ጓደኛሞች ናቸው። በተማሩበት የጤና ባለሞያ ትምህርት ዘርፍ በመንግሥት ጤና ተቋማት እያገለገሉ ይገኛሉ። በየተቋማቸው መደበኛ የሕክምና ሥራቸውን ሲያከናውኑ ከብዙ ታካሚዎች ጋር ይገናኛሉ። ታካሚዎች ሕክምና ፈልገው ሲመጡ ከገጠማቸው የጤና ችግር በተጓዳኝ የአእምሮ ህመም ሲያጋጥማቸው ያያሉ። ለአንዳንዶቹ የአእምሮ ታማሚዎችም ምክር ቢጤ ይሰጣሉ።
በዚሁ አጋጣሚም ወደጤና ተቋም ለሕክምና መጥተው የአእምሮ ህመም የሚያጋጥማቸው ታካሚዎች ራሱን የቻለ ሕክምናና የምክር አገልግሎት እንደሚያስፈልጋቸው ተረዱ። ይህንኑ ሃሳባቸውን ወደተግባር በመለወጥ የእርዳታ ድርጅት አቋቁመው የአእምሮ ህመም የሚያጋጥማቸው ሰዎች ምስጢራቸው ተጠብቆ የምክር አገልግሎት የሚያገኙበትን መንገድ አመቻቹ። አሁን ደግሞ በአእምሮ ህመም ምክንያት ጎዳና ላይ የወደቁ እናቶችንና ሕፃናትን ለማንሳት ሥራዎች ጀምረዋልⵆ የብሩህ ሕይወት እርዳታ ድርጅት መሥራች ወጣቶች።
ሲስተር ነፃነት ሙሉ የብሩህ ሕይወት እርዳታ ድርጅት መሥራችና የሕዝብ ግንኙነት ናት። በሞያዋ ነርስ ስትሆን በካውንስሊንግ ሳይኮሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪ አላት። በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ጤና ጣቢያ ውስጥ ትሠራለች። በአእምሮ ጤና ማማከር ሥራ ላይ ያተኮረ የእርዳታ ድርጅት የማቋቋሙ ሃሳብ በእርሷና ጓደኛዋ ከሁለት ዓመት በፊት ነበር የተጀመረው። ሁለቱም ጤና ዘርፍ ላይ እንደመሥራታቸው በሀሳቡ ላይ ብዙ አውርተውበታል። ታካሚዎች ከሚያገኙት ሕክምና አገልግሎት በተጨማሪ በሽታቸው ሳይታወቅ በተደጋጋሚ የሚመላለሱ እንዳሉም አይተዋል። ትንሽ ጊዜ ሰጥተዋቸው ሲያወሯቸው ህመሙ የሥነ ልቦና ጉዳትና ከአእምሮ ጋር የተያያዘ ችግር እንደሚገጥማቸው ተረድተዋል። ከሕክምናው በተጓዳኝ ጥቂት ምክሮችን ሲለግሷቸው ለውጥ ሲያሳዩ ተመልክተዋል።
በዚህም በአእምሮ ህመም ላይ ብዙ መሥራት እንዳለባቸው ሲያወሩ ቆዩ። በተለይ ደግሞ በሚሠሩበት ጤና ጣቢያ የምትታከም አንድ እናት በተደጋጋሚ እየታመመች ስትመላለስ የሥነ ልቦና ሕክምና አድርገውላት ተሽሏት ወደቤቷ ስትሄድ ከመደበኛ ሕክምና አገልግሎት ጎን ለጎን የሥነ ልቦናና የአእምሮ ህመም ሕክምና ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ተረድተዋል። በተለይ ደግሞ የአእምሮ ጤና የሁሉም የሰውነት ጤና መሠረት እንደሆነ ለመገንዘብ ችለዋል።
በዚህ መካከል እርሷና ጓደኛዋ አንድ ሌላ የሕክምና ባለሞያ በመጨመር በወጣቶች ዙሪያ ከሚሠራ አንድ ድርጅት ጋር በመሄድ በሥራ ፈጠራ ውድድር ላይ ሃሳቡን ይዘው ቀረቡ። በውድድሩ የያዙት ሃሳብ ወደ እርዳታ ድርጅት ቢቀየር የሥነ ልቦናና የአእምሮ ህመም ሕክምናና ምክር አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ እንደሚሆን ተነገራቸው። ሃሳባቸውም አሸናፊ ሆኖ ፍቃድ የማውጣቱንና ሌሎች ሥራዎችን መሥራት ቀጠሉ።
