‹‹የ12ኛ ክፍል አገራዊ ውጤት ምርቱን ከገለባ የለየ ነው። በተለይም የሚሰሩ ተቋማትን ትጋትና የተማሪዎቻቸውን ጥረት አሳይቷል። የአቅም ውስንነታችን ምን ላይ እንደሆነም ያመላከተ ነበር። የት የት አካባቢ በስፋት መስራት እንደሚያስፈልግም ጠቁሟል። የትምህርት ቤቶች የማስተማር ብቃትን ለይቷል። ምክንያቱም ከዚህ በፊት በነበረው አሰራር ሙሉ ማሳለፍ እንጂ ጥራት የሚባል ነገር ለውድድር አይቀርብም።
በዚህም ዩኒቨርሲቲ የሚገባው ጎበዙ ብቻ ሳይሆን በቂ እውቀት ያልጨበጡትም እንዲሆኑ አድርጓል። ምክንያቱም የመግቢያ ነጥቡ በኩረጃና መሰል ተገቢ ያልሆኑ ስራዎች ጋሽቧል። ስለዚህም ሰነፉ የጎበዙን ጭምር እድል ዘግቶበት ቆይቷል። በዘንድሮው ውጤት ይህ የተቀየረ ይመስላል›› ያነጋገርናቸው ሙሉ ለሙሉ ተማሪዎቻቸውን ያሳለፉ ትምህርት ቤቶች ሃሳብ ነው።
እንደ አገር ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበውንና ሙሉ ለሙሉ ተማሪዎቹን ያሳለፈውን መነሻ ስናደርግ የይሁኔ ወልዱ መታሰቢያ ደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ሲሆን፤ የትምህርት ቤቱ የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተናን ለመጀመሪያ ጊዜ ያስፈተነ ነው። የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች መግቢያ ዝቅተኛው 350 ቢሆንም የአዳሪ ትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ያመጡት ዝቅተኛው ውጤት 450 ነው። ከፍተኛው እንደአገር የተመዘገበው 666 ነውም። ለውጤቱ የተማሪዎች ትጋት የመጀመሪያ ሲሆን፤ የመምህራን መረጣና ሥራቸው ታክሎበት ስኬታማ አድርጓል።
የትምህርትቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ በለጠ ኃይሌ እንዳሉት፤ ቀጠናው የጦርነት በመሆኑ ምክንያት ለስድስት ወር ያህል ተማሪዎቹ መማር አልቻሉም ነበር። በኮሮና ምክንያትም እንዲሁ ግማሹን ሴሚስተር አልተማሩም። ትምህርትቤቱ ጥቃት ከደረሰባቸው መካከልም ነው። ሆኖም በልመና ግብዓቶችን አሟልተን ተማሪዎችን አስፈትነናቸዋል። እንደ አዳሪ ትምህርት ቤት ሳይሆን እንደ ሁለተኛ ደረጃ ነው የግብዓቱ ጉዳይም። ነገር ግን ሁሉንም በመቻል ለዚህ በቅተዋል።
በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ የሚተዳደረው የቀዳማዊ ምኒልክ ሳይንስ ሸርድ ካምፓስ ፕሪንሲፓል የሆኑት አቶ አቤል ጫላ እንደሚሉት፤ ትምህርት ቤቱ ከዚህ በፊት በነበረው የአፈታተን ሥርዓት ተማሪዎችን ዩኒቨርሲቲ ሳያስገባ ቀርቶ አያውቅም። በየዓመቱ የተሻለ ተማሪ እንጂ ዝቅተኛ አቅም ያለው ተማሪም አያወጣም።
ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የመማር ማስተማር ሥራውን በሚገባ ማከናወን መቻሉ ነው። ከዚያ ባሻገር ተማሪዎቹ ለውጤት ሳይሆን ለእውቀት የሚሰሩ መሆናቸው፣ ዓላማ ያላቸውና ለዚያ ስኬት የሚተጉ መሆናቸው ውጤታማ አድርጓቸዋል። በተመሳሳይ ምንም እንኳን መምህራኑ የተመረጡና ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው ሌክተሮች ቢሆኑም ተማሪው ጠንካራ ካልሆነ የሚያሰሩበት እድል አይገጥምምና ይህም መልካም እድሎችን ሰጥቷል።
