስገባት እንዲሁም ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች በመተካት ረገድ በንቅናቄው ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን ማስመዝገብ እንደተቻለ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገልጿል:: ለአብነት ያህል በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት በተከናወነው ተግባር ከአንድ ቢሊየን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸውን ምርቶች በሀገር ውስጥ ምርቶች መተካት፣ ማምረት ያቆሙ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ ማድረግ ተችሏል::
ንቅናቄው እየተተገበረባቸው ከሚገኙ ክልሎች አንዱ ከሆነው የኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ አስተዳደር የተገኘው መረጃም ይህንኑ ይጠቁማል፤ ንቅናቄው በኦሮሚያ ክልል በሚያዝያ 2014 ዓ.ም የተጀመረው ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት፣ ኦሮሚያ ታምርት››በሚል መርሃ ግብር ነው:: ይህም የክልሉን ኢንቨስትመንት አፈፃፀም ለማሻሻል ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ታምኖበታል:: ንቅናቄው ሲጀመር የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ያለ አምራች ዘርፉ ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደማይቻል ገልፀው፣ አርሶ አደሮችን በማበረታታት ጭምር ዘርፉን ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረው ነበር:: ከዚህ በተጨማሪም ‹‹የኦሮሚያ ክልል መንግሥትም የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ ተገቢውን ድጋፍ ያደርጋል:: ባለሃብቶች ዘርፉን ለማጠናከር በቁርጠኝነት ሊሠሩ ይገባል›› ሲሉ መግለጻቸው ይታወሳል::
የክልሉ መንግሥት አምራች ዘርፉ በምጣኔ ሀብቱ ውስጥ ያለውን ሚና ተገንዝቦ ለባለሀብቶች መሬት የማቅረብ፤ የሰው ኃይል የማዘጋጀት፤ የክልሉ የ15 ዓመት የኢንዱስትሪ ስትራቴጂና ፍኖተ ካርታ እንዲዘጋጅ፣ በ168 የክልሉ ወረዳዎች ላይ በየአካባቢዎቹ የሚገኙ ፀጋዎችን በመለየት አነስተኛ ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ ማምረቻዎች እንዲስፋፉና የኅብረተሰብን ግንዛቤ በማሳደግ የኢንዱስትሪ ሰላም እንዲሰፍን የማድረግ ተግባራትን አከናውኗል::
የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት፣ ኦሮሚያ ታምርት›› ንቅናቄ የምክክር መድረክ ሰሞኑን በአዳማ ከተማ ሲካሄድ የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ኃይሉ ጀልዴ እንዳስረዱት፤ በአገር ደረጃ ተጠናክሮ የቀጠለው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ መነቃቃት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል:: ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት እና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ትልቅ ሚና ያለው የኢንቨስትመንት ዘርፍ በንቅናቄው ሰፊ ድርሻ የሚኖረው በመሆኑ ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል:: ለዚህም ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ የሚችሉ ልዩ ልዩ ማሻሻያዎችን ማድረግና ባለሀብቶችን መደገፍ ይገባል::
በዚህ ረገድ የኦሮሚያ ክልል መንግሥትም ሆነ የአዳማ ከተማ አስተዳደር ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት፣ ኦሮሚያ ታምርት›› ንቅናቄ እንዲሳካና የኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲያድግ የሕግ ማሻሻያዎችን ከማድረግ ጀምሮ ሌሎች ምቹ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥሩ ከንቲባው አስታውቀዋል::
ንቅናቄው የባለድርሻ አካላትን ጥብቅ ትብብርና ተሳትፎ እንዲሁም ቁርጠኝነትን ይፈልጋል:: ግማሹ የሚሰራበት፣ ግማሹ ደግሞ በአቋራጭ የህዝብን መሬት በመያዝና በመሸጥ ሀብት የሚያከማችበት አሰራር እየቀረ ነው:: ጤናማ በሆነና በትክክለኛው መንገድ እየሰሩ ያሉትን የማበረታታትና የማጠናከር ሥራ መሥራት፣ መሬት ይዘው የሚያከራዩትን ደግሞ መምከርና ወደ ቀጥተኛው መስመር እንዲገቡ ማድረግ ያስፈልጋል:: ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት፣ ኦሮሚያ ታምርት›› ንቅናቄ የሚሳካው ሕጋዊ ያልሆኑና አቋራጭ አሰራሮችን በመዝጋት፣ በትክክለኛው መንገድ ሰርቶ ተወዳዳሪ መሆን ሲቻል ነው›› ሲሉም ከንቲባው አስገንዝበዋል::
አቶ ኃይሉ እንደሚሉት፣ በኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተያዘውን አቅጣጫ በመከተል በአዳማ ከተማ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተግባራዊ ሆኗል:: በዚህም በከተማዋ የሚገኙ ባለሀብቶች ከዚህ ቀደም ወደ ዘጠኝ ቢሮዎች በመሄድ ያገኙት የነበረውን አገልግሎት በአንድ ቦታ እንዲያገኙ ተደርጓል።
የአዳማ ከተማ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሶሬቻ አስፋው በበኩላቸው፣ ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት፣ ኦሮሚያ ታምርት›› ንቅናቄ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴውን ከነበረበት ደረጃ እንዲያድግ የራሱን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ ይገልፃሉ::