ሁሉም ሰው የተሟላ የአእምሮ ጤና አለው ማለት አይቻልም። የሁሉም ሰውነት ጤና መሠረቱም የአእምሮ ጤና ነው። የአእምሮ ጤና በቀላሉ ሊጠበቅ የሚችል ቢሆንም ካልተጠበቀ ከባድ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። አንዳንድ ሰዎች አእምሯቸው ጤነኛና የስኳር ታማሚ ሆነው ራሳቸውን እያከሙ ሕይወታቸውን ዘላቂ ሊያደርጉ ይችላሉ። ነገር ግን ደግሞ አእምሮውን የታመመ ሰው ምንም ዓይነት የጤንነት ችግር ባይኖርበት እንኳን በየትኛውም መስክ ውጤታማ ሊሆን አይችልም።
እነርሱም በአእምሮ ጤና ላይ ለመሥራት የፈለጉት በዚህ ምክንያት ነው። በተለይ ደግሞ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተከሰተው ጦርነት በብዙ መልኩ የፈጠረው ጫና የሰዎችን አእምሮ ጤናን በብዙ የሚጎዳ መሆኑን በመረዳት በአእምሮ ጤና ላይ ለመሥራት ይበልጥ ተገፋፍተዋል። በመቀጠል ስልክ ቁጥራቸውን በካርድ አሳትመው በመበተን ከመደበኛ ሥራቸው ጎን በአእምሮ ህመም ዙሪያ በስልክ የማማከር አገልግሎት በነፃ መስጠት ጀምረዋል። ተጠቃሚዎችም ስልካቸውን ለሌሎች በማጋራት እንዲደውሉላቸው በማድረግ ተጨማሪ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎችን ቁጥር ማሳደግ ችለዋል። ይህም አሠራር ተጠቃሚዎች ምስጢራቸው ተጠብቆ አገልግሎቱን እንዲያገኙ አስችሏል። የምክር አገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥር ሲበዛ ደግሞ ተጠቃሚዎቹን በአካል በማግኘት አገልግሎቱን እንዲያገኙ እያደረጉ ነው። የምክር አገልግሎቱን ይበልጥ ለማዘመንና የአእምሮ ሕክምና የምክር አገልግሎቱን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ መተግበሪያ የማበልፀግ ሥራም እየሠሩ ይገኛሉ።
በዚህም አገልግሎቱን ፈልገው ወደ እጅ ስልካቸው የሚደውሉ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ማረጋገጥ ችለዋል። የምክር አገልግሎቱን ያገኙ ሰዎች መረጃውን ለሌሎች በማጋራት ደውለው አገልግሎቱን እንዲያገኙም አስችለዋል። አገልግሎቱ ውስን መሆኑና ለሌላው ሰው በበቂ ሁኔታ እንዳልደረሰ አመላክቷቸዋል።
ምንም እንኳን ወጣቶቹ ከመደበኛ ሥራቸው ጎን ለጎን የምክር አገልግሎቱን በነፃ እየሰጡ የሚገኙ ቢሆንም ተቋማቸው የእርዳታ ድርጅት እንደመሆኑ በአእምሮ ህመም ምክንያት ጎዳና ላይ የወደቁ እናቶችንና ሕፃናትን የማነሳት እቅድ ስላላቸው ይህን ሊደግፍ በሚችል መልኩ የተወሰነ ክፍያ ሊኖረው የሚችልበትን አሠራር የመዘርጋት እቅድ አላቸው። በቀጣይ የነፃውንም ሆነ የክፍያውን የምክር አገልግሎት እኩል ለማስኬድም ሃሳብ አላቸው።
የድርጅታቸው ተቀዳሚ ዓላማም ሰዎች ስለ አእምሮ ጤና ግንዛቤ ኖሯቸው ህመሙን አስቀድመው እንዲከላከሉ ማድረግ ነው። የማማከር አገልግሎቱንም በስፋት ለማህበረሰቡ ተደራሽ ማድረግም የድርጅቱ ሌላኛው ዓላማ ነው። የማስተማር፣ ስልጠናዎችን የመስጠትና ሰዎች የአእምሮ ጤና ተገንዝበው ራሳቸውን በመጠበቅ ምርታማና ውጤታማ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራም ድርጅቱ ይሠራል።
ሲስተር ነፃነት እንደምትለው በአሁኑ ጊዜ ድርጅቱ በጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ የራሱን መዋቅር ዘርግቶ የአእምሮ ሕክምና ምክር አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። በዚሁ መዋቅር መሠረት በአእምሮ ጤና ዙሪያ ሥልጠና የሚሰጡና የማማከሩን ሥራ የሚሠሩ ሰዎች አሉት። የራሱ ሥራ አስኪያጅ፣ ገንዘብ ያዥ አለው። እነዚህ ሰዎች ግን ከመደበኛ ሥራቸው ጎን ለጎን ሥራውን የሚያከናውኑት በነፃ ነው።
ድርጅቱ በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ብቻ ታጥሮ መሥራት አይፈልግም። ከዚህ ይልቅ በአእምሮ ጤና ላይ እንደአገር መሥራት ይፈልጋል። ሁሉም ሰው የአእምሮ ጤናው እንዲጠበቅ፣ የአእምሮ ጤናን በሚመለከት በሰዎች ዘንድ ያለው ግንዛቤ እንዲሰፋ ፍላጎቱ አለው። ከዚህ አኳያ መንግሥትም ጉዳዩን ተረድቶ በተለይ የመሥሪያ ቦታ ማመቻቸት ይጠበቅበታል።
በአሁኑ ጊዜ ድርጅቱ ይህን መልካም ተግባር ቤት ተከራይቶ ለመሥራት ከፍተኛ ገንዘብ እየተጠየቀ ነው። በዚህም ምክንያት በድርጅቱ ውስጥ ያሉ የሕክምና ባለሞያዎችና ሌሎችም ባሉበት ቦታና በየቤታቸው ሆነው ሥራውን በነፃ እያከናወኑ ይገኛሉ። ከዚህ አንፃር ድርጅቱ መሥሪያ ቦታ ከመንግሥት ቢያገኝ በተለይ በአእምሮ ህመም ምክንያት ጎዳና ላይ የወደቁ እናቶችንና ሕፃናትን አነሳለሁ ብሎ ለያዘው ትልቅ ራእይ እውን መሆን አስተዋፅዖው የጎላ ነው።
ድርጅቱ በመነሻነት እናቶችን ከጎዳና ላይ ማንሳትና በአንድ ማዕከል ሆነው የሚረዱበትንና እንክብካቤ የሚያገኙበትን መንገድ የመቀየስ ውጥን ይዟል። ከዚሁ በተጓዳኝ በጎዳና ላይ የወደቁ ሕፃናትም እርዳታ የሚያገኙበትን ሁኔታ የመፍጠር ሀሳብ አለው። በተለይ ደግሞ ሕፃናቱ ከጎዳና ሕይወት ወጥተው ትምህርታቸውን በሚገባ ተከታትለው ውጤታማ ማድረግ ትልቁ ህልሙ ነው።
በሲስተር ነፃነት ሙሉ፣ ዶክተር ትዝታ አለሙና ዶክተር እሱባለው አብርሃም የሚመራው ብሩህ ሕይወት እርዳታ ድርጅት በስሩ ገንዘብ ያዥ፣ አስተዳደሮች፣ የማህበራዊ ጉዳይ ባለሙያዎች (ሶሻል ወርከሮችን) እና በጎ ፍቃደኛ ወጣቶችን አቅፏል። የአእምሮ ህመም ሕክምና ማማከር ሥራው ግን በሦስቱ ወጣቶች በነፃ ይከናወናል። ለዚሁ የማማከር ሥራ የሚረዳቸውን ትምህርትም ተከታትለዋል።
በቀጣይም ድርጅቱ በተለይ በአእምሮ ህመም ምክንያት በየጎዳናው ወድቀው የሚገኙ እናቶችን ከነልጆቻቸው በማንሳት በአንድ ማዕከል ሆነው ድጋፍና እንክብካቤ የሚያገኙበትን መንገድ ለማመቻቸት እቅድ ይዟል። በዋናነት ደግሞ ጤናማ አእምሮ ያለውና ምርታማነትን መጨመር የሚችል ትውልድ የመፍጠር ሀሳብም አለው።
ድርጅቱ ሕጋዊ ሰውነት አግኝቷል። ነገር ግን በቀጣይ በራሱ ቆሞ፣ ቢሮና ቋሚ አድራሻ ኖሮት የአእምሮ ሕክምና ማማከር አገልግሎቱ ለሁሉም ማህበረሰብ ተደራሽ የማድረግ እቅድም አለው። በዘርፉ ያሉ ባለሞያዎችን በማሳተፍ በአገር አቀፍ ደረጃ ጥሩ የሥነልቦና የማማከር አገልግሎት ማዕከል ሆኖ መገኘትም ይፈልጋል።
‹‹የአእምሮ ጤና ችግር በጣም ሰፊ ነው›› የምትለው ሲስተር ነፃነት ልክ እንደነርሱ ሁሉ ሌሎች ወጣቶችም በአእምሮ ጤና ምክር አገልግሎት ላይ በማተኮር እንዲሠሩና ኅብረተሰቡን እንዲጠቅሙ ጥሪ ታቀርባለች። በተለይ ደግሞ ከችግሩ አሳሳቢነት አንጻርና የአእምሮ ጤንነት የሁሉንም ተሳትፎ የሚጠይቅ እንደመሆኑ ሁሉም ወጣት ችግሩን ለመቀነስ ተደጋግፎና ተጋግዞ መሥራት እንደሚጠበቅበት ትጠቁማለች። ወጣቶች ብቻ ሳይሆን የሃይማኖት ተቋማትና ሌሎችም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባም ነው የምትጠቅሰው።
‹‹እኛም በአእምሮ ጤና ላይ የምንሠራውን ሥራ አግዘውን መሥራት ለሚፈልጉ ማንኛውም የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋማት በራችን ክፍ ነው›› ትላለች ሲስተር ነፃነት። እስካሁን በመውደቅ መነሳት እዚህ የደረስን ብንሆንም በደንብ ወደፊት መራመድ እንድንችል በተለይ በአእምሮ ሕክምና ዘርፍ ያሉ ባለሞያዎች አብረውን ይሥሩ ስትል ጥሪ ታቀርባለች።
ድርጅቱ ገና ሥራውን እንደጀመረ ከመንግሥት በኩል የነበረው ምላሽ ብዙም አርኪ እንዳልነበር የምትናገረው ሲስተር ነፃነት፤ በሂደት ሥራው እየጎላ ሲመጣ ግን በጎ ምላሽ እያገኘ መሆኑን ትናገራለች። ነገር ግን አሁንም ቢሆን ለአእምሮ ጤና በመንግሥት በኩል ትኩረት ተሰጥቶበት ሊሠራበት እንደሚገባ ትጠቁማለች።
የአእምሮ ጤና ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። የኅብረተሰቡ ጤናም በዚሁ የአእምሮ ህመም በእጅጉ እየተፈተነ ነው። ይህም የአእምሮ ጤና ጉዳይ ምን ያህል ትኩረት እንደሚሻ ያሳያል። የአእምሮ ጤና ችግርን ለመቅረፍ መንግሥት በጥቂቱም ቢሆን ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ቢገኝም በቂ ነው ማለት ግን አይቻልም። እንደነ ነፃነት ያሉና በራሳቸው ተነሳሽነት በአእምሮ ጤና ላይ የማማከር አገልግሎት የሚሰጡ ባለሞያዎች የጀመሯቸው ሥራዎች እጅግ የሚያበረታቱ ናቸው። ነገር ግን የምክር አገልግሎቱን በስፋት ለማህበረሰቡ ለማዳረስና የአእምሮ ህሙማን በቋሚነት ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ ከመንግሥት በኩል በቂ ድጋፍ ሊያገኙ ይገባል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ዓርብ ጥር 26 ቀን 2015 ዓ.ም