ተማሪዎችን ከመፈተናችን በፊት ሁሌም የተለየ ልምድ የማጋራት ሥራ ይሰራል። በተለይም ከፈተና ጋር በተያያዘ ተረጋግተው እንዲፈተኑ ከማድረግ አኳያ የማያሰልስ ጥረት ይደረጋል። በተለይም በዘንድሮው ዓመት ልዩ ክትትልና ዝግጅት ተደርጎ ነው ወደፈተናው የገቡት። ምክንያቱም አዲስ የፈተና ሥርዓት ተፈጥሯልና ጎበዝ ቢሆኑም የሥነልቦና ጫና ሊፈጥርባቸው ይችላል። ስለዚህም ዩኒቨርሲቲው ያለውን ልምድ በፕሬዚዳንቱ ዶክተር ብርሃነ መስቀል ጠና በኩል ከማጋራት ባሻገር የፈተና የሥነልቦና ዝግጅት ሥልጠና እንዲወስዱ አድርጓል። በዚህም ተስፋ የተጣለባቸውን ያህል ሰርተው እንዲያሳዩ ሆነዋል።
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ቀዳማዊ ምኒልክ ሳይንስ ሸርድ ካምፓስ በየዓመቱ 90 ተማሪዎችን የሚቀበል ሲሆን፤ በኮቪድ ወቅት ብቻ በክፍል ውስጥ የሚማሩትን ተማሪዎች ለመቀነስ ሲል 75 አድርጎ ነበር። የአቀባበል ሁኔታው የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ የፈተና ውጤት ሲለቅ ከፍተኛ ውጤቱን መሰረት በማድረግ ነው።
የመቀበል ሁኔታው በ12 የማማሪያ ክፍሎች በላይ የሚሸፍን ስላልሆነ ከትምህርት ቤቱ በጣም ርቀው ያሉ ተማሪዎች በትራንስፖርት ምክንያት፣ ሀብታም ከሚባል ቤተሰብ የወጡ ልጆች ትምህርት ቤቱን ላይመርጡ ይችላሉና ለውድድር እስከ 5ሺ ተማሪዎች ግምት ውስጥ እንዲገቡ ተደርጎ ምዝገባው ይካሄዳል።
የትምህርት ቤት መግቢያ ፈተናው ሲሰጥ የስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ውጤት ከ 15 በመቶ ማርክ አይበልጥም። ምክንያቱም ውጤቱ በኩረጃና መሰል መንገዶች ሊመጡ ይችላሉ። ስለዚህም ብቃት ያላቸውን ተማሪዎች ለመለየት ኬሚስትሪ፣ ባዮሎጂ፣ ሂሳብ፣ ፊዚክስ እና አፕቲቲዩድን የያዘ ጥራቱን የጠበቀ ፈተና ይወጣል። መምህራኑም ፈተናውን እንዲያርሙ የሚደረገው በሚስጥር ቁጥር (ኮድ) ነው። ስለዚህ እያንዳንዳቸው ትምህርቶች 15 በመቶ ማርክ እንዲይዙ ተደርገው ከስምንተኛ ክፍል (ሚኒስትሪ) ውጤት ጋር በመደመር በጥቅሉ 90 በመቶ ላይ ይደርሳል።
የቀረው 10 በመቶ ደግሞ ከፈጠራ ስራ፣ ከሳይንስ ዝባሌና ከቴክኖሎጂ ጋር የተገናኙ ጥያቄዎች ቦታ ተሰጥቷቸው ከዩኒቨርሲቲው የተውጣጡ ዶክተሮችና ፕሮፌሰሮች ቃለመጠይቅ እንዲያደርጉላቸው በማድረግ ይፈተናሉ። ይህ የሚሆነው በትምህርት ቤቶቹ ለመግባት በቂ ውድድር መደረግ ስላለበት ነው። በፈጠራ ሥራቸው በየጊዜው የተሻሉ ነገሮችን ለአገር ማበርከት ስለሚጠበቅባቸው ነው። ከዚህ ባሻገር በዩኒቨርሲቲና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የውጭ አገር የትምህርት እድል እንዲያገኙ ለማስቻል ታስቦ እየተሰራ ነው። ስለሆነም ይህንን ለማሳካት የጠራ ተማሪ ማስገባት ያስፈልጋልና ምልመላው በዚህ መልኩ ይደረጋል ይላሉ ፕሪኒስፓሉ።
