አዲስ አበባ ከተማ በየጊዜው የምታስተናግደው የትራፊክ አደጋ ቀላል የሚባል አይደለም። በየጊዜው በሰው ሕይወት፣ በአካልና ንብረት ላይ ከቀላል እስከ ከባድ ያለው አደጋ ይመዘገባል። በርካቶችም ይሞታሉ፣ ለአካል ጉዳት ይዳረጋሉ። ለወራት ያህል በሕክምና ተቋማት የሚያሳልፉም አሉ። ከፍተኛ የንብረት ውድመትም ያስከትላል። በአንድ ዓመት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሀብት ውድምትም ይከሰታል።
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን መረጃ እንደሚያሳየው በ2013 በጀት ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ በቀለበትና ከቀለበት መንገድ ውጭ ባሉት መንገዶች ላይ በተሽከርካሪዎች ግጭት ምክንያት ከዘጠኝ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የመንገድ ሀብት ተጎድቷል። የመንገድ ሀብት ላይ ከሚደርሰው ውድመት ባሻገር በአሽከርካሪው ንብረት እና በነዋሪዎች ሀብት ላይ የሚደርሰው ውድመትም በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
የባለሥልጣኑ ሌላው መረጃ እንደሚያሳየው በ2013 በጀት ዓመት በ12 ወራት ውስጥ 62 ግጭቶች በቀለበት መንገድ በሚገኙ ሀብቶች ላይ ደርሷል። 310 ግጭቶች ደግሞ ከቀለበት መንገድ ውጪ መድረሳቸውን ጠቁሟል። በበጀት ዓመቱም በአጠቃላይ 372 የሚሆኑ የመንገድ መሰረተ ልማቶች ተጎድተዋል።
የነዋሪዎቿ ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መምጣት እንዲሁም የተሽከርካሪዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ የትራፊክ እንቅስቃሴ መጨናነቅ በሚያደርሱት የትራፊክ አደጋ የከተማዋ ዕድገትም እየተፈተነ ይገኛል። የመንገዶች አመቺ አለመሆን፣ የመንገድ አጠቃቀምም ሆነ የማሽከርከር ግንዛቤ እጥረትና ቸልተኝነት፣ ጠጥቶ ማሽከርከር፣ ደህንነታቸው የሚያሰጉ ተሽከርካሪዎችን መንዳት ዛሬም ያልተቀረፉ የከተማዋ የመንገድ፣ የአሽከርካሪዎችና የእግረኞች ችግሮች ናቸው። በእግረኞች በኩል የመንገድ አጠቃቀም ግዴለሽነት፣ የተሽከርካሪን ሆነ የእግረኛ መንገዶችን በንግድ ማጨናነቅ እና ግንዛቤ ማነስ ለሚደርሱ አደጋዎች እና የመንገድ መዘጋጋት ከምክንያቶቹ መካከል ይጠቀሳሉ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራፊክ መጨናነቅ እና አደጋ ለመቀነስ የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂ ነድፎ ወደ ትግበራ መግባቱ ይታወሳል። በመንገድ ደህንነት ስትራቴጂው መሰረት እየተሰሩ ካሉ ሥራዎች መካከል አደባባዮችን በትራፊክ መብራት መተካት አንዱ ነው። በአዲስ አበባ ከተማ በዋና ዋና መንገዶች ላይ የሚገኙና ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ የሚስተዋልባቸው አደባባዮችን በጥናት በመለየት በትራፊክ መብራት የመተካት ሥራ እየተሠራ ይገኛል። በአሁኑ ወቅትም በመሠራት ላይ ይገኛል።
ከዚህ ቀደም በትራፊክ መብራት ከተተኩት አደባባዮች መካከል ኢምፔሪያል አደባባይ፣ ጦር ኃይሎች አደባባይ ቦሌ ሚካኤል አካባቢ የሚገኘው አደባባይ እንዲሁም አፍሪካ ህብረት አካባቢ የሚገኘው አደባባይ ተጠቃሾች ናቸው። በቅርቡ በትራፊክ መብራት የተተካው ካርል አደባባይም እንዲሁ የሚጠቀስ ነው።
ካርል አደባባይን ጨምሮ በተለያዩ አደባባዮች በትራፊክ መብራት መተካታቸው በተለይም በሥራ መግቢያ እና ከሥራ መውጫ ሰዓት ላይ የሚስተዋለውን ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ በመቀነስ የትራፊክ ፍሰቱን በማሳለጥ እና የትራፊክ አደጋዎችን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖራቸው ተስፋ ተጥሎባቸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኢያሱ ሰለሞን ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ የከተማዋ የመንገድ ኔትወርክ የተሻለ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲኖራቸው በየጊዜው ወቅቱን ታሳቢ ያደረገ የማስተካከያ እርምጃዎች ይወሰዳሉ። ከእነዚህ የማስተካከያ እርምጃዎች አንዱ በቀለበት መንገዶች ላይ በተለይም በመንገድ መጋጠሚያ ስፍራዎች ላይ ያለውን የትራፊክ መጨናነቅ ችግርን ለመቅረፍ የሚያስችሉ እርምጃዎች ሲወሰዱ ቆይተዋል።
