በኪነጥበብ፣በስፖርትና ዘርፎች ስኬታማ የሆኑ ግለሰቦች በንግድና ኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ ተሰማርተው ተጨማሪ ስኬቶችን ሲያስመዘግቡ ማየት የተለመደ ተግባር ነው።ይህ እውነት በኢትዮጵያም ገቢራዊ ሆኖ ይታያል። 27 የዓለም ክብረ-ወሰኖችን መስበር የቻለው የሩጫው ዓለም ንጉሥ፣ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ በግብርና፣ በሪልስቴት፣ በትምህርት፣ በሆቴልና ቱሪዝም እና በመዝናኛ ዘርፎች እያከናወነ የሚገኘው ስራ የዚህ መሰል ተግባር ቀዳሚ ማሳያ ተደርጎ ይጠቀሳል። ከ22 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በልዩ ልዩ የኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው ‹‹ኃይሌና ዓለም ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር››፣ የስራ እድል ፈጠራን ጨምሮ በሀገራዊ ምጣኔ ሀብት ውስጥ ያለው ተሳትፎ ከፍተኛ ነው።
አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ‹‹ኃይሌ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ግሩፕ›› (Haile Hotels and Resorts Group) በተሰኘው ተቋሙ ስር በሚተዳደሩ ሆቴሎችና ሪዞርቶች አማካኝነት የሚያከናውነው የሆቴልና ቱሪዝም ኢንቨስትመንት ደግሞ የሀገር ገፅታን መገንባትን ጨምሮ፣ ቱሪስቶችን በመሳብ፣ ለዜጎች የሥራ እድል በመፍጠርና ለአገልግሎት ፈላጊዎች አገልግሎቶችን በማቅረብ ለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ትልቅ አስተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል። የ‹‹ኃይሌ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ግሩፕ›› ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ መልካሙ መኮንን ስለተቋሙ የሆቴልና ቱሪዝም ኢንቨስትመንት የስራ እንቅስቃሴ ለ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የተቋሙ የኢንቨስትመንት ተግባራት
ከ12 ዓመታት በፊት በሐዋሳ ከተማ በሚገኘው ‹‹ኃይሌ ሪዞርት ሐዋሳ›› የሆቴል ዘርፍ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ‹‹ኃይሌ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ግሩፕ››፣ ኢትዮጵያ በሆቴልና ቱሪዝም ኢንቨስትመንት ዘርፍ ላስመዘገበቻቸው ስኬቶች ዋነኛ ተዋናይና ምሳሌ መሆን የቻለ ተቋም ነው። በኃይሌ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ግሩፕ ስር ካሉት ሆቴሎችና ሪዞርቶች መካከል አሁን አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት የሐዋሳ፣ አርባ ምንጭ፣ አዳማ፣ ባቱ፣ ሱሉልታ (ያያ ቪሌጅ) የጎንደር እና በቅርቡ ስራ የጀመረው ባለአምስት ኮከቡ የአዲስ አበባው ‹‹ኃይሌ ግራንድ አዲስ አበባ›› ሆቴሎችና ሪዞርቶች ናቸው። በፀጥታ ችግር ምክንያት ጉዳት ከደረሰባቸው ሁለት ሆቴሎችና ሪዞርቶች መካከል በባቱ ከተማ የሚገኘው ሆቴል እድሳትና ጥገና ተደርጎለት ወደ ስራ የተመለሰ ሲሆን፤ ሌላኛው ጉዳት ያስተናገደው የሻሸመኔው ሆቴል ደግሞ ከቀድሞ አገልግሎቱ በላቀ አቋም