ሥራው የተጀመረው ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ እና ከአራዳ ክፍለ ከተማ ጋር በጥምረት ቢሆንም የትምህርት ቤቱን ወጪ መቶ በመቶ የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ከራሱ ባጀት ላይ ቀንሶ በመሆኑ ትምህርት ቤቱ የአንድ አካል ሳይሆን የመንግሥት ነው። በዚህ መልኩ ጠንክሮ ተማሪዎችን ለውጤት ማብቃቱ በአንድም በሌላም መንገድ ኢትዮጵያን ሊጠቅሙ የሚችሉ ተማሪዎችን የማፍራት አንድ አካለ ነው። ትምህርት ቤቱ ሁሉንም ተማሪ ሳይንቲስት ማድረግ በሚል መርህም እየሰራ ነው።
ትምህርት ቤቱ የ12ተኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተናን ለአራተኛ ጊዜ ሲያስፈትንም ይህን እያሰበ እንደሆነም ሃላፊው ያነሳሉ። አንደ አገር ለተከታታይ ዓመታት ከፍተኛ ውጤት ማምጣት ተችሏል። ነገር ግን ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤትን ለምን አላመጡም የሚለው ያነጋግራል። ምክንያቱም የገቡት በከፍተኛ ጥራት ውስጥ አልፈው ነው። ስለዚህም ልኬቱ ይህ ስለሆነ ሙሉ ለሙሉ ማለፋቸው አይደንቅም። በ12ኛ ክፍል ብቻ ሳይሆን በ10ኛ ክፍልም የሚታይ ተግባር ነው። በሌላ በኩልም እነዚህ ተማሪዎች አልፎ ተርፎ የዓለም አቀፍ ፈተና እንዲወስዱ እየተደረገ ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ ይመለከታሉ። በዚህም ውጤታማ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ስለዚህም በዘንድሮው ዓመት ብቻ የ 12 ክፍል መልቀቂያ (ማትሪክ) ሳይወስዱ የውጭ የትምህርት እድል አግኝተው በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የገቡ ተማሪዎችን ማፍራት ችለናል። በዚህም የአሁኑን ፈተና የወሰዱት 69 ተማሪዎች ሆነዋል። ከእነዚህ ውስጥም 16 ተማሪዎች ከ600 በላይ፤ 32 ተማሪዎች ከ500 በላይ፤ 20 ተማሪዎች ከ400 በላይ ፤ 1 ተማሪ 375 ማምጣት ችሏል። ለዚህ ውጤት ስኬት የመጀመሪያውን ድርሻ የሚወስደው የተማሪዎቹ የመማር ተነሳሽነት ሲሆን፣ መሆን የሚፈልጉትን አውቀው የሚሰሩ ስለሆኑ ለዚያ ግብም የሚሰሩ ናቸው፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ የመምህራን የመዘጋጀት ከፍታ፣ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ለትምህርት ቤቱ ልዩ ትኩረት መስጠታቸው የእነርሱ ጥረት መታከል ውጤቱን የሚጠበቀው ላይ አድርሶታል። አሁን የተጀመረው የመንግሥት ግልጸኝነት ብዙ ነገሮችን በቀጣይ የሚቀንስ እንደሆነ የሚያነሱት አቶ አቤል፤ ይሰረቅ ይሆን የሚለውን የጎበዝ ተማሪዎች ስጋት በብዙ መልኩ ገቶታል። የተማሪዎችን የሥራ ውጤትም አሳይቷል። በተመሳሳይ ይህ ውጤት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን ከታች የነበረውን ድክመት እንደሆነም አመላክቷል። ስለዚህም እንደ እኛ አይነት ተቋማት ሙሉ ለሙሉ ተማሪዎቻቸውን ቢያሳልፉም የሌሎቹ ትምህርት ቤት ጉዳይም ያሳስባልና በዚያ ላይ መስራት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።
