ወዳጄ ዘንድሮ እንደ ዘይት ተፈልጎ የሚታጣ ነገር አለ ይሆን። አሁን በባለፈው ሰሞን በመስሪያ ቤት ዘይት መጥቷል ውሰዱ ሲባል የነበረው ግርግርና ሽኩቻ የዚህ የምግብ ንጥረ ነገር ከኢትዮጵያ ምድር ለመጥፋት እየተመናመነ መሆኑን እንድረዳ ነው ያደረገኝ። ድሮ ድሮ ዘይትና ሽንኩርት ሳይሆን ብርቅዬ እንስሳዎቹ እነ “ዋሊያና” መሰል የዱር እንስሳት እንዳይጠፉ ነበር ስጋታችን። አሁን ጭራሽ የምግብ ሸቀጥ ብርቅዬ እየሆነ መምጣቱ ትንሽ ግርምትን እየጫረብን ነው። መቼም እናንተ ይሄን ስል “አንተ ግርምት ነው የጫረብህ እኛ ላይ ደግሞ ስጋት ነው የለቀቀብን እንደምትሉ አልጠራጠርም። ለነገሩ ልክ ናችሁ እኔ ያው ብዬው ብዬው ተስፋ ቆርጬ እንጂ ይሄው ነግቶ ሲመሽ እንደናንተው ስጋት እየጫረብኝ ነው።
መቼም ብርቅዬውን ዘይት እንደ ምሳሌ በመግቢያዬ ላይ አነሳሁት እንጂ ብርቅዬ ያልሆነ ሸቀጣ ሸቀጥ የምግብ ፍጆታም ያለ አይመስለኝም። አሁን በባለፈው ሰሞን በዓል እነ ዶሮና ፍየል ለመሸጥ ሳይሆን እንደ አንበሳ ግቢ የዱር እንስሶች ለመጎብኘት አውደ ርእይ አስፋልት ላይ የወጡ ነበር የሚመስሉት።
ይሄን ስል አንድ ነገር ትዝ አለኝ፣ አንድ ጓደኛዬ አይደርስ መስሎት ባለፈው ዓመት የግንቦት ልደታ ግዜ ለሚስቱ “ጉደኛ ሙክት ፍየል ነው የምገዛልሽ” ብሎ ምራቋን አስውጦ ቃል ይገባላታል። ሚስት ሆዬ ደግሞ አንዴ እንደ ካርቦን ቃል የገባላትን ጉዳይ ኮፒ አድርጋ ይዛ ቀን ቆጥራ የዘንድሮ ግንቦት ልደታ ሲደርስ “ነፍስ ውጪ ነብስ ግቢ” ፍየሏን ካላመጣህ ብላ ስንጉን ይዛ አላፈናፍን ትለዋለች።
ባል የሚይዘው የሚጨብጠው ጠፍቶት “አነስ ቢልም ሙክት ነው ብዬ እሸመጥጣለሁ ብሎ” ጠቦት
ፍየል ለመግዛት ከገበያ ይወጣል። ታዲያ በዚያ ውጥረት በበዛበት ገበያ መሃል እየተንጎማለለ የፍየሎቹን ማጅራትና ወገብ እየዳበሰ ዋጋ መጠያየቅ ይጀምራል። በዚህ ጊዜ ነጋዴዎቹ ዋጋውን ሲያረዱት (ሲነግሩት የሚለው ቃል እራሱ አሁን ብርቅዬ ሆኗል) እንደ መብረቅ ጭንቅላቱን ወቅሮት ወደ እኔ ዘንድ ይመጣል። እኔም ሃሳቡና ጭንቀቱ ገብቶኝ “ለመሆኑ ስንት ብለውህ ነው እንዲ አዝነህ የመጣኸው” ብዬ ብጠይቀው ድምፁን ስልል አድርግ “አስራ ሁለት ተኩል” አለኝ። እኔም ደንገጥ ብዬ ማወራው ሲጠፋኝ “እና ትተኸው መጣህ” አልኩት “ አይ አስራ ሁለት ተኩል ሲሉኝ ሰአት የነገሩኝ መስሎኝ ስድስት ተኩል ላይ እመጣለሁ ብዬ ተመለስኩ” በማለት በፌዝ መልክ ገላመጠኝ።
ይሄ ጓደኛዬ ታዲያ ግንቦት ልደታን ለሚስቱ ቃል የገባውን ሙክት ፍየል ሳይሆን እራሱን በጭንቀት እየፎከተ እኔን በሽምግልና መልክ ይዞ ገብቶ ነው ንፍሮውን እንደነገሩ ቀማምሶ በዓሉን ያሳለፈው።
እንዲያው ነገሩን በምሳሌና በፌዝ እናውራው ብለን እንጂ የኑሮ ውድነቱን ሰማይ የሰቀሉ ብዙ አሳዛኝ ጉዳዮች እያስተናገድን መሆኑን አገር ያወቀው ነው። ታዲያ ሁሌም ገበያ ውስጥ የምንሰማውና በመገናኛ ብዙሃን የምንሰማው መረጃ ለየቅል ነው። በገበያ አንድ ኪሎ ሽንኩርት በፍየል ሙክት ዋጋ እየገዛን በራዲዮንና የቴቪዥን የምንሰማው “መንግሥት የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ይሄን ያህል ኩንታል ሽንኩርት፤ ያን ያህል ጥራ ጥሬ አስገባ” የሚል ዜና ነው።
መንግሥት ‹‹ምርት አለ፣ ገበያው እንዳይረጋጋ የሚያደርጉት ደላሎች ናቸው፣ ገበያውን ለማረጋጋት በየሸማች ማህበሩ ምርቶች በየጊዜው አስገባለሁ፣ የገበያ ሰንሰለቱ አጭር እንዲሆን እየሰራሁ ነው›› እያለ በተደጋጋሚ ቢነግረንም ጠብ የሚል መፍትሄ ሳይሆን ይቀራል፡፡ ዛሬ መንግሥት ገበያውን ለማረጋጋት እርምጃ የወሰደበት ሸቀጥ ነገ አይነቱን ቀይሮና ዋጋውን አግዝፎ ከች ይላል፡፡ ለዚህ ማሳያው ከሆነ ጊዜ ወዲህ በዘይት ላይ ከፍተኛ እጥረት ነበር፣ የዘይት አቅርቦቱ ላይ መሻሻል ሲታይ ስኳር ቀጠለ፡፡
እስቲ ደግሞ ከሆዳችን ጉዳይ እንውጣና ወደ ኮንስትራክሽኑ ዘርፍ እንግባ። መቼም ባሳለፍነው ወራት የሲሚንቶ ጉዳይ ምን ያህል መነጋገሪያ እንደሆነ አሁንም ለቤት ሰሪው “ብርቅዬ ዋሊያ” እንደሆነበት የሚዘነጋ አይደለም። ታዲያ አሁንም ይሄን የሲሚንቶ ውድነት በአጠቃላይ የኑሮ ውድነት እየረበሹና ዋጋ እያናሩ ያሉት ደላሎች መሆናቸውን መንግሥትም ደጋግሞ ነግሮናል። ይሄን ችግር ለመቅረፍ ደግሞ በራሱ የሽያጭ ማእከል ሲሚንቶ ስም እየመዘገበ ከማከፋፈል ዋጋ እስከ መተመን መድረሱን ሰምተናል፡፡ ታዲያ ምን ዋጋ አለው ገበያ የሚያረጋጉት እራሱ ለደላሎቹ እንደሚሸጡት ሳይውል ሳያድር መታወቅ እየጀመረ ነው። ጭራሽ ሲሚንቶ እንደ ባቢሌ ብርቅዬ ዝሆኖች እየተመናመነ እየጠፋ መጣ። ገንዘቡ ያላቸውም ደላሎችን እያደኑ በውድ ዋጋ አሁንም ድረስ ይገዙ ጀምረዋል። ታዲያ መፍትሄው ም ን ይሆን?
መፍትሄው መቼም በምስኪን ሸማች እናቶችና አባቶች እጅ አይደለም። አቅሙም ሥልጣኑም መንግሥት እጅ ነው። ባይሆን ሕብረተሰቡ መተባበር ይችላል። ስለዚህ ሆን ብለው ዋጋውን የሚያንሩ በመንግሥት ጉያ ውስጥ የተሸሸጉ ደላሎችን መንግሥት “አንድ” ይበልልን። የገበያ ሰንሰለቱ ይጠር። ገበሬው ከተጠቃሚው ጋር ይገናኝ። እርሱም ይጠቀም እኛም ባለችን ጥሪት በልተን ነፍሳችንን እናቆይ። እነ በርበሬ፣ ዘይት፣ ሽንኩርት ከብርቅዬነት ጎራ ወጥተው በቀላሉ ገበያ ውስጥ የሚደፈሩ ሸቀጦች እንዲሆኑ መንግሥት ሆይ አሁንም በድጋሚ ደላሎቹን አንድ በልልን። ሰላም!
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 27 ቀን 2015 ዓ.ም