እርሳቸው እንደሚሉት፣ ንቅናቄው በኢንዱስትሪው ዘርፍ ያሉ ችግሮችን (የግብዓት አቅርቦት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት …) በዘላቂነት በመፍታት በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች ዘርፉን ወደተሻለ ደረጃ እንዲያሸጋግሩ እንዲሁም በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ስራቸውን ወደ አምራች ኢንዱስትሪ እንዲያሰፉ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ያግዛል::
ንቅናቄውን በመጠቀም በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ስራ ያቆሙ ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት ስራቸው እንዲመለሱ፣ ከአቅማቸው በታች የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች ደግሞ በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ እና በሙሉ አቅማቸው እያመረቱ የሚገኙ አምራቾች ስራቸውን የበለጠ እንዲያሰፉና በገቢ ግኝት፣ በምርት አቅርቦት ጭማሬ እና በስራ እድል ፈጠራ ረገድ የተሻሉ ጥቅሞችን እንዲያስገኙ ለማገዝ እየተሰራ መሆኑን አቶ ሶሬቻ ይጠቅሳሉ:: በዚህም ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆናቸውን አመልክተው፣ ውጤቶቹን አጠናክሮ በማስቀጠል የዘርፉ ባለሀብቶች በኢኮኖሚው ውስጥ የሚኖራቸውን ድርሻ ማሳደግና ተጨባጭ ለውጥ እንዲያስመዘግቡ ማድረግ ይገባል ይላሉ::
አቶ ሶሬቻ እንደተናገሩት፤ በአዳማ ከተማ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ አንድ ሺ 198 የኢንቨስትመንት ተቋማት ይገኛሉ:: መልሶ ማልማትን ታሳቢ ላደረገ የኢንቨስትመንት ስራም 175 ሄክታር መሬት ተዘጋጅቷል:: ይህ የዝግጅት ተግባር የተከናወነው ነዋሪዎችን በማያፈናቅልና የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነትና የባለሀብቶችን ተሳትፎ በሚያሳድግ መልኩ ነው::
ከተማዋ በሰላምና ጸጥታ እንዲሁም በእንግዳ ተቀባይነት መልካም ስም ያላት በመሆኗ ለኢንቨስትመንት ምቹ መዳረሻ ናት ያሉት አቶ ሶሬሳ፣ የፀጥታ ስጋት የለም፤ ህዝቡ የኢንቨስትመንት ተቋማትን ይጠብቃል ፤ ባለሀብቶችም ለፀጥታ መስፈን ድጋፍ ያደርጋሉ ሲሉ ይገልጻሉ:: ይህም የከተማዋ የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር ማስቻሉን ጠቅሰው፣ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማቀላጠፍ ስምንት ዘርፎችን ወደ አንድ ማዕከል በማምጣት ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ነው ያመለከቱት::
ንቅናቄው የአዳማ ከተማ የኢንቨስትመንት ዘርፍን ለማሳደግ እያበረከተ ስለሚገኘው አስተዋፅኦ አቶ ሶሬሳ ሲያብራሩ፣ ‹‹ንቅናቄው በኢንዱስትሪው ዘርፍ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች ዘርፉን ወደተሻለ ደረጃ እንዲያሸጋግሩ እድል እየፈጠረ ነው:: በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ስራ ያቆሙ ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት ስራቸው እንዲመለሱ እያስቻለ መሆኑን ይገልጻሉ:: በዚህም ከንቲባው በጉዳዩ ላይ የሰጡትን ሀሳብ ያጠናክራሉ:: ከአቅማቸው በታች የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች ደግሞ በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ እገዛ እያደረገላቸው መሆኑን ይናገራሉ::
የአገሪቱን የምጣኔ ሀብት መዋቅር ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የሚያግዙ በርካታ መልካም አጋጣሚዎችና እድሎች እንዳሉ ይታወቃል፤ ይሁን እንጂ እነዚህን መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳካት የተከናወኑ ተግባራት ሀገሪቱ ካላት አቅምና ፍላጎት በብዙ ርቀት ላይ የሚገኙ በመሆናቸው ለወቅቱ የሚመጥን ተግባራዊ ምላሽ መስጠት እጅግ ያስፈልጋል:: ለዚህ ደግሞ ሀገራዊ የማምረት አቅምን በማጎልበት የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ፣ ተጨማሪ የሥራ እድሎችን ለመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለማቃለልና ተወዳዳሪ አገራዊ ምጣኔ ሀብት ለመገንባት ያስችላል ተብሎ የታመነበት የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ አማራጭ የመፍትሄ አቅጣጫ ነው::
የአምራች ዘርፉን ችግሮች በመፍታት ረገድ አዎንታዊ አስተዋፅኦ የሚኖረውን ይህን ንቅናቄ ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ደግሞ ዘመቻው ምን ለውጥ እንዳስገኘ በየጊዜው ክትትል እያደረጉ መገምገምና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ ያስፈልጋል:: ለዚህ ደግሞ መንግሥት ንቅናቄውን እንዲሁም ዘርፉን ውጤታማ የሚያደርጉ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በማዘጋጀት ምቹ የኢንዱስትሪ ከባቢን መፍጠር ይጠበቅበታል:: የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራትና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ለመደገፍ ትኩረት መስጠት ይኖርበታል::
መንግሥት ማበረታቻዎችን ሲያደርግም ማበረታቻዎቹ ለታለመላቸው ዓላማ መዋላቸውን ማረጋገጥ አለበት:: ከዚህ በተጨማሪም የመርሃ ግብሩን አፈፃፀም እየተከታተለና እየገመገመ ማስተካከያዎችን በማድረግ የአመቻችነት ሚናውን ሊወጣ ይገባል:: ባለሀብቶችም አዳዲስ አሰራሮችን በመተግበር አቅማቸውን ማሳደግና ከመንግሥት የሚደረጉላቸውን ማበረታቻዎች በጥንቃቄ መጠቀም ይኖርባቸዋል::
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2015