በአሁኑ ፈተና ከፍተኛ ወጪ ወጥቶ ሊሆን ይችላል። ሆኖም የቀጣይ ተስፋን የሚያለመልምና የትምህርት ሥርዓቱን ስብራት የሚያክም ስለሚሆን ሁሉም ደስተኛ ሊሆንበት ይገባል። የአፈታተን ሥርዓቱም የአንድ ጊዜ ሥራ ስላልሆነ ሁሉም መረባረብ አለበት። ምክንያቱም ዘመቻው ትውልድ የመፍጠር ጉዳይ በመሆኑ ፤ ስለዚህ ስህተትን አይቶ፣ ችግርን ፈትቶ የተሻለ ተማሪ ለመፍጠር በጋራ መስራት ያስፈልጋል። በተለይም ምንም ያላሳለፉት ላይ ምክንያታቸውን እያዩ ማገዝ ይገባል። በተጨማሪም እንደመንግሥት አሁን ያለውን አቋም ማስቀጠል፤ ተማሪዎች በራሳቸው የመስራት ልምምዳቸው በዚህ እንዲቀጠል ማድረግ ይኖርባቸዋል ሲሉ አስተያየታቸው ሰጥተዋል።
የወላይታ ሊቃ አዳሪ ትምህርት ቤት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ግርማ ደነቀ በበኩላቸው ፤ የትምህርት አሰጣጡንና የአሁኑ አገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤት በተለያየ መንገድ እያነሱ ያብራራሉ። ትምህርት ቤታቸው የተለዩና አቅም ያላቸውን ተማሪዎች ማፍራትና ማሳለፍ የጀመረው ዛሬ ሳይሆን ከተቋቋመበት 2000 ዓ.ም ጀምሮ ነው። አቀባበላቸው ከአምስተኛ እስከ ሰባተኛ ክፍል ድረስ የሚማሩ ተማሪዎችን ሲሆን የቀደመውን የትምህርት ደረጃ ምን ያህል አውቀውታል መለያቸው ነው ፤ ስምንተኛ ክፍል ላይ ሌላ ተጨማሪ ተማሪ በፈተና ለይተው ይቀበላሉ።
ከ75 በላይ አማካኝ ውጤት እያስመዘገበ መቀጠል የማይችል ተማሪ በትምህርት ቤቱ እንዲቆይ አይደረግም። ስለዚህም ውድድሩ ከውጪ ካሉት ጋር ብቻ ሳይሆን ከውስጥ ካሉት ጋርም እንደሆነ ያነሳሉ። ምክንያቱም በትምህርት ቤቱ ውስጥ የመቆየትና ያለመቆየት ጉዳይ ስላለበት። ውጤታማ ተማሪ ለመሆን ሌት ተቀን ያጠናሉ። መምህራንን ሞጋችና ሳያውቁ የማያልፉ ናቸው። ተወዳዳሪነታቸው በአገር ደረጃ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ጭምር የሆነውም በዚህ ምክንያት ነው። አዲስ ነገር ሲፈጠርም ያልወደቁት በራስ መሥራትን እየተለማመዱ በመሄዳቸው ነው።
ከ2005 ዓ.ም እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ 721 ተማሪዎችን ያስፈተኑ ሲሆን፤ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎችን በተለያየ ደረጃ ተቀላቅለዋል። ስለዚህም ዩኒቨርሲቲ ማስገባት ዘንድሮ የተጀመረ አይደለም። ይህንን ልዩ የሚያደርገው ትምህርት ሚኒስቴር የፈተና አሰጣጡን ለየት ማድረጉ ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ተማሪዎች በራሳቸው አቅም ምን ያህል ይሰራሉ የሚለውን የፈተሽ በመሆኑ የእኛም ተማሪዎች ይህን አልፈው ዩኒቨርሲቲ ሙሉ ለሙሉ እንዲገቡ ሆነዋል። በእርግጥ ያስፈተናቸው ተማሪዎች ከሌሎች አኳያ ሲታይ ቁጥራቸው ትንሽ ነው። በዘንድሮው ዓመት የተፈተኑት 75 ተማሪዎች ብቻ ናቸው። እነርሱም 300 ቤት ያመጡት ሁለት ብቻ ሲሆኑ፤ ከ400 እስከ 499 ያመጡ ደግሞ 28 ናቸው። 500 እና ከዚያ በላይ ያመጡት ደግሞ 41 ሆነው ተገኝተዋል።