ለአብነት ያህል በኢምፔሪያል አካባቢ ቀደም ሲል የነበረውን አደባባይ በማንሳት በትራፊክ መብራት በመተካት ለጊዜው ችግሩን ለማስተካከል ተሞክሯል። አደባባዩ ፈርሶ በትራፊክ መብራት የተተካ ቢሆንም የተሽከርካሪ ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎም በአካባቢው የትራፊክ መጨናነቅ ችግር ተከስቷል።
አሁን ከተማዋ ካለችበት እንቅስቃሴ እድገት ምክንያት ሌላ አማራጭ ሁኔታ የሚጠይቅ በመሆኑ ከዓመታት በፊት በትራፊክ መብራት የተተካውን አደባባይ በተሸጋጋሪ የትራፊክ ማሳለጫ ድልድይ ለመተካት ጥረት እየተደረገ ይገኛል። በተለይም ውስጠኛው የቀለበት መንገድ ክፍል ላይ የሚታየውን የትራፊክ መጨናነቅ ችግር ለመፍታት ተግባራዊ እየተደረጉ ከሚገኙ የመፍትሔ እርምጃዎች አንዱ በዋና ዋና የመስቀለኛ መንገድ መጋጠሚያዎች ላይ የትራፊክ ማሳለጫ ተሸጋጋሪ ድልድይ (overpass) የመገንባት ሥራ ነው።
በዚሁ መሰረት በቦሌ ሚካኤል፣ በኢምፔሪያል እና በለቡ መጋጠሚያ መንገዶች (inter change) ላይ የትራፊክ ማሳለጫ ተሸጋጋሪ ድልድይ (overpass) እየተገነባ የሚገኝ ሲሆን፣ ግንባታዎቹን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው። በኢምፔሪያል አካባቢ እየተሰራ ያለው የትራፊክ ማሳለጫ ድልድይ እና የመቃረቢያ መንገድ ሥራ ከ61 በመቶ በላይ የደረሰ ሲሆን ማሳለጫ ድልድዩ ቀኝ ክፍል በቅርቡ ለትራፊክ ክፍት እንደሚሆን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል። የተሸጋጋሪ ድልድዩን የግራ ክፍል እና ሌሎች የመንገድ ግንባታውን ቀሪ ሥራዎች በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅም እየተሰራ ይገኛል።
በተመሳሳይ በዚሁ መንገድ ላይ ቦሌ ሚካኤል አካባቢም ቀደም ሲል የነበረውን አደባባይ ወደ ትራፊክ መብራት በመቀየር ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት መደረጉን የጠቆሙት አቶ ኢያሱ፤ በአሁኑ ሰዓት ያለው የትራፊክ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ችግሩን በዘላቂነት ሊፈታ ስላልቻለ ተሸጋጋሪ የትራፊክ ማሳለጫ ድልድይ ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል። የዚህ መንገድ አጠቃላይ አፈጻጸሙ ከ65 በመቶ በላይ መድረሱንም ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል ለቡ መጋጠሚያ መስመር ላይም የቀለበት መንገድ ላይ የነበረው አደባባይ ተነስቶ በተመሳሳይ ሁኔታ ትራፊክ ማሳለጫ ድልድይ ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል። የዚህ የትራፊክ ማሳለጫ ድልድይ ግንባታም ከ56 በመቶ በላይ ተጠናቋል። በየቀኑ ግንባታው መፋጠን ላይ ስለሆነ ቃለ ምልልሱ ከተካሄደ በኋላ የፕሮጀክቶቹ እድገት ጨምሮ ሊሆን እንደሚችል ይታሰባል።
እንደ አቶ ኢያሱ ማብራሪያ በቅርቡ ካርል አደባባይ ተብሎ በሚታወቀው ስፍራ ያለው የትራፊክ መጨናነቅ ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፤ በተለይም ወደ ሥራ መግቢያ እና በሥራ መውጫ ሰዓት አካባቢ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ያለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አደባባዩ ተነስቶ በትራፊክ መብራት ችግሩን ለመፍታት ተሰርቷል። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት አደባባዩ ተነስቶ ወደ ትራፊክ መብራት ተቀይሯል።
ይህ በአጠቃላይ የትራፊክ ፍሰቱን ከማሳለጥ አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው ነው። አሁን ላይ የውስጠኛው ቀለበት መንገድ ተብሎ የሚጠራው የመንገድ ክፍል በከተማ ዳርቻ የነበረው ሁኔታ ታሳቢ ተደርጎ ሲሰራ ነበር። አሁን ላይ በጊዜ ሂደት ከተማው በስፋት እየለማ ሲመጣ ዳር ተብሎ ይጠራ የነበረው ወደ መሃል ገብቷል። ስለዚህ በየጊዜው የሚሰሩ የማስተካከያ ሥራዎች የውስጠኛው የቀለበት መንገድ ተብሎ በሚጠራው የመንገድ ክፍል ላይ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት የተሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
አደባባዮቹ የተሰሩ የማስተካከያ ስራዎች የትራፊክ ፍሰቱን ስለሚያሳልጥ የትራፊክ ፖሊሶች አደባባዮች አካባቢ በመጨናነቅ ምክንያት የሚፈጠሩ ችገሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ ሌሎች ህጎችን ማስከበር ላይ እንዲያተኩሩ እድል ይፈጥራል። የትራፊክ መጨናነቅን ለማሳለጥ ጥረት ከማድረግ ይልቅ በተለይም ለትራፊክ አደጋ መንስኤ የሚሆኑ የሕግ ጥሰቶች ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርጉ ስለሚያስችል ለትራፊኮች ትልቅ እፎይታን የሚፈጥር ነው።
እንደ አቶ ኢያሱ ማብራሪያ ወደ ፊትም በከተማዋ ውስጥ ያሉትን የትራፊክ እንቅስቃሴዎች በመመልከት ባለሥልጣኑ ከአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ጋር በመነጋጋር ሌሎች የማስተካከያ ሥራዎች እየተከናወኑ የሚቀጥሉ ይሆናል ብለዋል።
አደባባዮችን በማፍረስ በትራፊክ መብራት መተካት እንዲሁም የትራፊክ መብራትን በማንሳት በተሸጋጋሪ ድልድይ በመተካት በየጊዜው ሀብትና ጉልበት ከማባከን ይልቅ በጥናት ላይ በመመርኮዝ በአንድ ጊዜ ለምን ተሸጋጋሪ የትራፊክ ማሳለጫ ድልድዮችን መገንባት አልተቻለም የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ኢያሱ ሀገሪቱ ያላት ሀብት ውስን እንደመሆኑ በአንድ ጊዜ ተሸጋጋሪ ድልድዮችን መገንባት አዳጋች መሆኑን አንስተዋል።
እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ መንገዶቹ በወቅቱ የነበረውን አጠቃላይ የትራፊክ እንቅስቃሴ ታሳቢ በማድረግ ነው የሚሰሩት። አገሪቱ ካላት ሀብት አንጻር በአንድ ጊዜ የትራፊክ ማሳለጫ ድልድይ ለመገንባት ከባድ ነው። ምክንያቱም የተሸጋጋሪ ድልድይ ግንባታዎች ትልቅ መዋቅር እንዲሁም ሰፊ በጀትም የሚጠይቅ ነው። ስለዚህ ከሀብት አንጻር ለወደፊት ተብሎ ታስቦ ለመሥራት ከባድ ነው። ትኩረት ተደርጎ የሚሰራው በወቅቱ ያለው የትራፊክ እንቅስቃሴ እና በቀጣይ ዓመታት የሚኖረው ሁኔታ ታሳቢ ተደርጎ ነው የሚሰራው። ከዚያ በኋላ ጫናዎቹ እየበረቱ ሲሄዱ ሌሎች አማራጮች እየተፈለጉ ይሄዳል።
አደባባይ ወደ ትራፊክ መብራት፣ የትራፊክ መብራት ደግሞ ወደ ተሸጋጋሪ ድልድይ የሚቀየረውም ለዓመታት አገልግሎት ከሰጠ እና መንገዶቹም መደበኛውን ጥገና በሚፈልጉበት፣ አንዳንዶቹ ደግሞ የመልሶ ግንባታ ደረጃ ላይ ሲደርሱ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ኢያሱ፤ አደባባዮችን አንስቶ በትራፊክ መብራት የመተካት እንዲሁም የኢኮኖሚ አቅም ሲፈቅድ የትራፊክ መብራትን አንስቶ በተሸጋጋሪ የትራፊክ ማሳለጫ ድልድዮች የመተካት ሥራዎች መሰራታቸው ተገቢ ስለመሆኑ መከራከሪያ አቅርበዋል።
የትራፊክ መጨናነቁ ብዙም አሳሳቢ ባልሆነባቸው የከተማዋ አካባቢዎች በአንድ ከፍተኛ በጀት የሚጠይቁ የትራፊክ ማሳለጫ ድልድዮችን ከመገንባት ይልቅ፤ መንገድ ባልደረሰባቸው አካባቢዎች መንገድ ማዳረስ ላይ ትኩረት ማድረግ እና በቀጣይ የትራፊክ መጨናነቁ እየበዛ ሲሄድ ማሳለጫዎችን እየገነቡ መሄድ የተሻለ አማራጭ መሆኑንም አንስተዋል።
የከተማ አስተዳደሩ በየጊዜው አደባባይን ወደ ትራፊክ መብራት፣ የትራፊክ መብራትን ደግሞ በትራፊክ ማሳለጫ ድልድዮች በመተካት በየጊዜው ሀብትና ጉልበት ከማባከን ይልቅ የረጅም ጊዜ የከተማዋን ፍላጎት ታሳቢ ባደረገ መልኩ ግንባታዎችን ማከናወን ለከተማዋ እድገት ፋይዳው የጎላ ነው።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 27 ቀን 2015 ዓ.ም