ወደ አገልግሎት እንዲመለስ እየተሰራ ይገኛል። የአራት ኮከብ ደረጃ ያላቸውና በግንባታ ላይ የሚገኙ የወላይታ ሶዶ፣ የደብረ ብርሃን እና የጅማ ሆቴሎች እንዲሁም በፀጥታ መደፍረስና በሌሎች ችግሮች ምክንያት ግንባታው ተቋርጦ የሚገኘው ባለሦስት ኮከቡ የኮንሶ ሆቴል የግሩፑ ተጨማሪ ሆቴሎች ናቸው። የወላይታ ሶዶው ሆቴል በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ይጠናቀቃል። በቀጣይም ግሩፑ በወልቂጤ ከተማ ሆቴል ለመገንባት መሬት ተረክቧል።
በስራ ላይ የሚገኙት የኃይሌ ሆቴሎችና ሪዞርቶች እስካሁን ለአንድ ሺ 700 ዜጎች ቋሚ የሥራ እድል ፈጥረዋል። የሆቴልና ቱሪዝም ስራው እየሰፋ ሲሄድ በሚፈጠረው የግብዓት አቅርቦትና የገበያ ትስስር አማካኝነት ደግሞ ሌሎች ተጨማሪ የኅብረተሰብ ክፍሎችም በቀጥታና በተዘዋዋሪ የስራ እድል ተጠቃሚ ይሆናሉ። አሁን በግንባታ ላይ የሚገኙት ሆቴሎች በግንባታ ወቅትና ግንባታቸው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ ተጨማሪ የስራ እድሎችን ይፈጥራሉ። ቱሪዝም በመንግሥት ትኩረት ከተሰጣቸው የምጣኔ ሀብት ዘርፎች መካከል አንዱ መሆኑ ለሆቴል ዘርፍ ኢንቨስትመንት ትልቅ እድልን ይፈጥራል።
የሆቴሎቹ ልዩ መገለጫዎች
በኃይሌ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ግሩፕ ስር የሚገኙት ሆቴሎችና ሪዞርቶች በደንበኞች ዘንድ ተመራጭ እንዲሁም በዘርፉም ስኬታማ ለመሆን እንዲችሉ የሚከተሏቸው ልዩ መገለጫዎችና አሰራሮች አሏቸው። ከእነዚህ መገለጫዎቻቸው መካከል አንዱ፣ ሆቴሎቹና ሪዞርቶቹ ለቤተሰብ መዝናኛ እንዲሆኑ በሚገባ ዲዛይን የተደረጉ መሆናቸው ነው።
ለሆቴሎቹና ሪዞርቶቹ ግንባታ የሚመረጡት የመሬት አቀማመጦች ሰፋ ያሉና ልዩ የተፈጥሮ ገጽታዎችን ማዕከል ያደረጉ ናቸው። ሆቴሎቹና ሪዞርቶቹ ሁሉንም አገልግሎቶች (መዝናኛ፣ ስራ፣ ጤናና ውበት መጠበቂያ …) ከፍተኛ በሆነ ጥራት በአንድ ቦታ አካተው ለማቅረብ የሚያስችሉ (All Inclusive Service Providers) መሆናቸውም ከሌሎች መሰል አገልግሎት ሰጪ የዘርፉ ተቋማት ልዩ የሚያደርጋቸው ባህርያቸው ነው።
ሀገር በቀል የአገልግሎት አሰጣጥ ባህልን ወደ ንግድ (ቢዝነስ) የመቀየር ስኬትና ልምድም የሆቴሎቹና ሪዞርቶቹ መለያ ባህርይ ነው። ተቋሙ የእንግዶች ደህንነትን ጨምሮ ፈፅሞ ለድርድር የማይቀርቡ ጥብቅ መርሆች አሉት። በሁሉም ደረጃዎች ያሉት የሆቴሎቹና ሪዞርቶቹ ሰራተኞች በላቀ ንቃትና ትህትና ለእንግዶች ፍላጎቶች መሟላት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው መስራታቸው የዚህ ስኬትና ልምድ ባለቤት ለመሆን አብቅቷቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ኃይሌ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ግሩፕ የአገልግሎት ጥራት ዘላቂ በሆነ መንገድ እንዲጠበቅ የሚያደርግና ደንበኞች በሁሉም የግሩፑ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል በኮርፖሬት ደረጃ የሚመራ የጥራት ዋስትና መርሃ ግብር (Quality Assurance Program) አለው። ይህ መርሃ ግብርም ከግሩፑ ልዩ ባህርያትና መገለጫዎች መካከል አንዱ ተደርጎ ይጠቀሳል።
ሆቴሎቹና ሪዞርቶቹ በአንድ አካል ባለቤትነትና መለያ ስር የሚተዳደሩ (Chain Hotels) ናቸው። ይህም ሆቴሎቹን በዚህ የአደረጃጀትና አመራር ዓይነት የሚንቀሳቀሱ ግንባር ቀደም ሀገር በቀል ሆቴሎች (Local Chain Hotel) ያደርጋቸዋል። ይህ የሆቴሎቹ አደረጃጀትና አስተዳደር ‹‹ኃይሌ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ግሩፕ›› ወደፊት በዘርፉ ተስፋ የሚጣልበት እንዲሁም ለሌሎች አርዓያ መሆን የሚችል ተቋም እንዲሆን ያስችለዋል። ይህም ተቋሙ ‹‹መገለጫዬ ነው›› ብሎ በልዩነት የሚጠቅሰው ሌላው መለያው ነው።
የ12 ዓመታት ዐበይት ስኬቶች
ከ12 ዓመታት በፊት በሐዋሳ ከተማ በሚገኘው ‹‹ኃይሌ ሪዞርት ሐዋሳ›› የሆቴል ዘርፍ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ‹‹ኃይሌ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ግሩፕ››፣ በሆቴልና ቱሪዝም ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያሳካቸው ስኬቶች ሀገሪቱ በዘርፉ ያስመዘገበቻቸው እድገቶች ማሳያዎች ናቸው። ተቋሙ የተወዳዳሪነት ደረጃው ከኢትዮጵያ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲሆን በማለሙ በዘርፉ ብዙ እመርታዎችን ማሳየት ችሏል። ከተቋሙ ዐበይት ስኬቶች መካከል የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት እና የሆቴል አመራር ተጠቃሽ ናቸው። ከዚህ ቀደም የማይቻል የሚመስለውን የአገልግሎት አሰጣጥ በአንድ ስያሜና አስተዳደር ስር ከሚተዳደሩ ዓለም አቀፍ ሆቴሎች በተሻለ መልኩ እውን ማድረግ ችሏል። የስራ ሂደቶቹን በማዘመንና በማሻሻል ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ያደረገው ጥረት ለሌሎች ሆቴሎች ምሳሌ መሆን የሚችል አሰራር ነው። ብዙ ሆቴሎችን በአንድነት መምራት መቻልና ስራውንም ለሌሎች የዘርፉ ተዋንያን በማስተዋወቅና በማስረፅ ረገድ ስኬት ማስመዝገብ የቻለ ድርጅትም ነው።
የ‹‹ኃይሌ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ግሩፕ›› ሆቴሎችና ሪዞርቶች ለሚሰጧቸው አገልግሎቶች በርካታ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሽልማቶችንና እውቅናዎችን አግኝተዋል።
በ‹‹ቡኪንግ ዶት ኮም›› (Booking.com)፣ በ‹‹ትሪፕ አድቫይዘር›› (Trip Advisor) እና በሌሎች ዓለም አቀፍ የእንግዳ አስተያየት መሰብሰቢያና ሆቴል መያዣ (Booking) ድረ ገፆች አማካኝነት ሽልማቶችን አግኝተዋል። ለአብነት ያህልም በ‹‹ቡኪንግ ዶት ኮም›› የሐዋሳ እና አርባ ምንጭ ኃይሌ ሪዞርቶች ጥራት ያለው አገልግሎት ከሚያቀርቡ ምርጥ ዓለም አቀፍ ሆቴሎች መካከል በመካተት ተሸልመዋል። ባለአራት ኮከቦቹ የግሩፑ ሆቴሎች በ‹‹ትሪፕ አድቫይዘር›› በአገልግሎት ልህቀት በየዓመቱ እውቅና ያገኛሉ። ሪዞርቶቹ የሆቴል ግብይት ባለሙያዎች ማኅበርን የ‹‹ምርጥ ሁሉን አቀፍ አገልግሎት አቅራቢ ሪዞርቶች›› ሽልማትንም አሸንፈዋል። ከዚህ በተጨማሪም ተቋሙ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርም በተለያዩ ጊዜያት የላቀ አገልግሎት ሽልማቶችን አግኝቷል። የ‹‹ኃይሌ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ግሩፕ›› ሆቴሎችና ሪዞርቶች በየክልሎች በሚዘጋጁ የአገልግሎት ልህቀት እውቅናና ሽልማቶች ላይም በተደጋጋሚ እውቅናዎችን አግኝተዋል።
የሆቴል ዘርፍ ተግዳሮቶችና መውጫ መንገዶች
የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ልማት እንደሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች ሁሉ በርካታ ተግዳሮቶች ያሉበት ዘርፍ እንደሆነ ተደጋግሞ ይገለፃል። ‹‹ኃይሌ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ግሩፕ››ም በ12 ዓመታት የስራ እንቅስቃሴው ሂደት የተለያዩ ችግሮች አጋጥመውታል። ከእነዚህ ተግዳሮቶች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ብቁ የሆነና ሙያዊ ስነ ምግባር የተላበሰ የሰው ኃይል እጥረት ነው። ዘርፉ የእንግዶች/የደንበኞች ደህንነት ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጥበት እንደመሆኑ ይህን ተግባር በብቃት ለመወጣት ለአገልግሎቱ የሚመጥን ብቁ የሰው ኃይል ማግኘት አስፈላጊ ግብዓት ነው።
የሆቴል አገልግሎትን በጥራት ለማቅረብ በሚስችሉ ግብዓቶች አቅርቦት ዙሪያ ያለው ውጣ ውረድ፣ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር ማነስና ጎብኚዎቹን በማበረታታት ረገድ የሚስተዋሉ ድክመቶች፣ የሰላምና ፀጥታ መደፍረስ እንዲሁም የኮሮና ቫይረስ (COVID-19) ወረርሽኝ በ ‹‹ኃይሌ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ግሩፕ›› የስራ እንቅስቃሴ ላይ መሰናክል የፈጠሩ ሌሎች ችግሮች ናቸው።
ተቋሙ ያጋጠሙትን ችግሮች ለማለፍ የተለያዩ አሰራሮችን ይተገብራል። በ‹‹ይቻላል›› መንፈስና በቡድን/በቅንጅት የመስራት ባህል፣ ከችግሮችና መሰናክሎች ይልቅ የመውጫ መንገዶችና መፍትሄዎች ላይ የማተኮር ስልት፣ ፈተናዎችን እንደመልካም እድልና አጋጣሚ የመጠቀም ጥበብ እንዲሁም ቁርጠኛ በሆነ ተከታታይና ዘላቂ የመሻሻልና የማደግ መርህ (ከትናንት ዛሬ፣ ከዛሬ ደግሞ ነገ መማርና መሻሻል) ላይ ተመስርቶ የመስራት ልምድ ‹‹ኃይሌ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ግሩፕ›› የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች በብቃት የሚያልፍባቸው መርሆቹ ናቸው። እነዚህ መርሆቹም ተቋሙ በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት አንድም ሰራተኛ ሳይቀነስ እና ሆቴሎቹንና ሪዞርቶቹን ሳይዘጋ እንዲቀጥል፤ የአሰራር ስርዓቶቹን እንዲፈትሽ፤ የማኅበራዊ ኃላፊነት ተግባራቱን እንዲያጠናክር አስችለውታል።
የወደፊት እቅዶች
አገልግሎት እየሰጡ ያሉ እንዲሁም በግንባታና መልሶ ግንባታ ላይ የሚገኙ 12 ሆቴሎችንና ሪዞርቶችን ያካተተው ‹‹ኃይሌ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ግሩፕ›› በምስራቅ አፍሪካ ሆቴሎችን በማልማትና በማስተዳደር በዘርፉ መሪ የሆነ ድርጅት እውን የማድረግ ርዕይ አለው። በኢትዮጵያ ብዙ ሆቴሎችን በማልማትና በማስተዳደር መሪ የሆነው ይህ ተቋም፣ ሆቴሎችንና ሪዞርቶችን ከመገንባትና ከማስተዳደር በተጨማሪ ሌሎች ባለሀብቶች የገነቧቸውን ሆቴሎችንና ሪዞርቶችን በስሙ በማስተዳደር የአገልግሎት መለያውን (Brand) ከኢትዮጵያ አልፎ በጎረቤት ሀገራት ጭምር የማስፋፋት እቅድ አለው። ይህን እቅድ ለማሳካት በሚያስችለው ጥሩ አፈፃፀም ላይም ይገኛል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ጥር 25 ቀን 2015