በአንድ ክፍል የተማሪ ቁጥር በዛ ቢባል 38 ሲሆን፤ ይህ ደግሞ መምህራንና ተማሪዎች ተቀራርበው እንዲሰሩ አስችሏል። በወላይታ ልማት ማህበር መደገፉና አስፈላጊ ነገሮች መሟላታቸው እንዲሁም የአሰራር ሥርዓቱ ተወዳዳሪ የሚያደርግ መሆኑ ለተማሪዎች ውጤት ከፍ ማለት አስተዋጽኦ ነበረው። ትምህርት ቤቱ በዚህን ያህል ልክ ውጤታማ ስራን ይስራ እንጂ የአጥር ግቢው በደንብ የታጠረ ባለመሆኑ አንዳንድ ችግሮች ያጋጥሙታል። በዚህ ላይ መንግሥት ቢያግዝ የበለጠ ለመሥራት ያስችላል ሲሉ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።
የተማሪዎች ውጤትን ከፍ ለማድረግ የመጀመሪያ የሚሆነው ዓላማ ያለው ተማሪ መፍጠር ነው። በተለይም በሥነ ምግባር ማነጽ ከተቻለ በራሱ ሰርቶ የማለፍና ለሌሎች የሚያሳልፍ ዜጋ መፍጠር ይቻላል። አሁን ያለው የትምህርት ጥራት ጉዳይም በዚያው ልክ እየተረጋገጠ እንዲሄድ መስመር ያስይዛል። እናም በዘንድሮው የውጤት አተናተንና የማለፍ ምጣኔ ሁሉም መደሰት አለበት። ምክንያቱም ተማሪ ስለወደቀ ሳይሆን ለአገር የሚሆን ተስፋ መሰረት ስለተጣለ።
እስከዛሬ በነበረው ተግባር የትምህርት ጥራት እንደአገር አደጋ ውስጥ ገብቷል ይባላል። ሆኖም መፍትሄ ሰጪ አካል አልነበረም። መንግሥት ጭምር ኃላፊነቶችን መውሰድ አይፈልግም ነበር እኛንና እኛን የሚመስሉ ትምህርትቤቶች ላይ ጭምር ይህ አካሂድ አደጋ ፈጥሮ ነበር። ምክንያቱም ለፍተን እንዳለፋን ሲያደርገን ቆይቷል።
24 ሰዓት ሲያነብና ለተሻለ ነገር ሲጥር የነበረውን ልጅ እድል አሳጥቶታልም። ይህ ደግሞ ተመርቆ ሥራ ላይ የተሰማራውን ሰው ጭምር እንዲበላሽ አድርጎታል። የማንመክተው ነገር እንደ 㙀ገር የገጠመንም በዚህ ምክንያት ነው የሚሉት አቶ ግርማ፤ ዛሬ ግን ነገር ተቀይሯል። ትውልድ በመግደል ላይ የተስማማው ዛሬ በኔ ይብቃ ማለት ጀምሯል። መንግሥት ራሱን ግልጽ ከማድረግ ጀምሮ ያሉትን ችግር አሳይቷል። መፍትሄው ምን እንደሆነም አመላክቷል ብለዋል።
ትምህርት አሁን ላይ ቀጥተኛ የሆነ ለውጥ ያስፈልገዋል። ምክንያቱም ትውልድን በብዙ መልኩ ሳንገራው አልፏል። አሁን ግን የእስካሁኑ ይብቃ ሌሎች ይዳኑ በማለት ለውጡን ቀጣይነት ባለው መልኩ ማፋጠን ተገቢ ነው። በተለይም ትምህርት ሚኒስቴር አሁን እየሄደበት ያለውን ጉዞ ማጠናከር አለበት። ሌሎች ከትምህርት ተቋማት ውጪ ያሉ ሊያግዙት ይገባል። ምርጫም ቢሆን የሚደረገው ጥራትና ብቃት ታይቶ ነው። እናም ለመመረጥ ብቁ መሆን ግዴታ ነው። ለዚህ ደግሞ በብቃት መማር ያስፈልጋል። እውቀት ግድ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።
ሰባት ትምህርት ቤቶች ብቻ ሰርተው አገርን ሊያስቀጥሉ አይችሉም። የዘንድሮ የፈተና ውጤት እንደአገር ሲታይ ኪሳራው በኢኮኖሚም፣ በማህበራዊም ሆነ በፖለቲካውም ዘርፍ ነው። ስለሆነም በአገር ደረጃ ተረባርቦ መድሃኒት መፈለግ ያስፈልጋል። ስለዚህም ምንም ያላሳለፉ ትምህርት ቤቶችን ማንሳት ላይ መስራት ይገባል። ተሞክሮ ከማጋራት ባለፈ የሚደግፉበትን ሁኔታ ማመቻቸት የግድ ነው።
ውጤቱ እንደአገር ያለንበትን ሁኔታ አሳይቶናል። በተመሳሳይ የእርስ በእርስ መረዳዳቱ ላይ እንድንተጋም ያደርገናል። ስለሆነም ምንም ተማሪ ያላሳለፉ ትምህርት ቤቶች ማድረግ ያለባቸው ተስፋ መቁረጥ ሳይሆን ከችግራቸው መማርና ለመፍትሄው መስራት ነው።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም